መከራ በሚደርስብን ጊዜ ትክክለኛ አቋም መያዝ አስቸጋሪ ነው። በቀላሉ ተስፋ መቁረጥ ይቻላል። ታላቁ የወንጌል አገልጋይ ከአራት ዓመታት በላይ ወኅኒ ቤት ውስጥ ቆይቷል። በዚህ ጊዜ ለጳውሎስ እግዚአብሔር ተሳስቶ ይሆን? ብሎ ማሰብ ቀላል ነበር። የፊልጵስዩስ አማኞችም የቤተ ክርስቲያናቸው መሥራችና ወዳጃቸው የሆነው ሰው በመታሠሩ ተጨንቀው ነበር። ጳውሎስ በወኅኒ ቤት ውስጥ ቢሆንም፥ እግዚአብሔር ታላቅ አምላክ በመሆኑ ክፉውን ነገር ወደ መልካም ሊቀይር እንደሚችል በመግለጽ የፊልጵስዩስን አማኞች ያበረታታል። ጳውሎስ በመታሠሩ ምክንያት እንደሚከናወኑ የተናገራቸው መልካም ነገሮች የሚከተሉት ናቸው።
ሀ. ወንጌሉ ወደ ሮም ቤተ መንግሥት (እስከ ቤተ መንግሥት ጠባቂው ድረስ) ደርሷል። ቄሣርን ለመጠበቅ የተሰማሩ ወደ 6,000 ልዩ ወታደሮች ነበሩ። ምናልባትም በቄሣር ፊት ስለሚመረመር ሳይሆን አይቀርም። ከእነዚህ ወታደሮች አንዳንዶቹ ጳውሎስን ይጠብቁት ነበር። ጳውሎስም ለእነዚህ ወታደሮች ክርስቶስን መሰከረላቸው። በዚህም ጊዜ አንዳንዶቹ በክርስቶስ አመኑ። ወታደሮቹ በየተራ ጳውሎስን የሚጠብቁት በመሆናቸውና የዳኑትም ለሌሎች በመመስከራቸው ብዙም ሳይቆይ ወንጌሉ በቁልፍ ወታደሮች መካከል ተስፋፋ። ጳውሎስ ባይታሠር ኖሮ እነዚህ ሰዎች ወንጌሉን የመስማት ዕድል ላያገኙ ይችሉ ነበር።
ለ. ጳውሎስ ለክርስቶስ ለመሠቃየት መፍቀዱን ሲመለከቱ ክርስቲያኖች በድፍረት እምነታቸውን ለሌሎች ያካፍሉ ጀመር። ጳውሎስ ለክርስቶስ የሚመሰክሩ ሁለት ዓይነት ክርስቲያኖች እንደነበሩ ገልጾአል። በመልካም ልብ ጳውሎስን የሚያከብሩና ወንጌልን የሚሰብኩ ነበሩ። በጳውሎስ ላይ የሚቀኑም ደግሞ ነበሩ። እነዚህ ሰዎች ወንጌሉን የሚሰብኩት ሮማውያን ባለሥልጣናት በጳውሎስ ላይ የበለጠ ችግር እንዲፈጥሩ በማሰብ ነበር። ጳውሎስ ግን ለራሱ የግል ጉዳይ አልተጨነቀም። የእርሱ ትልቁ አሳብና ፍላጎት የወንጌሉ መሰበክ ነበር። ጳውሎስ የሚጠሉትን ሰዎች ልባዊ ፍላጎት እያጸደቀ አልነበረም። ጳውሎስ በሌላ ስፍራ ልባዊ ፍላጎታችን ትክክል ካልሆነ ላከናወንነው ተግባር ከእግዚአብሔር ዘንድ ሽልማትን እንደማናገኝ ይናገራል (1ኛ ቆሮ 3፡10-15)። ነገር ግን ጳውሎስ ከሰዎች መጥፎ የልብ ፍላጎት ባሻገር የወንጌሉ መልእክት እየተሰበከ መሆኑን ለመግለጽ ይፈልጋል። የእግዚአብሔር ቃል ኃይል ስላለው በእንዲህ ዓይነት ሰዎች በሚሰበክበት ጊዜ ሳይቀር የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል።
ሐ. ጳውሎስ በፊልጵስዩስ አማኞች ተግባር ስለተበረታታ እነርሱን መልሶ ያበረታታቸዋል። እንደሚጸልዩለት ስለሚያውቅ በዚሁ የእግዚአብሔር ሕዝብ ጸሎት ይበረታታል። እግዚአብሔር ጳውሎስን ጠንካራ፥ በምስክርነት አገልግሎት የሚተጋና ሞትን የማይፈራ ደፋር ለማድረግ የእነዚህን ወገኖች ጸሎት ተጠቅሟል። ጳውሎስ ቄሣር እንዲገደል ቢያዝ እንኳን እንደማይሸነፍ ስለሚያውቅ በእሥር ቤት ውስጥ በድፍረት ያገለግል ነበር። ሞት ክርስቲያንን ወደ ክርስቶስ ይወስደዋል እንጂ ለሽንፈት አይዳርገውም። ይህም ከእሥር ቤት ወይም ኃጢአትና ሥቃይ ካለበት ከየትኛውም ምድራዊ ሕይወት የበለጠ ነው። ነገር ግን ጳውሎስ እግዚአብሔር በሕይወቱ የሚፈጽመው ተግባር ስላለ ከወኅኒ እንደሚወጣ ተስፋ ያደርጋል።
የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ከክፉው የኮሚኒዝም ዘመን ቤተ ክርስቲያን ያገኘቻቸው አንዳንድ መልካም ነገሮች ምን ምንድን ናቸው? ለ) በትልቅ ችግር ሳቢያ በሕይወትህ ውስጥ የተከሠቱትን አንዳንድ መልካም ነገሮች ዘርዝር። ሐ) ይህ በሕይወታችንና በቤተ ከርስቲያናችን አስቸጋሪ ጊዜያት በሚመጡበት ጊዜ ምን ማድረግ እንዳለብን ያሳያል?
(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)