ለጉባኤ አምልኮ የተሰጡ መሠረታዊ መመሪያዎች (1ኛ ቆሮ. 14፡26-40)።

ጳውሎስ ለጉባኤ አምልኮ አንዳንድ መመሪያዎችን በሚሰጥበት ጊዜ ለማስተላለፍ የሚፈልገውን መልእክት ለመረዳት ቤተ ክርስቲያኒቱ ምን ትመስል እንደነበረ ማስታወሱ አስፈላጊ ነው። ዛሬ እንደምናደርገው ቤተ ክርስቲያኒቱ በትልቅ የስብሰባ አዳራሽ ውስጥ አትሰባሰብም ነበር። አማኞች የሚሰባሰቡት በግለሰቦች ቤት ውስጥ በመሆኑ የሰዎቹ ቁጥር ከ50 ወይም 60 አይበልጥም ነበር። ስለሆነም ቤተ ክርስቲያኒቷ የኅብረት ጸሎት ወይም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚካሄድባት እንጂ በግዙፍ ሕንጻ ውስጥ መንፈሳዊ ሥነ ሥርዓት የሚካሄድበት ዓይነት ቤተ ክርስቲያን አልነበረችም። የሰዎቹ ቁጥር ጥቂት ስለሆነ መዝሙር ለመምረጥ፥ ቃል ለማካፈል፥ በአስተርጓሚ አማካኝነት በልሳን ለመናገር፥ ወዘተ. ብዙ ነጻነት ነበራቸው። ጳውሎስ የሚከተሉትን መመሪያዎች ሰጥቷል።

  1. አምልኮ እንደ መሪዎች ወይም ኳዬርና ሰባኪ ያሉ ጥቂት ሰዎች ሁሉንም ተግባር የሚፈጽሙበትና ሌሎች በትዝብት የሚመለከቱበት ሳይሆን ምእመናን በሙሉ የሚሳተፉበት ነው። ጳውሎስም ሁሉም ትምህርት፥ ልሳን፥ ትንቢት፥ ወዘተ በማቅረብ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ እንዳለ አመልክቷል። ጳውሎስ ይህን ሲል ሁሉም ሰው ሁሉንም ነገር ማድረግ አለበት ማለቱ ሳይሆን ሁሉም ሰው ለመሳተፍ እንደሚችል መግለጹ ነበር።
  2. አምልኮው ሁሉ ለምእመናን በሙሉ ጠቃሚ መሆን አለበት። አስተርጓሚ ሳይኖር በልሳን መናገሩ ለሌሎች መንፈሳዊ ጥቅም የማያስገኝ በመሆኑ ተከልክሏል። ሰዎች የሚነገረውን አሳብ ተረድተው «አሜን» (እስማማለሁ) ሊሉ አይችሉም ነበር። የጉባኤ አምልኮ የሁሉም ስለሆነ፥ የሁሉም መረዳት ወሳኝ ነው። መልእክቱ በሚገባቸው ቋንቋ ሊተላለፍና ፕሮግራሙም እምነታቸውን የሚያንጹትን ነገሮች ሊያካትት ይገባል። (ይህ አንድ ሰው ለቡድኑ እንዲጸልይ በሚጠየቅበት ጊዜ ለራሱ መጸለይ ወይም በልሳን መናገሩ ትክክል እንዳልሆነ የሚያመለክት ይመስላል። ሁሉም የግለሰቡን ጸሎት ካልሰሙ ጥያቄውን ማጽደቃቸውን ለማሳየት «አሜን» ሊሉ አይችሉም። የጉባኤ አምልኮ ዓላማ የግል ጸሎት፥ ጥያቄ ወይም በረከት ሳይሆን፥ የሁሉም በአንድነት መሳተፍ ነው።)
  3. ነገሮች በሥርዓትና በአግባቡ ሊከናወኑ ይገባል። ሰዎች በራስ ወዳድነት ስጦታዎቻቸውን ለማሳየት በመፈለጋቸው ምክንያት የቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን በሁከት ሳትሞላ አትቀርም። ጉባኤው ብዙ ሰዎች በአንድ ጊዜ በሚናገሯቸው የልሳንና የትንቢት መልእክቶች፥ እንዲሁም በሴቶች ጫጫታ ይታወክ ነበር። ነገር ግን አምልኮ ሥርዓትን የተከተለና አግባብነት ያለው ሊሆን ይገባል። በሌላ አገላለጽ፥ አምልኮ ለሕዝቡ ባሕል በሚስማማ፥ በሚጥም፥ ሕዝቡን ደስ በሚያሰኝ መንገድ መካሄድ አለበት። ስለሆነም፥ ጳውሎስ ለቤተ ክርስቲያን አምልኮ የሚያገለግሉ መመሪያዎችን ሰጥቷል።

ሀ. ሰዎች በልሳን ለመናገር ከፈለጉ ሊፈቀድላቸው ይገባል። ነገር ግን ተራ በተራ መናገር ይኖርባቸዋል። በልሳን በሚናገሩበት ጊዜ ደግሞ መልእክቱ መተርጎም አለበት። ተርጓሚ ከሌለ ዝም ብለው በልባቸው መጸለይ አለባቸው። በአንድ የአምልኮ ጊዜ ሁለት ወይም ሦስት ሰዎች ብቻ በዚሁ መንገድ መናገር ይኖርባቸዋል።

ለ. ሰዎች ትንቢት መናገር ቢፈልጉ ተፈቅዶላቸው ነበር። ተራ በተራ ትንቢት መናገር ይቻላል። ትንቢትም ሆነ ልሳን በመንፈስ ቅዱስ ቁጥጥር እንጂ ራስን በመሳት (in a trance) ሊነገር አይገባም። መንፈስ ቅዱስ እንደ ሰይጣን ሰዎች ከአእምሯቸው ውጭ እንዲሆኑ አያደርግም። ግለሰቡ አእምሮውን ሳይስት መንፈስ ቅዱስንና እርሱ የሚናገረውን ይሰማል። ትንቢት የሚነገርበት ዓላማ ግለሰቡ የተሰማውን እንዲናገርና ለሌሎች መልእክት የማካፈል ዕድል እንዲያገኝ ሳይሆን፥ የእግዚአብሔርን መልእክት ለሕዝቡ ለማስተላለፍ ነው። ስለሆነም፥ እርሱ እየተናገረ ሳለ እግዚአብሔር ተጨማሪ ማብራሪያ ለመስጠት በሌላ ሰው አማካኝነት የትንቢትን ቃል ከላከ፥ የመጀመሪያው ተናጋሪ ተራ ሊለቅለት ይገባል። በመጨረሻም፥ እንደ ልሳን ሁሉ በአንድ ጉባኤ ሁለት ወይም ሦስት ሰዎች ብቻ ትንቢትን እንዲናገሩ ተፈቅዷል።

ከቡሉይ ኪዳን በተለየ መልኩ፥ የአዲስ ኪዳን ትንቢት እግዚአብሔር ራሱ የሚናገረውን ያህል ጠንካራ ሥልጣን ያለው አይመስልም። አንድም የአዲስ ኪዳን ነቢይ፥ «እግዚአብሔር እንዲህ ይላል» እያለ ሲናገር አንመለከትም። ክርስቲያኖችም ትንቢትን በሁለት መንገዶች እንዲመረምሩ ተነግሯቸዋል። በመጀመሪያ፥ ቃላቱ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር መስማማታቸውን ለመመርመር ትንቢትን እንፈትናለን። እግዚአብሔር ሊዋሽ ስለማይችል በአንድ በኩል (በሰው ወይም በመጽሐፍ ቅዱስ) የተናገረውን መልእክት አይቃረንም። ስለሆነም የተነገረው ትንቢት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በግልጽ ከተጻፈው ወይም ከመጽሐፍ ቅዱስ ዐበይት መርሆች ጋር የሚጻረር ከሆነ ትንቢቱን መቀበል አያስፈልግም። ሁለተኛ፥ ትንቢቱ ለሁሉም ሰው የሚጠቅም መሆኑን መመርመር አለብን። ለሕዝቡ ሁሉ የማያገለግልና ቤተ ክርስቲያንን የማያንጽ ከሆነ፥ ትንቢቱን መቀበል አያስፈልግም። ወይም ጉዳዩ ለሚመለከታቸው ብቻ ማካፈል ያሻል።

ሐ. ሴቶች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ዝም ሊሉ ይገባል። ይህ ምንባብ በክርስቲያኖች መካከል ብዙ ውይይቶችንና የተለያዩ አመለካከቶችን አስከትሏል። በሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ያልተደገፉ የሚመስሉ ሁለት የተራራቁ አመለካከቶች አሉ። በመጀመሪያ፥ አንዳንድ ክርስቲያኖች ሴት በፍጹም በጉባኤ ላይ መናገር የለባትም ይላሉ። እነዚህ ወገኖች ሴቶች ማስተማር፥ መስበክ፥ ማካፈል፥ መጸለይ፥ ወዘተ… እንደማይችሉ ይናገራሉ። ሁለተኛ፥ ሌሎች ክርስቲያኖች እነዚህ የጳውሎስ ትእዛዛት ከእኛ ጋር እንደማይዛመዱ ያስረዳሉ። እነዚህ ትእዛዛት የተሰጡት ወንዶች ሴቶችን በሚንቁበት ዘመንና የሴት የቤተ ክርስቲያን ውስጥ መናገር የተሳሳተ ወይም የዓመፅ ምልክት ተደርጎ በሚወሰድበት ባሕል ውስጥ ለነበሩት ሰዎች እንደሆነ ያስረዳሉ። ጊዜው ስለተቀየረና ዘመናዊ ባሕሎች የሴቶችን እኩልነት ስለተገነዘቡ፥ ሴቶች የወንዶችን ያህል እኩል ድርሻና ሥልጣን ይይዛሉ። ተገቢው መጽሐፍ ቅዱሳዊ አመለካከት የሚውለው በእነዚህ ሁለት የተራራቁ አመለካከቶች መሀል ይመስላል።

የትኛውንም አመለካከት ብንከተል፥ ጳውሎስ ቀደም ሲል በ1ኛ ቆሮንቶስ 11፡2-16 የተናገረውን ማስታወስ ይኖርብናል። በዚህ ክፍል ጳውሎስ ሴቶች የመጸለይና ትንቢት የመናገር ፈቃድ እንዳላቸው በማሰብ፥ ይህንኑ አገልግሎት በሚሰጡበት ጊዜ ከባሕላቸው ጋር ላለመቃረን ራሳቸውን መሸፈን እንዳለባቸው ገልጾአል። በኢዩኤል 2፡28-32 የተሰጠውና በሐዋርያት ሥራ 2፡17-21 የተጠቀሰው የመንፈስ ቅዱስ የተስፋ ቃል ወንዶችን ብቻ ሳይሆን ሴቶችንም ይጨምራል። ስለሆነም፥ የአዲስ ኪዳን ሴቶች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሊናገሩና ሊያገለግሉ እንደሚችሉ በግልጽ ያሳያል።

ክርስቲያኖች ከሚይዟቸው የተለያዩ አተረጓጎሞች አንዳንዶቹ ከዚህ በታች ተዘርዝረዋል። እንደ እግዚአብሔር ቃል ተማሪ፥ አንተና ቤተ ክርስቲያንህ ይህን ክፍል በምታዛምዱበት ሁኔታ ላይ መንፈስ ቅዱስ እንዲመራችሁ በጸሎት ጠይቁ።

አንዳንድ ምሁራን ጳውሎስ እግዚአብሔር የአስተዳደርና የሥልጣን ደረጃ ዎችን ስለወሰነ ሴቶች በቤትም ሆነ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ለባሎቻቸው እንዲገዙ ለማስረዳት መፈለጉን ይገልጻሉ። ስለሆነም፥ ሴቶች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ከመናገር ይልቅ ያልተገነዘቧቸውን ነገሮች ወደቤታቸው ከተመለሱ በኋላ ከባሎቻቸው በመጠየቅ አክብሮታቸውን ማሳየት ያስፈልጋቸው ነበር።

ሌሎች ምሁራን ጳውሎስ የተጋፈጠው ችግር ስለ መጽሐፍ ቅዱስ በቂ እውቀት ያልነበራቸውና በክርስትና እምነት ከወንዶች ጋር እኩል በመሆናቸው ምክንያት ባገኙት አዲስ ነጻነት የተደሰቱት ሴቶች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የፈጠሩት ሁከት እንደነበረ ይናገራሉ። እነዚህ ሴቶች ስለ ትንቢት አተረጓጎም፥ ወዘተ. እየተንጫጩ ይከራከሩ ነበር። ስለሆነም፥ ጳውሎስ እነዚህ ሴቶች ቤት ውስጥ ከባሎቻቸው ጋር እንዲወያዩና ቤተ ክርስቲያን ውስጥ መከራከራቸውን እንዲያቆሙ አዟል ይላሉ። ነገር ግን ጳውሎስ በክርክሩ ውስጥ ስለሚሳተፉት ወንዶች ምንም ሳይናገር ለምን ሴቶችን ብቻ እንደኮነነ መረዳቱ አስቸጋሪ ነው። ሴቶች መቼ መናገር እንዳለባቸው የሚያመለክት ተጨማሪ መመሪያ ሳይሰጥ በደፈናው ዝም እንዲሉ ያዘዛቸው ለምንድን ነው?

ሌሎች ደግሞ የጳውሎስ ትልቁ ግዳጅ አማኞች ለሌሎችና ለእግዚአብሔር አክብሮት በሚያሳይ መልኩ የጸጋ ስጦታዎቻቸውን በመጠቀም ቤተ ክርስቲያንን ማነጻቸው ነው ይላሉ። ለሌሎች ሰዎች አክብሮትን ማሳየት ከሚቻልባቸው መንገዶች አንዱ ለሴቶች ተገቢ የሆነውን ባሕላዊ ግንዛቤ መጠበቅ ነበር። የጥንቱ ባሕል ሴቶች በሕዝብ ፊት እንዳይናገሩ ስለሚከለክል፥ ሴቶች ባሕሉን በማክበር በቤተ ክርስቲያንም ይህንኑ ተግባር ከመፈጸም መታቀብ ነበረባቸው። ጳውሎስ ሴቶች በሕዝብ ፊት ሊጸልዩና ትንቢትን ሊናገሩ የሚችሉባቸው ጊዜያት እንዳሉ ቢናገርም። ጉዳዩ ባሕላዊ ጫና እንዳለው ግልጽ ነው። በአጠቃላይ መልኩ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ተገቢው ነገር የሴቶች በጉባኤ ዝም ማለት ነበር። በዘመናችን ባሕሉ ተለውጦ የሴቶች በጉባኤ ላይ መናገር ግራ መጋባትንና ነውረኝነትን የማያስከትል ከሆነ፥ ሴቶች እንዲናገሩ ሊፈቅድላቸው ይገባል።

በመጨረሻም፥ ስለ ትንቢትና ልሳን በሚናገሩ አሳቦች ላይ በማተኮር አስተያየታቸውን የሚሰጡ ወገኖች አሉ። ጳውሎስ ቤተ ክርስቲያን ትንቢቶችን በጥንቃቄ ስለምትመዝንበት ሁኔታ እያስተማረ ነበር። ሴቶችም በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ትንቢት ሊናገሩ እንደሚችሉ ተፈቅዶላቸው ነበር። ነገር ግን ቤተ ክርስቲያን ትንቢቶችን መዝና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ወይም ከእግዚአብሔር መሆን አለመሆናቸውን በምትወስንበት ሂደት ውስጥ ሴቶች ዝም ማለት ነበረባቸው፡፡ ወንዶች ስለ ትንቢት እንዲወያዩ በመፍቀድ በመጽሐፍ ቅዱስ መርሆ መሠረት ለወንዶች የተሰጠውን ሥልጣን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያንጸባርቁ ነበር። ሴቶች የተወሰነ አመለካከት ስለተወሰደበት ምክንያት ጥያቄ ቢኖራቸው በቤታቸው ውስጥ ባሎቻቸውን መጠየቅ ይኖርባቸዋል። ጳውሎስ ሴቶች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እውቅና በተሰጠው የማስተማር ተግባር በወንዶች ላይ እንዲሠለጥኑ አይፈልግም ነበር። የትንቢት ግምገማ አንድ ነገር ከእግዚአብሔር መሆን አለመሆኑን ለመወሰን እንደሚያስችል ሥልጣን ይታይ ነበር። እግዚአብሔርም ይህንን ኃላፊነት የሰጠው ለወንዶች ነበር። ስለሆነም፥ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ከእግዚአብሔር ዘንድ የሆነውንና ያልሆነውን የመወሰን ሥልጣንን ለሴቶች መስጠቱ ባሕላቸውን ከመጻረሩም በላይ እግዚአብሔር በፍጥረት ጊዜ የወሰነውን የሥልጣን ሥርዓት የሚያፋልስ ነበር። ጥያቄ፡- ሀ) በቤተ ክርስቲያንህ ውስጥ ሰዎች ልሳንን የሚጠቀሙበትን ሁኔታ ጳውሎስ ካስተማረው ጋር አነጻጽር። ልዩነቱና ተመሳሳይነቱ ምንድን ነው? ለ) አንዳንድ ጊዜ ክርስቲያኖች ያለ አስተርጓሚ በጉባኤ ውስጥ በልሳን ይጸልያሉ። ይህ ከመጽሐፍ ቅዱስ አስተምህሮ ጋር የሚጣጣም ይመስልሃል? መልስህን አብራራ። ሐ) የሚጣጣም ካልሆነ፥ አምልኳችሁ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር እንዲጣጣም ለማድረግ የቤተ ክርስቲያን ሽማግሌዎች ምን ማድረግ የሚገባቸው ይመስልሃል? መ) ስለ ሴቶች በጉባኤ ላይ መናገርን ከሚያስረዱት አመለካከቶች የትኛውን ታምናለህ? ለምን?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: