ጳውሎስ ስለ ዝሙት ተጨማሪ ትምህርት ሰጠ (1ኛ ቆሮ. 6፡9-20)

ጳውሎስ በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ ስለተከሰተው የዝሙት ኃጢአት ያቀረበውን ገለጻ ከፈጸመ በኋላ፥ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የትኛውንም ዓይነት ወሲባዊ ኃጢአት ማድረግ ስሕተት የሆነባቸውን ምክንያቶች ያብራራል።

ሀ. በማያቋርጥ ወሲባዊ ኃጢአት የሚኖሩ ሰዎች እውነተኛ የእግዚአብሔር ልጆች አለመሆናቸውን ስለሚያሳዩ፥ ወደ ዘላለማዊ የእግዚአብሔር መንግሥት ሊገቡ አይችሉም። በክርስቶስ በምናምንበት ጊዜ አሮጌው ሕይወታችን ተለውጦ አዲስ ሕይወት እንጀምራለን። ወሲባዊ ሕይወታችን ስለሚለወጥ ዝሙት፥ ሴተኛ አዳሪነትና ግብረ ሰዶማዊነት ከመፈጸም እንቆጠባለን። አምልኳችን ስለሚለወጥ እንደ ቀድሞው ጣዖት አናመልክም። (በሌላ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ከእግዚአብሔር በላይ የምንወደው ነገር ሁሉ ጣዖታችን እንደሆነ ተገልጾአል። ቆላ. 3፡5 አንብብ።) ከሌሎች ሰዎች ጋር ያለን ግንኙነት ይለወጣል። ሌሎች ሰዎችን በመስረቅ ወይም በማታለል (በመንጠቅ) ለመክበር አንፈልግም። በተጨማሪም፥ ሌሎችን ከመርዳት ይልቅ ነገሮችን ለራስ ማግበስበሱ የራስ ወዳድነት ኃጢአት ነው። የሰዎችን ስም በማጉደፍ ዝናቸውን ለማክሰም አንፈልግም። ከራሳችን ጋር ያለ ግንኙነትም ስለሚለወጥ ከእንግዲህ የመጠጥ ባሪያዎች አንሆንም። ምንም እንኳ ከማመናቸው በፊት በዚህ ዓይነት ላይኖሩ ቢችሉም፥ ጳውሎስ የቀድሞው አኗኗር እንዳበቃ ገልጾላቸዋል። በክርስቶስ ባመኑበት ወቅት የክርስቶስ ደም ከእነዚህ ኃጢአቶች አጥቧቸዋል። እናም በደሙ ተዋጅተዋል። ደሙ ለአዲስ ሕይወት ለይቷቸዋል (ቀድሷቸዋል)። ጥፋተኛ አይደላችሁም ተብለዋል፣ ጸድቀዋል)። እነዚህ ሦስቱ የክርስቶስና የመንፈስ ቅዱስ ሥራዎች ሕይወታቸውን ሙሉ በሙሉ ለውጠዋል።

ለ. ኃጢአትን የሚፈጽሙ ሰዎች ስለሚቆጣጠራቸው ነገር የተለያየ አመለካከት ይኖራቸዋል። ምናልባትም ጳውሎስ በኃጢአት እየተመላለሱ «ሁሉም ተፈቅዶልኛል» የሚሉትን አንዳንድ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች አባባል ጠቅሶ እየተናገረ ይሆናል። «እኛ በክርስቶስ ነፃ ነን። ከሕግ በታች ስላልሆንን እንደፈለግን ልንኖር እንችላለን» ሲሉ ተሟገቱ። ጳውሎስ ለዚህ ክርክር በተለያዩ መንገዶች ምላሽ ሰጥቷል።

  1. መጠየቅ ያለብን ጥያቄ «የተፈቀደልኝ ምንድን ነው?» የሚል ሳይሆን የሚጠቅመው የቱ ነው የሚለውን ነው። በሙያዊ ይዘታቸው ኃጢአት ያልሆኑና ለእኛ የማይጠቅሙ ነገሮች ሊኖሩ ይችላሉ። ስለሆነም፥ ለእኛ መልካም ያልሆኑትንና ክርስቲያናዊ ምስክርነታችንን የሚያጠፉትን ነገሮች ከመፈጸም መቆጠብ ይኖርብናል። እንደ ክርስቲያኖች እንድናድግ በሚረዱንና ለክርስቶስ ክብርን በሚያመጡ ነገሮች ነጻነታችን ሊገደብ ይገባል።
  2. ምንም ነገር ሰውነታችንን እንዲቆጣጠር መፍቀድ የለብንም። ሰውነታችን ለእግዚአብሔር ክብር የተሠራ መሆኑን መገንዘብ አለብን። በክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ በመተባበራችን ከሥጋ ፍላጎት ቁጥጥር ነፃ ወጥተናል። ስለሆነም፥ እነዚህ ክፉ ፍላጎቶች ሊቆጣጠሩን አይገባም። ሆዳምነት (የምግብ ፍቅር)፥ ወሲብ፥ ዕፅ፥ መጠጥ፥ ገንዘብ፥ ትምህርትን በመሳሰሉት ቁጥጥር ሥር መዋሉ ትክክል አይደለም። ከእነዚህ ነገሮች አንዱም እንኳ ቢቆጣጠረን ኃጢአት ነው። አንድ ቀን ሰውነታችን ፈርሶ ሌላ አካል ይሰጠናል። ስለሆነም፥ ወደ ኃጢአት የሚመሩ ወይም እግዚአብሔርን የማያስከብሩ ነገሮችን በማድረግ ለጊዜው ፍላጎቶቻችንን ከምናሟላ ይልቅ ዘላለማዊ ጠቀሜታ ያላቸውን ነገሮች ልንፈጽም ይገባል።
  3. ክርስቲያኖች የክርስቶስ አካል የራሱ ከፍሎች ናቸው። ስለሆነም፥ አንድን ተግባር በምንፈጽምባት ጊዜ ክርስቶስንም የዚያ ድርጊት ተሳታፊ እናደርገዋለን። ለእግዚአብሔር ምስጋናን ስንዘምር፥ ይህ ክርስቶስ ለእግዚአብሔር ምስጋናን የሚዘምርበት ዓይነት ነው። ስንመሰክር ክርስቶስ እንደሚመሰክር ነው፥ ለድሀ ስንመጸውት ይህ ክርስቶስ ለድሃ እንደሚመጸውት ያህል ነው። ጳውሎስ እንደሚለው፥ ከክርስቶስ ጋር ስለተባበርን የምናደርገው ክፉም ሆነ ደግ ተግባር ክርስቶስን ያሳትፈዋል (በሐዋርያት ሥራ 9፡4 ክርስቶስ ክርስቲያኖችን ማሳደድ እርሱን እንደ ማሳደድ መሆኑን በገለጸበት መልኩ ይህንኑ እውነት እንመለከታለን።)
  4. ጳውሎስ ወሲባዊ ኃጢአት ለፈጻሚው እንደ ውሸት ካሉት ሌሎች ኃጢአቶች የከፋ መዘዝ እንደሚያስከትል አመልክቷል። ጳውሎስ ይህን ሲል ምን ማለቱ እንደሆነ እርግጠኞች አይደለንም። ምናልባትም ወሲባዊ ኃጢአት ከሌሎች ኃጢአቶች በበለጠ ባሕሪያችንን፥ ቤተሰባችንና ጤንነታችንን እንደሚጎዳ መግለጹ ይሆናል። ዛሬ ሰዎችን የሚያሠቃዩ እንደ ኤድስ ያሉ በሽታዎች የወሲባዊ ኃጢአት ውጤቶች ናቸው።
  5. ወሲባዊ ኃጢአት የመንፈስ ቅዱስን ቤተ መቅደስ ያረክሰዋል። በቆሮንቶስ አረማዊ አምልኮ ወሲባዊ ኃጢአት የጣዖት አምልኮ አካል ነበር። ለክርስቲያኖች ግን እውነቱ የተገላቢጦሽ ነበር። እግዚአብሔር በብሉይ ኪዳን ዘመን በመገናኛው ድንኳንና በቤተ መቅደስ ውስጥ ይኖር እንደነበረ ሁሉ፥ መንፈስ ቅዱስ በእኛ ውስጥ እንደሚኖር እያንዳንዱ አማኝ መገንዘብ አለበት። ክርስቲያኖች ሁሉ ይህንን ሊያውቁ ይገባል። የአማኞች ኅብረት የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያ ስለመሆኑ ከሚናገረው 1ኛ ቆሮ. 3፡16 በተለየ መንገድ፥ ይህ ምንባብ እያንዳንዱ አማኝ የመንፈስ ቅዱስ ቤተመቅደስ በመሆኑ ላይ ያተኩራል። ለዚህም ምክንያቱ ኃጢአት ቢሠሩም እንኳ መንፈስ ቅዱስ በክርስቲያኖች ሕይወት ውስጥ የሚኖር መሆኑ ነው። እግዚአብሔር ቅዱስ አምላክ ስለሆነ፥ ማደሪያዎቹ የሆኑት ክርስቲያኖች እንዲቀደሱለት ይፈልጋል። ይህም በብሉይ ኪዳን ዘመን ሕዝቡ በተቀደሰ ሕይወት እንዲያመልከው ከተጠየቀበት ሁኔታ ጋር ተመሳሳይ ነው።
  6. ወሲባዊ ኃጢአት የማን መሆናችንን እንድንዘነጋ ያደርጋል። ጳውሎስ እንደሚለው፥ የእግዚአብሔር ልጆች ከሆንን በራሳችን ሕይወት ላይ መብት አይኖረንም። ክርስቶስ በመስቀል ላይ በመሞት ገዝቶናል። ስለሆነም ክርስቶስ በሕይወታችን ላይ መብት ስላለው እርሱ የሚፈልገውን ማድረግ አለብን። ሰውነታችንንና ሰውነታችንን የምንጠቀምበትን ሁኔታ ሊቆጣጠር የሚገባው በባለቤትነት የሚያስተዳድረን ክርስቶስ ነው። የክርስቶስ ትልቁ ፍላጎት እግዚአብሔርን ማስከበር ስለሆነና ሰውነታችንን ለእግዚአብሔር ክብር ለመጠቀም ስለሚፈልግ፥ ተግባራችን ሁሉ ለእግዚአብሔር ክብርን ማምጣት አለበት። ወሲባዊ ኃጢአት እግዚአብሔርን አያስከብርም። ስለሆነም፥ የክርስቶስ የሆነውን ሰውነታችንን እርሱ ለማይፈልገው ተግባር መጠቀሙ ትክክል አይሆንም።

የውይይት ጥያቄ፡– ሁለት ወጣቶች ወደ አንተ መጥተው፥ «እርስ በርሳችን እንፋቀራለን» በሚቀጥሉት ሦስት ወራት ውስጥ ጋብቻችንን ስለምንፈጽም አብረን መተኛት ብንጀምር ምን ይመስልሃል? ይሄ ማንንም አይጎዳም» ቢሉህ፥ ጳውሎስ ስለ ወሲባዊ ኃጢአት ካስተማረው በመነሣት ምን ብለህ ትመክራቸዋለህ?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: