የሐዋርያትን ምሳሌነት በመከተል መከፋፈልን ማስወገድ (1ኛ ቆሮንቶስ 4፡1-21)

ተመስገን በቅርቡ ከሥነ መለኮት ኮሌጅ የተመረቀ ክርስቲያን ነው። ወደ አካባቢው ሲመለስ የቤተ ክርስቲያኒቱ የአውራጃው መንፈሳዊ አገልግሎቶች ኃላፊ ሆኖ ይሠራ ጀመር። የአውራጃው ቤተ ክርስቲያን፥ መንፈሳዊነት እንዲያድግ ይፈልግ ነበር። «እኔ ዲግሪ ያለኝ ሊቅ ነኝ። ኃላፊነቱም በእጄ ውስጥ ስላለ ሰዎች ምን ማድረግ እንዳለባቸው ልነግራቸው እችላለሁ። እንዲህ ዓይነት ጠቃሚ ዲግሪና እንዲህ ዓይነት አገልግሎት ስላለኝ፥ ሊያከብሩኝና ጥሩ ደመወዝ ሊከፍሉኝ ይገባል። በተጨማሪም፥ በተለይ በወጣቱ ዘንድ ታዋቂ መሆን ስላለብኝ ምንም እንኳ ፕሮግራሞቹ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ባይመሠረቱም እነርሱ የሚወዷቸውን ፕሮግራሞች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ መጀመር አለብኝ» ሲል አሰበ።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) አንዳንድ ጊዜ የተመስገን አስተሳሰብ በሌሎች የቤተ ክርስቲያን መሪዎች የሚታየው እንዴት ነው? ለ) የዚህ ዓይነቱ አመላካከት በቤተ ክርስቲያን ላይ ምን ዓይነት ለውጥ ያመጣል? ሐ) 1ኛ ቆሮ. 4ን አንብብ። ጳውሎስና ተመስገን ለአገልግሎት ያላቸውን አመለካከት አነጻጽር። ጳውሎስ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ መሪነትን በተመለከተ የተመስገንን ዓይነት አመለካከት ላላቸው መሪዎች ምን የሚል ይመስልሃል?

ክርስቲያኖች በቀላሉ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ስላለ አመራር የተሳሳተ መረዳት ሊኖራቸው ይችላል። በተሳሳተ መንገድ ሊረዱ ይችላሉ። ስለ መሪዎች የተሳሳቱ ሃሳቦችን ይዘው ከእገሌ ይልቅ እገሌን እከተላለሁ በሚሉ ምእመናን ምክንያት አንዳንድ ክፍፍሎች ተከስተዋል። አንዳንድ ጊዜም መሪዎቹ ራሳቸው ስለ ክርስቲያናዊ አመራር የተሳሳተ አመለካከት በመያዝ፥ ምእመኖቻቸው እንዲያከብሯቸውና እንዲከተሏቸው ይሻሉ። ይህ ሰይጣን ክርስቲያኖች እንደ እግዚአብሔር ጥበብ ሳይሆን እንደ «ዓለም ጥበብ» እንዲያስቡ ለማድረግ የሚጠቀምበት አንድ አቅጣጫ ነው። ክርስቶስ የቤተ ክርስቲያንን መሪዎች ራሳቸውን እንደ ባሪያዎች እንዲመለከቱ በግልጽ አሳስቧል (ማቴ. 20፡24-28 አንብብ።) ነገር ግን ብዙውን ጊዜ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች የዓለምን ምሳሌነት በመከተል ራሳቸውን እንደ አለቆች ይቆጥራሉ። መጽሐፍ ቅዱስ ግን የሚያተኩረው በአገልጋይ መሪዎች አገልግሎት ላይ ነው። ሰይጣን ግን ብዙውን ጊዜ መሪዎች በሥልጣንና ክብር ላይ እንዲያተኩሩ ያደርጋል። መሪዎቿ ወይም ምእመናኖቿ ስለ አመራር ተገቢውን ግንዛቤ ካልጨበጡ ቤተ ክርስቲያኒቱ ለትልቅ አደጋ ትጋለጣለች።

ለዚህ ነው ጳውሎስ አመራር በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ምን እንደሚመስል የጻፈው። የቤተ ክርስቲያን አመራር ከዓለማዊ አመራር ሙሉ በሙሉ የሚቃረን ስለሆነ፥ ይህንን ትምህርት መገንዘቡ ጠቃሚ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረውን እንጂ በአስተዳደር ዘዴዎች፥ በትምህርትና በሥልጠና ላይ የሚያተኩረውን የዛሬውን ዘመን የዓለም የአመራር ጥበብ እንዳንከተል መጠንቀቅ አለብን። ጳውሎስ ስለ መሪነት የሚከተሉትን እውነቶች አመልክቷል።

ሀ. መሪዎች እንደ ጳውሎስና አጵሎስ የክርስቶስ ባሪያዎች ሲሆኑ፥ የእግዚአብሔርን እውነት በአደራ የተረከቡ ናቸው። መሪዎች ማንን የማክበር ኃላፊነት እንዳለባቸው ማወቃቸው በጣም ጠቃሚ ነው። የመሪዎቹ ጌታ የሽማግሌዎች ቦርድ ወይም አውራጃ ሳይሆን፥ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ለአመራር ተግባራቸውም በኃላፊነት የሚጠይቃቸው ክርስቶስ ነው። ሽማግሌዎችን ለማስደሰት የሚሠራ መሪ የሽማግሌዎች ባሪያ ነው። ምእመናኑን ለማስደሰት የሚሠራ መሪ የቤተ ክርስቲያኒቱ ባሪያ ነው። ዋነኛው ፍላጎታችን ክርስቶስን ማስከበር በሚሆንበት ጊዜ የእርሱ ባሪያዎች እንሆናለን (ገላ. 1፡10ን አንብብ።)።

የቤተ ክርስቲያን መሪዎች አንድ ዐቢይ አገልግሎት አላቸው። የእግዚአብሔር እውነት ተሰጥቷቸዋል። ይህንን እውነት ሊያውቁ፥ ሊኖሩትና ሊሰብኩት ይገባል። ጳውሎስ ብዙ ክርስቲያኖችና የማያምኑት ስለማያውቁት «የእግዚአብሔር ምሥጢር» የሚለውን ይህንኑ የእግዚአብሔርን ቃል እውነት መሪዎች በአግባቡ መጠቀማቸው ወሳኝ ነው። እግዚአብሔር በኃላፊነት የሚጠይቃቸው በዚህ ተግባራቸው ነውና። መሪዎች እንደ ጥሩ አኗኗር፥ ተጨማሪ እውቀት፥ ጥሩ ደመወዝ፥ የፈውስ አገልግሎት፥ የማኅበረሰቡን ተወዳጅነት በመሻት፥ ወዘተ… ከኃላፊነታቸው ሊዘናጉ ይችላሉ። እነዚህ ነገሮች የእግዚአብሔርን ቃል ምሥጢራት ከማካፈል ካደናቀፉአቸው የመሪነት ተግባራቸውን ሊወጡ አልቻሉም ማለት ነው።

ሰዎችን የሚያስደንቅ የጸጋ ስጦታ ያላቸውም ሆኑ ተራ የሚመስሉ መሪዎች በእኩል ደረጃ የእግዚአብሔር አገልጋዮች ናቸው። ስለሆነም አንዱን በመውደድና ሌላውን በመጥላት መሪዎችን የማወዳደር መብት የለንም።

ለ. እግዚአብሔር ከመሪዎች የሚፈልገው ዋናው በሕርይ ታማኝነት ነው። የአንድ መልካም መሪ ዋነኛ ባሕርይ ጥበብ፥ የባሕርይ ጽናት፥ ጥሩ የጊዜ አጠቃቀም ወይም የአመራርና አስተዳዳር ችሎታ አይደለም። ጳውሎስ ታማኝነት ከሁሉም እንደሚበልጥ ያስረዳል። ለቤተ ክርስቲያን፥ ለሽማግሌዎች ታማኝ መሆኑ አስፈላጊ ነው። ከሁሉም በላይ ግን እግዚአብሔር የወንጌሉን እውነት እንዲሰብኩ የሰጣቸውን «አደራ» በመወጣት መሪዎች ታማኝነታቸውን ማረጋገጣቸው ወሳኝ ነው።

ሐ. ዋናው ነገር የመሪው ታዋቂነት አይደለም። ጳውሎስ ውጤታማነቱን የለካው የቆሮንቶስ አማኞች ታላቅ መሪ ነው ብለው በማሰባቸው ላይ ተመሥርቶ አልነበረም። ነገር ግን እግዚአብሔር በሰጠው ችሎታና ስጦታ አማካኝነት ጥሪውን በትክክል ለመፈጸሙ ሕሊናው ይመሰክርለት ነበር። ጳውሎስ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ምስጋናም ሆነ ወቀሳ አገልግሎትን ለመመዘን የሚጠቅም ዋነኛ ጉዳይ ነው የሚል ግምት አልነበረውም። ይህ ዘላለማዊ ሁኔታውን ሊለውጥ አይችልም ነበር። ነገር ግን ጳውሎስ የወንጌሉን እውነት በመስበኩ በኩል ምን ያህል የታማኝነት ተግባር እንዳከናወነ በዘላለም ፈራጅ ፊት የሚመዘን መሆኑን ያውቅ ነበር። ዋናው ነገር ደግሞ ይሄ ነበር። እግዚአብሔር ሰዎች የሚመለከታቸውን ውጫዊ ነገሮች (ርቱዕ አንደበት፥ የሰዎችን ስሜት ማስደሰት፥ ታዋቂነት፥ ትምህርት) አልፎ ልብን ያያል። ከመሪዎች ተግባር በስተጀርባ ያለውን የተነሣሽነት ምክንያት ያያል። እግዚአብሔር እንዲያከብረን የማያደርጉት ወይም የሚያደርጉት እነዚህ የተነሣሽነት ምክንያቶች እንጂ ሰዎች የሚመለከቷቸው ውጫዊ ተግባራት አይደሉም።

መ. ለሁሉም ክርስቲያኖችና መሪዎች ስጦታዎችን የሚሰጣቸው እግዚአብሔር ነው። ችሎታውን ያገኙት የበለጠ ስለተማሩ፥ የበለጠ መንፈሳውያን ስለሆኑ፥ ተግተው ስለሚሠሩ ወይም ከሌላው ሰው የተለዩ ስለሆኑ አይደለም። ስለሆነም በችሎታቸው ወይም በታዋቂነታቸው ሊመኩ አይገባም። ከእነርሱ ያነሰ ችሎታ ያላቸውን ሰዎች መናቅ የለባቸውም። ከእነርሱ የበለጠ ችሎታ ባላቸው ሰዎችም ላይ ሊቀኑ አይገባም።

ሀ. የቤተ ክርስቲያን መሪነት መንገድ ብዙውን ጊዜ ብዙ ጥቅሞችን ሳይሆን ብዙ ሥቃዮችን ያስከትላል። ጳውሎስ የራሱን ሕይወት ከቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ሕይወት ጋር አነጻጽሯል። ጳውሎስ ከአሥራ ሦስቱ እጅግ ወሳኝ የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች አንዱ የሆነ ሐዋርያ ነበር። ነገር ግን በጦርነት ከተማረኩ በኋላ ሕዝብ እንዲያያቸውና በኋላም እንዲገደሉ ወደ ስታድዬም እንደሚወሰዱ የዘመኑ ወታደሮች ፥ እርሱም ለመሳለቂያነት መዳረጉን ያስረዳል። ጳውሎስም ሆነ ሌሎች ሐዋርያትና የቤተ ክርስቲያን መሪዎች የመከራ ሕይወት ከመግፋት አልፈው እንደ ጠቢብና ባለጸጋ ሊከበሩ አልቻሉም ነበር። ሰዎች እንደሚያሳድዷቸውና እንደሚቀልዱባቸው ለማኞች ነበሩ።

በአንጻሩ፣ የቆሮንቶስ አማኞች ቀላልና ምቹ ሕይወት ይመሩ ነበር። ብዙ ገንዘብ ነበራቸው። ልጆቻቸው የተሻለ የትምህርት ዕድል ያገኙ ነበር። የተሻለ ቤት፥ የተሻለ ገቢ፥ ወዘተ… ነበራቸው። ጳውሎስ ይህ ትክክክል አይደለም እላለም። እርሱ የሚለው መሪዎችና መእመናን አብረው ሊያድጉ ይገባል ነው። የቤተ ክርስቲያን ምእመናን ለመሪዎቻቸው በቂ ደመወዝ እለመክፈላቸውና እነርሱ እየበለጸጉ መሪዎች በኑሮ ሲቸገሩ ይሄ ለእግዚአብሔር ነገሮች ብዙም ትኩረት አለመስጠታቸውን ያሳያል። በሌላ በኩል፥ መሪዎቹ ከምእመናን የበለጠ ደመወዝ ማግኘታቸውና ምእመኖቻቸው የገንዘብ ችግር እያጋጠማቸው እነርሱ እየከበሩ መሄዳቸው ይሄም በእግዚአብሔር ዓይኖች ፊት ትክክል አይደለም። ነገር ግን የመሪነት ወይም የወንጌላዊነት ሕይወት ተጨማሪ በረከትን ሳይሆን ተጨማሪ ሥቃይን እንደሚያስከትል ጳውሎስ ከራሱ ሕይወት ጠቅሶ አስረድቷል። ይህም ሙሉ ለሙሉ መጥፎ አይደለም። ምክንያቱም የቤተ ክርስቲያን አመራር ከከባድ ሥቃይ ይልቅ ብዙ ጥቅም የሚያስገኝ ቢሆን ኖሮ ሰዎች የተሳሳቱ ምክንያቶች እያቀረቡ መሪዎች ለመሆን ይፈልጉ ነበር።

ረ. አብያተ ክርስቲያናት ለመሪዎች፥ በተለይም እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን ለመትከል ለሚጠቀምባቸው አገልጋዮች ልዩ ክብር መስጠት አለባቸው። የቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን የበለጠ ስጦታ ያለው ሰባኪ በሚመጣበት ጊዜ በእርሱ ላይ ከመሳለቅ ይልቅ ጳውሎስን ማክበር ነበረባት።

ሰ. መሪነት በቀዳሚነት ተግባራዊ የሚሆነው ከቃላት ይልቅ በሕይወት ምሳሌነት ነው። ብዙውን ጊዜ የተማሩ ወጣቶች ለመሪነት ይሾማሉ። ነገር ግን የክርስቶስ አርአያ ለመሆን የሚያበቃ ብስለት የላቸውም። ስለሆነም፥ ስለ መሪነት የተሳሳቱ አመለካከቶችን በሚያንጸባርቁበት ጊዜ ልንፈርድባቸው አይገባም። ለመሪነት ወሳኙ ቅድመ ሁኔታ መንፈሳዊ ብስለት ሲሆን፥ ይህም ብዙ ጊዜ የሚወስድ ሂደት ነው። ጳውሎስ ልቡም ሆነ ተግባራቱ ትክክል መሆናቸውን ስለሚያውቅ፥ «እኔን ምሰሉ» ለማለት ችሏል (1ኛ ቆሮ. 4፡16)። ምእመኖቻችን መንፈሳውያን እንዲሆኑ፥ በመንፈሳዊ ሕይወታቸው እንዲያድጉ፥ እንዲቀደሱና ስለ አመራር ተገቢውን ግንዛቤ እንዲያገኙ ከፈለግን እኛ መሪዎች ይህንን እንዴት እንደሚያከናውኑ ማሳየት አለብን። በራስ ወዳድነትም ይሁን ለእግዚአብሔር ክብር አመራር በምንሰጥበት ጊዜ የእኛን ምሳሌ ይከተላሉ።

ሸ. ጳውሎስ ሐዋርያ እንደ መሆኑ «በትር» ሲል የገለጸው ልዩ ሥልጣን ነበረው። ጳውሎስ ይህን ሥልጣኑን በዓመፀኞች የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ላይ ፍርድን ለማምጣት ሊጠቀም እንደሚችል ገልጾአል። ነገር ግን ንስሐ ገብተው አመለካከታቸውንና ተግባራቸውን ከቀየሩ በፍቅርና በገርነት እንደሚመጣላቸው አስታውቋል።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) የተመስገን ቤተ ክርስቲያን ሽማግሌ ነህ እንበል። ጳውሎስ በ1ኛ ቆሮንቶስ 4 ስለ አመራር የገለጻቸውን አሳቦች በመጠቀም፥ ተመስገንን እንዴት ትመክረዋለህ? ለ) የቤተ ክርስቲያን አመራር አመለካከታቸውን መለወጥ የሚያስፈልጋቸው አንዳንድ መሪዎች አሉ? በዚህ ክፍል ውስጥ ስለ መሪነት የተማርኸውን እንዴት በአግባቡ ልታካፍላቸው ትችላለህ?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: