መግቢያ፡- (1ኛ ቆሮ. 1፡1-9)

  1. ጳውሎስ የመጽሐፉ ጸሐፊ መሆኑን ይናገራል (1ኛ ቆሮ. 1፡1)። ሰላምታው በእግዚአብሔር የተመረጠ ሐዋርያ መሆኑን ያመለክታል። ጳውሎስ የክርስቶስ ወኪል ሆኖ ስለሚናገር፥ የቆሮንቶስ አማኞች በጥንቃቄ ሊሰሙት ይገባ ነበር። ምሁራን የጥንቷ ቤተ ክርስቲያን ይህንን መልእክት በአዲስ ኪዳን ውስጥ ማካተቷ ጳውሎስ የእግዚአብሔር ቃል አቀባይ ሆኖ መናገሩን እንደሚያሳይ ያስረዳሉ።
  2. ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን መጻፉን ገልጾአል (1ኛ ቆሮ. 1፡2-3)። ብዙውን ጊዜ የጳውሎስ መግቢያ የደብዳቤውን ትኩረት ያሳያል። ለዚህም ነው በሮሜ መልእክቱ ወንጌል ላይ ያተኮረው። በዚህ ክፍል ጳውሎስ የመልእክቱ ዓላማ ስለ ቅድስና ማብራራት እንደሆነ ገልጾአል። እግዚአብሔር በክርስቶስ የሚያምኑትን ሁሉ ቅዱሳን ብሎአቸዋል። ይሁንና፥ በአኗኗራችን ይህንኑ ቅድስና ማሳየት አለብን።
  3. ጳውሎስ የቆሮንቶስን አማኞች ያመሰግናቸዋል (1ኛ ቆሮ. 1፡4-9)። አብዛኛዎቹ ጥንታዊ ደብዳቤዎች የሚጀምሩት በምስጋና ወይም ጸሐፊው ስለ አንባቢዎቹ እንደሚያስብ በሚያሳዪ ቃላት ነበር። በቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ብዙ ችግሮች ቢኖሩም ጳውሎስ ተስፋ አልቆረጠም ነበር። በአንጻሩ ጳውሎስ እግዚአብሔርን በቆሮንቶስ አማኞች ሕይወት ውስጥ ስለሚሠራው ሥራ ያመሰግነዋል። እግዚአብሔርን ያመሰገነባቸው ምክንያቶችም የሚከተሉት ናቸው።

ሀ. ለቆሮንቶስ ቤተ ክርቲያን ስለ ሰጠው ብዙ በረከት። ምንም እንኳ አማኞቹ ከእነዚህ ስጦታዎች ብዙዎቹን ተገቢ ባልሆነ መንገድ ቢጠቀሙም፥ ስጦታዎቹ ያው የእግዚአብሔር በረከቶች ነበሩ። ከስጦታዎቹ አንዱ የንግግርና የእውቀት ችሎታ ነበር። ችግሩ እማኞቹ ትክክል ባልሆነ እውቀት (ጥበብ) እና በመንፈሳዊ ኩራት ላይ ማተኮራቸው ነበር። ሌላው በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚታዩ መንፈሳዊ ስጦታዎች ነበሩ። ጳውሎስ መንፈስ ቅዱስ ሊሰጣቸው ከፈለገው ስጦታዎች እንድም እንዳልጎደለባቸው ገልጾአል። አሁንም ችግራቸው ለተወሰኑ መንፈሳዊ ስጦታዎች የነበራቸው አመለካከትና ለሰዎች ሁሉ ከማገልገል ይልቅ ለራስ ወዳድነት ዓላማ ለማዋል መፈለጋቸው ነበር።

ለ. የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች የጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን መመለስ ይጠባበቁ ነበር። የሚያስቡትም በዚህ ዓለም ውስጥ እንዴት እንደሚኖሩ፥ እንዴት ብዙ ሀብት፥ ብዙ መሬት የተሻለ ሥራ ወይም ትምህርት እንደሚያገኙ አልነበረም። ዓይኖቻቸውና ልባቸው በኢየሱስ ክርስቶስ መንግሥት ላይ ነበር። ነገር ግን የዚያን መጭ መንግሥት አንዳንድ ዝርዝር ጉዳዮች በተለይም የሙታንን ትንሣኤና በምድር ላይ እያሉ የእግዚአብሔር ዘላለማዊ መንግሥት አካል ሆነው የሚኖሩበትን ሁኔታ በተሳሳተ መልኩ ነበር የተረዱት።

ሐ. ጳውሎስ እግዚአብሔር በልጆቹ ሕይወት ውስጥ ለሚያከናውነው በትዕግሥት የተሞላና ዳሩ ግን ጥብቅ የሆነ ተግባር ልበ ሙሉነት ይሰማው ነበር። እኛ በኃጢአትና በራስ ወዳድነት የተሞላን፥ መንፈሳዊ ብስለትም የጎደለን ልንሆን እንችላለን። ጳውሎስ ግን በእግዚአብሔር ባሕርይ ምክንያት ልበ ሙሉነት ይሰማዋል። እግዚአብሔር ታማኝ ነው። እያንዳንዱን አማኝ ስለመረጠ፥ በኢየሱስ ክርስቶስ ፊት በምንቆምበት ጊዜ እንከን የለሽ እንሆን ዘንድ በሕይወታችን ውስጥ ይሠራል። የቤተ ክርስቲያን መሪዎች እንደ መሆናችን፥ ይህንን ማስታወስ አለብን። ብዙውን ጊዜ ዓይኖቻችን የሚያርፉት በአብያተ ክርስቲያኖቻችን ድክመቶችና በክርስቲያኖች ችግሮች ላይ ነው። ጳውሎስ በእግዚአብሔር ላይ ስላተኮረና በክርስቲያኖች ሕይወት ውስጥ በሚያከናውነው ተግባር ላይ ልበ ሙሉነት ስለተሰማው፥ ዐበይት የቤተ ክርስቲያን ችግሮች በሚታዩበት ጊዜ ሳይቀር በመተማመን ይመላለስ ነበር።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) በቤተ ክርስቲያንህ ውስጥ ያሉትን ችግሮች ዘርዝር። ለ) በእነዚህ ችግሮች ላይ ማተኮር ተስፋ መቁረጥን ወይም ፍራቻን እንዴት ሊያስከትል እንደሚችል ግለጽ። ሐ) እግዚአብሔር በግለሰቦችና አብያተ ክርስቲያናት ሕይወት በመሥራት ስሙን ሊያስከብር በመቻሉ ላይ ብናተኩር አመለካከታችን እንዴት ይቀየራል?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

Discover more from

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading