የፊልጵስዩስ መልእክት ዓላማ፣ ልዩ ባሕሪያት፣ መዋቅርና አስተዋጽኦ

የፊልጵስዩስ መልእክት ዓላማ

 1. የፊልጵስዩስ ቤተ ክርስቲያን በአፍሮዲጡ መታመም ላይ የነበራትን ስጋት አስመልክቶ መረጃ መስጠት። የጳውሎስ ደብዳቤ የመጣው በሮምና ፊልጵስዩስ መካከል ተከታታይ መልእክቶች ከተላለፉ በኋላ ነበር። በፊልጵስዩስ የነበሩ ክርስቲያኖች ስለ ጳውሎስ መታሠር በሰሙ ጊዜ፥ ሁኔታውን ይከታተል ዘንድ አፍሮዲጡን ወደ እርሱ ላኩት። መጠነኛ ገንዘብም ሰደዱለት (ፊልጵ. 4፡10-18)። አፍሮዲጡ የጳውሎስን የተጎሳቆለ አኗኗር ከተመለከተ በኋላ ተጨማሪ ገንዘብ ይልኩለት ዘንድ መልእክተኛ ላከ (ፊልጵ. 2፡25፡30)። ከዚያም አፍሮዲጡ ለሞት እስከሚያሰጋ ድረስ በጣም ታመመ። የፊልጵስዩስም ቤተ ክርስቲያን የመታመሙን ዜና በሰማች ጊዜ በጣም ሰጋች (ፊልጵ. 2፡26-27፥ 30)። አፍሮዲጡም የፊልጵስዩስ ሰዎች በእርሱ መታመም መስጋታቸውን ሰምቶ ተጨነቀ (ፊልጵ. 2፡26)። እግዚአብሔር አፍሮዲጡን ፈወሰው። ጳውሎስም የፊልጵስዩስን ሰዎች ጭንቀት ለማርገብ ሲል ደብዳቤ አስይዞ ወደ ፊልጵስዩስ ሊመልሰው ወሰነ። ጳውሎስ አጋጣሚውን በመጠቀም ላበረከቱለት የገንዘብ ድጋፍ ምስጋናውን ለማቅረብና ስለ መታሰሩ እንዳይጨነቁ ሊያሳስባቸው ፈለገ። ከዚህም በላይ፥ ጳውሎስ ይጎበኛቸው ዘንድ ጢሞቴዎስን እንደሚልክና ፈጥኖ ከተፈታም መጥቶ እንደሚጎበኛቸው ገልጾአል።
 2. ጳውሎስን የሚቃወሙ፥ የሐሰት ወንጌል የሚያስተምሩ ወይም በአንድነት የማይኖሩ ሰዎች የሚያስከትሉትን ክፍፍል በተመለከተ የፊልጵስዩስን ሰዎች ለማስጠንቀቅ። ጳውሎስን ያሳሰቡ ሦስት ቡድኖች የነበሩ ይመስላል።

በመጀመሪያ፥ በሮም ምናልባትም በመቄዶንያ ጳውሎስን የማትወድ ቤተ ክርስቲያን አካል የሆኑ ቡድኖች የነበሩ ይመስላል። እነዚህ ቡድኖች የጳውሎስን መታሠር በተመለከቱ ጊዜ በሌሎች አብያተ ክርስቲያናት ላይ ተጽዕኖአቸውን ለማጠናከር ተስፋ አደረጉ። በጳውሎስ ላይ ተጨማሪ ስደት ለማምጣት የሚያስችል ስብከትም ያቀርቡ ነበር። ጳውሎስ ግን ከእነርሱ ጋር ግብግብ ሊገጥም አልፈለገም። ወንጌል በመስበካቸው ግን ደስ ተሰኘ (ፊልጵ. 1፡16-18)። ለጳውሎስ ዋናው ነገር የእርሱ መታሠር ወይም የዝናው መጉደፍ ሳይሆን የወንጌሉ መሰበክ ነበር።

ሁለተኛ፥ አንዳንድ ሐሰተኛ አስተማሪዎች የሐሰት ወንጌል እያስተማሯቸው ነበር። ይህም ለገላትያ ሰዎች ከቀረበው ትምህርት ጋር የሚመሳሰል ነበር። እነዚህ ሰዎች አሕዛብ በክርስቶስ ከማመናቸው በተጨማሪ መገረዝ እንዳለባቸው የሚያስገድዱ አይሁዶች ሳይሆኑ እይቀሩም። ጳውሎስ እነዚህን አስተማሪዎች «ክፉ ሠራተኞች» (ፊልጵ. 3፡2) እና «የመስቀሉ ጠላቶች» (ፊልጵ 3፡18) ይላቸዋል። ጳውሎስ የፊልጵስዩስ ክርስቲያኖች ይህንን የሐሰት ትምህርት እንዳይቀበሉ ያስጠነቅቃቸዋል።

ሦስተኛ፥ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ክፍፍል ተፈጥሮ ነበር። ይህም ክፍፍል የተከሠተው በሁለት ሴቶች ምክንያት ሳይሆን አይቀርም (ፊልጵ. 4፡2)። ክፍፍሉ የተከሠተው beሃይማኖታዊ አስተምህሮ ምክንያት ሳይሆን በራስ ወዳድነት ሳቢያ ነበር (ፊልጵ. 1፡27፤ 2፡2-4፥ 14)። እናም ጳውሎስ አንድነትን እንዲመሠርቱ ይለምናቸዋል። ወንጌሉ የምናምንበት ብቻ ሳይሆን እውነትነቱን በሚያሳይ መልኩ የምንኖርበትም ነው። ፍቅርና እውነት የወንጌሉ ቁልፍ መረጃዎች ናቸው። ጳውሎስ ይህንን የራስ ወዳድነት አመለካከት ለመመከት በአዲስ ኪዳን ውስጥ ከታወቁት መዝሙሮች አንዱን ይጠቅሳል። በፊልጵስዩስ 2፡6-11 ጳውሎስ ክርስቶስ ራስን የማዋረድና የራስን መብቶች በመሥዋዕትነት ለሌሎች ከመስጠት የሚመጣ ክብር ምሳሌ መሆኑን ያብራራል። ጳውሎስ በዚህ መዝሙር ውስጥ ስለ ክርስቶስ አምላክነትና ሰብአዊነት እጅግ ግልጽ የሆኑትን አሳቦች አቅርቧል።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) እነዚህ ሦስት ዓይነት ክፍፍሎች በቤተ ክርስቲያናችን ውስጥ ስለሚገኙበት ሁኔታ ግለጽ። ለ) አብያተ ክርስቲያናት እነዚህን ሦስት ዓይነት ክፍፍሎች የሚያስተናግዱባቸውን መንገዶች የሚያሳዩትን ምሳሌዎች ጥቀስ። ሐ) እያንዳንዱ የክፍፍል ዓይነት መጽሐፍ ቅዱሳዊ በሆነ መንገድ እንዴት ሊስተናገድ ይገባል?

 1. ለአገልግሎቱ ስላበረከቱት የገንዘብ ድጋፍ የፊልጵስዩስ ክርስቲያኖችን ለማመስገን። እርሱ ቢታሠርም፥ ወንጌሉ አልታሠረም ነበር። እናም በስፋት እየተሰራጨ ነበር። በጳውሎስ አማካኝነት ምርጥ የሮም ወታደሮች ሳይቀር በክርስቶስ እያመኑ ነበሩ። ስለሆነም፥ በእሥራቱ ከማዘን ይልቅ አብረውት ደስ እንዲሰኙ አበረታቷቸዋል። ለክርስቶስ ሲሉ ስደትን ለመጋፈጥ በመፍቀድ ምሳሌነቱን እንዲከተሉ መክሯቸዋል።

የፊልጵስዩስ መልእክት ልዩ ባሕርያት

 1. በፊልጵስዩስ መልእክት ውስጥ ከብሉይ ኪዳን የተወሰደ ጥቅስ አልሰፈረበትም። ጳውሎስ ብዙውን ጊዜ ትምህርቱን በብሉይ ኪዳን ምሳሌዎች ስለሚያጠናክር፥ ይኼ ያልተለመደ ነገር ነው። ጳውሎስ ይህን ያደረገው ምናልባትም ከአንባቢዎቹ አብዛኞቹ አይሁዶች ባለመሆናቸውና ብሉይ ኪዳንን ባለመረዳታቸው ይሆናል።
 2. ይህ የጳውሎስ እጅግ ግላዊ መልእክት ነው። መልእክቱ «እኔ» በሚሉና በመሳሰሉ ግላዊ ቃላት የተሞላ ነው። ይህም ከፊልጵስዩስ ቤተ ክርስቲያን ጋር የነበረውን ጥብቅ ግንኙነት የሚያሳይ ነው። ጳውሎስ በግለሰብ ደረጃ ለሚያውቁትና ለሚወዱት፥ እርሱም ለሚወዳቸው ሰዎች ነበር የሚጽፈው።
 3. ይህ መልእክት የጳውሎስን ውስጣዊ ፍላጎት ያንጸባርቃል። ምንም እንኳ ታላቅ ሐዋርያና እግዚአብሔርም ብዙ አብያተ ክርስቲያናትን ለመመሥረት የተጠቀመበት ቢሆንም፥ ጳውሎስ ገና ብዙ ለማደግ እንደሚፈልግ ያስረዳል። ስለሆነም፥ ስለ ክርስቶስ ገና ብዙ ለማወቅና ኃይሉን ለመለማመድ ወደ ፊት እንደሚዘረጋ ይገልጻል። ጳውሎስ በመንፈሳዊ ሕይወቱ ለማደግ የቆረጠ ሰው በመሆኑ፥ ከመጨረሻው የብስለትና የመንፈሳዊነት ደረጃ ላይ እንደ ደረሰ አያስብም ነበር። ብዙውን ጊዜ ክርስቲያኖች ባለን የዕድገት ደረጃ እንረካለን። በመሆኑም፥ ለመማር አንጥርም። ስለ ክርስቶስ የበለጠ ለማወቅ አንሞክርም። በሕይወታችን የክርስቶስ ኃይል በበለጠ ኃይል እንዲገለጥ አንሻም። ይኼ አሳዛኝና አደገኛ ነገር ነው። ምክንያቱም ወደፊት ካላደግን ወደኋላ እየሄድን ነው።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ብዙ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች በመንፈሳዊ ሕይወታቸው ማደግ ያቆሙበትን ሁኔታ ግለጽ። ይኼ አደገኛ የሚሆነው ለምንድን ነው? ለ) ባለፈው ዓመት በእምነትህ ያደግህበትን ሁኔታ ግለጽ።

 1. ክርስቶስ ሰው በሆነ ጊዜ የተፈጸመውን ሁኔታ ጥርት አድርገው ከሚያብራሩት ክፍሎች አንዱ ፊልጵስዩስ 2፡5-11 ነው። ክርስቶስ ከድንግል ማርያም ከመወለዱ በፊት ከእግዚአብሔር ጋር እኩል ነበር። በባሕርይ በመብት፥ በኃይል ከእግዚአብሔር ጋር እኩል ነበር። ጳውሎስ እንደሚለው ግን ከርስቶስ ሰው በሆነ ጊዜ “ራሱን ባዶ አደረገ”፡፡ ይህ ክርስቶስ መለኮታዊ ባሕርዩን እንዳጣ አያሳይም። መለኮትነቱን ይዞ በሰብአዊነት ኖሯል። እንደኛው ቢፈተንም ኃጢአትን አልፈጸመም። በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ነበር። እኛም እንዲሁ ልንመላለስ ይገባል። በተራራው ላይ ክርስቶስ ከመለኮታዊ ክብሩ የተወሰነውን በማንጸባረቅ ልብሶቹና ፊቱ እንዲለወጥ አድርጓል (ማቴ. 17፡1-13)። የዕብራውያን መልእክት ጸሐፊ እንደሚለው፥ ይህ ራሱን ባዶ የማድረጉ ተግባር ክርስቶስ ሊቀ ካህናችን እንዲሆን አብቅቶታል (ዕብ. 2፡17-18)።

የፊልጵስዩስ መልእክት መዋቅር

ብዙውን ጊዜ የጳውሎስ መልእክቶች በሁለት ዐበይት ክፍሎች ይከፈላሉ። የመጀመሪያው ክፍል ጠቃሚ አስተምህሮዎችን፥ ሁለተኛው ክፍል ደግሞ ከእግዚአብሔር ጋር ያለንን ግንኙነት በሚያንጸባርቅ መንገድ እንዴት መመላለስ እንዳለብን ያስተምራል። የፊልጵስዩስ መልእክት ግን ይህን ስልት አይከተልም። መልእክቱ የግል ደብዳቤን ይመስላል። በውስጡ የምንመለከተው የጳውሎስን ግላዊ መረጃና ወዳጆቹ እንዲያውቁ የሚፈልጋቸውን አንዳንድ ትምህርቶች ነው። በመሠረታዊነት ደረጃ ጳውሎስ ስለ እሥራቱ በመናገር ይጀምርና (ፊልጵ. 1፡1-26) ክርስቲያኖች የእግዚአብሔር ልጆች መሆናቸውን በሚያሳይ መልኩ መኖር እንዳለባቸው ያስተምራል (ፊልጵ. 1፡27-2፡18)። ከዚያም ጳውሎስ ጢሞቴዎስንና አፍሮዲጡን ስለመለኩ ይናገራል (ፊልጵ. 2፡19-30)። በመጨረሻም፥ ስለ ሐሰተኛ አስተማሪዎችና እግዚአብሔርን ስለሚያስከብር አኗኗር ያስተምራል : (ፊልጵ. 3፡1-4፡23)።

የፊልጵስዩስ መልእክት አስተዋጽኦ

 1. መግቢያ (ፊልጵ. 1፡1-11)
 2. የግል መረጃ፡- ጳውሎስ ስለ እሥራቱ ያብራራል (ፊልጵ. 1፡12-26)
 3. የመጀመሪያው ትምህርት፡- ጳውሎስ ለክርስቶስ እንዴት ልንኖር እንደሚገባን ያስተምራል (ፊልጵ. 1፡27-2፡18)
 4. የግል መረጃ ፡- ጳውሎስ ስለ አፍሮዲጡ መመለስና የጢሞቴዎስ መምጣት ይናገራል (ፊልጵ. 2፡19-30)
 5. ሁለተኛው ትምህርት፡- ጳውሎስ ስለ ክርስቲያናዊ አኗኗር ተጨማሪ ትምህርቶችን ይሰጣል (ፊልጵ. 3፡1-4፡19)

ሀ. ጳውሎስ ስለ ሐሰተኛ አስተማሪዎች ያስጠነቅቃል (ፊልጵ. 3፡1-21)

ለ. ጳውሎስ በአንድነት ለክርስቶስ እንዲኖሩ ያበረታታል (ፊልጵ. 4፡1-9)

 1. ጳውሎስ የፊልጵስዩስን ክርስቲያኖች ለስጦታቸው አመሰገነ (ፊልጵ. 4፡10-20)
 2. ማጠቃለያ (ፊልጵ. 4፡21-23)

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: