ተስፋጽዮን በጀማ የወንጌል ስብከት ላይ ስለ ክርስቶስ ሰምቶ በክርስቶስ አመነ። ከዚያ በኋላ ከተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት ተወካዮች ጋር ተገናኘ። በስብሰባው ላይ የቃለ ሕይወት፥ የመካነ ኢየሱስ፥ የሙሉ ወንጌል፥ የመሠረተ ክርስቶስ፥ የሕይወት ብርሃንና የሌሎች ብዙ አብያተ ክርስቲያናት መሪዎች ነበሩ። ሁሉም ተስፋጽዮን ወደ ቤተ ክርስቲያናቸው እንዲመጣ ገፋፉት። ሁሉም ወደ ቤተ ክርስቲያናቸው እንዲመጣ ለማግባባት፥ «ከሁሉም የሚበልጡ ብዙ ምእመናን አሉን። ቃሉን እናስተምራለን። የመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎች አሉን» ሲሉ አዋከቡት። ተስፋጽዮን በዚህ ሁኔታ ግራ ተጋባ። «ቤተ ክርስቲያን ምንድን ናት? እንዲህ ቤተ እምነቶች የበዙት ለምንድን ነው? ትክክለኛው ቤተ እምነት የትኛው ነው?» ሲል ራሱን ጠየቀ።
ጥያቄ፡- ሀ) የተለያዩ ቤተ እምነቶች አዳዲስ ክርስቲያኖችንና አማኞች ያልሆኑትን ሰዎች ግራ የሚያጋቡት እንዴት ነው? ለ) ቤተ እምነቶች የበዙት ለምንድን ነው? ሐ) ጤናማ ይመስልሃል? ለምን? መ) በአማርኛ ቋንቋ «ቤተ ክርስቲያን» የሚለው ቃል ምን ትርጉም ይሰጣል?
በአሁኑ ዘመን ብዙ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት የሚገኙ ሲሆን፥ ሌሎች ብዙዎችም እዚሁ ቅርንጫፎችን ለመመሥረት ከምዕራባውያን አገሮች እየጎረፉ ናቸው። እነዚህ ብዙ ቤተ እምነቶች የሚመጡት ከየት ነው? ቤተ እምነቶች የበዙትስ ለምንድን ነው? በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙት አብዛኛዎቹ ቤተ እምነቶች ከሚከተሉት ምንጮች የመጡ ናቸው።
በመጀመሪያ፥ ከምዕራቡ ዓለም የመነጩ ቤተ እምነቶች አሉ። የተለያዩ ሚስዮናውያን ወደ ኢትዮጵያ መጥተው በአገራቸው ያሉትን ዓይነት ቤተ እምነቶች መሥርተዋል። እነዚህ ቤተ እምነቶች ከየት የመጡ ናቸው? አብዛኞቹ የምዕራቡ ዓለም ቤተ እምነቶች በትናንሽ የአስተምህሯዊ ልዩነቶች ምክንያት የተፈጠሩ ናቸው። ከእነዚህ አስተምህሯዊ ልዩነቶች መካከል አንዳንዶቹ የሕፃናት ወይም የአዋቂዎች ጥምቀት፥ የቅዱስ ቁርባን ፍችና የመንፈስ ቅዱስ ቀዳሚ አገልግሎት ምንነትን የሚመለከቱ ናቸው።
ሁለተኛ፥ ሌሎች ቤተ እምነቶች የራሳቸውን ቤተ እምነቶች የጀመሩትን ታላላቅ መሪዎች፥ ሰባኪዎች ወይም የፈውስ አገልጋዮች በመከተል የተመሠረቱ ናቸው። ይህ በኢትዮጵያ ብዙም ያልተለመደ ቢሆንም፥ በሌሎች የአፍሪካ አገሮች ግን በመቶዎች የሚቆጠሩ ቤተ እምነቶች በመሪዎች ስም ተመሥርተዋል።
ሦስተኛ፥ የአንዲት ቤተ ክርስቲያን መእመናን በሰላም ለመኖር ባለመቻላቸው ምክንያት የተጀመሩ ቤተ እምነቶችም አሉ።
ባለመስማማታቸው ምክንያት ተከፋፍለው የየራሳቸውን ቤተ እምነቶች ይመሠርታሉ። ብዙውን ጊዜ የእነዚህ ክፍፍሎች ምክንያቶች፥ ጎሰኝነት በተወሰኑ ልምምዶች ላይ በሚከሰቱ የአመለካከት ልዩነቶች ወይም ሰብአዊ ኩራት ናቸው።
የሚያሳዝነው ከእነዚህ ምክንያቶች አንዳቸውም አዲስ ቤተ እምነት ለመመሥረት የሚያበቁ አለመሆናቸው ነው። ሁልጊዜም በትናንሽ የመጽሐፍ ቅዱስ አስተምህሮዎች ላይ የአሳብ ልዩነት የሚያሳዩ ክርስቲያኖች ይኖራሉ። ዓይን ለዓይን እንኳን መተያየት የማይፈልጉ መሪዎችም ይኖራሉ። ሁልጊዜም በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በተወሰኑ ጉዳዮች ወይም ልምምዶች ላይ ውጥረቶች ይኖራሉ። እግዚአብሔር ግን ከእነዚህ ምክንያቶች አንዱም አዲስ ቤተ እምነት ለመጀመር ብቁ መሆናቸውን አያረጋግጥም። ክርስቲያኖች ባለመስማማታቸው ምክንያት መከፋፈል መከሰቱ እጅግ አሳዛኝ ነገር ነው። በዮሐንስ 17 ክርስቶስ ተከታዮቹ አንድነትን እንዲመሠርቱ ጸልዮአል። ጳውሎስ ክርስቲያኖች አንድ አሳብ እንዲኖራቸው ተማጽኗል (ፊልጵ. 2፡1-2)። ነገር ግን ከኃጢአተኝነታችንና ከኩራታችን የተነሣ ክፍፍሎች ይከሰታሉ።
የቤተ እምነቶች መፈጠር ስሕተት ነውን? የተመሠረቱበት ዓላማ ስሕተት ከሆነ፥ እንዲሁም የውድድርና የኩራት መንፈስ የሚታይባቸው ከሆነ፥ የቤተ እምነቶች መፈጠር ትክክል ሊሆን አይችልም። አንዱ ቤተ እምነት ከሌሎች እንደሚበልጥ ሲያስተምርና የተለያዩ ቤተ እምነቶች ተከታዮች እርስ በርሳቸው ቢጣሉ፥ ወይም አንዱ የሌላውን አባላት ለመውሰድ ቢሞክር፥ ይህ የአንድ ቤተሰብ አባላት የሆኑ ወንድማማቾችን ማጣላት ያህል አስከፊ ነው።
በሌላ በኩል፥ የተለያዩ ቤተ እምነቶች መፈጠር እግዚአብሔርን ሊያስከብር ይችላል። የተለያዩ ብዙ ዓይነት ዛፎች ለአንድ አካባቢ ውበትን እንደሚጨምሩ ሁሉ፥ የተለያዩ የአምልኮ ስልቶችና ልምምዶች ያሏቸው ብዙ ቤተ እምነቶች የውበት መገለጫዎች ሊሆኑ ይችላሉ። ነገር ግን ይህ የቤተ እምነቶች ልዩነት የታላቁ የክርስቶስ አካል ክፍሎች የመሆናችንን አንድነት ያገናዘበ ሊሆን ይገባል። በፍጥረት ውስጥ የምንመለከተው በአንድነት ውስጥ ያለ ልዩነት በቤተ ክርስቲያንም ውስጥ ሊንጸባረቅ ይገባል።
የኤፌሶን መልእክት በክርስቶስ አካል ወይም በቤተ ክርስቲያን ላይ ያተኩራል። ቤተ ክርስቲያን ምንድን ናት? በአማርኛ ቋንቋ፥ ቃሉ ሕንፃ ወይም የክርስቲያኖችን መሰብሰቢያ ያመለክታል። አዲስ ኪዳን ግን ሕንፃን ለማመልከት «ቤተ ክርስቲያን» የሚለውን ቃል የተጠቀመበት ስፍራ የለም። እንዲያውም፥ ከሐዋርያት ዘመን ጀምሮ ለብዙ መቶ ዓመታት ክርስቲያኖች ሁነኛ የመሰባሰቢያ ስፍራ አልነበራቸውም። በአዲስ ኪዳን ቤተ ክርስቲያንን የሚለው ቃል በሰዎች ላይ ያተኩራል። በግሪክ ቋንቋ፥ ቃሉ «ጉባኤ»ን ወይም የተወሰኑ ሰዎችን «አብሮ መሰባሰብ» ያመለክታል። የአንዲት ከተማ ነዋሪዎች ለስብሰባ ተጠርተው የሚያካሂዱት ስብሰባ ቤተ ክርስቲያን ይባል ነበር። ስለሆነም ከዓለም ወደ ክርስቶስ አካል የተጠሩት ክርስቲያኖች የሚያካሂዱትም ስብሰባ ቤተ ክርስቲያን ይባላል።
በአዲስ ኪዳን፥ ቤተ ክርስቲያን የሚለው ቃል ሦስት የክርስቲያን ቡድኖችን ሊያመለክት ይችላል። በመጀመሪያ፥ ብዙውን ጊዜ የአጥቢያ ክርስቲያኖችን በአንድ አካባቢ መሰባሰብ ሊያመለክት ይችላል (ሮሜ 16፡5)። አብዛኞቹ የቀድሞዎቹ አብያተ ክርስቲያናት በግለሰቦች ቤቶች ውስጥ ይሰባሰቡ ነበር። ወደ 50 የሚሆኑ ሰዎች በመደበኛነት በግለሰቦች ቤቶች ውስጥ እየተሰባሰቡ ያመልኩና መጽሐፍ ቅዱስ ያጠኑ ነበር። ሁለተኛ ቤተ ክርስቲያን የሚለው ቃል በአንድ መልክዓ ምድራዊ ክልል ውስጥ የሚገኙትን ክርስቲያኖች ሊያመለክት ይችላል። ለምሳሌ ያህል፥ ጳውሎስ ለሮሜ ወይም ለቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ጽፎአል። እነዚህ አብያተ ክርስቲያናት ከአንድ ሕንፃ ሥር የሚሰባሰቡ ሳይሆኑ፥ በተለያዩ ቤቶች ውስጥ የሚሰባሰቡ የአንድ አካባቢ ክርስቲያኖች ነበሩ። ዛሬ በተመሳሳይ ሁኔታ «የአፍሪካ ቤተ ክርስቲያን» ወይም «የብሪታኒያ ቤተ ክርስቲያን» ልንል እንችላለን። ሦስተኛ፥ ዓለም አቀፋዊት (ዩኒቨርሳል) ቤተ ክርስቲያን አለች። ይህ የሞቱትንና በሕይወት ያሉትን፥ በሰማይና በምድር ያሉትን ጨምሮ የክርስቶስ አካል የሆኑትን ሁሉ ያጠቃልላል (ዕብ. 12፡23)። ጳውሎስ በኤፌሶን መልእክት ውስጥ ስለ አጽናፈ አቀፉዋ ቤተ ክርስቲያን ደጋግሞ ጠቅሷል።
ሐዋርያው ጳውሎስ፥ እግዚአብሔር በዓለም ውስጥ የሚያከናውነው ታላቁ ሥራ የክርስቶስን አካል መገንባት እንደሆነ ተገንዝቧል። ኢየሱስ ክርስቶስ በእርሱ ያመኑና የሚከተሉት ሰዎች ሁሉ የሚገኙባት ዓለም አቀፋዊት ቤተ ክርስቲያን ራስ ነው። እግዚአብሔር በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ለእያንዳንዱ አማኝ የተለየ ስጦታ ይሰጣል። አማኙ በዚህ ስጦታው ሌሎችን በማገልገል ክርስቶስን ያገለግላል። ይህ የአማኞች አካል በምድር ላይ ክርስቶስን ይወክላል። ወንጌሉን ስንመሰክር አፉ፥ እርስ በርሳችንና ሌሎችን ስንረዳ እጆቹ፥ እንዲሁም ወንጌሉን ወደ ዓለም ሁሉ ስናዳርስ እግሮቹ ሆነን እንሠራለን። ጳውሎስ ይህንን የአማኞች መሰባሰብ የእግዚአብሔር «ቤተ መቅደስ» ወይም የመንፈስ ቅዱስ ቤተ መቅደስ ይለዋል (ኤፌ. 2፡21)። ምንም እንኳ ክርስቶስ በእያንዳንዱ ክርስቲያን ልብ ውስጥ ቢኖርም፥ ከዚያ በላቀ ሁኔታ በአማኞች ኅብረት ውስጥ ይኖራል።
ዛሬ ትኩረት የሚደረገው በግለሰቦች ድነት (ደኅንነት) ላይ ነው። የሰዎችን መዳን አለመዳን እንጠይቃለን። ብዙ ሰዎች ለማምለክ ለራሳቸው ብቻ ቃሉን ለመማር ወደ ቤተ ክርስቲያን ይመጣሉ። ነገር ግን የአማኞች ኅብረት ንቁ ተሳታፊዎች አይሆኑም። በአዲስ ኪዳን ውስጥ እግዚአብሔር ለራሱ ክብር ለማምጣት በሚሠራበት የአማኞች ኅብረት ላይ ትኩረት ተደርጓል። እግዚአብሔር እያንዳንዱ ክርስቲያን በአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በንቃት በመሳተፍ የድርሻውን እንዲያበረክት ይፈልጋል።
የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) አዲስ ኪዳን «ቤተ ክርስቲያን» ሲል የሚገልጸውን ሃሳብ ዛሬ ብዙ ሰዎች ስለ ቤተ ክርስቲያን ከሚገነዘቡት ጋር አነጻጽር። ለ) «ቤተ ክርስቲያን» የሚለው ቃል በቀዳሚነት ሰዎችን ሳይሆን የቤተ ክርስቲያንን ሕንፃ እንደሚያመለክት ስናስብ፥ ምን ምን ችግሮች ይከሰታሉ? ሐ) በቤተ ክርስቲያንህ ውስጥ የሚያመልኩት አብዛኞቹ ሰዎች መንፈሳዊ ስጦታዎቻቸውን በትጋት ይጠቀማሉ? ለምን? መ) አብዛኛዎቹ ሰዎች በትጋት ሳይሳተፉ እንደ ተመልካች በየጉባኤዎች ላይ ተገኝተው መመለሳቸው ምን ዓይነት አሉታዊ ውጤቶችን ያስከትላል?
የውይይት ጥያቄ፡- ስለ ኤፌሶን ከመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት አንብብና ስለ ጸሐፊው፥ ስለ ቤተ ክርስቲያኒቱ፥ ስለ ደብዳቤው ዓላማና ስለ ከተማው፥ ወዘተ… ጠቅለል ያለ አሳብ ጻፍ።
የወኅኒ ቤት መልእክቶች
የውይይት ጥያቄ፡– ኤፌ. 3፡1፤ ፊልጵ. 1፡12-13፤ ቆላ. 1፡24፤ ፊል. 1 አንብብ። ጳውሎስ እነዚህን መልእክቶች በጻፈበት ወቅት የት ነበር?
ምሁራን የኤፌሶንን፥ የፊልጵስዩስን፥ የቆላስይስንና የፊልሞናን መልእክቶች «የወኅኒ ቤት መልእክቶች» ብለው ይጠሯቸዋል። ለዚህም ምክንያቱ ጳውሎስ እስር ቤት (ምናልባትም ሮም) ውስጥ ሆኖ ስለ ጳፋቸው ነው። የጥንት የቤተ ክርስቲያን መሪዎች የጳውሎስን የተለያዩ መልእክቶች ባደራጁ ጊዜ ሦስቱን ረዣዥም የእስር ቤት መልእክቶች (ኤፌሶን፥ ፊልጵስዩስ፥ ቆላስይስ) አንድ ላይ አስቀምጠዋል። ከሁሉም አጭር የሆነው ፊልሞና ከጳውሎስ መልእክቶች የመጨረሻውን ስፍራ ይዟል።
(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)