መንፈሳዊ መሪ ለአዲሱ ኪዳንና ለእግዚአብሔር የማስቻል ኃይል አጽንኦት ይሰጣል (2ኛ ቆሮ. 2፡14-3፡18)።

ጳውሎስ ወደ በኋላ ቲቶን አግኝቶ ስለ ቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ንስሐና የአመለካከት ለውጥ ስለመስማቱ ይናገራል። ይህ የልብ ለውጥ የጳውሎስን ልብ በደስታ ሞላው (2ኛ ቆሮ. 7፡5-16)። ከቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ጋር ስለነበረው ግንኙነት ማሰብ ሲጀምር አእምሮው እግዚአብሔርን ስለማገልገሉ አስደናቂ ምሥጢር ያስብ ጀመር። ስለሆነም፥ ከ2ኛ ቆሮ. 2፡14 እስከ 2ኛ ቆሮ. 7፡1 ድረስ ጳውሎስ ስለ አገልግሎቱና እግዚአብሔር በመሪዎች ሕይወት ውስጥ ስለሚያከናውናቸው ተግባራት የተለያዩ ነገሮችን ያብራራል።

ሀ. በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የትኛውም ዓይነት ድልና ዕድገት ሊገኝ የሚችለው ከእግዚአብሔር ሥራ የተነሣ ነው (2ኛ ቆሮ. 2፡14-16)። ጳውሎስ ይህንኑ አሳብ ለማብራራት ስለ ሮም ጀኔራል የሚያስረዳ ምሳሌ ተጠቅሟል። ጀኔራሉ በጦርነት በሚያሸንፍበት ጊዜ በወታደሮቹና በምርኮኞቹ ታጅቦ ከጦር ሜዳ በፈረስ ይመለሳል። የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች ጀኔራል የሆነው ክርስቶስ ሁልጊዜም ባሪያዎቹንና ቤተ ክርስቲያንን በድል ይመራል። ብዙውን ጊዜ ጄኔራሉ ወደ ከተማ በሚገባበት ጊዜ ዕጣን ያጥኑለት ነበር። በተመሳሳይ ሁኔታ የክርስቶስ ወታደሮች (ክርስቲያኖች) ለክርስቶስ በሚሠሩበት ጊዜ እንደ ዕጣን የሚያውድ መዓዛ ይረጫሉ። ወንጌሉን ሰምተው ለሚድኑ ሰዎች የዘላለምን ሕይወት መዓዛ እናውዳለን። ወንጌሉን ሰምተው ለማመን ለማይፈልጉ ሰዎች ግን የሞትን መዓዛ እናውዳለን። የሞት ምርኮኞች ብዙውን ጊዜ እንደሚገደሉ ሁሉ የማያምኑ ሰዎችም የዘላለምን ሞት ይጋፈጣሉና።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) በማኅበረሰብህ ውስጥ የሕይወትና የሞት መዓዛ የምትሆንባቸውን መንገዶች ግለጽ። ለ) ያ መዓዛ ሊበላሽ የሚችልባቸውን መንገዶች ግለጽ።

ለ. ማንም ሰው የራሱን ጥበብና ችሎታ በመጠቀም ድል ሊነሣና ሌሎችን ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊመራ አይችልም። ይህንን ሊያደርግ የሚችለው እግዚአብሔር ብቻ ነው (2ኛ ቆሮ. 2፡16)፡፡

ሐ. በመንፈሳዊ ጦርነት ለክርስቶስ የሚዋጉ ሰዎች ንጹሕ ልብ ይዘው መዝለቃቸው በጣም አስፈላጊ ነው። የምንዋጋው ለራሳችን ሳይሆን ራሱ እግዚአብሔርን በመወከል ስለሆነ፥ ወንጌሉን በእውነትና በታማኝነት መስበክ እለብን (2ኛ ቆሮ.2፡17)። ምናልባትም ጳውሎስ ይህንን የተናገረው በቆሮንቶስ የተለየ የአገልግሎት እመለካከት የያዙ መሪዎች ወይም የሐሰት አስተማሪዎች እንደነበሩ ለማመልከት ይሆናል። እነዚህ ሰዎች ከወንጌል አገልግሎት የተነሣ በሚያገኙት ገንዘብና ክብር ላይ ያተኩሩ ነበር። ወንጌሉን እንዳሻቸው በመጠምዘዝ ከእግዚአብሔር መልእክት ይልቅ ለሰዎች ጆሮ እንደሚጥም አድርገው ያቀርቡ ነበር።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) የቤተ ክርስቲያን መሪዎችና ወንጌላውያን በሰይጣን ወጥመድ ተይዘው የተሳሳቱ ምክንያቶችን ሊያገለግሉ የሚችሉባቸውን መንገዶች ግለጽ። ለ) የቤተ ክርስቲያን መሪ ከሆንህ በጸሎት መንፈስ ሆነህ የአገልግሎት መነሻ ምክንያትህን መርምር። ሰይጣን አነሣሽ ምክንያቶችህን አበላሽቶ እንደሆነ ለማወቅ ልብህን መርምር። እንደዚያ ከሆነ፥ በጸሎት የእግዚአብሔርን ይቅርታ ጠይቅ። ካልሆነ፥ እግዚአብሔርን ስለጠበቀህ አመስግነውና በሙሉ ልብህ እርሱን የምትከተልበትን ጥበብ እንዲሰጥህ ጠይቅ።

መ. የጳውሎስ የሁለተኛው የወንጌል መልእክተኝነት ጉዞ ምስክርነት ውጤት፥ አስፈላጊዎቹ የደብዳቤ ማስተዋወቂያዎች ራሳቸው የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ነበሩ (2ኛ ቆሮ. 3፡1-3)። አንዳንድ የሐሰት አስተማሪዎች ከታዋቂ መሪዎች ወይም ከኢየሩሳሌም ቤተ ክርስቲያን የድጋፍ ደብዳቤ ይዘው በመምጣት እውነተኞቹ የቤተ ክርስቲያን ተወካዮች መሆናቸውን ሳይናገሩ አልቀሩም። (የኢየሩሳሌሟ ቤተ ክርስቲያን ቀደም ሲል ለጳውሎስ እንዲህ ዓይነት ደብዳቤ ሰጥታ ነበር- የሐዋ. 15፡23-29 አንብብ።) ነገር ግን ጳውሎስ በብጣሽ ወረቀት ወይም በሰዎች ድጋፍ ላይ አልተደገፈም ነበር። ነገር ግን እግዚአብሔር በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት በሕይወቱ ውስጥ በመሥራቱ ሰዎች በክርስቶስ አምነው ዳኑ። ጳውሎስ የፈለገው የእግዚአብሔር ተቀባይነትና ማረጋገጫ ይኸው ብቻ ነበር። የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች በክርስቶስ ማመን እግዚአብሔር ብዕር አንሥቶ በልባቸው ውስጥ ጳውሎስ አገልጋይ እንደሆነ የጻፈላቸው ያህል ነበር። ጳውሎስ ማንኛውንም ዘላቂ ተግባር ሊፈጽም የሚችለው እግዚአብሔር እንደሆነ ስለሚያውቅ፥ በራሱ ችሎታና ስሜት ላይ አልተደገፈም ነበር። እንደ ጳውሎስ ያሉትን ሰዎች በስጦታ ሞልቶ የተጠቀመባቸው ራሱ እግዚአብሔር ነበር።

ሠ. ጳውሎስ ከብሉይ ኪዳን ሕግጋት ይልቅ እጅግ በሚልቀው በአዲስ ኪዳን ላይ ትኩረት ሰጥቷል (2ኛ ቆሮ. 3፡4-18)። አይሁዳውያን የነበሩት የሐሰት አስተማሪዎች በብሉይ ኪዳን ሕግጋት ላይ በማተኮር የቆሮንቶስን ክርስቲያኖች ግራ ሳያጋቡ አልቀሩም። ሙሴንና ብሉይ ኪዳንን በመጥቀስ ሰዎች በዚያ ዓይነት ሕይወት ሊመላለሱ እንደሚገባ አስተማሩ። ይህም ጳውሎስ አሮጌውንና አዲሱን ኪዳን እንዲያነጻጽር አነሣሣው።

  1. ሞትን ያስከተለው ብሉይ ኪዳን በድንጋይ ላይ ነበር የተጻፈው። ከእግዚአብሔር ዘንድ በሙሴ በኩል ስለተላለፈ በክብር ነበር የመጣው። ይህ ኪዳን በክብር ቢመጣም (ሙሴ ከእግዚአብሔር ጋር በተገናኘ ጊዜ ፊቱ እንዳንጸባረቀው)፥ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየደበዘዘ መጥቷል። የተመለከቱት ክብር የሌሎቹን አይሁዶች ልብ ሊለውጥ አልቻለም ነበር። ይህን ክብር በመፍራታቸው ምክንያት ሙሴ ፊቱን እንዲሸፍን ጠየቁት። እግዚአብሔር በሙሴ በኩል የሰጣቸውን ሕግጋት ከመጠበቅ ይልቅ በልባቸው ውስጥ ያለማመንን መጋረጃ አኖሩ። ጳውሎስ አሁንም አብዛኞቹ አይሁዶች በዚህ መጋረጃ ተሸፍነው በክርስቶስ ከማመን እንደራቁ ገልጾአል።
  2. አዲስ ኪዳን የዘላለምን ሕይወት ያመጣል። ይህ ኪዳን በድንጋይ ላይ ሳይሆን በእያንዳንዱ ክርስቲያን ልብ ውስጥ ተጽፎአል። ክብሩም የሚደበዝዝ ሳይሆን እያደገ የሚሄድ ነው፡፡ ለደኅንነታቸው ወደ ክርስቶስ ለሚመለከቱ ሰዎች ያለማመን መጋረጃ ተወስዶላቸዋል። ራሳቸው የሚፈልጉትን ሳይሆን እግዚአብሔር የሚፈልግባቸውን እንዲሆኑ የሚረዳ መንፈስ ቅዱስ ተሰጥቷቸዋል። ከክርስቶስ ጋር ስንዛመድና ስለ እርሱ ባለን እውቀት ስናድግ፥ እኛም የክርስቶስን ክብር እናንጸባርቃለን። የእግዚአብሔር ክብር በእኛ ሕይወት ውስጥ አይደበዝዝም፤ ነገር ግን ክርስቶስን እንመስል ዘንድ ሕይወታችንን ይለውጠዋል። ምንም እንኳን ሁልጊዜ ኃጢአት መሥራታችን ባይቀርም ስንሞትና ከርስቶስን ስንመለከት፥ እርሱን እንደምንመስል ተነግሮናል (1ኛ ዮሐ 3፡2)።

የውይይት ጥያቄ፡- ጳውሎስ ከውጫዊ ነገሮች ይልቅ በልባችን ውስጥ ስላለው ስለ ክርስቶስ ስውር ክብር ይናገራል። ሀ) ብዙውን ጊዜ እንደ ጳውሎስ እግዚአብሔር የሰዎችን ውስጣዊ ሕይወት በመለወጥ ከርስቶስን እንዲመስሉ ከሚያደርግበት ሁኔታ ይልቅ እንደ ሐሰት አስተማሪዎቹ በውጫዊ ነገሮች ላይ የምናተኩረው እንዴት ነው? ለ) ለእግዚአብሔር አስፈላጊ የሆኑና ክርስቶስን በመምሰል ማደጋችንን የሚያሳዩ አንዳንድ ውስጣዊና ድብቅ ነገሮች ምን ምንድን ናቸው?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

Discover more from

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading