የፊልጵስዩስ መልእክት መግቢያ

ወንጌላዊ ተገኘወርቅ ከነበረበት ስፍራ ወደ ሌላ አካባቢ ሄዶ ወንጌልን እንዲሰብክ ተልኮ ነበር። በዚሁ ስፍራ ለ10 ዓመታት ሲያገለግል እግዚአብሔር በሚገባ ባረከው። ከ20 የሚበዙ አብያተ ክርስቲያናት ተመሠረቱ። ይሁንና፥ ብዙም ጎልቶ ሳይታይ የቆየው ተቃውሞ ይበልጥ እየተጠናከረ መጣ። አንድ ቀን ተገኘወርቅ በነበረባት ከተማ ውስጥ የሚገኝ አንድ ሱቅ ተዘረፈ። በዚህም ጊዜ ጠላቶቹ ተገኘወርቅ ዝርፊያውን ሲፈጽም መመልከታቸውን ተናገሩ። በመሆኑም፥ ተገኘወርቅ በፖሊስ ተይዞ ፍርድ ቤት ከቀረበ በኋላ የ5 ዓመታት እስራት ተፈረደበት። ተገኘወርቅ ራሱን በወኅኒ ቤት ውስጥ ሲያገኘው ደነገጠ። ንጹሕ ሆኖ ሳለ እግዚአብሔር እንዴት እንዲህ ዓይነት ሁኔታ እንዲደርስበት ፈቀደ? አገልግሎቱስ እንዴት ይሆናል? «እግዚአብሔርን ለማገልገሌ የማገኘው ወሮታ ይኼ ከሆነ፥ ማገልገሉ ተገቢ አይደለም» ሲል አሰበ። በምሬት ተሞልቶ በእግዚአብሔር ላይ ተቆጣ።

ብዙነሽ በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ በዋናነት ከሚታወቁ ሴቶች አንዷ ነበረች። ይህች እኅት የጸሎት ቡድኖችንና የሴቶች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን በታማኝነት ትመራ ነበር። አንድ ቀን ባሏና ልጆቿ ዘመድ ለመጠየቅ በአውቶቡስ ተሳፍረው ይጓዙ ነበር። በዚህ ጊዜ አውቶቡሱ ተገልብጦ ገደል ውስጥ በመግባቱ ባሏና ልጆቿ ሞቱ። ብዙነሽ ጥልቅ ኃዘን ደረሰባት። ባለቤቷ የሚያመጣው ገቢ ከቆመ በኋላ እንዴት ልትኖር እንደምትችል ሊገባት አልቻለም። ምንም እንኳን ጥያቄዎች አእምሮዋን ቢያጨናንቁና እግዚአብሔር እንዲህ ዓይነቱ አሳዛኝ ሁኔታ እንዲከሰት እንዴት ሊፈቅድ እንደቻለ ባትረዳም፣ እግዚአብሔር ሁኔታዎችን በመቆጣጠር ላይ እንደሆነና ምንም ዓይነት ክፉ ነገር እንዲከሰት እንደማይፈቅድ ታውቅ ነበር። ስለሆነም፥ ምንም እንኳን ልቧ በኃዘን ቢቆስልም፥ እግዚአብሔርን በደስታ ከማገልገል አልተቆጠበችም።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) የብዙነሽ አመለካከት ከተገኘወርቅ የሚለየው እንዴት ነው? ለገጠሟቸው ሁኔታዎች የተለያዩ ምላሾችን የሰጡት ለምንድን ነው? ከሁለቱ እግዚአብሔርን ይበልጥ ደስ የሚያሰኘው የትኛው ምላሽ ነው? ለ) ፊልጵስዩስ 1፡12-19፤ 4፡4 አንብብ። ጳውሎስ ለደረሰበት እሥራት ምን ዓይነት አመለካከት ነበረው? ጳውሎስ ክርስቲያኖች በሁሉም ሁኔታዎች ውስጥ ምን እንዲያደርጉ አዘዘ? ሐ) በሕይወታችን ውስጥ ነገሮች እንደምንጠብቃቸው በማይሆኑበት ጊዜ የብዙነሽን ዓይነት ምላሽ ለመስጠት እንችል ዘንድ ስለ እግዚአብሔር ልናስታውሳቸው የሚገቡ አንዳንድ ነገሮች ምን ምንድን ናቸው?

ጳውሎስ በኢየሩሳሌም ለሚገኙ መሪዎች ለመታዘዝ ሲል ወደ ቤተ መቅደስ ተጉዞ መሥዋዕት አቀረበ። አይሁዶች ተግባሩን በተሳሳተ መንገድ በመረዳታቸው ሊገድሉት ሞከሩ። ይሁንና፥ የሮም ወታደሮች ጳውሎስን አሠሩት። ጳውሎስ ወንጌሉን ይዞ ወደ ሮምና ከዚያም ወደ ስፔይን የመሄድ ዕቅድ ነበረው። ጳውሎስ ይህ እግዚአብሔር የፈቀደለት ተግባር እንደሆነ ያስብ ነበር። እግዚአብሔር ግን የተለየ ዕቅድ ነበረው። እግዚአብሔር እጅግ የላቀ የወንጌል ሰባኪነት ስጦታ ያለው አገልጋዩ ከቦታ ቦታ ተዘዋውሮ እንዳይሠራ እስር ቤት ውስጥ የሚያጉረው ለምን ይሆን? ከኢየሩሳሌም እግዚአብሔር ለከተማይቱ ትመሰክርልኛለህ እንዳለው ሁሉ ወደ ሮም ሄደ። ነገር ግን ጳውሎስ ጉዳዩን ከፍርድ ችሎት ፊት ለማቅረብ ለሁለት ዓመታት ያህል መጠበቅ ነበረበት። ይህም ወንጌሉን ወደ ስፔይን የማድረስ ዕቅዱን አጓተተበት። እግዚአብሔር ከብዙ ዓመታት በፊት ጴጥሮስን እንዳዳነው ለምን ጳውሎስን ከእስራት ነፃ አላወጣውም? (የሐዋ. 12)

ለጳውሎስ እንደ ተገኘወርቅ በመራርነት መሞላቱ ቀላል ነበር። ጳውሎስ ግን እግዚአብሔር በሚያስቀምጠው ስፍራ ሁሉ ደስ ሊሰኝ እንደሚችል ተናግሯል። በነጻነትም ሆነ በእሥራት ጊዜ በጌታ ደስ ይለዋል። ይህንን ሊያደርግ የቻለው እንዴት ነበር? ቀዳሚው ምክንያት ጳውሎስ እግዚአብሔርን ማወቁ ነው። እግዚአብሔር ሁኔታዎችን እንደሚቆጣጠርና በእሥር ቤት ውስጥ መገኘቱ በአጋጣሚ የተከሠተ ጉዳይ እንዳልሆነ ተገንዝቦ ነበር። እግዚአብሔር ልጆቹን ስለሚወድ የዕቅዱ አካል ያልሆነና ለልጆቹ መልካም ያልሆነ ነገር እንዲፈጸም የሚያደርግ አለመሆኑን ያውቅ ነበር። ስለሆነም፥ ጳውሎስ በመከራ፥ በሥቃይ፥ በስደትና ግራ በመጋባት መካከል ሆኖ ደስ ሊሰኝ ችሏል።

ጳውሎስ የፊልጵስዩስ፥ የኤፌሶን፥ የቆላስይስና የፊልሞና መልእክቶችን የጻፈው በእስር ቤት (ምናልባትም ሮም) ውስጥ ሆኖ ነበር። ጳውሎስ ለመራርነት ራሱን አሳልፎ ባለመስጠቱ እግዚአብሔር በእሥር ቤት ውስጥ በነበረበት ጊዜ እጅግ አስፈላጊዎቹን መልእክቶች እንዲጽፍ አድርጎ ሊጠቀምበት ችሏል። ስለሆነም፥ ይህ የእሥራት ጊዜ በጳውሎስ ሕይወት ውስጥ የባከነ ጊዜ አልነበረም። ጳውሎስ ወንጌሉን በይፋ ለመስበክ ያልቻለባቸው ሁለቱ ዓመታት በመልእክቶቹ አማካኝነት ለሁለት ሺህ ዓመታት እንዲሰብክ ያሚያስችሉት መሆናቸውን አልተገነዘበም ነበር። የፊልጵስዩስ መልእክት በጳውሎስ ደስተኛነት ላይ ያተኩራል። «ደስታ» የሚለው ቃል በዚህ መልእክት ውስጥ ለ16 ጊዜያት ያህል የተጠቀሰ ሲሆን፥ ጳውሎስ ለአማኞች ለማስተማር ከፈለጋቸው ወሳኝ እውነቶች አንዱ ነበር።

የውይይት ጥያቄ፡- ፊልጵስዩስ 1፡1ን አንብብ። የመጽሐፉ ጸሐፊ ማን ነው? መጽሐፉ የተጻፈው ለማን ነው?

የውይይት ጥያቄ፡– ስለ ፊልጵስዩስ በመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት ውስጥ የተጻፈውን አንብብ። ስለ ጸሐፊው፥ ስለ ከተማይቱ፥ ስለ ቤተ ክርስቲያኒቱና ስለ መልእክቱ ዓላማ የተገለጸውን አሳብ ጠቅለል አድርገህ ጻፍ።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d