ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ስለ ራሱ ሁኔታ እብራራላቸው (2ኛ ቆሮ. 1፡12-2፡13)

  1. ጳውሎስ በዕቅዱ መሠረት ለምን እንዳልጎበኛቸው ገለጸላቸው (2ኛ ቆሮ. 1፡12-2፡4)

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ለሌሎች የገባኸውን ቃል መጠበቅ አስፈላጊ የሚሆነው ለምን ይመስልሃል? ለ) መሪዎች ለምእመናን የገቧቸውን የተስፋ ቃሎች በማይፈጽሙባቸው ጊዜያት ምን ይከሰታል? ሐ) ለመሪዎች በሚያክናውኗቸው ተግባራት ሁሉ በንጹሕ ሕሊና መመላለስ አስፈላጊ የሚሆነው ለምንድን ነው? መ) ስለ ራስህ ሕይወት አስብ። ሰዎች ቢያውቋቸው የሚያሳፍሩህ አንዳንድ ነገሮች ምን ምንድን ናቸው? ይህ ስለ እውነተኛነትህና ስለ ሕሊናህ ምን ያሳያል?

የተለያዩ የቤተ ክርስቲያን ሰዎች ጳውሎስን ስለተለያዩ ምክንያቶች የሚከሱት ይመስላል። በመጀመሪያ፥ አንዳንዶች ግልጽ ያልሆኑ ነገሮችን በመልእክቱ ውስጥ በማካተቱ ከሰሱት። ጳውሎስ በመልእክቶቹ ሊያታልላቸው የሚፈልግ መሰላቸው። ሁለተኛ፥ ሌሎች ቃሉን አይጠብቅም ብለው አሰቡ። ወደ መቄዶንያ ከመሄዱ በፊት እንደሚጎበኛቸው በቲቶ በኩል ሳይልክባቸው አልቀረም። ነገር ግን እነርሱ ዘንድ ሳይደርስ ወደ መቄዶንያ መሄዱን ሲሰሙ፥ «ቃሉን የማይጠብቅ ሰው እንዴት ሊታመን ይችላል?» ብለው ጠየቁ።

ጳውሎስም በተሳሳተ መንገድ ስለተረዱት አዘነ። ከእነርሱ ጋር የሚያደርገው ግንኙነት ሁልጊዜም በግልጽነት፥ በቅድስናና በእውነተኛነት ላይ የተመሠረተ መሆኑን እንዲረዱለት ፈለገ። በጻፈላቸው አሳብ ሊያታልላቸው ስላልፈለገ ሕሊናው ንጹሕ መሆኑን አብራራላቸው። እንዲሁም፥ ወደ ኢየሩሳሌም ከመሄዱ በፊት ሊጎበኛቸው ሁለት ጊዜ ስላቀደ ሕሊናው ንጹሕ ነበር። ጳውሎስ በሁኔታዎች ላይ ተመሥርቶ ቃሉን የማይለውጥ ሰው መሆኑን ገለጸላቸው። ጳውሎስ በቃሉ እንደ እግዚአብሔር ግልጽና እውነተኛ ለመሆን ይፈልግ ነበር። የእግዚአብሔር የተስፋ ቃሎች በክርስቶስ በኩል እውነት (አሜን፥ አዎን) ናቸው። እግዚአብሔር ከሰጣቸው የተስፋ ቃሎች አንዱ ልጆቹ እስከ መጨረሻው ድረስ ጸንተው እንደሚቆሙ የሚያስረዳ ነው። ይህንኑ የተስፋ ቃል እውን ለማድረግ እግዚአብሔር ለእያንዳንዱ ክርስቲያን የባለቤትነት ማኅተም የሆነውን መንፈስ ቅዱስ ሰጥቷል። ይህም እግዚአብሔር ተስፋ የሰጠንን ውርስ እንደምንቀበል ዋስትና ይሰጠናል።

ጳውሎስ ይህን ያለመተማመን መንፈስ ያሸነፈው እንዴት ነው? በመጀመሪያ፥ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች በተሻለ ሁኔታ እንዲያውቁት ጠየቃቸው። አንድን ሰው በደንብ ስናውቅ ብዙም አንጠራጠረውም። ጳውሎስ በእርሱ ከማፈራቸው በፊት የበለጠ እንዲያውቁትና ከዚያ በኋላ እንዲተማመኑት፥ ብሎም እንዲመኩበት ጠየቃቸው። ጳውሎስ ይህን ሲል በተለይም የሁሉም ሥራና ልብ በሚመዘንበት የክርስቶስ ምጽአት ቀን በጳውሎስ ሥራ እንደሚኮሩ መግለጹ ነበር። ጳውሎስ በዚህ ሁሉ፥ ከእነርሱ ጋር ግልጽና እውነተኛ ግንኙነት እንደሚያደርግ ቃል ገባላቸው።

ሁለተኛ፥ ጳውሎስ የጉብኝቱን ጊዜ የለወጠባቸውን ምክንያቶች ዘርዝሯል። ጳውሎስ ወደ ቆሮንቶስ የሚያደርገውን ጉዞ ያዘገየበት ዋነኛው ምክንያቱ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ማሰቡ ነበር። እርሱንና እነርሱን የሚጎዱ የግንኙነት ችግሮች እያሉ ሊጎበኛቸው አልፈለገም ነበር። ቀደም ሲል ጳውሎስ ቆሮንቶስን በጎበኘ ጊዜ ጥሩ ሁኔታ አላጋጠመውም ነበር። ስለሆነም፥ እንደ ሐዋርያ እግዚአብሔር የሰጠውን ሥልጣን በመጠቀም ፍርድ የሚሰጥበትን ተጨማሪ ጉብኝት ለማድረግ አልፈለገም ነበር። ቀደም ሲል በጻፈላቸው ጠንካራ ደብዳቤ አሳዝኗቸው ነበር። ይህን ጠንካራ ደብዳቤ የጻፈው በቀላሉ ሳይሆን፥ በዕንባ፥ በጭንቀትና በሥቃይ ነበር። ጳውሎስ የቆሮንቶስን ክርስቲያኖች አጥብቆ ስለሚወድ በቀላሉ ሊያሳዝናቸው ወይም በተሳሳተ ሕይወታቸው እንዲቀጥሉ ዝም ብሎ ሊተዋቸው አይችልም ነበር።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ዛሬ ብዙውን ጊዜ ሰዎች መሪዎችን የሚጠራጠሩት እንዴት ነው? ለ) ጳውሎስ የወሰዳቸው ሁለት እርምጃዎች እንዲህ ዓይነት ጥርጣሬዎችን ለመፍታት የሚረዱት እንዴት ነው?

  1. ንስሐ የገባውን ኃጢአተኛ ይቅር ስለ ማለት (2ኛ ቆሮ. 2፡5-11)

ጳውሎስ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖችን ለምን በዕቅዱ መሠረት እንዳልጎበኘ በ2ኛ ቆሮንቶስ 2፡12-13 እና በ2ኛ ቆሮንቶስ 7፡5-16 አብራርቷል። ነገር ግን ብዙውን ጊዜ በዚህ መልእክቱ ውስጥ እንደሚያደርገው፥ ጳውሎስ ዋነኛ ርእሰ ጉዳዩን ከቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ጋር ስለተፈጠረው የግንኙነት መበላሸት ያነሣል።

አንድ ሰው ግልጽ ኃጢአት በሚሠራበት ጊዜ ቤተ ክርስቲያን ብዙውን ጊዜ ከሁለት መንገዶች በአንዱ ምላሽ ትሰጣለች። አንዳንድ ጊዜ ኃጢአቱን ዝቅ አድርጋ በመመልከት ኃጢአተኛውን ከመቅጣት ወይም ንስሐ ለመግባት በማይፈልግበት ጊዜ የሥነ ሥርዓት እርምጃ ከመውሰድ ትታቀባለች። በ1ኛ ቆሮንቶስ ምዕራፍ 5 ከክርስቲያኖቹ አንዱ ከአባቱ ሚስት ጋር እያመነዘረ ሳለ ቤተ ክርስቲያኒቱ ምንም ዓይነት እርምጃ አለመውሰዱ ተገልጾአል። ጳውሎስ በዚያ ደብዳቤ ግለሰቡን ከቤተ ክርስቲያን ኅብረት በማውጣት እንዲቀጡት ጠይቋል። በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚከሰተውን ኃጢአት በጥብቅ ካልተከታተልን በፍጥነት ሊስፋፋና የጠቅላላይቱን ቤተ ክርስቲያን ቅድስና ሊያጠፋ ይችላል። ይህ ደግሞ የክርስቶስን ስም ያሰድባል። ሁለተኛ፥ ቤተ ክርስቲያን በኃጢአተኛው ግለሰብ ላይ የመረረ ቅጣት ልትበይን ትችላለች። ቤተ ክርስቲያን ግለሰቡ ንስሐ ከገባ በኋላ እንኳ ይቅርታና ዕርቅ ለመስጠት ላትፈቅድ ትችላለች። ጳውሎስ የ2ኛ ቆሮንቶስን መልእክት በሚፈጽፍበት ጊዜ ቤተ ክርስቲያኒቱ ይህንኑ ችግር እየተጋፈጠች ነበር።

ምናልባትም ጳውሎስና የቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን መጀመሪያ ያልተስማሙት ኃጢአተኛውን ግለሰብ ስለ መቅጣት የተለያየ አሳብ በመያዛቸው ሳይሆን አይቀርም። (በዚህ ክፍል የተጠቀሰው ግለሰብ በ1ኛ ቆሮ. 5 የተጠቀሰው ሰው ስለመሆኑ እርግጠኞች አይደለንም። አንዳንድ ምሁራን ይህ ሰው ጳውሎስን በመቃወምና በመሳደብ አንዳንድ ክርስቲያኖች እንዲያምፁበት ያደረገ ነበር ይላሉ።) መጀመሪያ የቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን በኃጢአት ውስጥ የነበረውን ግለሰብ ለመቅጣት አልፈለገችም ነበር። ጳውሎስ ግን የግድ መቀጣት እንዳለበት አሳሰባቸው። ምናልባትም የጠፋው መልእክት ስለዚሁ ጉዳይ የሚናገር ይሆናል (2ኛ ቆሮ. 2፡9)። ከተወሰነ ጊዜ በኋላ አብዛኞቹ ክርስቲያኖች ከጳውሎስ አሳብ ጋር በመስማማት ግለሰቡን ከቤተ ክርስቲያን ኅብረት አገለሉት። በኋላም ግለሰቡ ከልቡ ንስሐ እንደገባና የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ግን ወደ ኅብረቱ እንዳይገባ እንደከለከሉት ሰማ። ጳውሎስ በዚህ ጊዜ ይቅር እንዲሉትና በፍቅር ወደ ቤተ ክርስቲያን እንዲመልሱት ነገራቸው። የቤተ ክርስቲያን የሥነ ሥርዓት እርምጃ ዓላማ ንስሐ እንጂ ቅጣት አይደለም። ስለሆነም፥ ግለሰቡ ንስሐ በሚገባበት ወቅት ይቅር ለማለት መዘጋጀት አለብን። ጳውሎስ በሐዋርያዊ ሥልጣኑ ኃጢአተኛውን ይቅር ስላለ፥ እነርሱም ይህንኑ ማድረግ ነበረባቸው። ይቅር ለማለት አለመፈለግ ከሳሹ ሰይጣን በሁኔታው ውስጥ ድልን እንዲቀዳጅ ያደርጋል። ሰይጣን በኃጢአተኛው ሕይወት ውስጥ በመንገሥ እምነቱን ትቶ ወደ ዓለም እንዲመለስ ያደርገዋል። በጉዳዩ ላይ ክፍፍል እንዲፈጠር በማድረግ፥ በቤተ ክርስቲያንም ላይ ድል ይነሣል። በተጨማሪም፥ ቤተ ክርስቲያን ከምሕረት፥ ከይቅርታ፥ ከፍቅርና ከአንድነት ይልቅ የቤተ ክርስቲያን ደንብ በመሳሰሉት ውጫዊ ነገሮች ላይ ማተኮር ትጀምራለች።

የውይይት ጥያቄ፡- በቤተ ክርስቲያንህ የሥነ ሥርዓት እርምጃ የተወሰደበትን ሁኔታ ግለጽ። ሀ) ቅጣቱን እንዴት በቀላሉ ማካሄድ ይቻል እንደነበረ ግለጽ። ለ) ቅጣቱን እንዴት ጠንከር ባለ ሁኔታ ማካሄድ ይቻል እንደነበር ግለጽ። ሐ) ለዚህ የሥነ ሥርዓት እርምጃ የጳውሎስ ምክር ምን የሚሆን ይመስልሃል?

እንደ ክርስቲያኖች ምሕረት የሌለንና ይቅር የማንል ሰዎች ሆነን እንዳንታወቅ መጠንቀቅ አለብን። ሁላችንም በእግዚአብሔር ፊት ኃጢአተኞችና ቅጣት የሚገባን ሰዎች ነን። ማናችንም የመሪነት፥ የኳዬር፥ የጌታ እራት፥ ወዘተ. ተካፋይነት የሚገባን አይደለንም። ሰው ከልቡ ንስሐ በሚገባበት ጊዜ ይቅርታን እንደሚያገኝ መገንዘብ አለብን። የክርስቶስ ደም ከኃጢአት ሁሉ ያነጻናልና (1ኛ ዮሐ 1፡9)።

  1. ጳውሎስ ለምን እንዳልጎበኛቸው ማብራራቱን ይቀጥላል (2ኛ ቆሮ. 2፡12-13)

ምናልባትም በአካባቢው በተከሰተው ከፍተኛ ስደትና የሞት ዛቻ ሳቢያ ጳውሎስ ካሰበው ጊዜ ቀድሞ ኤፌሶንን ለቅቆ ሳይወጣ አልቀረም። ጳውሎስ ብዙ ክርስቲያኖች ለእርሱ መልካም አመለካከት እንዳልነበራቸው ከማወቁ በቀር ለጻፈው ደብዳቤ ስለሰጡት ምላሽ የሰማው ነገር ባለመኖሩ፥ ወደ ቆሮንቶስ ለመሄድ አልፈለገም ነበር። ስለሆነም፥ ወደ ጢሮአዳ ሄዶ ለጥቂት ጊዜ አገለገለ። ጳውሎስ በኋላ የጠፋውን መልእክት ወደ ቆሮንቶስ ያደረሰው ቲቶ በመቄዶንያ በኩል ወደ ጢሮአዳ እንዲመጣ የነገረው ይመስላል። ቲቶ ሳይመጣ ሲቀር ጳውሎስ ከአካይያ በስተሰሜን ወደምትገኘው መቄዶንያ ሄዶ ፈለገው። (ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: