የ1ኛ ቆሮንቶስ መልእክት ዓላማ

ጳውሎስ በአብዛኞቹ ሌሎች መልእክቶቹ ውስጥ እንደሚያደርገው፥ በ1ኛ ቆሮንቶስ ውስጥ ለሥነ መለኮታዊ እውነቶች ትኩረት እልሰጠም። በመሆኑም፥ መጽሐፉን በሥነ መለኮታዊና ተግባራዊ ክፍሎች አልከፈለም። (ይህም ከሮሜና ከኤፌሶን መልእክቶች የተለየ ነው።) በ1ኛ ቆሮንቶስ ውስጥ ጳውሎስ ቤተ ክርስቲያኒቱ ለሚያጋጥሟት ችግሮች መፍትሔ በመጠቆሙ ሂደት ላይ ሁሉንም ሥነ መለኮታዊና ተግባራዊ እውነቶች ይዳስሳል።

ጳውሎስ በንድፈ አሳባዊ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩር የሥነ መለኮት ምሁር ሳይሆን፥ አማኞች እንደ ክርስቶስ ተከታዮች በእውነት ላይ ተመሥርተው እንዲኖሩ የሚሻ አገልጋይ ነበር። ጳውሎስ 1ኛ ቆሮንቶስን ከጻፈባቸው ምክንያቶች አንዳንዶቹ የሚከተሉት ናቸው።

  1. የመንፈሳዊ ብስለትን ምንነት ለማስረዳት። መንፈሳዊ ትኩሳት ወይም የጸጋ ስጦታዎች አንድ ክርስቲያን ወይም ቤተ ክርስቲያን በሳልና መንፈሳዊ ጤንነቱ የተሟላ መሆኑን በትክክል አያመለክቱም። ጳውሎስ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ከፍተኛ የጸጋ ስጦታዎች እንደነበሯቸው መስክሯል። (1ኛ ቆሮ. 1፡5-7 አንብብ።) ነገር ግን ከሌሎች ጥንታዊያን አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ የባሰ መንፈሳዊ ትግል አድርገዋል። ስለዚህ ጳውሎስ ለእነዚህ ላልበሰሉና መንፈሳዊያን ላልሆኑ ክርስቲያኖች እንደ ክርስቶስ እንዴት ሊኖሩ እንደሚገባቸው በደብዳቤው ገለጾላቸው (1ኛ ቆሮ. 3፡1-4)። የአንድ ሰው ችሎታ ወይም መንፈሳዊ ስጦታዎች መንፈሳዊነቱን ሊገልጹ እንደማይችሉ ጳውሎስ አካፍሎአል። ይልቁን የአንድ ሰው መንፈሳዊ ብስለት ምልክቱ አንድነት፥ ፍቅርና ለሌሎች ክርስቲያኖች ግድ የሚለው ሲሆን ነው። ጳውሎስ የተወሰኑ ችግሮችን ማለትም እንደ መከፋፈልና ልቅ የግብረ ሥጋ ግንኙነት በተመለከተ ከቤተ ክርስቲያን በደረሰው መረጃ መሠረት መንፈሳዊ ብስለት ምን እንደሆነና መንፈሳዊ ብስለት ያላቸው ሰዎች እንዴት መመላለስ እንደሚገባቸው ለማስረዳት ይጥር ነበር።

የውይይት ጥያቄ፡– ሀ) ዛሬ ምን ያህል ክርስቲያኖች እንደ ልሳንን የመሳሰሉትን መንፈሳዊ ስጦታዎች እንዴት እንደ ዋነኛ የመንፈሳዊ ብስለት ምልክቶች አድርገው እንደሚወስዱና አንድነት፥ ፍቅር፥ ንጽሕና በመሳሰሉት መንፈሳዊ ባሕርያት ላይ እንደማያተኩሩ ግለጽ። ለ) በተወሰኑ መንፈሳዊ ስጦታዎች ላይ ትኩረት ማድረጉ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ አንድነት፥ ፍቅር፥ መንፈሳዊነትና ቅድስና እንዲጨምር አስተዋጽኦ ያደርገ ይመስልሃል? ለምን?

  1. በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚታዩትን ትክክለኛ ያልሆኑ አስተምህሮዎችና ተግባራት ለማረም። ጳውሎስ በኤፌሶን በሚያገለግልበት ጊዜ የተለያዩ ክርስቲያኖች ሊጎበኙት ከቆሮንቶስ መጥተው ነበር። የቀሎዔ ቤተ ሰዎች በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ ስለነበረው ክፍፍል ነግረውታል (1ኛ ቆሮ. 1፡11)። ሦስት ቁልፍ የቆሮንቶስ መሪዎች ለጳውሎስ የተወሰነ ገንዘብና ደብዳቤ አምጥተውለታል። ምናልባትም በቆሮንቶስ ስለነበረው ሁኔታ ዘርዘር ያለ መረጃ ሳይሰጡት አልቀሩም። ስሞቻቸውም እስጢፋኖስ፥ ፈርዶናጥስና አካይቆስ ይባል ነበር (1ኛ ቆሮ. 16፡17)። (ምሁራን እነዚህ ሦስት ሰዎች የቀሎዔ ቤተ ሰዎች ይሁኑ ወይም ሌሎች በርግጠኝነት አያውቁም። አብዛኛዎቹ ግን ከሌላ ወገን ናቸው ይላሉ።) ኤፌሶን ከቆሮንቶስ በጀልባ ለመሄድ ከ300 ኪሎ ሜትሮች በላይ ስለሚርቅና ጳውሎስም በኤፌሶን የጀመረውን እገልግሎት ለማቋረጥ ባለመቻሉ፥ የቆሮንቶስን ቤተ ክርስቲያን ችግሮች ለመፍታት ይህን ጠቃሚ መልእክት ጽፎላቸዋል። ጳውሎስ በዚህ መልእክቱ ያነሣቸው ጉዳዮች የሚከተሉት ናቸው።

ሀ. ቤተ ክርስቲያኒቱን የሚከፋፍሉ ዐበይት ችግሮች ነበሩ። ክርስቲያኖች በክርስቶስ የነበራቸውን አንድነት ዘንግተው በሕይወታቸው ላይ ለውጥ ያመጡትን ወይም ጠቃሚዎች ናቸው ብለው ያሰቧቸውን የተለያዩ መሪዎች ይከተሉ ነበር (1ኛ ቆሮ. 1፡11-12)።

ለ. የጳውሎስን የሐዋርያነት ሥልጣን የሚጠራጠሩ ሰዎች ነበሩ። ስለሆነም፥ ጳውሎስ በኢየሱስ ክርስቶስ ሥልጣን የሚናገር ሐዋርያ መሆኑን ገልጾላቸዋል። ጳውሎስ በ2ኛ ቆሮንቶስ መልእክቱ ስለዚህ ጉዳይ የበለጠ ያስተምራል።

ሐ. ጳውሎስ ምእመናን ግልጽ ወሲባዊ ርኩሰት እንደሚፈጽሙና መሪዎችም በኃጢአት ላይ አቋም ከመውሰድ ይልቅ የግልጽነትና የቸርነት ምልክት ነው በሚል የተሳሳተ ግምት ኃጢአት ሳይቀጣ እንዲቀር ያደርጉ እንደነበር ሰማ።

መ. በተጨማሪም፥ አንዳንድ ክርስቲያኖች ከሌሎች ክርስቲያኖች ጋር በሚጋጩበት ጊዜ ወደ ፍርድ ቤት ይወስዷቸው እንደነበር ሰምቶ ነበር።

ሠ. በጌታ እራት ጊዜ ሰዎች የሚበሉት የሌሏቸውን ድሆች ቸል እያሉ በራስ ወዳድነት ይበሉና ይጠጡ ነበር።

ረ. ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ጥያቄዎች መልስ ሰጥቷል። እነዚህም ጥያቄዎች፥ 1) ክርስቲያን ማግባት አለበት ወይስ በላጤነት መኖር አለበት? 2) ክርስቲያን ለጣዖት የተሠዋውን ሥጋ ከገበያ ገዝቶ መብላት ይችላል? 3) ሴቶች ወደ ቤተ ክርስቲያን ሲመጡ አለባበሳቸው ምን ዓይነት መሆን አለበት? 4) በልሳን መናገር ክርስቲያኖች ሁሉ ሊፈልጉት የሚገባ እጅግ አስፈላጊ ስጦታ ነው ወይስ ሊከለከል ይገባል? 5) ክርስቲያኖች ከሞት ሊነሡ ይችላሉ? 6) ለኢየሩሳሌም ክርስቲያኖች የሚወሰደው ገንዘብ እንዴት መሰብሰብ አለበት?

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ከእነዚህ ጉዳዮች ዛሬም በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ችግር እየፈጠረ ያለው የትኛው ነው? ለ) ለቤተ ክርስቲያን መሪዎች የጳውሎስን መልስ መረዳቱ ጠቃሚ የሚሆነው ለምንድን ነው?

ምሁራን 1ኛ ቆሮንቶስ የጥንቱ ቤተ ክርስቲያን ላጋጠማት ችግር ጥሩ ምሳሌ እንደሆነች ያምናሉ። ምንም ወይም ጥቂት የብሉይ ኪዳን ግንዛቤ የነበራቸው አሕዛብ ወደ ቤተ ክርስቲያን በሚመጡበት ጊዜ፥ የራሳቸውን ባሕላዊ ግንዛቤ ይዘው ነበር የመጡት። ነገር ግን መጽሐፍ ቅዱስ በሁሉም ባሕሎች ላይ በመፍረድ ወደ ራሱ ይመልሳቸዋል እንጂ ራሱን ከየትኛውም ባሕል ጋር እያስማማም። ጳውሎስ ምእመናን እንደ ዓለም አባላት ሳይሆን እንደ እግዚአብሔር መንግሥት አባላት መመላለስ እንዳለባቸው በመግለጽ ያስተላለፈው ትምህርት ከቆሮንቶስ ሰዎች ባሕል ያፈነገጠ ነበር።

ጳውሎስ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ለነበሩት ጉዳዮችና ችግሮች እንዴት መልስ እንደሰጠ አጢን። ለጳውሎስ «እንዲህ አድርጉ አታድርጉ» የሚሉ የትእዛዛት ዝርዝር መስጠት ይቀለው ነበር። ብዙ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ችግሮችን የሚያስተናግዱት በዚህ መንገድ ነው። ትልቁን ግንዛቤያቸውን በመጠቀም፥ ሰዎች እንዲከተሉ የሚፈልጓቸውን ዝርዝር ደንቦች ያወጣሉ። (ወደ ሲኒማ ቤት አትሂዱ፤ ጫት አትቃሙ፤ ፋሽን ልብስ አትልበሱ፤ የከንፈር ቀለም አትቀቡ) የሚሉትን ዓይነት ትእዛዛት ይሰጣሉ። ምንም እንኳ ብዙ ሰዎች የዚህ ዓይነቱን ክርስትና ቢመርጡም፥ ይህ አደገኛ ልምምድ ነው። ሰይጣን እንደዚህ ዓይነት ሰው ሠራሽ ደንቦችን በመጠቀም ሰዎች ከእግዚአብሔር ጋር ግንኙነት ሳያደርጉና ውስጣዊ ለውጥ ሳያካሂዱ በውጫዊ ደንቦች ላይ እንዲያተኩሩ ይገፋፋቸዋል።

ጳውሎስ ግን ለችግሮቹ ምላሽ የሰጠው በተለያዩ ሁኔታዎች ውስጥ ሊያገለግሉ የሚችሉትን መርሆች በማቅረብ ነበር። ክርስቲያኖች በፍርድ ቤት የማይካሰሱት ለምንድን ነው? አንድ ክርስቲያን ለጣዖት የተሠዋ ሥጋ መብላት ያለበት ወይም የሌለበት ለምንድን ነው? በልሳን መናገር የሚከለከለውና የሚፈቀደው ለምንድን ነው? የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች የፈለጉት ዝርዝር ትእዛዛትን ነበር። ጳውሎስ ግን በየትኛውም ሁኔታ ውስጥ ለሚገኙ ክርስቲያኖች ሊያገለግሉ የሚችሉትን አመለካከቶች ሰጥቷቸዋል። ለክርስቲያኖች የሚያስፈልጉት ፍቅርና አንድነት መሆናቸውን አመልክቷል። ራስ ወዳድነት፥ ሌሎችን ከመረዳት ይልቅ የራስን መብት ለማስከበር የሚደረግ ጥረት ሁሉ ትክክል አይደለም። ከእግዚአብሔርና ከሌሎች ሰዎች ጋር ያለንን ግንኙነት የማያደናቅፍ ማንኛውንም ነገር ለማድረግ ነጻነት አለን።

የውይይት ጥያቄ፡– በቤተ ክርስቲያንህ ውስጥ የሚገኝ አንድ ችግር ግለጽ። ሀ) የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ደንቦችን በማውጣት ለችግሩ እልባት ሊሰጡ የሚችሉበትን ሁኔታ በምሳሌ ግለጽ። ለ) መጽሐፍ ቅዱሳዊ መርህ በመፈለግ ችግሩን መፍታት የሚቻለው እንዴት ነው? ሐ) ችግሩን ለመፍታት የትኛው መንገድ ይሻላል? ለምን?

ሌላው በሕግጋትና በደንቦች ላይ ተመሥርቶ ችግሮችን መፍታት ከሁሉም የተሻለ አማራጭ የማይሆንበት ምክንያት፥ ችግሮች ሁልጊዜም የሚለዋወጡ በመሆናቸው ነው። በአንድ ዘመን ተቀባይነት ያልነበራቸው ነገሮች በሌላው ዘመን ተቀባይነት ያገኛሉ (ለምሳሌ፥ ዘመናዊ የሙዞቃ መሣሪያዎችን ለአምልኮ ዝማሬ መጠቀም)። በአንድ ባሕል ተቀባይነት የሌለው ነገር በሌላው ባሕል ተቀባይነት ይኖረዋል (ለምሳሌ፥ የአሳማ ሥጋ መብላት)። ነገር ግን ሁልጊዜም የምንጋፈጣቸው ችግሮች አሉ። ብዙ ዓይነት ችግሮችን ለመፍታት የሚያገለግሉ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መርሆችን በማቅረብ ለአንድ ጉዳይ መፍትሔ በምንሰጥበት ጊዜ መፍትሔው ወደፊት ለሚከሰቱት ሌሎች ችግሮችም የሚሠራ ሆኖ እናገኘዋለን።

  1. ወንጌልን የተቃወሙትን ወይም በተሳሳተ መንገድ የተረዱትን ለማረም። እግዚአብሔር አንድን ክርስቲያን መሪ በከፍተኛ ደረጃ በሚጠቀምበት ጊዜ ብዙውን ጊዜ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚቃወሙት ሰዎች ይነሣሉ። ይህ እውነት በሐዋርያው ጳውሎስ ላይ ደርሷል። በሚሄድበት ስፍራ ሁሉ ከማያምኑ አይሁዶች ተቃውሞ ይደርስበት ነበር። ስለ ክርስትና ከጳውሎስ የተለየ አመለካከት የነበራቸው የተለያዩ የቤተ ክርስቲያን ሰዎችም ተቃውመውታል። ለምሳሌ ያህል፥ አንዳንድ አይሁዳውያን ክርስቲያኖች አሕዛብ በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘት መገረዝና የብሉይ ኪዳን ሕግጋትን መጠበቅ እንደሚገባቸው በመግለጽ የጳውሎስን ትምህርት እንደተቃወሙ ከመልእክቶቹ እንረዳለን።

1ኛ ቆሮንቶስ በተጨማሪም የጳውሎስን ትምህርቶች ስለሚቃወሙት ወይም ከራሳቸው አሳብ ጋር እንዲሄድላቸው ስለሚያጣምሙ የተለያዩ ቡድኖች ያስረዳል። በመጀመሪያ፥ አንድ ሰው የፈለገውን (ኃጢአትንም ጨምሮ) ሊያደርግ እንደሚችል በመግለጽ በክርስቲያኑ ነጻነት ላይ የሚያተኩሩ ነበሩ። በሥጋችን ላይ የምናደርገው ነገር በነፍሳችን ላይ የሚያስከትለው ተጽዕኖ አይኖርም። ትክክል ካልሆነ ደግሞ በኋላ ይቅርታ ልንጠይቅ እንችላለን» ብለው ያስቡ ነበር። በ1ኛ ቆሮንቶስ 5 በወሲብ ኃጢአት ውስጥ የነበረውን ክርስቲያን ለመቅጣት ያልፈለጉት ከዚሁ ስለ ቅድስናና ይቅርታ ከነበራቸው የተሳሳተ ግንዛቤ ሳቢያ ሳይሆን አይቀርም። ሁለተኛ፥ ሌሎች ደግሞ ክርስትና የምንኩስና ዓይነት የአኗኗር ስልት ሊከተል ይገባል ብለው ያስባሉ። ትዳር አለመመሥረትና፥ ከሥጋ ይልቅ አትክልቶችን መመገብ አንድን ሰው የተሻለ ክርስቲያን ያደርገዋል ብለው ያስባሉ (2ኛ ቆሮ. 2፡20-23)። ሦስተኛ፥ አንዳንዶች ደግሞ መንፈስ ቅዱስ የሰጣቸው የልሳን ስጦታ ከሁሉም በላይ እስፈላጊ ስጦታ እንደሆነ ከማመናቸውም በላይ፥ ለአምልኮ በሚሰባሰቡበት ጊዜ የበለጠ ስሜታዊ ከሆኑ የሌሎችን አምልኮ ሲረብሽም እንኳን አምልኳቸው የተሻለ እንደሚሆን ያስቡ ነበር፡፡ ጳውሎስ አማኞች ወንጌሉን፥ እውነተኛውን መንፈሳዊነትና ሁልጊዜም ፍቅር ማሳየትን ይረዱ ዘንድ የእነዚህን የተለያዩ ቡድኖች የተዛቡ አመለካከቶች ለማስተካከል ጥረት አድርጓል።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: