በጌታ እራት ጊዜ ትክክለኛው ባሕርይ ምንድን ነው? (1ኛ ቆሮ. 11፡17-34)።

«አሁን የጌታን እራት እንወስዳለን» ሲባል ጉባኤው በዝምታ ይዋጣል። ንግግርና ጭውውት አብቅቶ ጉባኤው ያረምማል። ይህ እጅግ የተቀደሰ የአምልኮ ጊዜ ነው። ብዙ አብያተ ክርስቲያናት የተጠመቁ አባሎቻቸው ብቻ የጌታን እራት እንዲወስዱ ያደርጋሉ። ንስሐ ስላልገቡባቸው ኃጢአቶች ጠንካራ ማስጠንቀቂያ ይሰጣቸዋል። ዛሬ ስለ የጌታ እራት በጥብቅ የሚያሳስበን ነገር አለ። ይኽውም የጌታን እራት አለአግባብ ልንጠቀም የምንችለው እንዴት ነው? የሚል ነው።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) የጌታ እራት ለአንተ ልዩ የሚሆነው ለምንድን ነው? ለ) 1ኛ ቆሮ. 11፡17-34 አንብብ። በጌታ እራት ጊዜ የተከሰተውንና ጳውሎስ የተቃወመውን ችግር ግለጽ። ሐ) ስለ የጌታ እራት ሊያስተካክል የፈለገው የተሳሳተ አመለካከት ምን ነበር? መ) ጳውሎስ ስለ ጌታ እራት የሰጠውና ዛሬ ከእኛ ጋር የሚዛመደውን መመሪያ ዘርዝር።

ችግሩ፡- የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች የተቸገሩበት ሁለተኛው የአምልኮ ክፍል በጌታ እራት ጊዜ ትክክለኛው ባሕርይ ምን ዓይነት ነው? የሚል ነበር፡፡ ችግሩን ለመረዳት እንችል ዘንድ የቀድሞዪቱ ቤተ ክርስቲያን የጌታን እራት ስለምትወስድበት ሁኔታ ማወቅ አለብን። የጥንቷ ቤተ ክርስቲያን የጌታን እራት የምትወስድበት ሁኔታ በተለያዩ መንገዶች ከዛሬው ዘመን የተለየ ነበር። በመጀመሪያ፥ ክርስቲያኖች ሁሉ በጌታ እራት ተካፋይ ነበሩ። የጥንቷ ቤተ ክርስቲያን ሰዎችን ወዲያውኑ እንዳመኑ ታጠምቃቸው ስለነበር፥ አንድ ሰው በሚያምንበትና የጌታን እራት በሚወስድበት መካከል ብዙ የጊዜ ርቀት አልነበረም። በአባሎችና እንዲሁ ለመካፈል በመጡት ሰዎች መካከልም ልዩነት አልነበረም። ሁለተኛ፥ ዛሬ በአብዛኞቹ አብያተ ክርስቲያናት በወር አንድ ጊዜ እንደሚሰጠው ሳይሆን፥ በጥንቷ ቤተ ክርስቲያን የጌታ እራት በየአምልኮ ፕሮግራሙ ላይ ይደረግ ነበር። ሦስተኛ፥ የጌታ እራት ሰዎች የዳቦ ቁራሽና አነስተኛ መጠጥ የሚጠጡበት ሥርዓት ብቻ አልነበረም። ነገር ግን ምእመናኑ በአምልኮው ሰዓት መጨረሻ ላይ አብረው የሚበሉት ምግብ ነበር። የጌታ እራት ዳቦና መጠጥ የሚቀርበው ከምግቡ በኋላ ነበር።

በቆሮንቶስ እያንዳንዱ ቤተሰብ ምግቡን አምጥቶ በጋራ ይመገብ የነበረ ይመስላል። ምእመናኑ ያመጡትን ምግብ አብረው ከበሉ በኋላ የጌታን እራት ሥርዓት ያካሄዳሉ። ነገር ግን ሰይጣን ይህን መልካም ልማድ ወደ ራስ ወዳድነት ተግባር ለወጠው። በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሀብታምና ድሀ ክርስቲያኖች ነበሩ። ሀብታም ክርስቲያኖች ብዙ ጥሩ ጥሩ ምግቦች (እንደ እንጀራና ወጥ ያለ) ይዘው ሲመጡ፥ ድሆቹ ግን ምንም ወይም ደከም ያለ (እንደ ንፍሮ ዓይነት) ምግብ ያመጡ ነበር። ሀብታም ክርስቲያኖች ጥሩ ምግባቸውን በልተውና ወይናቸውን ጠጥተው ሲሰክሩ፥ ድሆቹ ጥሩ ምግብ ለመብላት አልቻሉም ነበር። ድሆቹ ሀብታሞቹ የሚበሉትን እየጓጉ ከመመልከት ያለፈ ሚና አልነበራቸውም። ወደ ቤተ ክርስቲያን ብዙ ምግብ ይዘው ሊመጡ ስለማይችሉ ዝቅተኛነት ይሰማቸው ነበር። ስለሆነም፥ የጌታ እራት የፍቅርና የአንድነት መዘከሪያ ከመሆን ይልቅ የመከፋፈልና የራስ ወዳድነት መገለጫ ሆኖ ተገኘ። ጳውሎስ ክፍፍልና ራስ ወዳድነት እያሉ የጌታን እራት በአግባቡ ማካሄድ እንደማይቻል አመልክቷል። ጳውሎስ በዚህ ክፍል የተቃወመውም ይህንኑ ክፍፍልና ራስ ወዳድነትን ነው።

መርሁ፡- እግዚአብሔር የሚቀበለው አምልኮና የጌታ እራት በአንድነት፥ በፍቅርና ለሌሎች በማሰብ ሊካሄድ ይገባል። ራስ ወዳድነትና ከፍፍል ካሉ የአምልኮ፥ የዝማሬ፥ የአሥራት፥ የስብከትና የጌታ እራት ሥርዓት ማካሄዱ ለእኛም ሆነ ለሌሎች የሚያበረክተው ፋይዳ አይኖርም።

ትእዛዛት፡

  1. ጳውሎስ መፍትሔ መስጠት የጀመረው ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ስለ የጌታ እራት ዓለማ በማስታወስ ነው። ትኩረት ሊሰጥ የሚገባው በሚበሉት ምግብ ላይ ሳይሆን፥ ስለ እነርሱ የሞተውን ክርስቶስን በማስታወሱ ላይ ነበር። ስለሆነም ከራባቸው በቤታቸው እንዲበሉና ሰይጣን የኢኮኖሚ ልዩነታቸውን ለማጉላት የሚጠቀምበትን ብዙ ምግብ ይዞ የመምጣት ተግባራቸውን እንዲያቆሙ መክሯቸዋል።
  2. የጌታ እራት ዓላማ ሰዎች ክርስቶስ ስለ እኛ በመስቀል ላይ መሞቱን እንዲያስታውሱ ማገዝ ነው፡፡ ክርስቶስ ብዙውን ጊዜ በተለያዩ ነገሮች ስለምንጣደፍ ይህ የእምነታችን መሠረታዊ እውነት እንደሚዘነጋ ያውቅ ነበር። በመጀመሪያ፥ የጌታ እራት ከኃጢአት መዳናችንን፥ መንፈስ ቅዱስ መቀበላችንን፥ የእግዚአብሔር ልጆች መሆናችንን የዘላለም ሕይወት ማግኘታችንን ጨምሮ፥ ደስ የምንሰኝባቸውን በረከቶች ሁሉ እንድናስታውስ ይረዳናል። እነዚህ በረከቶች ሁሉ የተገኙት ክርስቶስ ለኃጢአታችን በመሞቱ ምክንያት ነው። ሁለተኛ፥ የጌታ እራት ክርስቲያኑ ማኅበረሰብ እምነቱና ተስፋው በክርስቶስ የመስቀል ላይ ሞት እንዳረፈ የሚመሰክርበት ነው።
  3. በአማኞች ማኅበረሰብ የጌታ እራት በከፍተኛ ጥንቃቄ ሊወስድ ይገባል። በግለሰብም ሆነ በአማኞች አካል ደረጃ ልባችንን በመመርመር ኃጢአታችንን ልንናዘዝ ይገባል። በመካከላችን ክፍፍልና ራስ ወዳድነት፥ እንዲሁም ሌሎች ያልተናዘዝናቸው ኃጢአቶች እያሉ የጌታን እራት መውሰድ በክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ላይ ማላገጥ ይሆናል። ክርስቶስ የሞተው ለኃጢአታችን ስለሆነ ንስሐ ሳንገባ የጌታ እራት የምንወስድ ከሆነ፥ ክርስቶስ ለኃጢአታችን እጅግ ተሠቃይቶ በደሙ እኛን ስለ መግዛቱ ግድ የለንም ማለት ነው። አሁንም በዓመፀኛነታችን እንቀጥላለን ማለት ነው። ጳውሎስ አንዳንድ ክርስቲያኖች ለጌታ እራት እንዲህ ዓይነት የግድየለሽነት አመለካከት በማሳየታቸው በሞት እንደተቀጡ ገልጾአል። አንዳንዶች በሕመም ሌሎች ደግሞ በሞት ተቀጥተዋል (አንቀላፍተዋል)። አሁንም ሆነ የኋላ ኋላ የእግዚአብሔርን ፍርድ ከመቀበል ይልቅ ሕይወታችንን መመርመር፥ ኃጢአታችንን መናዘዝና በኅብረት መብላቱ ጠቃሚ ይሆናል።
  4. የጌታ እራት ልዩነቶችንና የራስ ወዳድነትን ሁኔታ ከማሳየት ይልቅ ፍቅርንና አንድነትን ሊያንጸባርቅ ይገባል። አማኞች እርስ በርሳቸው ተጠባብቀው አንድ ላይ እንዲመገቡ ተነግሯቸዋል። የጌታ እራቱ በክርስቶስ ሞት እንጂ በምግባቸው ላይ ሊያተኩር አይገባም ነበር። የተራበ ሰው ቢኖር ወደ ቤተ ክርስቲያን ከመምጣቱ በፊት መብላት አለበት።

የውይይት ጥያቄ፡– ሀ) ብዙ ጊዜ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የመከፋፈል ወይም ሌሎች ኃጢአቶች ቢኖሩም ክርስቲያኖች የጌታን እራት መውሰዳቸውን ይቀጥላሉ። ጳውሎስ ስለዚህ ጉዳይ ምን የሚል ይመስልሃል? ለ) የጌታን እራት ፍች በትክክል ብንረዳ፥ ይህ ቤተ ክርስቲያንን ሊያነጻ የሚችለው እንዴት ነው?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: