1ኛ ቆሮንቶስ ጸሐፊ

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) 1ኛ ቆሮንቶስ 1፡1ን አንብብ። ጸሐፊው ማን እንደሆነና ራሱን እንዴት እንደሚገልጽ ተናገር። ) ይህን መግቢያ ከሮሜ 1፡1 ጋር አነጻጽርና ጸሐፊው ስለ ራሱ አጽንኦት ሰጥቶ በጠቀሳቸው ነገሮች መካከል ያሉትን ልዩነቶች ግለጽ።

ጳውሎስ በመልእክቶቹ ሁሉ መጀመሪያ ራሱን፥ «በእግዚአብሔር ፈቃድ የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ ሊሆን የተጠራ ጳውሎስ» ብሎ በማስተዋወቅ ጥንታዊ የደብዳቤ አጀማመር ይከተላል። የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ከሚከፋፈሉባቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ የጳውሎስ ሥልጣን በኢየሩሳሌም ከነበሩት ሐዋርያት ጋር እኩል የመሆኑ ወይም ያለመሆኑ ጉዳይ ነበር። ለዚህም ነበር ሐዋርያው ጴጥሮስ የበለጠ ሥልጣን አለው ብለው ያሰቡት ወገኖች «እኛ የጴጥሮስ ነን» ያሉት። ከ2ኛ ቆሮንቶስ መልእክት አብዛኛው ጳውሎስ ከሌሎች ሐዋርያት ጋር እኩል መሆኑን በመግለጽ የተከራከረበት ነው። ጳውሎስ በ1ኛ ቆሮንቶስ መግቢያው የኢየሱስ ክርስቶስ «ሐዋርያ» መሆኑን በአጽንኦት ገልጾአል። ኢየሱስ ክርስቶስን ወክሎ ለዓለም ሁሉ እንዲያገለግል እግዚአብሔር ነበር ለይቶ የመረጠው። ጳውሎስ ራሱ ሐዋርያ ለመሆን እንዳልመረጠና ራሱን በሚያስደንቀው ሁኔታ እግዚአብሔር እንደመረጠው ገልጾአል። ስለሆነም፥ ጳውሎስ የሚናገረውን አለመስማት ማለት ኢየሱስ ክርስቶስ የሚናገረውን አለመስማት እንደ ማለት ነበር።

ይህ ልናስታውሰው የሚገባን ጠቃሚ እውነት ነው። አንድ ሰው መጽሐፍ ቅዱስን ወይም እንደ ጳውሎስ ያሉ ሰዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሰጧቸውን ትእዛዛት በማይፈጽምበት ጊዜ ሁሉ፥ በእግዚአብሔር ላይ እያመፀ ነው ማለት ነው። እግዚአብሔር የሚናገረውን ለመስማት አይፈልግም ማለት ነው። ዛሬ የምንኖረው፥ ሰዎች ከመጽሐፍ ቅዱስ አሳብ ጋር ወደማይጣጣሙ አስደናቂ ነገሮችና ልምምዶች በሚሳቡበት ዘመን ውስጥ ነው። እነዚህ ልምምዶች ስለሚያስደንቋቸውና መልካም ስለሚመስሏቸው ብዙ ክርስቲያኖች ይከተሏቸዋል። «ይህ ከመጽሐፍ ቅዱስ አሳብ ጋር ይስማማል?» የሚል ጥያቄ በሚያነሡበት ጊዜም ስድብ ይሰነዘርባቸዋል። «ለእኛ ጥሩ ስሜት እንዲሰጠን ያደርጋል። መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሆን አለመሆኑን ልትጠይቀን ምን መብት አለህ? ልምምዳችንን እያበላሸህብን ነው።» የሚል ምላሽ ይሰጣሉ። በዚህ ዓይነት በእግዚአብሔር ትእዛዝና ሥልጣን የጻፉትን የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊያን ከመታዘዝ እንቆጠባለን። ራሳችንንና ሌሎች ሰዎችን ለልምምዶቻችን መመዘኛዎች አድርገን እንወስዳለን። ጳውሎስ የጻፈው መልእክት የግል አሳብ ላይሆን የእግዚአብሔር ቃል እንደሆነ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖችና እኛም እንድንገነዘብ ይፈልጋል። ለመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች አለመገዛት ማለት ለእግዚአብሔር አለመገዛት ነው።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) አንዳንድ ክርስቲያኖች ለእግዚአብሔር ቃል ከመገዛት ይልቅ ከመጽሐፍ ቅዱስ አሳብ ጋር በማይስማሙ አስደናቂ ነገሮች ሲወሰዱ የተመለከትህበትን ሁኔታ ግለጽ። ለ) ይህ ለቤተ ክርስቲያን አደገኛ የሚሆነው ለምንድን ነው? ሐ) አንዳንድ ክርስቲያኖች መጽሐፍ ቅዱስ የሚያቀርበውን ግልጽ ትምህርት እየጣሱ የሚያከናውኗቸውና ሌሎችን ወደ ጥፋት የሚመሩባቸው ነገሮች ምን ምንድን ናቸው? መ) ለብዙ ክርስቲያኖች የአንዳንድ ነገር እውነት መሆን ወይም አለመሆን አሳሳቢ የማይሆነው ለምን ይመስልሃል?

ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ራሱን ያስተዋወቀበት ሁኔታ ከሮሜ ቤተ ክርስቲያን ይልቅ አጠር ያለው ለምንድን ነው? ምናልባትም ይህ የሆነው ጳውሎስ የቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን መሥራች በመሆኑና በዚያ የነበሩት ክርስቲያኖች በሚገባ ስለሚያውቁት ይሆናል። ነገር ግን የሮሜ ክርስቲያኖች ጳውሎስን ስለማያውቁት ማንነቱንና የሮሜን መልእክት የጻፈበትን ሥልጣን በጥንቃቄ አብራርቶላቸዋል።

ጳውሎስ የ1ኛ ቆሮንቶስን መልእክት እንደጻፈ የሚጠራጠሩ ምሁራን ጥቂት ናቸው። 1ኛ ቆሮንቶስ ከተጻፈ ከ40 ዓመታት በኋላ (በ95 ዓ.ም) የሮሜው ክሌመንት የተባለው እውቅ ግለሰብ ይህን መልእክት ጠቅሶታል። በዚያን ጊዜ መልእክቱ እንደ ሮም ባሉት የአሕዛብ አብያተ ክርስቲያናት እየተገለበጠ ተሰራጭቶ ነበር።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: