ክርስቲያኖች የተለየ አመለካከት ያላቸውን ክርስቲያኖች የሚያስቀይም ነገር ባለማድረግ ፍቅራቸውን ያሳያሉ (ሮሜ 13፡14-15፡13)

ሰላማዊት በአጥባቂ ቤተሰብ ውስጥ ያደገች ክርስቲያን ነበረች። ጥሩ ክርስቲያኖች ጌጣጌጥ እንደማይጠቀሙ፥ ከንፈራቸውንም ሆነ ጥፍራቸውን ቀለም እንደማይቀቡ፥ ፊልም ቤት እንደማይሄዱ፥ ፋሽን ልብስ እንደማይለብሱ፥ በቤተ ክርስቲያን ስካርፎችን እንደማይለብሱ፥ ወዘተ… ገና በትንሽነቷ ተምራለች። ፍቅርተ ደግሞ ክርስቲያን ባልሆኑ ሀብታም ቤተሰብ ውስጥ ያደገች ሴት ነበረች። ሁልጊዜም ሕይወቷ በፋሽን ልብሶች፥ ጌጣጌጦች፥ ፊልሞች፥ የፀጉር ስታይሎች፥ ወዘተ… የታጀበ ነበር። ፍቅርተ ክርስቲያን ስትሆን፥ እነዚህ ነገሮች በመጽሐፍ ቅዱስ ስላልተከለከሉ መተው አለብኝ ብላ አላሰበችም። አንድ ቀን የአንድ ቤተ ክርስቲያን መእመናን የነበሩት ሰላማዊትና ፍቅርተ መነጋገር ጀመሩ። በዚህ ጊዜ ሰላማዊት ለፍቅርተ፥ «ከአለባበስሽ እንደምረዳው፥ አንቺ ጥሩ ክርስቲያን አይደለሽም አለቻት።

ይህ ወደ ትልቅ ፀብ በመለወጡ፥ ሰላማዊትና ፍቅርተ ከመነጋገርና በጸሎት ከመተጋገዝ ታቀቡ። ይባስ ብለውም በጓደኞቻቸው መካከል አንዳቸው ስለሌላቸው መጥፎ ወሬዎችን ያዛምቱ ጀመር።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ጥሩ ክርስቲያን ሊያደርግ በሚችላቸውና በማይችላቸው ነገሮች ላይ የሚከሰተው የአሳብ ልዩነት ክፍፍልን ሲፈጥር የተመለከትከው እንዴት ነው? ለ) ጳውሎስ በሮሜ 14፡1–15፡13 ባስተማረው አሳብ መሠረት፥ ለሰላማዊትና ፍቅርተ ምን ምክር ትሰጣለህ? ሐ) ክርስቲያኖች በአሳብ የሚለያዩባቸውን ሌሎች ልምምዶች ዘርዝር።

ሁልጊዜም ክርስቲያኖች የትኞቹን ልምምዶች ሊያደርጉ እንደሚገባቸው ወይም እንደማይገባቸው በአሳብ መለያየታቸው የማይቀር ነው። በተለይም ልምምዶቹ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በግልጽ ካልተብራሩ። መጽሐፍ ቅዱስ ዝሙት ኃጢአት እንደሆነ በግልጽ ስለሚያስተምር ብዙ ክርስቲያኖች በዚህ ጉዳይ ላይ አይከራከሩም። ነገር ግን ሌሎች ሰላማዊትና ፍቅርተ ያነሡዋቸው ዓይነት ጉዳዮች ቤተ ክርስቲያንን እስከ መከፋፈል ድረስ ይደርሳሉ። ለምሳሌ፥ አንዳንድ ክርስቲያኖች ምንም ዓይነት የአልኮል መጠጥ መጠጣት የለብንም ሲሉ፥ ሌሎች ደግሞ አልኮል መጠጣት ኃጢአት እንዳልሆነ ያስረዳሉ። በክርስቲያኖች መካከል መከፋፈልን የሚፈጥሩትን ጉዳዮች እንዴት ልናስተናግዳቸው ይገባል?

በሮሜ 14፡1-15፡13፥ ጳውሎስ መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ያልጠቀሳቸው ነገሮች የአሳብ ልዩነቶችን በሚያስከትሉበት ጊዜ ክርስቲያኖች እንዴት አንድነታችንን ጠብቀን ልናቆይ እንደምንችል አብራርቷል። በሮምና ከፍልስጥኤም ውጭ ባሉት አብዛኞቹ አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ አይሁዶችና አሕዛብ በአንድ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያመልኩ ነበር። ሁልጊዜም በሁለቱ ወገኖች መካከል የአሳብ ልዩነቶችን የሚያስከትሉ ባሕላዊ ልምዶች ነበሩ። ከእነዚህ ጉዳዮች አንዱ ክርስቲያኖች በገቢያ ውስጥ የሚሸጥ ሥጋ መብላት ይችላሉ ወይ? የሚል ነበር። በገበያ ውስጥ ከሚሸጥ ሥጋ አብዛኛው በሚታረድበት ጊዜ ለጣዖት የተሠዋና ከፊሉ ለጣዖት አምልኮ ያገለገለ ነበር። የተቀረው ገበያ ውስጥ ይሸጣል። የአይሁድ ክርስቲያኖችና አንዳንድ አሕዛብ ክርስቲያኖች ይህን ለአረማዊ ጣዖት የተሠዋ ሥጋ መብላት ትክክል አይደለም የሚል አሳብ አቀረቡ። ለእነርሱ ሥጋውን መብላት በጣዖት አምልኮ እንደ መካፈል ቆጠሩት። ብዙ ክርስቲያኖች ደግሞ ሥጋውን መብላት ምንም ስሕተት መስሎ አልታያቸውም። «ሥጋ ሥጋ ነው። ጣዖታትን በፈቃዳችን እስካላመለክን ድረስ ሥጋውን ልንበላ እንችላለን። ሥጋውን በላን ማለት ጣዖት አመለክን ማለት አይደለም» ሲሉ አስተማሩ። ይህ በገበያ ላይ የሚሸጠውን ሥጋ ስለመብላት የቀረበው ሁለት ዓይነት አመለካከት በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ክፍፍልን አስከተለ። (ይህ በደቡብ ኢትዮጵያ የመስቀል በዓል ምግብ ስለመብላት ከሚነሣው ክርክር ጋር ተመሳሳይ ነው።) ቅዳሜ ወይስ እሑድ ልናመልክ ይገባል? የሚሉ ዓይነት ሌሎች ጉዳዮችም ክፍፍል አስከትለዋል።

ስለሆነም፥ ጳውሎስ የሮሜ ክርስቲያኖች ችግሩን ማስገናገድ እንደሚገባቸው ለሮሜ ክርስቲያኖች ጽፎላቸዋል። (ጳውሎስ ቀደም ሲል ለጣዖት የተሠዋን ምግብ ስለመብላት በ1ኛ ቆሮንቶስ 8-10 ለቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን አብራርቷል። በሮም የተከሰተው ችግር ደግሞ ከሥጋ በተጨማሪ የአምልኮ ቀንንም ያካትት ነበር።)

ጳውሎስ ለሮሜ ክርስቲያኖች ያስተማራቸውን መርሆች መረዳት ጠቃሚ ነው። ሁልጊዜም ጥሩ ክርስቲያኖች ሊያደርጉ በሚገቧቸውና በማይገቧቸው ጉዳዮች ላይ የአመለካከት ልዩነቶች መከሰታቸው የማይቀር ነው። ጳውሎስ የጠቀሳቸውን መሮሆች ካላወቅን በቤተ ክርስቲያናችን ወይም በክርስቲያኖች መካከል ክፍፍል በመፍጠር፥ ከሌሎች ክርስቲያኖች የተሻልን ነን የሚል የትዕቢት አመለካከት በመያዝ፥ ወይም የጥሩ ክርስቲያንነት ማረጋገጫዎች ናቸው የምንላቸውን የ«አድርጉ/አታድርጉ» ትእዛዛት በመዘርዘር ችግሮችን ልንጋብዝ እንችላለን። ሁልጊዜም መጽሐፍ ቅዱስ መንፈሳዊነት የልብ ጉዳይ እንጂ የውጫዊ ተግባራችን መግለጫ አለመሆኑን ያስረዳል። በቀዳሚነት ክርስቲያንነታችንን የምናሳየው በምናደርገው ወይም በማናደርጋቸው ነገሮች ሳይሆን፥ በሮሜ 12-13 እንደተገለጸው ከሌሎች ሰዎች ጋር በምንዛመድበት ሁኔታና በልባችን ዝንባሌዎች ነው።

ከዚህ በታች ጳውሎስ ያስተማራቸው ስምንት ዐበይት እውነቶች ቀርበዋል።

ሀ. ክርስቲያኖች መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ባላስተማረው ጉዳይ ላይ በአሳብ በሚለያዩበት ጊዜ፥ ሁልጊዜም «ደካማ» እና «ጠንካራ» ክርስቲያኖች ይኖራሉ። ደካማና ጠንካራ የሚሉት ቃላት አንዱ ከሌላኛው የበለጠ መንፈሳዊ መሆኑን አያሳዩም። ጳውሎስ እንደሚለው፥ «ደካማ» ክርስቲያኖች መልካም ክርስቲያኖች የተወሰኑ ነገሮችን ማድረግ የለባቸውም የሚል አቋም ሲይዙ፥ «ጠንካሮች» ክርስቲያኖች እነዚህን ነገሮች ለማድረግ እንደተፈቀደላቸው ያምናሉ።

ለ. መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ በማያስተምራቸው ጉዳዮች ላይ የአሳብ ልዩነት በሚከሰትበት ጊዜ፥ ሁለቱም ወገኖች ከእነርሱ በአሳብ የተለየውን ወገን ከመተቸትና መንፈሳዊ አይደለም ከማለት መቆጠብ አለባቸው። መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ባላስተማራቸው ጉዳዮች ላይ ክርስቲያኖች ነጻነት አላቸው። ያለማድረግ (አትክልት ብቻ የመመገብ) ወይም የማድረግ (ሥጋ የመብላት) ነጻነት አለን።

ሐ. ግልጽ ባልሆኑት ጉዳዮች ላይ ተመሥርተን የአንድን ሰው መንፈሳዊ ሁኔታ ከመመዘን የምንጠነቀቅባቸው ሁለት ምክንያቶች አሉ። ሀ) የሰውን ልብና አመለካከት ለመለካት የሚችለው እግዚአብሔር ብቻ ነው። ስለሆነም፥ እውነተኛ መንፈሳዊነት የሚገኝበት ልቡን ስለማናውቅ፥ በአከራካሪ ጉዳዮች ላይ ተመሥርተን ግለሰቡን ልንጠራጠር አይገባም። ለ) የኋላ ኋላ፥ ሁሉም ክርስቲያን የእግዚአብሔር ባሪያ ስለሆነ ተጠያቂነቱ ለእርሱ ነው። አንድ አማኝ በእንዲህ ዓይነቱ ጉዳይ ላይ አቋም እንዲይዝ መምራቱ የቤተ ክርስቲያን ሽማግሌዎች ወይም የሌሎች ክርስቲያኖች ሳይሆን የእግዚአብሔር ኃላፊነት ነው። ፈራጅ ክርስቶስ እንጂ እኛ አይደለንም።

መ. ክርስቲያኖች በአንድ ልምምድ ላይ በሃሳብ በሚለያዩበት ጊዜ፥ በሁለቱም ወገን የሚገኙ ሰዎች በሚያደርጉት ነገር እግዚአብሔርን እያከበሩ ለመሆናቸው እርግጠኞች መሆን አለባቸው። ቢራ መጠጣት ትክክል ነው ብለው ቢያስቡና ቢራ የሚጠጡትን ክርስቲያኖች ምሳሌነት መከተል ቢጀምሩ፥ ዳሩ ግን ልባቸው ውስጥ ጥርጣሬ ካለ ኃጢአትን ሠርተዋል ማለት ነው። ኃጢአትን የሠሩት ቢራ በመጠጣታቸው ሳይሆን ትክክል ስላልሆነውና ስለሆነው ጉዳይ አቋም ባለመውሰዳቸው ነው። ያለ እምነት የምናደርገው ነገር ሁሉ ኃጢአት ነው።

ሠ. የክርስቲያኖች ሁሉ ትልቁ ፍላጎት «እግዚአብሔርን ማስደሰት» ሊሆን ይገባል። ከእሑድ ቀጥሎ ባለው ቀን አምልኮ ለማካሄድ፥ የተወሰነ ምግብ (ለምሳሌ የእስላም ሥጋ፥ የርኩስ እንስሳት ሥጋ) ለመብላት፥ ወይም የተወሰነ ልብስ ለመልበስ ብንፈልግ፥ «በማደርገው ነገር ለእኔ ሲል የሞተውን ክርስቶስን እያስደሰትሁት ነው?» ብለን ልንጠይቅ ይገባል።

ረ. ክርስቲያኖች ሁሉ ለምናካሂዳቸው ልምምዶችና የእኛን ዓይነት እምነት ለማይከተሉ ክርስቲያኖች ለምንይዛቸው አመለካከቶች ተጠያቂዎች እንደምንሆን መገንዘብ አለብን። ሁላችንም በእግዚአብሔር የፍርድ ወንበር ፊት ስለምንቆም፥ ለተግባራችንና ለአስተሳሰባችን ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርብናል።

ሰ. ለክርስቲያኖች አስፈላጊ ከሆኑት ነገሮች አንዱ ፍቅርና ለሌሎች መስጠት ስለሆነ፥ ተግባራችን ሌሎች ክርስቲያኖችን በመጉዳት ወደ ኃጢአት እየመራቸው አለመሆኑን ማረጋገጥ አለብን። በፍቅር መኖር፥ በእምነት ለማደግ መደጋገፍና አንድነትን መፍጠር ከነጻነቶቻችን፥ ከግል መብቶቻችንና እምነቶቻችን በላይ ጠቃሚዎች ናቸው። ቀዳሚው ምስክርነታችንና ክርስቶስን የምናስከብርበት መንገድ የሚገለጸው የግል እምነቶቻችንና መብቶቻችንን በማሳየት ሳይሆን፥ በፍቅራችንና በአንድነታችን ነው።

ሸ. ከየትኛውም ጎሳ ብንመጣ (ለምሳሌ አይሁዳዊ፥ አሕዛብ፥ አማራ፥ ኦሮሞ) ወይም በተለያዩ ልምምዶች ላይ የትኛውንም አቋም ብንይዝ፥ ክርስቶስ ሁለቱንም አቋማት ለሚይዙ ክርስቲያኖች ስለ ሞተ፥ አንድነታችንን ልናጠብቅ ይገባል። የአይሁድ ክርስቲያኖች እነርሱ የማይቀበሏቸውን ነገሮች ስለሚያደርጉ ከአሕዛብ ክርስቲያኖች መለየት አልነበረባቸውም።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) በቅርቡ በቤተ ክርስቲያንህ ውስጥ የተከሰተውን ዐቢይ ክፍፍል ግለጽ። ለ) እነዚህን እውነቶች ተግባራዊ ማድረግ ያንን ክፍፍል በመቀነስ አንድነትን ሊያመጣ የሚችለው እንዴት ነው? ሐ) የተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት ወይም ክርስቲያኖች የሚከራከሩባቸውን ልምምዶች ዘርዝር። ጳውሎስ ባስተማራቸው በእነዚህ እውነቶች መሠረት ክርስቲያኖች ምን ዓይነት ምላሽ ሊሰጡ ይገባል? በእነዚህ ትምህርቶች ምክንያት በሰዎች እምነቶችና ተግባራት ላይ ምን ምን ለውጦች ይከሰታሉ?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

1 thought on “ክርስቲያኖች የተለየ አመለካከት ያላቸውን ክርስቲያኖች የሚያስቀይም ነገር ባለማድረግ ፍቅራቸውን ያሳያሉ (ሮሜ 13፡14-15፡13)”

  1. Pingback: የሮሜ መልእክት ጥናት – ወንጌል በድረ-ገፅ አገልግሎት

Leave a Reply

%d bloggers like this: