የኤፌሶን መልእክት ዓላማ
በድነት (ደኅንነት) ላይ ከሚያተኩረው የገላትያ መልእክት በተቃራኒ በኤፌሶን ውስጥ የቀረበ ዐቢይ የሐሰት ትምህርት ወይም ችግር አይታይም። የኤፌሶን መልእክት እግዚአብሔር ለአማኞች የሰጠውን በረከትና ከቤተ ክርስቲያን ጋር ያለውን ግንኙነት የሚያብራራ የትምህርት መጽሐፍ ነው። በኤፌሶን ውስጥ ጳውሎስ ስለሚከተሉት ነገሮች ጽፎአል።
ሀ. ክርስቶስ በክፋት ኃይላት ሁሉ ላይ ሥልጣን እንዳለውና ከሰይጣን ጥቃቶች የሚከላከሉ መንፈሳዊ የጦር መሣሪያዎች እንዳሉን (ኤፌ. 1፡20-22፤ 6፡10-18)። አንዳንድ ምሁራን ይህ የመንፈሳዊ ውጊያ ትምህርት የኤፌሶን ዋነኛ ርዕስ እንደሆነ ያስባሉ። የኤፌሶን አማኞች ቀደም ሲል ከፍተኛ የጣዖት አምልኮ ያካሂዱ ስለነበር የሰይጣንን ኃይል ይፈሩ ነበር። ስለሆነም፥ ጳውሎስ የክርስቶስ ኃይል ከሁሉም ኃይላትና ሥልጣናት እንደሚበልጥ ገልጾላቸዋል። እንዲሁም ሁሉም ክርስቲያኖች ክርስቶስ የሰጣቸውን የጦር ዕቃዎች በመጠቀም ሰይጣንን ሊያሸንፉ እንደሚችሉ ያሳያቸዋል።
ለ. ቤተ ክርስቲያን የእግዚአብሔር ዘላለማዊ ዕቅድ እምብርት ነች። ጳውሎስ ቤተ ክርስቲያንን የክርስቶስ አካል (ኤፌ. 1፡23)፥ የእግዚአብሔር ቤተሰብ (ኤፌ. 3፡3)፤ ሕንፃ፤ ቅዱስ መቅደስ፥ የእግዚአብሔር ግዛት (ኤፌ. 2፡21-22)፥ ምሥጢር (ኤፌ. 3፡3)፥ ወዘተ. በማለት ይገልጻታል። ቤተ ክርስቲያን እግዚአብሔር የመረጣቸው፤ የጠራቸውና በመንፈሳዊ ሁኔታ የባረካቸው ሰዎች ክምችት ነች። ቤተ ክርስቲያን የክርስቶስ አካልና (ኤፌ. 1፡22-23) ለታሪክ የወጠነው ዕቅድ መነሣሣት ናት። እግዚአብሔር ከቤተ ክርስቲያን በአይሁዶችና በአሕዛብ መካከል የነበሩትን ዓይነት የዘር ክፍፍሎች አስወግዷል። አማኞች የእግዚአብሔር ታላቅ ቤተሰብ አካል ናቸው። ሁሉን ቻዩ አምላክ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ይኖራል (ኤፌ. 2፡19– 22)።
ሐ. እማኞች በክርስቶስ ያገኟቸው አስደናቂ በረከቶች። ከመዳናችን በፊት ተስፋ የሌለን፥ በኃጢአታችን የሞትንና ያለመታዘዝ ልጆች ነበርን (ኤፌ. 2፡1-4)። እግዚአብሔር ከጸጋው የተነሣ ክርስቶስን በመላኩ በእርሱ በማመን ከርኩሰትና ከቅጣት ነፃ ወጥተናል። አሁን፥ ለእግዚአብሔር ለመኖር የሚያስችል ኃይል እንዳለንና የበረከቶቹ ወራሾቹ እንደሆንን እናውቃለን (ኤፌ. 1፡3-12)። በክርስቶስ ስናምን የቀደመውን ኃጢአታችንን ለመሸፈን የሚያስፈልገንን ነገር፥ እግዚአብሔርን ለማስደሰትና ሰይጣንን ለማሸነፍ የሚያስችለንን ኃይል፥ እንዲሁም የወደፊቱን የበረከት ተስፋዎች እናገኛለን። እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስን ስለሰጠን (ኤፌ. 1፡13)፥ ከኃጢአት መርገምና ከእስራት ወጥተን ወደ እግዚአብሔር ቀርበናል (ኤፌ. 2፡1-10)። አማኞች በአንድነትና በንጽሕና (ኤፌ. 4፡17-6፡9)፥ ወዘተ. ሊመላለሱ ይገባል።
መ. የእያንዳንዱ ክርስቲያንና ቤተ ክርስቲያን ዓላማ ለእግዚአብሔር ምስጋናና ክብር ማምጣት ነው (ኤፌ. 1፡6)።
ሠ. የእግዚአብሔር የመጨረሻ ግብ ክርስቶስን ማስከበርና በሰማይና በምድር ያሉትን ነገሮች ሁሉ በእርሱ ሥልጣን ሥር ማዋል ነው (ኤፌ. 1፡10)።
ረ. አማኞች በሥራ ሳይሆን በእግዚአብሔር ጸጋ እንደ ዳኑ፥ የትኛውም ጎሳዊ ክፍፍል በክርስቶስ ሞት እንደ ተወገደና በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ስፍራ እንደሌለው ለማስታወስ (ኤፌ. 2፡11-22)።
ሰ. ሽማግሌዎች ክርስቲያኖች ሁሉ በመንፈሳዊ ሕይወታቸው እንዲያድጉ በማገዙ በኩል የሚጫወቱት ሚና (ኤፌ. 4፡1-16)።
ሸ. የቤተሰቡ አባላት እግዚአብሔርን በሚያስከብር መንገድ እንዴት እርስ በርሳቸው ሊያያዙ እንደሚገባቸው ለማስተማር (ኤፌ. 4፡1፤ 5፡22-6፡9)።
የውይይት ጥያቄ፡– የቤተ ክርስቲያንህ አማኞች እነዚህን እውነቶች ማወቅና ተግባራዊ ማድረግ የሚያስፈልጋቸው እንዴት ነው?
የኤፌሶን መልእክት ልዩ ባሕርያት
- የኤፌሶን መልእክት ከቆላስይስ መልእክት ጋር በቅርብ የተዛመደ ነው። ሁለቱም በተመሳሳይ ጊዜ እንደ ተጻፉ ግልጽ ነው። የኤፌሶን ከ50 በመቶ የሚበልጡ ጥቅሶች በቆላስይስ ውስጥ ተደግመዋል። ቲኪቆስ የተባለ ግለሰብ ሳይሆን አይቀርም ሁለቱንም መልእክቶች ያደረሰው (ኤፌ. 6፡21፤ ቆላ. 4፡7-8)። የኤፌሶንም ሆነ የቆላስይስ መልእክቶች በክርስቶስና በቤተ ክርስቲያን ላይ ያተኩራሉ። የኤፌሶን መልእክት ቤተ ክርስቲያን የክርስቶስ አካል መሆኗ ላይ ሲያተኩር፥ የቆላስይስ መልእክት ደግሞ ክርስቶስ የአካሉ ራስ በመሆኑ ላይ ያተኩራል።
- በዚህ መልእክት ውስጥ ስለ መንፈስ ቅዱስ እያሌ እውነቶች ተጠቅሰዋል። እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ፣ ቅዱስ (ኤፌ. 1፡13)፥ የጥበብ ምንጭና እውነትን ገላጭ ነው (ኤፌ. 1፡17፤ 3፡5)። መንፈስ ቅዱስ ሊያዝን (ኤፌ. 4፡30)፥ አማኞችንም ሊያትም (ኤፌ. 1፡13)፥ የአማኞች ውርስ መያዣ ሊሆን (ኤፌ. 1፡14)፥ ወደ እግዚአብሔር አብ የመቅረቢያ መንገድ ሊከፍት (ኤፌ. 2፡18)፥ ቤተ ከርስቲያንን ሊያንጽ (ኤፌ. 2፡22)፥ አማኞችን ሊሞላና ሊያበረታታ (ኤፌ. 3፡16፤ 5፡18)፥ ለአማኞች የእግዚአብሔርን ቃል ሊሰጥ (ኤፌ. 6፡17) እና እንዲጸልዩ ሊረዳቸው ይችላል (ኤፌ. 6፡18)።
- ከሌሎች የጳውሎስ መልእክቶች በተቃራኒ፡ ይህንን መልእክት እንዲጽፍ ያነሣሣው ሁነኛ ምክንያት (የቤተ ክርስቲያን ወይም የአስተምህሮ ችግር) የለውም። ነገር ግን ለአማኞች ጠቃሚ መንፈሳዊ እውነቶችን ለማስተላለፍ የተጻፈ ነው።
- ጳውሎስ ከእነዚህ እውነቶች አብዛኞቹን በሁለት ታላላቅ ጸሎቶቹ አስተምሯል (ኤፌ. 1፡15-23፤ 3፡14-21)። እነዚህ ሁለት ጸሎቶች ለእርስ በርሳችን ለመጸለይ እንጠቀምባቸው ዘንድ የጸሎት ምሳሌዎች ሆነው ያገለግላሉ።
የኤፌሶን መልእክት መዋቅር
የኤፌሶን መልእክት እንደ አብዛኞቹ የጳውሎስ መልእክቶች በሁለት ክፍሎች የተከፈለ ነው። በመጀመሪያው ክፍል ጳውሎስ በእምነታችን ላይ ተጽዕኖ በሚያሳድሩት መንፈሳዊ እውነቶች ላይ ትኩረት ሲያደርግ፥ በሁለተኛው ክፍል ደግሞ እግዚአብሔርን በሚያስከብር መንገድ እንዴት መመላለስ እንዳለብን ያስተምራል።
- ጳውሎስ ለኤፌሶን ክርስቲያኖች ጠቃሚ መንፈሳዊ እውነቶችን ያስተምራል (ኤፌ. 1-3)። እንደ አማኞች እኛ ማን ነን? ቤተ ክርስቲያን ምንድን ናት? እነዚህ በመጀመሪያዎቹ የኤፌሶን ሦስት ምዕራፎች ውስጥ መልስ የተሰጠባቸው ዐበይት ጥያቄዎች ናቸው። እንደ አማኞች፥ አስደናቂ መንፈሳዊ በረከቶች በሰማያዊ ስፍራ ተሰጥተውናል (ኤፌ. 1፡3)። እግዚአብሔር በሁሉም ዐበይት የሕይወታችን ክፍሎች በከፍተኛ ደረጃ ባርኮናል። ጠላቶቹ የነበርን ብንሆንም፥ ክርስቶስ እንዲሞትልን ልኮታል። በአስደናቂ ጸጋው አድኖናል።
ቤተ ክርስቲያን ምንድን ናት? ጳውሎስ ቤተ ክርስቲያን በዓለም ውስጥ የእግዚአብሔር ዋነኛ የትኩረት ስፍራ እንደሆነች አስረድቷል። እግዚአብሔር ታላቅ ክብር የሚያመጡለትን የአማኞች ማኅበረሰብ እየመሠረተ ነው። ይህም ማኅበረሰብ ከአይሁዶችና ከአሕዛብ ተውጣጥተው በክርስቶስ ያመኑ፥ ቅዱሳንና የተለዩ ሕዝብ የሚገኙበት ነበር። ይህ በፍቅር፥ አንድነትና ንጽሕና ተለይቶ የሚታወቅና ጎሳዊ እውቅና ከእንግዲህ ወዲህ የማይታይበት ማኅበረሰብ ነው።
- ጳውሎስ የኤፌሶን አማኞች እንደ የክርስቶስ አካል ክፍሎች እንዴት ሊመላለሱ እንደሚገባቸው ያስተምራል (ኤፌ. 4-6)። እግዚአብሔር የባረካቸው ሰዎች እንደ እግዚአብሔር ልጆች መኖር ይጠበቅባቸዋል። እኛ የአንድ አካል ወይም የአንድ ቤተስብ አባላት ስለሆንን፥ በፍቅርና በአንድነት ልንኖር ይገባል። እግዚአብሔር የአካሉን ክፍል በመንፈሳዊ ብስለት ለመገንባት ሲል ለመሪዎች ስጦታዎችን ይሰጣል። አማኞች ሰማያዊ አባታችንን የሚመስል የተቀደሰ ሕይወት መምራት ይኖርብናል። በዚህ ቤተሰብ ውስጥ በፍቅር፥ በሥርዓት፥ በአንድነትና በመቻቻል ልንኖር ይገባል። የክርስቶስንና የቤተ ክርስቲያንን ምሳሌ በመከተል ሚስቶች ለባሎቻቸው ሊገዙ፥ ባሎች ደግሞ ሚስቶቻቸውን ሊወዷቸው ይገባል። በሥራ ቦታ በሠራተኞች (ባሮችን) እና በቀጣሪዎች (ጌቶች) መካከል መከባበር ሊኖር ይገባል። በመንፈሳዊ ውጊያችን ደግሞ ክርስቶስ የሰጠንን የጦር መሣሪያ በመጠቀም ነቅተን ራሳችንን ልንጠብቅ ይገባል።
የኤፌሶን መልእክት አስተዋጽኦ
- ጳውሎስ ለኤፌሶን ክርስቲያኖች፥ አማኞች በክርስቶስ ማን እንደሆኑና ቤተ ክርስቲያን ምን እንደሆነች ያስተምራል (ኤፌ. 1-3)፡፡
ሀ. መግቢያ (ኤፌ. 1፡1-2)
ለ. የእግዚአብሔር ልጆች መንፈሳዊ በረከቶች (ኤፌ. 1፡3-14)
ሐ. ጳውሎስ አማኞች እንደ እግዚአብሔር ልጆች ያላቸውን መንፈሳዊ ስፍራ እንዲረዱ ይጸልያል (ኤፌ. 1፡15-23)።
መ. ሙት የነበሩ የእግዚአብሔር ጠላቶች በጸጋው ሕያዋን ሆነው ድነዋል (ኤፌ. 2፡1-10)
ሠ. ሁሉም አማኞች ሰብአዊ ክፍፍሎች በማይታሰቡባት አንዲት ቤተ ክርስቲያን ተጠልለዋል (ኤፌ. 2፡11-22)
ረ. ጳውሎስ ስለ ክርስቶስና ቤተ ክርስቲያን የሚናገረውንና የእግዚአብሔር ምሥጢር የሆነውን ወንጌል ለማወጅ የተመረጠ አገልጋይ ነው (ኤፌ. 3፡1-13)
ሰ. ጳውሎስ አማኞች የክርስቶስንና ከእርሱ ጋር ያላቸውን ግንኙነትና ታላቅነት ይረዱ ዘንድ እግዚአብሔር ጉልበት እንዲሰጣቸው ይጸልያል (ኤፌ. 3፡14-21)።
- ጳውሎስ የኤፌሶን አማኞች ለወንጌሉ እንደሚገባ ይመላለሱ ዘንድ ያደፋፍራቸዋል (ኤፌ. 4-6)።
ሀ. ለወንጌሉ እንደሚገባ መመላለስ ማለት እንደ አማኞች አንድነትን መፍጠርና እርስ በርሳችን መዋደድ ነው (ኤፌ. 4፡1-6)
ለ. እግዚአብሔር የአካሉ ክፍሎች እርስ በርሳቸው እንዲረዳዱና በብስለት እንዲያድጉ የተለያዩ ስጦታዎችን ሰጥቷቸዋል (ኤፌ. 4፡7-16)።
ሐ. እግዚአብሔር ልጆቹ በቅድስና በመመላለስ እርሱን እንዲመስሉ ይፈልጋል (ኤፌ. 4፡17-5፡20)
መ. እግዚአብሔር የቤተሰብ አባላቱ እርስ በርሳቸው እንዴት መዛመድ እንዳለባቸው አብራርቷል (ኤፌ. 5፡21–6፡9)።
ሠ. እግዚአብሔር ልጆቹ ራሳቸውን ከሰይጣን ጥቃቶች እንዲጠብቁና የድል ነሺነትን ሕይወት እንዲመሩ መንፈሳዊ የጦር ዕቃዎችን ሰጥቷቸዋል (ኤፌ. 6፡10-20)
ረ. የመጨረሻ ሰላምታ (ኤፌ. 6፡21-24)
(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)
እግዚአብሔር ፀጋውን ያብዛልህ፡፡