ሕዝብ በሚሰበሰብበት ይፋዊ አምልኮ ላይ የሴቶችና ወንዶች ትክክለኛ አለባበስ ምን ዓይነት መሆን አለበት? (1ኛ ቆሮ. 11፡2-16)።

1ኛ ቆሮንቶስ 11-14 ብዙ ሕዝብ ስለሚካፈልበት ይፋዊ አምልኮ ይናገራል። በመጀመሪያ፥ ጳውሎስ በአምልኮ ጊዜ ተገቢውን የአለባበስና የባሕርይ ሥርዓት መከተል እንደሚያስፈልግ ያስረዳል (1ኛ ቆሮ. 11፡2-16)። ሁለተኛ፥ በጌታ እራት ላይ የሚከሰቱትን ችግሮች ለማረም ይፈልጋል (1ኛ ቆሮ. 11፡17-34)። ሦስተኛ ጳውሎስ ስለ መንፈሳዊ ስጦታዎች፥ በተለይም በልሳን ስለመናገር ክርስቲያኖች የነበሯቸውን የተሳሳቱ ግንዛቤዎች ለማረም ይፈልጋል (1ኛ ቆሮ. 12፡14)።

የውይይት ጥያቄ፡- 1ኛ ቆሮ. 11፡2-16 አንብብ፡፡ ሀ) እግዚአብሔር የመሠረተውን የሥልጣን ቅደም ተከተል ዘርዝር። ለ) ስለ ወንዶችና የአለባበስ ሥርዓት የተሰጠውን ድንጋጌ ግለጽ። ሐ) ስለ ሴቶችና የአለባበስ ሥርዓት የተሰጠውን ድንጋጌ ግለጽ።

1ኛ ቆሮንቶስ 11፡2-16 ዛሬ እንዴት ተግባራዊ ሊሆን ይገባል? የሚለው ጥያቄ በምሁራን መካከል ከፍተኛ ክርክሮችን አስከትሏል። ጳውሎስ ሴቶች ራሳቸውን እንዲሸፍኑና ወንዶች ጸጉራቸውን እንዲያሳጥሩ የሰጠው ሕግ ዛሬም ይሠራል? ወይስ ይህ በጳውሎስ ዘመን የነበረ ባሕላዊ ጉዳይ በመሆኑ ዛሬ ዝርዝር ደንቦቹን ሳይሆን መርሆዎቹን ብቻ ተግባራዊ የምናደርግበት ነው? ጳውሎስ ሴቶች ፀጉራቸውን እንዲሸፋፈኑ በማዘዝ የሰጠው ድንጋጌ እርሱ የነበረበትን ዘመን እንጂ የእኛን ዘመን የማይመለከት ከሆነ፥ ወንድ ከሴት የመብለጡም ጉዳይ ባሕላዊ መሠረት ያለውና ተመሳሳይ ግንዛቤ የሚያሻው ነው? ይህንን ምዕራፍ አስቸጋሪ የሚያደርገው ስለ ጥንት ሰዎች ባሕልና ጳውሎስ ይህን ጉዳይ ለማንሣት የተገደደበትን ምክንያት አለማወቃችን ነው። ጳውሎስ በቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንደነበሩ የሰማቸውን ችግሮችና ቤተ ክርስቲያኒቱ ያነሣቻቸውን ጥያቄዎች ለመመለስ ጥረት በማድረግ ላይ ነበር። ስለሆነም፥ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች በአምልኮ ወቅት ሊለበሱ ስለሚገባቸው ተገቢ ልብሶች የጠየቁት ይመስላል።

እንደ ሌሎች ምንባቦች ሁሉ፥ የዛሬውን ዘመን አለባበስ ሳይሆን የጥንቱን ዘመን ባሕላዊ ልምምዶች ለመረዳት መሞከር ይኖርብናል። በጥንት ጊዜ ሰዎች ቦላሌ ሱሪዎችን፥ ሸሚዞችን፥ ጫማዎችን፥ ቀሚሶችን፥ ወዘተ አይለብሱም ነበር። በጳውሎስ ዘመን ለሴቶች ተለምዷዊ አለባበስ ሁለት ባሕላዊ መመዘኛዎች ነበሩ። (በእስያና መካከለኛው ምሥራቅ) ሴቶች በአደባባይ ወይም ከእንግዶች ጋር በሚሆኑበት ጊዜ ፊታቸውን የመሸፋፈን ልማድ ነበራቸው (ዘፍጥ. 24፡65)። በግሪክ ግን ሴቶች የራስ መሸፋፈኛ አልነበራቸውም። ምሁራን በ1ኛ ቆሮንቶስ ውስጥ የተገለጸው የራስ መሸፈኛ ጭንብልን ወይም ረዥም ፀጉርን ስለማመልከቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ተመራማሪዎች ይከራከራሉ።

በተጨማሪም፥ ምሁራን የዚህ ምዕራፍ ዋነኛ ጉዳይ ሴቶች ራሳቸውን ሳይሸፋፈኑ ወደ ቤተ ክርስቲያን መሄዳቸው ይሆን? ወይስ ፀጉራቸውን ሸብ አድርገው ሳያስሩ ከትከሻቸው ላይ ማዘናፈላቸው ይሆን? በሚለውም አሳብ ላይ ይከራከራሉ። ጳውሎስ የሚናገረው ረዥም ፀጉር ስላላቸው ምዕራባውያን ሴቶች እንጂ ስለ አፍሪካውያን ሴቶች አልነበረም። ፀጉራቸውን ሳያስይዙ ማዘናፈል በጥንት ባሕል አንድም የአልቃሽነት ወይም የዘማዊነት ምልክት ነበር።

የትኛውንም አመለካከት ብንቀበል፥ ከዚህ በፊት ታይቶ የማይታወቅ ነጻነትና አክብሮት ያገኙት አንዳንድ የቆሮንቶስ ሴቶች ከባሕላቸው ያፈነገጡ ይመስላል። ቤተ ክርስቲያን ከእንግዲህ «ወንድ፥ ሴት፥ ባሪያ ወይም ነፃ ሰው» የለም፥ ሁሉም በክርስቶስ አንድ ሰው ናቸው ብላ ታስተምር ነበር (ገላ. 3፡28 አንብብ።) የራስ መሸፈኛ ማድረግን ወይም ፀጉራቸውን ማስያዝ አቆሙ። ይህ ደግሞ በዘመኑ ባሕል ተቀባይነት አልነበረውም። ስለሆነም ጳውሎስ ሴቶች አዲሱን ነጻነታቸውን ባሕላቸው በማይፈቅደው መንገድ መጠቀም እንደሌለባቸው ያስረዳል። ጳውሎስ ባሕላቸውን አክብረው ሊለብሱና በአደባባይ ከመናገር ሊቆጠቡ እንደሚገባቸው ገለጻ (1ኛ ቆሮ. 14፡34)።

ይህን ምንባብ በጥንቃቄ በምናጠናበት ጊዜ የሚከተሉትን ነገሮች እንረዳለን።

  1. እግዚአብሔር የሥልጣንን ቅደም ተከተልና አስተዳደር አዋቅሯል። ከሁሉም የሚበልጠው ባለሥልጣን እግዚአብሔር አብ ሲሆን፥ ከእርሱ ቀጥሎ ከርስቶስ ነው። (እዚህ ባይጠቀስም፥ ቀጣዩ መንፈስ ቅዱስ መሆኑን ከሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች እንረዳለን።) ቀጣዩ ወንድ ሲሆን፥ ሴት የመጨረሻውን ስፍራ ትይዛለች። ጳውሎስ ይህን የሥልጣን ቅደም ተከተል «ራስ» ይለዋል። አንዳንድ ምሁራን «ራስ» ከበላይ ያለ አካልን ማክበርን የሚያመለክት ነው ይላሉ። ስለሆነም፥ ሴት ወንድን፥ ወንድ ክርስቶስን፥ ክርስቶስ ደግሞ እግዚአብሔር አብን ማክበር አለበት ይላሉ። ሌሎች ራስ የሚለው ቃል ሥልጣንን እንደሚያመለክት ይናገራሉ። ስለሆነም፥ የእግዚአብሔር የሥርዓት ቅደም ተከተል ከእግዚአብሔር አብ ወደ ክርስቶስ ከዚያ ወደ ወንድና ብሎም ወደ ሴት እንደሚተላለፍ ያስረዳሉ። ይህ የሥልጣን ቅደም ተከተል በአምልኮ ውስጥ በተለያዩ ባሕሎች ሊገለጥ የሚችለው እንዴት ነበር? ይህ ወንዶች ባርኔጣቸውን በማውለቅና ፀጉራቸውን በአጭሩ በመቆረጥ እግዚአብሔርን ማክበር እንደነበረባቸው ያመለክታል። ሴቶች በአምልኮ ሰዓት ራሳቸውን በሻሽ፥ መጎናጸፊያ አልያም በረጅም ፀጉር መሸፈን እንደነበረባቸው ያመለክታል።

ስለዚህ ምንባብ የትኛውንም እመለካከት ብንከተል፥ ጳውሎስ ሴቶች ከወንዶች ያንሳሉ ማለቱ እንዳልሆነ መገንዘብ ይኖርብናል። በተቃራኒው ግን ስለ እግዚአብሔር የአስተዳደር ሥርዓት መግለጹ ነበር። ክርስቶስ ከእግዚአብሔር አብ ጋር በባሕርይና በኃይል የሚስተካከል ፍጹም አምላክ ሆኖ እያለ በሥልጣን ተዋረድ ከእግዚአብሔር አብ በታች እንዳለ ሁሉ፥ ሴቶችም በባሕርይና በጠቀሜታቸው ከወንዶች እኩል ናቸው። ነገር ግን ሴቶች በወንዶች አስተዳደር ሥር ይኖራሉ። ጳውሎስ የወንዶችና የሴቶች ግንኙነት በእግዚአብሔር አብና በእግዚአብሔር ወልድ መካከል ባለው ግንኙነት ምሳሌነት የተዘጋጀ መሆኑን አመልክቷል።

  1. የቤተ ክርስቲያን አምልኮ የአካባቢውን ባሕል ያንጸባርቃል። ትክክለኛ ያልሆነ አለባበስና ባሕርይ ወንጌሉን በማሰደብ ሰዎች ስለ ክርስትና የተሳሳተ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ስለሚያደርግ፥ ክርስቲያኖች ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር የማይቃረኑትን ባሕላዊ መመዘኛዎች መከተል ይኖርባቸዋል። ስለሆነም፥ አንድ ወንድ ራሱን ተሸፋፍኖ ትንቢት መናገሩ ባሕሉ ለወንድ ተገቢ እንደሆነ ከሚገልጸው ድርጊት ያፈነገጠ በመሆኑ ትክክል አይሆንም። በጳውሎስ ዘመን ወንዶች ለእግዚአብሔር ያላቸውን አክብሮት ለማሳየት ባርኔጣቸውን ማንሣትና ራሳቸውን አለመሸፈን የሚጠበቅባቸው ይመስላል። ከሴቶች ይልቅ ፀጉራቸውን ማሳጠር ይኖርባቸዋል። ይህንን ማድረግ ቢያቆሙ ግን በውጪ ባሉት ዘንድ ለእግዚአብሔር ተገቢውን ክብር እንደማይሰጡ ያስቆጥርባቸዋል። በሌላ በኩል፥ ሴት ራሷን ሳትሸፋፈን ትንቢት ብትናገር፥ ባሕሉ ትክክል ነው ብሎ ከሚያስበው ግንዛቤ መውጣቷ ነበር። የጠበቀ ሥነ ምግባራዊ አኗኗር የማይከተሉ ሴቶች ፀጉራቸውን አይሸፋፈኑም ነበርና። ይህ ለዝሙት ወይም ጋለሞታነት የሚሰጠውን ፀጉርን የመላጨት ተግባርን ያህል አሳፋሪ ነበር። በተጨማሪም፥ ይህ ሴቶች የባሎቻቸውን ሥልጣን ባለመቀበል ያሻቸውን እንደሚያደርጉ የሚያሳይ ድርጊት ነበር። (ጳውሎስ ሴት በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ትንቢት ልትናገር እንደምትችል ይናገራል።) ስለሆነም፥ ጳውሎስ ሴቶች በአምልኮ ወቅት ባሕላቸው በሚፈቅደው መሠረት ባሎቻቸውን ማክበራቸውን እንዲያሳዩ ይጠይቃል። በቆሮንቶስ ይህ ማለት የሴቶች በአምልኮ ሰዓት ራሳቸውን መሸፋፈን ነበር። ይህም ሚስት ባሏንና እግዚአብሔርን ማክበሯን የሚያሳይ ሲሆን፥ የእግዚአብሔር ልጆች የሚያከናውኑትን ተግባር ለሚመለከቱት መላእክት መልካም ምስክርነት ነው።
  2. በእግዚአብሔር ዓይኖች ፊት ወንድና ሴት፥ ባሎችና ሚስቶች እኩልና አንዳቸው ያለ ሌላቸው ሊኖሩ የማይችሉ ናቸው። ጳውሎስ ይህ ትምህርት ከመጠን በላይ እንዲለጠጥና ወንዶች ሴቶችን የመቆጣጠር፥ የመግዛትና የመጨቆን ሥልጣን አለን ብለው እንዲያስቡ አይፈልግም። ወንዶች ለሴቶች እንደሚያስፈልጓቸው ሁሉ፥ ሴቶችም ለወንዶች ያስፈልጓቸዋል። እግዚአብሔር መጀመሪያ ሰውን ወንድና ሴት አድርጎ በአምሳሉ እንደፈጠረ አስታውስ (ዘፍጥ. 1፡27)።

ይህ ክፍል ከዛሬዪቱ ቤተ ክርስቲያን ጋር ስለሚዛመድበት ሁኔታ ክርስቲያኖች ቢያንስ ሦስት አመለካከቶች አሏቸው።

ሀ. እነዚህ በሁሉም ዘመን ለሚሠሩ ክርስቲያኖች ሁሉ የተሰጡ ትእዛዛት ናቸው። ይህን አመለካከት የሚቀበሉ ሰዎች ሴቶች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በሚሆኑበት ጊዜ ሁሉ በራሳቸው ላይ አንድ ነገር ማድረግ እንዳለባቸው ያስተምራሉ። መንፈስ ቅዱስ በታሪክ ሁሉ እግዚአብሔርን የሚፈሩ ክርስቲያኖች እነዚህ ትእዛዛት ለሁሉም ባሕሎች የተሰጡ ናቸው ብለው እንዳያስቡ ያደረገው ባሕላዊ መሠረት ስላላቸው ሳይሆን አይቀርም።

ለ. በዛሬው ዘመን ትክክለኛ በሆነው ጉዳይ ላይ የተለያዩ ባሕላዊ ግንዛቤዎች ስላሉ፥ የጳውሎስን ዝርዝር ትእዛዛት መከተል አያስፈልግም። ነገር ግን ሚስቶች ለባሎቻቸው በመገዛት አክብሮታቸውን ማሳየት እንዳለባቸው የሚያመለክተው የጳውሎስ አስተምህሮ በሁሉም ዘመን በሁሉም ባሕሎች ውስጥ ለሚኖሩ ሰዎች የሚሠራ ዐቢይ መርሆ ነው። ዋናው ነገር የአለባበስ ጉዳይ ሳይሆን እግዚአብሔርን እየፈሩ በተገዢነት መኖር ነው። ከሕይወታችን ጋር ልናዛምደው የሚገባን መርህ በባሕላችን ውስጥ ዓመፀኝነትን ሳይሆን ለእግዚአብሔር ጨዋነትንና አክብሮትን በሚያሳይ መልኩ መልበስ እንዳለብን ነው።

ሐ. ጳውሎስ ወንዶች ፀጉራቸውን በአጭሩ እንዲቆረጡና እንዳይሸፋፈኑ ሴቶች ረዥም ፀጉር እንዳያሳድጉና እንዲሸፋፈኑ፥ ወንዶች በሴቶች ላይ ሥልጣን እንዲኖራቸው ያዘዘው ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ብቻ ነው። በ1ኛ ቆሮ. 11፡11-12 ጳውሎስ የወንዶችንና የሴቶችን እኩልነትና አንዳቸው የሌላቸው ጥገኛ መሆናቸውን ገልጾአል። ይህ ዛሬ ተግባራዊ ልናደርገው የሚገባን እውነት ነው።

ጳውሎስ ስለ እግዚአብሔር አብና ወልድ የሥልጣን ደረጃ መናገሩ ባል በሚስቱ ላይ አስተዳደራዊ ሥልጣን እንዳለው ሊያመለክት ይችላል። ነገር ግን ይህ ወንዶችና ሴቶች አንዳቸው ለሌላቸው ስለሚገዙበት ሁኔታ ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ከሚናገሩት አሳብ ጋር መዛመድ አለበት (ኤፈ. 5፡21)። ክርስቶስ ለኃጢአታቸው በመሞት ክርስቲያኖችን እንደወደደ ሁሉ፥ ባሎችም የሚስቶቻቸውን ፍላጎት ከራሳቸው በማስቀደም በመሥዋዕትነት ማፍቀር አለባቸው (ኤፌ. 5፡25)። ወንዶች በሴቶች ላይ የሚኖራቸው ሥልጣን ሚስቶቻቸውን ለመበደል፥ እንደ ባሪያ ለማዘዝ፥ ዝቅ አድርጎ ለመመልከት፥ ወዘተ… መብትን አይሰጣቸውም። ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ሳይሆን የሰይጣን አስተምህሮ ነው።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ጳውሎስ ራስን ስለመሸፋፈን ላቀረበው ትምህርት ከተሰጡት ከእነዚህ ሦስት ግንዛቤዎች የትኛውን ታምናለህ? ለምን? ለ) የገጠርና የከተማ፥ እንዲሁም ወጣቶችና አዋቂዎች ስለ ትክክለኛ አለባበስ ያላቸውን ግንዛቤ አነጻጽር። ሰዎች ትክክለኛ አለባበስ ነው ብለው የሚያስቡት ከባሕል ባሕል የሚለያየው እንዴት ነው? ) ሚስቶች ለባሎቻቸው አክብሮታቸውን የሚያሳዩባቸው አንዳንድ ባሕላዊ መንገዶች ምን ምንድን ናቸው? መ) የባልና የሚስትን ተደጋጋፊነት፥ ተከባባሪነትና ተገዥነት፥ እንዲሁም ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያንን በወደደበት መንገድ ባል ሚስቱን መውደድ እንዳለበት የሚያስረዳውን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ለማንጸባረቅ ይቻል ዘንድ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ሊታረሙ የሚገባቸው የወንዶች የበላይነት የተሳሳቱ ገጽታዎች ምን ምንድን ናቸው? ሠ) በቤተ ክርስቲያንህ ውስጥ የሚገኙ አብዛኞቹ ጋብቻዎች የእግዚአብሔርን ፍጹማዊ ግንኙነት የሚያንጸባርቁ ይመስልሃል? ለምን? ረ) በቤተ ክርስቲያንህ ውስጥ ለሚገኙ ባለትዳሮች ስለ ትክክለኛው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ግንኙነት ምን ታስተምራለህ?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: