መንፈሳዊ መሪ ወደፊት ዘላለማዊ ሽልማት እንደሚያገኝ ስለሚተማመን በአገልግሎቱ ይጸናል (2ኛ ቆሮ. 4፡13-5፡10)።

ጳውሎስ መከራ መቀበልን ይወድ ነበር? አይወድም። እንግዲያው ነገሮች አስቸጋሪ ሲሆኑበት፥ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖችና ሌሎችም ሲቃወሙት፥ ስሙን ሲያጎድፉ፥ ዓለም ስታሳድደው ለምን አገልግሎቱን አላቋረጠም? የዚህ ምሥጢሩ ጳውሎስ ዓይኖቹን ከሞት በኋላ በሚሆነው ሁኔታ ላይ ማኖሩ ነው።

ሀ. ጳውሎስ ቢሞትም እንኳ እንደሚነሣ ስለሚያውቅ መከራን እየተጋፈጠ ወንጌሉን ሰብኳል (2ኛ ቆሮ. 4፡13-15)። ሞትን ስለማይፈራ ከመሰከርህ ትሞታለህ ቢባል እንኳ አገልግሎቱን አያቋርጥም ነበር። ከዚህም የተነሣ ወንጌሉ እንደ ቆሮንቶሳውያን ላሉ ሰዎች በመዝለቅ ወደ ዘላለማዊ ሕይወት መርቷቸዋሉ።

ለ. ጳውሎስ ከሞት በኋላ አንድ ታላቅ ነገር እንደሚጠብቀው በማወቁ መከራን እየተጋፈጠ ወንጌሉን ሰብኳል (2ኛ ቆሮ. 4፡16-18)። ጳውሎስ ሥጋው እየደከመ መሄዱንና ስደቱም ዘመኑን በፍጥነት እያሳጠረው መሆኑን ተረድቶ ነበር። ይህ ግን አላሳሰበውም። ምክንያቱም ጳውሎስ ለክርስቶስ ታማኝ በመሆኑ በየዕለቱ በመንፈሱ እየታደሰ ስለነበረ ነው። ሲሞትም ከክርስቶስ ታላቅ ዘላለማዊ ሽልማት እንደሚጠብቀው ያውቅ ነበር። እንዲያውም ምድራዊ መከራዎች ያንን ሰማያዊ ክብር ይጨምራሉ።

ሐ. ጳውሎስ ሞት ወደሚወደው ጌታ እንደሚወስደው በማወቁ በወንጌል አገልግሎቱ ቀጥሏል (2ኛ ቆሮ. 5፡1-9)። ጳውሎስ ምድራዊ ሥጋውን ለለቅሶ ከሚተከል ድንኳን ጋር አነጻጽሯል። የለቅሶ ድንኳን ለጥቂት ቀናት ከቆየ በኋላ ይነሣል። ዘላለማዊ ሕይወቱን በሰማይ ከሚገኝ ዘላለማዊ ቤት ጋር አነጻጽሯል። ጳውሎስ ከድንኳን ጋር ባነጻጸረው ሥጋው ውስጥ ቢኖርም፥ ዘላለማዊ ማደሪያውን ይናፍቃል። በምድራዊ ድንኳን፥ መከራ፥ በሽታ፥ ሥቃይና የመሳሰሉት ይፈራረቃሉ። በሰማያዊ ቤት ግን ይህ ሁሉ አይኖርም። ጳውሎስ ደስ ከተሰኘባቸው የመንፈስ ቅዱስ አገልግሎቶች አንዱ መንፈስ ቅዱስ ወደፊት ለሚመጣው በረከት መያዣ መሆኑ ነበር። መንፈስ ቅዱስ በልቡ ውስጥ ሆኖ ጳውሎስ አንድ ቀን ከዘላለማዊ ቤቱ እንደሚደርስ ያረጋግጥለታል። ከበሽታም ሆነ ከስደት የተነሣ የሚደርስበት ሞት ከድንኳኑ አውጥቶ ወደ ቤቱ እንደሚወስደው መገንዘቡ፥ ጳውሎስ በብዙ መከራ መካከል ለእግዚአብሔር በታማኝነት እንዲያገለግል ረድቶታል።

መ. ጳውሎስ እግዚአብሔር በሰውነቱ ውስጥ ላስቀመጠው የወንጌል መዝገብ ባለአደራነት አንድ ቀን ኢየሱስ ክርስቶስ በኃላፊነት እንደሚጠይቀው ስለሚያውቅ ወንጌሉን በታማኝነት ማካፈሉን ቀጥሏል (2ኛ ቆሮ. 5፡10)። በቆሮንቶስ ወንጀለኞች ለፍርድ የሚቀርቡበት ትልቅ የድንጋይ ችሎት ነበር። ይህ ስፍራ አትሌቶች ውድድራቸውን በአሸናፊነት በሚጨርሱበት ጊዜ የክብር ሽልማት የሚቀበሉበትም ነበር። ጳውሎስ ሁላችንም በታላቁ ዳኛ በኢየሱስ ክርስቶስ ፊት እንደምንቀርብ ተናግሯል። ክርስቲያኖች ላይ ፍርድ የሚሰጠው ክርስቲያን ስለመሆናቸውና ስላለመሆናቸው ሳይሆን በሥጋ ሳሉ ለፈጸሟቸው ተግባራት ነው። ምንም እንኳ ሥጋ የሚጠፋ ድንኳን ቢሆንም፥ እግዚአብሔር የከበረ ዕቃውን ያኖረበት ነው። ስለሆነም፥ የክብር ዕቃውን የምናስተናግድበትና ሕይወታችንን የምንመራበት ሁኔታ ዘላለማዊ አስከትሎት ይኖረዋል። (እግዚአብሔርን የሚያሳስበው የመንፈሳችን ጉዳይ ስለሆነ በሥጋችን እንዳሻን ልንሆን እንችላለን የሚሉ አንዳንድ ክርስቲያኖች አሉ። ከዚህም የተነሣ ብዙዎች ዝሙትንና ሌሎች ኃጢአቶችን ይለማመዳሉ። ጳውሎስ በዚህ ስፍራ በሥጋችን የምንፈጽመው ተግባር ዘላለማዊ ጠቀሜታ እንዳለው ገልጾአል።) 21ኛ ጥያቄ ሀ) ሁልጊዜም ዋናው ነገር ዘላለማዊ ቤታችን እንጂ ጊዜያዊ ድንኳናችን እንዳልሆነ ብታስታውስ ሕይወትህና አገልግሎትህ እንዴት እንደሚለወጥ ግለጽ። ለ) በሥጋህ ለፈጸምሃቸው ነገሮች ሁሉ ተጠያቂ መሆንህን ብታውቅ አገልግሎትህና ሕይወትህ እንዴት ይለወጣል? ሐ) በክርስቶስ ፊት በምትቆምበት ጊዜ የምታፍርባቸውን ነገሮች ያሳይህ ዘንድ መንፈስ ቅዱስን ጠይቅ። ስለ እነዚህ ነገሮች ንስሐ ግባና በዚያን ጊዜ ከማፈር ይልቅ በምትከብርበት መንገድ ለመኖር ቁርጥ ውሳኔ አድርግ።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d