የፊልጵስዩስን መልእክት ማን ጸፈው፣ ለማን ተጻፈ፣ መቼና የት ተጻፈ

የፊልጵስዩስ መልእክት ጸሐፊ

ጳውሎስ ይህንን መልእክት ለፊልጵስዩስ ሰዎች ያቀረበው ራሱንና የአገልግሎት ተባባሪው የነበረውን ጢምቴዎስን በማስተዋወቅ ነው። መልእክቱን የጻፈው ጢሞቴዎስ ነበር። ነገር ግን ጢሞቴዎስ ከጳውሎስ ጋር አብሮ ስለነበረና መጀመሪያ ወንጌሉን ለፊልጵስዩስ ሰዎች ከጳውሎስ ጋር አብሮ ስላደረሳ፥ ጳውሎስ ሰላምታውን ሊያካትትለት ፈለገ።

ጳውሎስ በሌሎች መልእክቶቹ ውስጥ ከሚያሳየው ሁኔታ በተለየ መልኩ ሐዋርያነቱን አለመግለጹ አስገራሚ ነው። ጳውሎስ በዚህ መልእክት ውስጥ ራሱን “ባሪያ” ሲል ያስተዋውቃል። ይህ የግሪኩ ቃል ትክክለኛ ትርጉም ነው። አንድ አገልጋይ ለማን እንደሚያገለግል የመምረጥ መብት አለው። ባሪያ ግን ይኼ መብት የለውም። በእስራኤል ሁለት ዓይነት ባሪያዎች ነበሩ። ለአንድ ሰው ተሽጠው ሕጋዊ ንብረት የሆኑ ባሮች ነበሩ። በገዛ ፈቃዳቸው ባሮች የሚሆኑም ነበሩ። ለምሳሌ ያህል አንድ ሰው የተበደረውን ገንዘብ ለመክፈል ባለመቻሉ ለ10 ዓመታት ባርነት ቢሸጥ፥ እንዲህ ዓይነቱ ሰው ጌታው የሚያዘውን ሁሉ የመፈጸም ግዴታ ይወድቅበታል። ከ10 ዓመታት አገልግሎት በኋላ ግን ነፃ ይወጣል። ከ10 ዓመታት በኋላ ግን ሰውዬው ጌታውን በመውደዱ ምክንያት በባርነቱ ለመቀጠል ቢፈልግ፥ ምርጫው የራሱ ይሆናል። በዚህም ጊዜ ጆሮውን ይበሳና ከፍቅሩ የተነሣ ለቀረው ዘመኑ ሁሉ ጌታውን ሲያገለግል ይኖራል (ዘጸ. 21፡4-6)። በጳውሎስ አእምሮ ውስጥ የነበረው ይኸው ሁለተኛው ዓይነት ባርነት ሳይሆን አይቀርም። ጳውሎስ ክርስቶስን እጅግ በመውደዱ ምክንያት በገዛ ፈቃዱ ባሪያው ለመሆንና ለተቀረው ዘመኑ ሁሉ እርሱን ለማገልገል ፈቀደ (1ኛ ቆሮ. 6፡20 አንብብ)። ጳውሎስ እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ ባሪያ፥ ሕይወቱን ሙሉ በሙሉ ለክርስቶስ ፈቃድ አስገዝቷል። ስለሆነም፥ ለሚሄድበት፥ ለሚያደርገውና በአጠቃላይም በሕይወቱ ውስጥ ለሚያከናውነው ተግባር የራሱ ፈቃድ አልነበረውም። ምንም እንኳን ይኼ ሥቃይንና እስራትን የሚጨምር ቢሆንም፥ ጳውሎስ ጌታው ኢየሱስ ክርስቶስ የፈለገውን ብቻ ነበር የሚቀበለው።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) በአገልጋይና ባሪያ መካከል ያለው የአመለካከት ልዩነት ምንድን ነው? ለ) ለክርስቲያኖች በክርስቶስ መዋጀታችንን ማስታወሱ ለምን ይጠቅማል? ሐ) ክርስቲያኖች የክርስቶስ ባሪያዎች መሆናችንን ብናስታውስ፥ አመለካከታችንና ተግባራችን እንዴት ይለወጣል? መ) እየተመላለስህ ያለኸው እንደ ክርስቶስ ባሪያ ነውን? ክርስቶስ በሕይወትህ ውስጥ ሙሉ ተቆጣጣሪነት እንዳይኖረው የምትከለከልባቸውን ክፍሎች መንፈስ ቅዱስ እንዲያሳይህ በጸሎት ጠይቅ፡፡ ኃጢአትህን ተናዘዝና ይህንኑ የሕይወትህን ክፍል ዛሬውኑ ለክርስቶስ አሳልፈህ ስጥ።

ጳውሎስ የጻፈው ለማን ነበር?

የውይይት ጥያቄ፡– ሀ) ጳውሎስ ይህንን መልእክት የጻፈው ለማን ነበር? ለ) የሐዋ. 16፡6–40 አንብብ። የፊልጵስዩስ ቤተ ክርስቲያን እንዴት እንደተ መሠረተችና በዚያ ስፍራ በጳውሎስ ላይ ስለደረሰው ሁኔታ ጠቅለል ያለ አሳብ ጻፍ።

ጳውሎስ በመግቢያው ውስጥ፥ «በፊልጵስዩስ ለሚኖሩ ከኤጲስ ቆጶሳትና ከዲያቆናት ጋር በክርስቶስ ኢየሱስ ላሉት ቅዱሳት ሁሉ» ሲል የመልእክቱን ተቀባዮች ይጠቅላል። ጳውሎስ መልእክቱን የጻፈው በፊልጵስዩስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ለነበሩት ሁለት ቡድኖች ነበር። ከእነዚህም የመጀመሪያዎቹ የቤተ ክርስቲያን ምእመናን ነበሩ። ጳውሎስ እነዚህን ወገኖች «ቅዱሳን»፥ ማለትም በክርስቶስ ከማያምኑ ሰዎች በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት የተለዩ ብሎ ይጠራቸዋል። ሁለተኞቹ ቡድኖች የፊልጵስዩስ ቤተ ክርስቲያን መሪዎች ናቸው። ጳውሎስ መልእክቱን ለመሪዎች መላኩን የጠቀሰበት ብቸኛው ስፍራ ይኼ ነው። ጳውሎስ ስለ መሪዎች ያነሣው አሳብ በጥንቷ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የነበሩትን ሁለት ዓይነት ዐበይት መሪዎች ያመለክታል። በመጀመሪያ፥ ኤጲስ ቆጶሳት ነበሩ። አዲስ ኪዳንን በጥንቃቄ ስናጠና ዐበይት የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ሽማግሌዎችና ኤጲስ ቆጶሳት ይባሉ እንደነበረ እንረዳለን። በግሪክ ባሕል፥ ኤጲስ ቆጶስ የሃይማኖታዊ ወይም የፖለቲካዊ ድርጅት መሪ ነበር። ጳውሎስ በዚህ ስፍራ ቃሉን የጠቀሰው የቤተ ክርስቲያንን መሪዎች ለማመልከት ነው። በሌሎች ስፍራዎች፥ ይህ ቃል «ሽማግሌዎች» የሚል ፍች ተሰጥቶታል (የሐዋ. 14፡23፣ 1ኛ ጢሞ. 5፡17)። ሁለቱም ተመሳሳይ ዓይነት መሪዎች ናቸው። በአዲስ ኪዳን ቤተ ክርስቲያን ውስጥ፥ ከአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ሽማግሌዎች ያለፈ የአመራር ደረጃ አልነበረም (ከሐዋርያት በስተቀር)። ክልላዊ ወይም ብሔራዊ የቤተ እምነት መሪዎች አልነበሩም። እነዚህ የአመራር ደረጃ ዎች የተመሠረቱት በኋላ ነው። አዲስ ኪዳን ቤተ ክርስቲያንን በሥልጣን ማስተዳደሩ የተዋረዳዊ መሪዎች ሳይሆን የአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን መሪዎች ኃላፊነት እንደሆነ ያስረዳል። አጥቢያዊ መሪዎች የአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ምእመናንን የመምራት፥ የመጠበቅና የማስተማር ኃላፊነት ተጥሎባቸዋል።

ሁለተኛ፥ «ዲያቆናት» ነበሩ። በኮሚኒዝም ዘመን የወጣት ቡድኖችን አባላት ዲያቆናት እያሉ መጥራት የተለመደ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ ግን ይህንን ቃል የሚጠቀመው የተወሰነ የመሪነት ዓይነትን ለማመልከት ነው። በግሪክ ቋንቋ፥ ቃሉ «የሚያገለግል» የሚል ፍች አለው። እንዲህ ዓይነት መሪዎች የተመሠረቱት በሐዋርያት ሥራ 6፡1-6 ነው። እነዚህ ወገኖች ኤጲስ ቆጶሳት በጸሎት፥ በማስተማርና ቤተ ክርስቲያንን በመምራቱ አገልግሎት ላይ ያተኩሩ ዘንድ በማገዝ ድሆችን እንደ መንከባከብ ያሉትን ተግባራት ያከናውኑ ነበር። በአዲስ ኪዳን ቤተ ክርስቲያን፥ ዲያቆናት መባ መሰብሰብ ብቻ ሳይሆን ጠቃሚ አገልግሎቶችን ያካሂዱ ነበር።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) እነዚህ ሁለት የአመራር ደረጃዎች በቤተ ክርስቲያንህ ውስጥ አሉ? ለ) ከሆነ፥ በእያንዳንዱ የመሪነት ኃላፊነት ላይ የሚገኙ ሰዎች የሚያከናውኗቸው ተግባራት ምን ምንድን ናቸው? ሐ) እነዚህ መሪዎች የአገልግሎት ደረጃዎቹ በአዲስ ኪዳን ውስጥ ካገለገሉበት ሁኔታ ጋር የሚነጻጸሩት እንዴት ነው?

ጳውሎስ መጀመሪያ ወንጌሉን ወደ ፊልጵስዩስ ያደረሰው በ49 ወይም በ50 ዓ.ም በሁለተኛው የወንጌል መልእክተኝነት ጉዞው ነበር። በአውሮፓ ወንጌልን ለመጀመሪያ ጊዜ የሰበከው በዚህች ከተማ ነበር። የፊልጵስዩስ ከተማ ጳውሎስ ከመርከብ ከወረደበት ስፍራ 15 ኪሎ ሜትሮች ያህል ርቃ ትገኝ ነበር። ፊልጵስዩስ በሮም የመቄዶንያ ግዛት ውስጥ ከሚገኙት አውራጃ ዎች ትልቋ ነበረች። ጥድፍያ በበዛበት የንግድ መንገድ ላይ ከመገኘቷ የተነሣ የፊልጵስዩስ ከተማ ለአካባቢዋ አገሮች ዐቢይ የገበያ ማዕከል ነበረች። የዚህች ከተማ ነዋሪዎች በአብዛኛው የሮም ዜግነት ያላቸው፥ የሮማውያንን የአለባበስ ስልት የሚከተሉና የሮም ቋንቋ የሆነውን ላቲን የሚናገሩ ነበሩ። ከተማይቱ ከሮም ሹመት ውጭ ራሷን የማስተዳደር መብት ነበራት። በከተማይቱ ውስጥ ጥቂት አይሁዶች ብቻ ስለነበሩ፥ ጳውሎስ የስብከት ተግባሩን የሚያከናውንበትን ምኩራብ ሊያገኝ አልቻለም። ይህ ሕዝቡ ለአይሁዶች የነበረውን ጥላቻ የሚያመለክት ሊሆን ይችላል።

ወንጌሉ ወደ መቄዶንያና ወደ ፊልጵስዩስ የመጣው በጳውሎስ ዕቅድ ሳይሆን በእግዚአብሔር ጣልቃ ገብነት ነበር። ጳውሎስ በሁለተኛው የወንጌል መልእክተኝነት ጉዞው ወንጌል ያልደረሰባቸውን የትንሹ እስያ አካባቢዎች ለማካለል ሞክሮ ነበር። ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ ከመንገድ ላይ አስቆመው። በመጨረሻም፥ ጳውሎስ በትንሹ እስያ ምዕራባዊ ጫፍ ወደምትገኘው ጢሮአዳ (የዛሬዋ ቱርክ) ደረሰ። ጳውሎስ ወዴት እንደሚሄድ አያውቅም ነበር። ከዚያ በኋላ ግን እግዚአብሔር ለፊልጵስዩስ ራእይ አሳየው። በራእዩ ውስጥ ጳውሎስን አንድ ሰው ወደ መቄዶንያ አልፎ እንዲረዳው ይጠይቀዋል። በ50 ዓ.ም አካባቢ ጳውሎስ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ አውሮፓ አደረሰው። ወዲያውም ክርስትና በአውሮፓ ታላቅ ሃይማኖት ሆነ። ጳውሎስ በዋና ዋና ከተሞች ውስጥ በመስበኩ ላይ ስለሚያተኩር ነበር ወደ ፊልጵስዩስ ከተማ የተጓዘው። በዚያ ስፍራ ምኩራብ ስላልነበረ፥ ጳውሎስ ከወንዙ አካባቢ ለተሰበሰቡት አይሁዶች ወንጌሉን በመስበክ አገልግሎቱን ጀመረ። በዚያም ሊድያ የተባለች ሴት የመጀመሪያዋ አማኝ ሆነች። ከአፍታ በኋላ አነስተኛ ቤተ ክርስቲያን ተመሠረተች። በሰይጣን ኃይል ወደፊት ምን እንደሚከሠት እየጠነቆለች ለጌቶቿ ገንዘብ ከምትሰበስብ ባሪያ ላይ አጋንንትን ባስወጡ ጊዜ ግን ጳውሎስና ሲላስ ወደ ወኅኒ ቤት ተወረወሩ። በወኅኒ ቤቱ ውስጥ ድብደባ ተፈጸመባቸው። ይሁንና ጳውሎስና ሲላስ ለእግዚአብሔር የምስጋና መዝሙር እየዘመሩ በደስታ ያመልኩ ነበር። ምስክርነታቸውም የወኅኒ ቤቱን ጠባቂ ቤተሰቦች ወደ ክርስቶስ አፈለሱ።

የፊልጵስዩስ ቤተ ክርስቲያን ምን ያህል ሰፊ እንደነበረች አናውቅም። ምእመኖቿ ሙሉ በሙሉ ማለት ይቻላል አሕዛብ ነበሩ። ጳውሎስ በፊልጵስዩስ ብዙ ሊቆይ ባለመቻሉ ወደ ተሰሎንቄ ተጓዘ። ነገር ግን ጳውሎስ ከፊልጵስዩስ ቤተ ክርስቲያን ጋር የጠበቀ ግንኙነት ስለነበረው ፊልጵስዩስ ለእርሱ ተወዳጅ ቤተ ክርስቲያን ነበረች። ይህች ቤተ ክርስቲያን የጳውሎስን አገልግሎት ትደግፍ ነበር (2ኛ ቆሮ. 11፡9፤ ፊልጵ. 4፡15)። እንዲያውም ጳውሎስ ይህን መልእክት ከጻፈባቸው ምክንያቶች አንዱ ለስጦታቸው ማመስገን ነበር።

ጳውሎስ በሦስተኛው የወንጌል መልእክተኝነት ጉዞው የፊልጵስዩስን ቤተ ክርስቲያን ሁለት ጊዜ ጎብኝቷታል።

ጳውሎስ የፊልጵስዩስን መልእክት የጻፈበት ዘመንና ስፍራ

ጳውሎስ «የእሥር ቤት መልእክቶችን (ፊልጵስዩስን ጨምሮ) ከእሥር ቤት ውስጥ ሆኖ እንደ ጻፋቸው ከኤፌሶን ጥናት ተመልክተናል።» ምሁራን ጳውሎስ ፊልጵስዩስን በጻፈበት ወቅት የት ቦታ ታሥሮ እንደነበረ የሚያስረዱ ሦስት አሳቦችን ያቀርባሉ። ጥቂት ምሁራን ቂሣሪያ ሊሆን እንደሚችል ይናገራሉ። ይኼ አሳብ ግን ብዙ ድጋፍ የለውም። ሌሎች ኤፌሶን ነበር ይላሉ። የፊልጵስዩስን መልእክት ቀረብ ብለን በምናጠናበት ጊዜ፥ ስለ ጳውሎስ መታሠርና የአፍሮዲጡ መታመም የተገለጹት አሳቦች በእሥር ቤቱና በፊልጵስዩስ መካከል ከአምስት እስከ ስድስት ጉዞዎች መደረጋቸውን እንደሚያመለክቱ እንረዳለን። ጳውሎስ በሮም ታሥሮ ከነበረ፥ ከ1500 ኪሎ ሜትሮች የሚበልጠውን ርቀት ለመሸፈን ቢያንስ አንድ ወር ይፈጃል። ኤፌሶን ግን 250 ኪሎ ሜትሮች ርቃ ስለምትገኝ በቀላሉ መመላለስ ይቻላል። ነገር ግን ጳውሎስ በኤፌሶን እስቸጋሪ ጊዜያትን እንዳሳለፈ ቢጠቅስም (2ኛ ቆሮ. 1፡8-11)፥ በኤፌሶን መታሠሩን በቀጥተኛ አገላለጽ ስለማይናገር ይህንን አማራጭ ውድቅ የሚያደርጉ ምሁራን አሉ።

አብዛኞቹ ምሁራን የሚስማሙት ጳውሎስ ይህንን መልእክት የጻፈው ከሮም እሥር ቤት ነው በሚለው አሳብ ላይ ነው። የፊልጵስዩስ መልእክት ብዙ ሰዎች ከሮም ወደ ፊልጵስዩስ፥ ከፊልጵስዩስ ወደ ሮም ይመላለሱ እንደነበረ ያመለክታል። ይህ የሆነው ምናልባት ለሁለት ዓመታት ሳይሆን አይቀርም። ጳውሎስም በቅርቡ ከእሥር ቤት ለመውጣት ተስፋ እያደረገ ነበር (ፊልጵ. 2፡23-24)። ይህም መልእክቱ ጳውሎስ ከመጀመሪያው እሥራቱ ሊፈታ በተቃረበበት ጊዜ ምናልባትም በ61 ዓ.ም አካባቢ እንደ ተጻፈ ያሳያል።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: