ጳውሎስ እውነተኛ ሐዋርያነቱን በመግለጽ ተከራከረ (2ኛ ቆሮ. 10፡1-13፡14)

ቲቶ በመቄዶንያ ከጳውሎስ ጋር በተገናኘ ጊዜ አብዛኛዎቹ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች እንደሚደግፉት ገለጸለት። ነገር ግን ጳውሎስን አጥብቀው የተቃወሙ ሌሎችም ሰዎች ነበሩ። ስለሆነም፥ በመልእክቱ መጨረሻ አካባቢ ጳውሎስ ሐዋርያነቱን ለተቃወሙት ሰዎች ጠንካራ የመከላከያ ሙግት ያቀርባል።

የውይይት ጥያቄ፡– 1ኛ ቆሮ. 10-13 አንብብ። ጳውሎስ እውነተኛ የክርስቶስ ሐዋርያ መሆኑን እንደሚያረጋግጡ የገለጻቸውን የተለያዩ ነገሮች ዘርዝር።

ሀ. ጳውሎስ የሚቃወሙትን ሰዎች እንደሚቀጣ ገልጾአል (2ኛ ቆሮ. 10፡1-6)። ምናልባትም ጳውሎስን የሚቃወሙ ሰዎች አብሯቸው በሚሆን ጊዜ እንደሚያፍርና መልእክቶችን በሚጽፍበት ጊዜ ግን እንደሚበረታ ተናግረው ነበር። በደብዳቤ እንጂ ከሰዎች ጋር ፊት ለፊት የመጋፈጥ ብቃት እንደሌለው ተናግረው ነበር። (ጳውሎስ ስለ ማፈርና መድፈር የተናገረው በምጸት ሰዎች በሰነዘሩበት ነቀፋ ላይ ምላሽ በመስጠት ነው።) ጳውሎስ ሐዋርያዊ ትምህርቱንና ሥልጣኑን የተቃወሙትን ሰዎች እንደሚጎብኝና ዓመፀኝነታቸውን እንደሚቀጣ አስረድቷል።

ነገር ግን ጳውሎስ ተቃዋሚዎቹን በዓለማዊ መንገድ ሊዋጋ አልፈለገም። ለመከራከር፥ ለመጣላት፥ የሰዎችን ባሕርይ ሊያጠቃ፥ ወዘተ… አልፈለገም። ካለመታዘዝ ተግባራቸው በስተጀርባ መንፈሳዊ ጦርነት እንዳለ ያውቅ ነበር። በመንፈሳዊ ውጊያው ሰይጣን የሚያነሣበትን ሙግት ለማጥፋት የሚያስችል የእግዚአብሔር ኃይል ነበረው። ጳውሎስ ታላላቆች ነን እያሉ የሰይጣን መጠቀሚያ በመሆን በእግዚአብሔር እውቀት ላይ የሚነሡትን ሰዎች ይዋጋ ነበር። ጳውሎስ ከመበቀልና ሰዎችን ከማጥቃት ይልቅ አሳቦቹን ሁሉ ለክርስቶስ ለመማረክ ወሰነ።

የሐሰት አስተማሪዎች ወይም በመንፈሳዊ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ላይ ተቃውሞ የሚሰነዝሩ ሰዎች የሰይጣን መጠቀሚያዎች ናቸው። ሰይጣን ዕቅዶቹን ለማስፋፋትና የእግዚአብሔርን ሥራ ለማፍረስ ሰዎችን ይጠቀማል። ጳውሎስ መራርነት፥ ቁጣና በሰዎች መካከል የሚከሰት ጠብ የሰይጣን ይዞታ (ሰይጣን የሚቆጣጠረው «ምሽግ») እንደሆነ ገልጾአል። ሰይጣን የውሸት አባት ስለሆነ፥ ክርክሮችንና የግብዝነትን ተግባራት በመፈጸም እውነትን ለማጥቃት ይሞከራል። ከሰይጣን ጋር በምናደርገው ትግል፥ «በኢየሱስ ስም ራቅ!» ማለቱ ብቻ በቂ አይደለም። አእምሯችንን (ስለ ሰዎች የምናስበውን፥ የቁጣና የመለያየት ስሜቶቻችንን) በመቆጣጠርና እውነትን በማወቅ ተግተን ልንሠራ ይገባል።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ሰይጣን በሕይወትህ ውስጥ ጠንካራ ይዞታ ስላገኘበት ሁኔታ ግለጽ። ለ) ያ ጠንካራ ይዞታ በተሳሳቱ አሳቦች፥ እምነት ወይም ውሸት ላይ የተመሠረተበትን ሁኔታ ግለጽ። ሐ) አሳባችንን መማረክና መቆጣጠር አስፈላጊ የሚሆነው ለምንድን ነው? መ) የሰይጣንን ውሸት በእውነት ማፍረስ አስፈላጊ የሚሆነው ለምንድን ነው?

ለ. ጳውሎስ ሰዎችን እያነጻጸሩ አንዳንዶችን እንደ ደካሞች ሌሎችን ደግሞ እንደ ብርቱዎች መፈረጁ ሞኝነት እንደሆነ አመልክቷል። ዋናው ቁም ነገር የእግዚአብሔር ለአንድ ሰው ያለው ምዘና ነው (2ኛ ቆሮ. 12፡7-18)። ጳውሎስን የተቃወሙት ሰዎች እንዲህ ሲሉ ደረጃውን ዝቅ አደረጉ። «የጳውሎስን መልእክት በምታነብበት ጊዜ ጠንካራ ቢመስልም፥ የመናገር ብቃት የሌለው ደካማ አገልጋይ ነው።» ራሳቸውን ወይም ሌሎች ዝነኛ ሰባኪያንን ከጳውሎስ ጋር በማነጻጸር የጳውሎስን ደካማነት ለማጉላት ሞከሩ። ጳውሎስ ለዚህ ዓይነቱ የኩራት አስተሳሰብ በሚከተለው መንገድ ምላሽ ሰጥቷል።

  1. ዋናው ነገር ወይም የሚሻለው የበለጠ ስጦታ ያለው ማን ነው? የሚለው አይደለም። ይህ የዓለም አስተሳሰብ ነው። ዋናው ነገር አንድ ሰው የክርስቶስ መሆኑና ታማኝ ክርስቲያን መሆኑ ነው።
  2. ጳውሎስ ራሱን ከሌሎች ጋር ከማነጻጸር ይልቅ ትምክህቱን ባከናወናቸው ተግባራት ወስኗል። እግዚአብሔር ወንጌሉን ወደ ቆሮንቶስ ለማምጣት በእርሱ በኩል ሠርቷል። በቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ትብብር እግዚአብሔር ወንጌሉን ወዳልሰሙት ለማዳረስ እንደሚጠቀምበት ጳውሎስ ተስፋ ያደርግ ነበር። የሐሰት አስተማሪዎች ግን ክርስቲያኖች ወደሚገኙባቸው አካባቢዎች በመሄድ ሕዝቡን ግራ ለማጋባት ፈለጉ። እነዚህ የሐሰት አስተማሪዎች እንደ ጳውሎስና አጵሎስ ያሉ አገልጋዮች ባከናወኗቸው ሥራዎች ይመኩ ነበር። ደግሞም በቤተሰባቸው ስም፥ በዘር ሐረጋቸው ወይም በትምህርታቸው ይመኩ ነበር።
  3. በመጨረሻም፥ ዋናው ነገር እኛ ስለ ራሳችን ወይም ስለ አገልግሎታችን የምንናገረው ሳይሆን እግዚአብሔር የሚናገረው ነው። እግዚአብሔር ወንጌል ባልደረሰባቸው ስፍራዎች ወንጌልን ለማድረስ እየተጠቀመበት ከጳውሎስ ጋር አብሮ በመሥራት ላይ መሆኑን አሳይቷል። በመጨረሻም፥ ጌታ ኢየሱስ ጳውሎስና የሐሰት አስተማሪዎች ያከናወኑትን ተግባር በመመዘን ላከናወኑት ተግባር ያመሰግናቸዋል ወይም ይወቅላቸዋል።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ዛሬ ክርስቲያኖች (አብያተ ክርስቲያናት) ራሳቸውን ከሌሎች ጋር በማነጻጸር ወይም ከሌሎች የተሻለ አገልግሎት እንደሚሰጡ በማሰብ ለሰይጣን ወጥመድ የሚጋለጡት እንዴት ነው? ለ) ሰዎች በሚተቹን ጊዜ የመጨረሻው ፈራጅ እግዚአብሔር እንደሆነ ማስታወስ አስፈላጊ የሚሆነው ለምንድን ነው?

ሐ. ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ግድ የተሰኘበትን ምክንያት ያብራራል (2ኛ ቆሮ. 11፡1-6)። ሐሰተኛ አስተማሪዎች በጳውሎስ ሐዋርያነት ላይ ጥርጣሬ በመዝራት አገልግሎቱን ለማዳከም ይጥሩ ነበር። ጳውሎስን ከዋነኞቹ ሐዋርያት፥ ማለትም ኢየሱስ ካሠለጠናቸው ከ12ቱ ሐዋርያት ጋር አነጻጸሩት (ለምሳሌ ዮሐንስ፥ ጴጥሮስ)። ጳውሎስ ተገቢውን ትምህርት አላገኘም፤ «የሠለጠነ ሰባኪ» አይደለም ይሉ ነበር።

ጳውሎስ ራሱን ከሁሉም ሐዋርያት እኩል አድርጎ እንደሚመለከት ገልጾአል። ነገር ግን ጳውሎስ ሐዋርያነቱን የሚያረጋግጡ አሳቦችን ከማቅረቡ በፊት፥ ለእርሱ የነበራቸው አመለካከት ለምን እንዳሳሰበው ያስረዳል። የእርሱ ራእይ ቆሮንቶስን ጨምሮ የመሠረታቸውን አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ ለጌታ ለኢየሱስ ክርስቶስ እንደ ንጽሕት ሙሽራ ማቅረብ ነበር። በኃጢአት ወይም የሐሰት ትምህርቶችን በመከተላቸው ምክንያት የክርስቲያኖች ንጽሕና እንዲጓደል አልፈለገም ነበር። ቤተ ክርስቲያን ከኃጢአት ጸድታ፥ በፍቅር አድጋ፥ እውነትን በመከተልና በመታዘዝ ለክርስቶስ ንጹሕ ድንግል እንድትሆን ይፈልጋል። ስለሆነም፥ ጳውሎስ በክፍፍልና የሐሰት ትምህርቶች አማካኝነት የቤተ ክርስቲያንን ንጽሕና ያጓደሉትን የሐሰት አስተማሪዎች በጽናት ይታገላል። ጳውሎስ የሐሰት ሐዋርያት ስሙን ከማጉደፋቸውም በላይ ንጹሕ ያልሆነ ወንጌል እያስተማሩ መሆናቸውን ተረድቶ ነበር። የተዛባ ወንጌል ድነት (ደኅንነትን) የሚያስገኝ እየመሰለ ወደ ዘላለማዊ ኩነኔ የሚመራ በመሆኑ አደገኛ ነው።

መ. ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ላበረከተው አገልግሎት የገንዘብ ክፍያ ያልተቀበለበትን ምክንያት ያስረዳል (2ኛ ቆሮ. 11፡7-12)። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የምናገኘው የተለመደ አሠራር ቤተ ክርስቲያንን የሚያገለግሉ ሰዎች ከቤተ ክርስቲያኒቱ ደመወዝ መቀበል እንዳለባቸው የሚያሳይ ነው (1ኛ ቆሮ. 9፡7-18ን እንብብ።) ጳውሎስ ግን በአብያተ ክርስቲያናት ውስጥ በሚያገለግልበት ጊዜ ይህንን አሠራር አልተከተለም። ከሚያገለግልባቸው አብያተ ክርስቲያናት ለአገልግሎቱ ገንዘብ ለመቀበል አልፈለገም ነበር። የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች አስፈላጊ ሙያተኞች ሁሉ ደመወዝ መቀበል አለባቸው የሚል ባሕላዊ አመለካከት ነበራቸው፡፡ በዚህም ምክንያት የጳውሎስን ዓላማ በተሳሳተ መንገድ ተረዱት። ጳውሎስ ገነዘቡን ያልጠየቀው አገልግሎቱ ዋጋ እንደማያወጣ በማሰብ ነበር? ጳውሎስ ደመወዝ መቀበልን ያልፈለገው ማንም ሰው ወንጌሉን የሚሰብከው ሀብታም ለመሆን ሲል ነው ብሎ እንዳያስብ ነበር። ጳውሎስ ሕዝቡ የአገልግሎት መነሣሻ ምክንያቱን ከመመርመር ይልቅ በወንጌሉ እውነት ላይ እንዲያተኩሩ ነበር የፈለገው።

ሰዎች የወንጌል መልእክተኛው የተነሣሣበትን ምክንያት በሚጠራጠሩበት ጊዜ ወንጌሉን ለመቀበል ይቸገራሉ። እንግዲህ ጳውሎስ የሚተዳደርበትን ንዘብ ከየት ያገኛል? ጳውሎስ ሌሎች አብያተ ክርስቲያናትን እንደ «ዘረፈ» ይናገራል። ጳውሎስ ከእነዚያ አብያተ ክርስቲያናት ገንዘብ አልሰረቀም። ነገር ግን የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ገንዘባችንን ፈልጎ መጣ ብለው እንዳያስቡ ለማድረግ የወሰደውን እርምጃ ለማሳየት ጠንካራ አገላለጽ ይጠቀማል። ጳውሎስ በቆሮንቶስ አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ በሚያገለግልበት ጊዜ ከእነርሱ ደመወዝ አልጠየቀም ነበር። ነገር ግን ወደ ሌሎች የአገልግሎት ስፍራዎች በሚሄድበት ጊዜ እንደ መቄዶንያ አማኞች ያሉ ሌሎች አብያተ ክርስቲያናት በገንዘብ እንዲደግፉትና የወንጌል አገልግሎቱ ተካፋይ እንዲሆኑ ጠይቋል።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ገንዘብን መቀበል አንድን በአገልግሎቱ ላይ ያለን ሰው እንዴት ለጥርጣሬ እንደሚያጋልጥ ግለጽ። ለ) የቤተ ክርስቲያን የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች ወንጌሉን የሚሰብኩት ገንዘብ ለማግኘት ነው የሚል ትችት እንዳይሰነዘርባቸው መጠንቀቅ ያለባቸው ለምንድን ነው? ሐ) ለቤተ ክርስቲያን አገልጋይ ብዙ ደመወዝ መቀበል እደገኛ የሚሆነው ለምንድን ነው?

ሠ. ጳውሎስ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች መልካም እየመሰሉ የሰይጣን መሣሪያዎች ሆነው ከሚሠሩት ሐሰተኛ ሐዋርያት እንዲጠነቀቁ አስጠነቀቃቸው (2ኛ ቆሮ. 11፡13-15)። ጳውሎስ ስሙን ለማጥፋትና የቆሮንቶስ ክርስቲያኖችን ከእርሱ ለማራቅ ስለሚሞክሩት ሰዎች በቀጥተኛ አገላለጽ ብዙም አልተናገረም። «ሐሰተኛ» ሐዋርያት ብሏቸዋል። በአዲስ ኪዳን ቤተ ክርስቲያን ሁለት የሐዋርያነት ደረጃዎች ነበሩ። 12ቱ ሐዋርያትና ጳውሎስ በቤተ ክርስቲያን ላይ ልዩ ሥልጣን ነበራቸው። ሌሎች በተወሰኑ ጉዳዮች ላይ ጠቃሚ አገልግሎት ያበረከቱ ሐዋርያትም ነበሩ (ሮሜ 16፡7)። ጳውሎስ ግን በቆሮንቶስ የነበሩትን የሐሰት አስተማሪዎች «ሐሰተኛ ሐዋርያት» ብሏቸዋል። እነዚህ ሰዎች በኢየሩሳሌም ከሚገኙ ታላላቅ ሐዋርያት እንደተላኩ ተናግረው ይሆናል። ግለሰቦቹ ማንነታቸውን የሚገልጽ የማስተዋወቂያ ደብዳቤ ይዘው ቢመጡም፥ መልእክታቸው ከእግዚአብሔር ባለመሆኑ ሐሰተኛ ሐዋርያት ነበሩ። ጥሩ ስጦታ ያላቸውና፥ በንግግር ችሎታ የተካኑ፥ መልካም መልእክት የያዙ የሚመስሉና በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የተወደዱ ሊመስሉ ይችላሉ። ጳውሎስ እንዴት ሐሰተኛ ናቸው ሊል ቻለ? ጳውሎስ እነዚህ ሰዎች እንደ መንፈሳዊ አባታቸው ሰይጣን በመሆናቸው መልካም መስለው ተወዳጅነትን እንዳተረፉ በመግለጽ የቆሮንቶስን ክርስቲያኖች ያስጠነቅቃል። ሰይጣን ብዙውን ጊዜ የእግዚአብሔርን ልጆች ግራ ለማጋባት በሚፈልግበት ጊዜ እንደ ክፉ ሰው ሳይሆን እንደ ብርሃን መልአክ ሆኖ ነው የሚመጣው። ቃላቱና ትምህርቶቹ ለጆሮ የሚጥሙ ቢመስሉም የኋላ ኋላ ግን ግራ መጋባትንና ሞትን ያስከትላሉ። በተመሳሳይ ሁኔታ፥ የሐሰት አስተማሪዎች መንፈሳዊና ጥሩ መልእክት የሚናገሩ ይመስላሉ። ክፉ ባሕርያቸው ለሰዎች የሚታወቀው ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ነው።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) የሐሰት አስተማሪዎች የጽድቅ አገልጋዮች መስለው በመቅረብ የእግዚአብሔርን ሕዝብ ሲከፋፍሉና ሲጎዱ የተመለከትህበትን ሁኔታ ግለጽ። ለ) ይህ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች እውነትን በሚገባ ስመረዳት፥ ጥሩ የሚመስሉ ቃላት እየተናገሩና ከመጠን ያለፈ «መንፈሳዊነትን» እያሳዩ ከሚመጡ ሰዎች ስለመጠንቀቃቸው አስፈላጊነት ምን ያስተምራል?

ረ ጳውሎስ ለወንጌሉ ከተቀበለው መከራ ስለ እውነተኛነቱና ሐዋርያነቱ መረዳት ይቻላል (2ኛ ቆሮ. 11፡16-33)። የሐሰት አስተማሪዎቹ ምናልባትም የአብርሃም ዘሮች መሆናቸውን በትምክህት የተናገሩ አይሁዶች ሳይሆኑ አይቀሩም። ምንም እንኳ ጳውሎስ ስለ ራሱ ለመናገር ባይፈልግም፥ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ስለ ሐዋርያነቱ የተሳሳተ አመለካከት እንዳይኖራቸው ለመከላከል ሲል ስለ ሕይወቱ የሚከተለውን ብሏል።

  1. ጳውሎስ ከአብርሃም ዘር የተገኘ አጥባቂ አይሁዳዊ ነበር። እርሱ ጥርት ያለ አይሁዳዊ ነበር።
  2. ጳውሎስ ሙሉ በሙሉ ሕይወቱን ለጌታ ለኢየሱስ ክርስቶስ ሰጥቷል። ይህም ወንጌሉን ለመስበክ ሲል በተቀበላቸው ብዙ የስደትና የአደጋ ዓይነቶች ታይቷል። ብዙውን ጊዜ ለግል ክብርና ለገንዘብ ጥቅም የሚያገለግሉ ሰዎች ከመከራ ይሸሻሉ። ለወንጌሉ ራሳቸውን፥ ምኞቶቻቸውንና ሕይወታቸውን የሚሠዉት የተሰጡ ግለሰቦች ናቸው።
  3. ጳውሎስ ለቤተ ክርስቲያን የነበረው ጭንቀት ከፍተኛ ነበረ። ጳውሎስ ቤተ ክርስቲያንን መመሥረት ብቻ ሳይሆን የአማኞች መንፈሳዊ ዕድገትም በጥልቅ ያሳስበው ነበር። ስለሆነም፥ ክርስቲያኖች በሚጎዱበት ጊዜ እርሱም አብሯቸው ይጎዳል።

ሰ. የጳውሎስ መንፈሳዊ ልምምድ ከሌሎቹ የጠለቀ ነበር (2ኛ ቆሮ. 12፡1-10)። ብዙውን ጊዜ ሐሰተኛ አስተማሪዎች መንፈሳዊነታቸውን አለአግባብ ለማሳየት ይተጋሉ። በልሳን የመናገር፥ የመፈወስ፥ የመጸለይና የመሳሰለው ችሎታ እንዳላቸው ለማሳየት ይተጋሉ። ጳውሎስም ከእነርሱ የላቀ መንፈሳዊ ልምምድ እንዳለው ይነግራቸዋል። እግዚአብሔር በራእይ ወደ መንግሥተ ሰማይ፥ ገነት ወይም ሦስተኛ ሰማይ ወስዶ ለሌሎች መናገር ያልተፈቀደለትን ነገር አሳይቶታል።

ነገር ግን ጳውሎስ መንፈሳዊ ኩራት ለቤተ ክርስቲያን መሪዎች እጅግ አደገኛ ከሆኑት ነገሮች አንዱ መሆኑን ያውቃል። እግዚአብሔር ሰው በችሎታው ወይም በመንፈሳዊ ልምምዱ መኩራራቱን ይጠላል። እግዚአብሔር ኩራተኞች (ትዕቢተኞችን) ለማዋረድ ወስኗል (ያዕ. 4፡6)። ስለሆነም፥ ጳውሎስ ዋናው ነገር በክርስቶስ ላይ ሙሉ በሙሉ መደገፍ እንጂ መንፈሳዊ ልምምድ እንዳልሆነ ያስረዳል። እግዚአብሔር ጳውሎስ በትሕትና ይመላለስ ዘንድ የሥጋ መውጊያ ሰጠው። ጳውሎስ እግዚአብሔር ይህን መውጊያ እንደሰጠው እየተናገረ በተመሳሳይ ጊዜ መውጊያው «የሰይጣን መልእክተኛ» ነው ማለቱ አስገራሚ ነው። ይህም እግዚአብሔር ሰይጣን በልጆቹ ላይ የሚያመጣውን ጥቃት ጨምሮ ሁሉንም ነገር እንደሚቆጣጠር ያሳያል። ምንም እንኳ ጳውሎስን በመውጊያው በቀጥታ ያጠቃው ሰይጣን ቢሆንም፥ ጳውሎስ ሰይጣን እርሱን ትሑትና የእግዚአብሔር ጥገኛ ለማድረግ የተላከ የእግዚአብሔር መሣሪያ መሆኑን ተረድቷል። ይህ የሥጋ መውጊያ ምን እንደሆነ አናውቅም። አንዳንድ ምሁራን ይህ እንደ እይታ ችግር ያለ የአካል ጉድለት እንደነበር ይናገራሉ። ጳውሎስ ይህ ችግር እንዲወገድለት ሦስት ጊዜ ቢጸልይም የፈለገውን ምላሽ አላገኘም። እግዚአብሔር ጸሎታችንን እኛ በምንፈልገው መንገድ አይመልስም። አንዳንድ ጊዜ «አይሆንም» የሚልባቸው ጊዜያት አሉ። እግዚአብሔር ለጳውሎስ «አይሆንም» ያለው ለምን ነበር? ጳውሎስ ከዚህ ምን ተማረ? ጳውሎስ እግዚአብሔር አንዳንድ ጊዜ ለልጆቹ መውጊያ በመስጠት በጸጋው ላይ ተደግፈን እንድንገዛለት እንደሚያደርግ ገልጾአል። ሰዎች የእግዚአብሔርን ኃይል ሊያዩ የሚችሉት እግዚአብሔር ከድካማችን ባሻገር ሲጠቀምብን ነው።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ስለ ጸሎት፥ እግዚአብሔር ጸሎትን ስለሚመለከትበት ሁኔታና ስለ መከራ ከጳውሎስ ሕይወት ምን እንማራለን? ለ) እግዚአብሔር ለአንድ ሰው መውጊያ ሰጥቶ ሳለ በከፍተኛ ሁኔታ የተጠቀመበትን ሁኔታ ግለጽ።

ሸ. እግዚአብሔር ጳውሎስ እንደ «ታላላቆቹ ሐዋርያት» ተአምራትን እንዲሠራ አድርጓል (2ኛ ቆሮ. 12፡11-13)፡፡

ቀ. ጳውሎስና ወኪሎቹ ለቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን የገንዘብ ሸክም ለመሆን አልፈለጉም (2ኛ ቆሮ. 12፡14-21)። ጳውሎስ እንደገና እንደሚጎበኛቸውና ነገር ግን የገንዘብ ሸክም እንደማይሆንባቸው ገልጾአል። ጳውሎስ እንደ መንፈሳዊ አባታቸው በእምነታቸው እንዲያድጉ ለማበረታታት ሁሉንም ነገር ሊሰጣቸው ፈቃደኛ ነበር። ነገር ግን መንፈሳዊ ልጆቹ እንደመሆናቸው መጠን ምንም ዓይነት የገንዘብ ችግር እንዲደርስባቸው አልፈለገም። ጳውሎስ ቤተ ክርስቲያኒቱን በሚጎበኝበት ጊዜ ክርስቲያኖቹ በክፍፍልና በወሲባዊ እርኩሰቶች ተሞልተው እንዳይቆዩና እርሱ እንደሚፈልገው በፍቅር ሳይሆን በቁጣና በቅጣት እንዳያገኛቸው ሰግቷል።

ስ. ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች የመጨረሻ ማስጠንቀቂያውን ሰጣቸው (2ኛ ቆሮ. 13፡1-10)። ጳውሎስ በቅርቡ ለሦስተኛ ጊዜ እንደሚጎበኛቸው ገልጾአል። በሚመጣበት ጊዜ የትዕግሥትና የመቻቻል ገደብ ስለሚያበቃ እርሱንና እግዚአብሔርን በተቃወሙት ሰዎች ላይ ፍርድን ይበይናል። ወንጌሉን ለመስበክ ብቻ ሳይሆን ንስሐ ለመግባት ባልፈለጉት ዓመፀኛ ክርስቲያኖች ላይ ቅጣት ለመስጠት ሐዋርያዊ ሥልጣን እንዳለው ያሳያቸዋል።

ጳውሎስ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ራሳቸውን እንዲመረምሩ ያበረታታቸዋል። ጳውሎስ የሰበከላቸውን እምነት ይዘው እየተመላለሱ ናቸው ወይስ ሌላ ወንጌል ተቀብለዋል? በትሕትና፥ ንጽሕናና ታዛዥነት እየተመላለሱ ናቸው ወይስ የዓመፀኝነት መንፈስ አለባቸው። መንፈሳዊ ምዘና ለሁላችንም ጠቃሚ ነው። ከጊዜ ወደ ጊዜ ራሳችንን ካልመረመርን፥ በቀላሉ በኃጢአት ልንወድቅ፥ ለክርስቶስ ካለን የመጀመሪያ ፍቅር ልንወሰድና ለክርስቶስ የነበረንን ቅንዓት ልናጣ እንችላለን። ሕይወታችንን፥ ልባችንን፥ ተግባራችንንና አሳባችንን የመመርመርና የማረም ልማድ ካለን፥ ክርስቶስን ወደ መምሰል እናድጋለን።

ተ. ጳውሎስ ለአማኞች የስንብት ሰላምታ ያቀርባል (2ኛ ቆሮ. 13፡11-14)። ጳውሎስ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ለፍጹምነት እንዲተጉና እግዚአብሔር በሚፈልጋቸው መንገድ እንዲኖሩ ያበረታታቸዋል። እርስ በርሳቸው በአንድነት እንዲኖሩ ይማፀናቸዋል። የኢየሱስ ጸጋ፥ የእግዚአብሔር አብ ፍቅርና የመንፈስ ቅዱስ ኅብረት ከእነርሱና ከእኛ ጋር እንዲሆን ይጸልያል። ይህም ተግባራዊ የሚሆነው እግዚአብሔርን ለማስደሰት በማሰብ በፍቅር፥ በታዛዥነትና በአንድነት ስንመላለስ ነው።

የውይይት ጥያቄ፡- 2ኛ ቆሮንቶስ የጳውሎስ እጅግ ግላዊ መልእክት ነው። ሀ) ከጳውሎስ፥ ከመነሣሻ ምክንያቶቹ፥ ከተግባሮቹና ከሙከራዎቹ ያስገረመህን ዘርዝር። ለ) ከዚህ መልእክት ስለ ቤተ ክርስቲያን አመራር ምን እንማራለን?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: