ጳውሎስ ለክርስቶስ እንዴት ልንኖር እንደሚገባ ያስተምራል (ፊልጵ. 1፡27-2፡18)

ክርስቶስን የግል አዳኝ አድርጎ ማመኑ አስፈላጊ ነው። ይህ ወደ ሲዖል እንዳንገባና የእግዚአብሔር ልጆች እንድንሆን ያስችለናል። ነገር ግን እግዚአብሔር በሚያድነን ጊዜ ከዚህ የበለጠ ብዙ ይጠብቅብናል። ለእኛ ያለውን ታላቅ ፍቅር በሚያንጸባርቅ መልኩ እንድንኖርለት ይሻል። ምንም እንኳ እግዚአብሔር ከእኛ የሚፈልገው ምስጋናችንን ብቻ ነው ብንልም፥ አዲስ ኪዳን ግን እርሱን በሚያስከብር መንገድ እንድንኖርም ያስተምራል። ጳውሎስም ለተጠራችሁለት የክርስቶስ ወንጌል እንደሚገባ ተመላለሱ ይለናል።

ለመሆኑ ከተቀበልነው ወንጌል ጋር በሚስማማ መንገድ መኖራችንን የሚያመለክቱ አንዳንድ ነገሮች ምን ምንድን ናቸው?

፩. ከሌሎች ክርስቲያኖች ጋር በአንድነት መኖር አለብን። በፊልጵስዩስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሆነ ክፍፍል ተፈጥሮ ነበር። ሁለት ሴቶች እየተጣሉ ነበር። ይህም በሌሎች አማኞች መካከል ክፍፍልን ያስከተለ ይመስላል። ስለሆነም፥ ጳውሎስ አማኞች በኅብረት አብረው እንዲኖሩ ሊያስተምራቸው ይፈልጋል።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) መክ 4፡9-12 እና ምሳሌ 27፡17 አንብብ። እነዚህ ጥቅሶች ሰዎች በኅብረት አብረው በሚኖሩበት ጊዜ ስለሚገኘው ጥንካሬ ምን ያስተምራሉ? ለ) ፊልጵ. 1፡27 እና 2፡1-11ን አንብብ። ጳውሎስ በዚህ ክፍል ውስጥ «አንድነት» «ኅብረት»፥ «አንድ» የሚሉትን ቃላት ምን ያህል ጊዜ በተደጋጋሚ ጠቅሷል? ሐ) አንድነት እንዲኖር ሰዎች ምን ዓይነት ባሕርይ ሊኖራቸው ይገባል? መ) ክርስቲያኖች በአንድነት እንዲኖሩ መሠረት የሚሆኗቸውን ነገሮች ዘርዝር።

ያለነው ብዙ አብያተ ክርስቲያናት በተከፋፈሉበት ዘመን ውስጥ ነው። ጳውሎስ ካስተማረው እውነት አንጻር፥ ይህ ለተቀበልነው ወንጌል የሚገባውን አኗኗር እንደማንከተል ያሳያል። ወንጌሉ አማኞች ከቤተ እምነት ውክልናቸው፥ ከቤተሰባዊ ውርሳቸው ወይም ከጎሳዊ አባልነታቸው ባሻገር አንድ መሆናቸውን ያስተምራል። ከሌሎች ክርስቲያኖች ጋር መጣላቱ እናምናለን የምንለውን ሁሉ ይቃረናል።

ክርስቲያኖች በአንድነት ሊኖሩ የሚገባቸው ለምንድን ነው? ጳውሎስ ሁለት ዐበይት ምክንያቶችን ሰጥቷል።

ሀ. ጳውሎስ በኅብረት ሊኖሩ የሚገባቸው እንዲህ ዓይነቱ ሕይወት ጥንካሬን የሚፈጥር በመሆኑ ነው ይላል። ስለሆነም ክርስቲያኖችን በአንድ ልብ ስለ ወንጌል አብራችሁ እየተጋደላችሁ፥ «በአንድ መንፈስ እንድትቆሙ» ሲል ይመክራል። ሰሎሞን ሁለት ሰዎች እንኳን በኅብረት ቢኖሩ የሕይወትን ማዕበሎች ተቋቁመው እንደሚጸኑ ገልጾአል። እንዲሁም ሰዎች በመንፈሳዊ ሕይወታቸውና በእውቀት ስለታም ሊሆኑ የሚችሉት ብረት ቢላዋን እንደሚስል እርስ በርሳቸው የተሣሣሉ እንደሆነ ብቻ ነው ብሏል። ክፍፍል ይህንኑ ጥንካሬ በማስወገድ ሰዎች ለጠላቶቻቸው ጥቃቶች እንዲጋለጡ ያደርጋል። እነዚህም ጠላቶች ዓለም፥ ሰይጣንና የኃጢአት ተፈጥሮ ናቸው። ማንም ክርስቲያን ብቻውን ወደ ጥንካሬ ወይም መንፈሳዊ ብስለት ሊያድግ አይችልም። ሁላችንም ሌሎች እንዲረዱን እንሻለን።

ጳውሎስ የሚጽፈው ስለ ምን ዓይነቱ አንድነት እንደሆነ ማወቁ መልካም ነው። በመጀመሪያ፥ ጳውሎስ እውነትን የሚሠዋ አንድነት መሥርቱ እንዳላለ መረዳት ይኖርብናል። መጽሐፍ ቅዱሳዊ አንድነት በጋራ እምነት ላይ የሚመሠረት ነው። እነዚህም እምነቶች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በግልጽ የቀረቡ ናቸው። ጳውሎስ የእግዚአብሔር ቃል የማይደግፋቸውን ነገሮች ከሚያስተምሩ ሌሎች ሃይማኖቶች ጋር አንድነት መሥርቱም አላለም። ከሌሎች ሃይማኖቶች ጋር ጸብ ሳንፈጥር በሰላም ልንኖር እንጂ አንድነትን ልንመሠርት አንችልም። መጽሐፍ ቅዱሳዊ አንድነት ችግሮችንና ኃጢአቶችን በማስወገድ ላይ የተመሠረተ እንጂ መደባበቅን አያበረታታም። ብዙውን ጊዜ ክፍፍል እንዳይከሠት ወይም ሰዎች እንዳይጎዱ በማሰብ ችግሮችን ወይም ኃጢአትን እንደብቃለን። ይህ ዘዴ ጊዜያዊ ሰላምን ሊያመጣ ቢችልም፥ የችግሩ ሥር ስላልተነካ የኋላ ኋላ ጸብን ማስከተሉ አይቀርም። ይቅርታን ልናገኝና ልንፈወስ የምንችለው ኃጢአት መፈጸማችንንና ችግሮች መኖራቸውን አምነን ስንቀበል ብቻ ነው። አንድነት በእውነትና በቅድስና መሠረት ላይ መታነጽ አለበት።

ሁለተኛ፥ ጳውሎስ የሚገልጸው የአንድነት ዓይነት ከፍቅር ጋር በተዋሃደ እውነት ላይ የተመሠረተ ነው። በዚህ ዓይነቱ አንድነት ውስጥ ፍቅር፥ ለሌሎች ማሰብና መራራቱ፥ እንዲሁም እግዚአብሔር እንዲሆኑለት የሚፈልጉትን ሁሉ ሲሆኑ ለማየት የመጓጓት ፍላጎት ይኖራል። ይህም ኃጢአታቸውን ሳይናዘዙ ኖረው ውስጣዊ ሕይወታቸውን እንዲያወድሙ አይቶ እንዳላየ ዝም ከማለት ይልቅ ኃጢአታቸውን ተናዝዘው ከጎጂ መዘዞቹ እንዲላቀቁ ለማገዝ መፍቀድን ይጨምራል። እንዲሁም እውነትን፣ ሁሉም ሰው ስለ ክርስቶስ ባለው እውቀት የሚያድግበትንና የእግዚአብሔርን ቃል በመጠበቅ እውቀቱን የሚያንጸባርቅበትን ቆራጥነትም ያካትታል።

ሦስተኛ፣ ጳውሎስ በእሑድ ቀን ብቻ ተሰባስበው ስለሚያመልኩት ሰዎች አንድነት አይደለም የጻፈው። ጳውሎስ የሚጽፈው በክርስቲያኖች ድካምና ተጠያቂነት ላይ ስለተመሠረተ አንድነት ነው። የሌሎችን ጸሎትና እገዛ በመሻት ትግሎቻችንን ለሌሎች ለማካፈል መፍቀድ ይኖርብናል። የተጠያቂነት አንድነትም ሊኖረን ይገባል። ይህም እንደ ቃሉ እንድንኖር የምንጠየቅበትና ሌሎችም ለክርስቶስ ክብር እንዲኖሩ የምናበረታታበት ነው።

ምእመናን በዚህ ዓይነት መንገድ አንድነትን እስካልመሠረቱ ድረስ የትኛውም ቤተ ክርስቲያን ወይም ክርስቲያን ሊጠናከሩ አይችሉም።

የውይይት ጥያቄ፡– በቤተ ክርስቲያንህ ውስጥ የተፈጠረ አንድ አለመግባባት ምረጥ። ሀ) ያ አለመስማማት እውነትን በመሽፋፈን እንዴት ሊረግብ ይችል ነበር? ለ) አንድ ሰው ከፍቅር ይልቅ በእውነት ላይ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት ክፍፍሉን ሊያባብስ የሚችለው እንዴት ነው? ሐ) እውነትንና ፍቅርን በመቀላቀል ችግሩን ለመፍታት ምን ማድረግ ይቻላል? መ) የእውነትና የፍቅር የቅርብ ግንኙነት አብዛኞቹን ክፍፍሎች ሊያስወግድ የሚችለው እንዴት ነው?

ለ. ጳውሎስ በአንድነት ስንኖር ጌታችንና ምሳሌያችን የሆነውን ክርስቶስን እንደምንመስል ያስረዳል። በፊልጵስዩስ 2፡6-11 በአዲስ ኪዳን ውስጥ ስለ ክርስቶስ ከተሰጡት እጅግ ጠቃሚ ትምህርቶች አንዱን እናገኛለን። ብዙ ምሁራን ይህ ግጥም የቀድሞይቱ ቤተ ክርስቲያን ምእመናን የሚዘምሩት መዝሙር እንደነበረ ያምናሉ። ምናልባትም ይህ ጳውሎስ የጻፈው መዝሙር ሳይሆን አይቀርም። ይህ መዝሙር ክርስቶስ ሰው ከመሆኑ በፊት ምን ይመስል እንደነበረ፥ ሰው በሆነ ጊዜ ምን እንደ ተከሠተና የውርደቱም ውጤት ምንን እንዳስከተለ ይናገራል። ነገር ግን ይህ ትልቅ ትምህርት የቀረበው በቀዳሚነት ክርስቶስን ታላቅ ያደረገውን አስተሳሰብ ለእኛ ለማሳየት ነው። ጳውሎስ ለፊልጵስዩስ ክርስቲያኖች ስለያዟቸው መሠረታዊ እምነቶች በማውሳት ይጀምራል። አቀራረቡ፥ «ይህን ታምናላችሁ?» ብሎ የሚጠይቅ ይመስላል። ሁሉም «አዎን» ብለው እንዲመልሱለትም ይጠብቃል። ከዚያም እነዚህ እውነቶች እንዴት ወደ አንድነት እንደሚያመሩ ያሳያቸዋል።

  1. «ከክርስቶስ ጋር በመተባበራችሁ (አንድ በመሆናችሁ)» ደስ ይላችኋል? ጳውሎስ ከክርስቶስ ጋር ወይም በክርስቶስ መሆን ሲል፥ «በመዳናችሁና ከክርስቶስ ጋር የቅርብ ግንኙነት በመመሥረታችሁ ደስተኞች ናችሁ?» ማለቱ ነበር። ሁላችንም ለዚህ ጥያቄ አዎንታዊ ምላሽ መስጠታችን የማይቀር ነው።
  2. ክርስቶስ ስለሚወዳችሁ ደስ ይላችኋል? በሮሜ 8፡31-39 ጳውሎስ ማንም ከክርስቶስ ፍቅር ሊለየን እንደማይችል ይናገራል። እንድንድን ያደረገን ያ ፍቅሩ ነው። ያ ፍቅር እሁን ዋስትናን ይሰጠናል። እግዚአብሔር እንደሚጠብቀን ቃል ገብቶልናልና። ያ ፍቅር ከእግዚአብሔር ጋር በመንግሥተ ሰማይ ለዘላለም እንደምንኖር ያረጋግጣል። አሁንም ምላሻችን የሚሆነው «አዎን» ነው።
  3. በሁላችሁ ውስጥ ካለው መንፈስ ቅዱስ ጋር ኅብረት አላችሁ? መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ልጆች እንደ መሆናችን፥ መንፈስ ቅዱስ በልባችን ውስጥ እንደሚኖር ይናገራል (ሮሜ 8፡9-10)። እርሱ ሊያጽናናን፥ ሊረዳን፥ ሊጠብቀን፥ ኃይልን ሊሰጠንና በውስጣችን ሊሠራ ተዘጋጅቶ ከልባችን ውስጥ ይኖራል። ለዚህም «አዎን» ብለን እንመልሳለን።
  4. እግዚአብሔር ለሚጎዱ ሰዎች የምትራሩበትን ኃይል ሰጥቷችኋል? ይህም የሕይወታችን መለያ ባሕርይ ሊሆን ይገባል።

እነዚህ አራት ነገሮች እውነት ከሆኑ፥ ከሌሎች ክርስቲያኖች ጋር በአንድነት ለመኖር እንችላለን። በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ የተለያየ አቋም ልንይዝ ብንችልም፥ እምነታችን አንድ በመሆኑ ምክንያት አንድ ዓይነት አስተሳሰብ ይኖራል። እርስ በርሳችን በመዋደድ ክርስቶስን በማስከበሩ አንድ ዓላማ ላይ እንሳተፋለን። መንፈስ ቅዱስም ይህንኑ ተግባር ከዳር እንድናደርስ ያግዘናል።

ሁላችንም ይህንን የምንፈልግ ከሆነ፥ ያለመተባበርና መከፋፈል ከየት ይመጣል? መሪዎች ለምን ይጣላሉ? ቤተ እምነቶች ለምን እርስ በርሳቸው ይጣላሉ? ጳውሎስ ለዚህ ችግሩ አመለካከታችን፥ ራስ ወዳድነታችንና በትሕትና ለመቀባበል አለመፈለጋችን እንደሆነ ያስረዳል። የኃጢአት ሥር ራስ ወዳድነት ነው። ይህም ነገሮችን በራስ መንገድ ለማከናወን፥ ለራስ ለመጠቀምና ሌላውን ሳይሆን ራስን የመንከባከብ ፍላጎት ነው። የአንድነት ምሥጢሩ ራስን የሕይወት ማዕከል አለማድረግ ነው። ይህም ስለ ሌሎች ሰዎችና ስለ ፍላጎቶቻቸው ማሰብ ነው።

ለመሆኑ ከሌሎች ይልቅ የራስን ፍላጎት ማስቀደም ምን ክፋት አለው? ጳውሎስ ይህ ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌነት ውጭ እንደሆነ ያስረዳል። እርሱ የተወልን ምሳሌነት ምን ነበር?

ሀ. እርሱ ማን እንደነበረ፡- ክርስቶስ በባሕርዩ ፍጹም አምላክ ነበረ። ክርስቶስ የእግዚአብሔር አብ ባሕርያት ሁሉ ነበሩት። በምንም መንገድ ከእግዚአብሔር አላነሰም ነበር። መላእክት እያመለኩትና እየታዘዙት ከምናስበው ባለፈ ክብርና ተድላ በመንግሥተ ሰማያት ይኖር ነበር።

ለ. አመለካከቱ (እሳቡ) ምን ነበር፡- ከእግዚአብሔር ጋር እኩል የመሆን ደረጃ ውን ይዞ በሰማያዊ በረከቶች ደስ ለመሰኘት አልፈለገም። እነዚህን ነገሮች የሙጥኝ ብሎ ሳይዝ ጥሏቸዋል። አምላክ የነበረው ክርስቶስ ራሱን አዋርዶ ሰው ሆነ።

ሐ. ጊዜያዊው ውጤት ምን ነበር፡- ክርስቶስ በአምላክነቱ ያገኛቸው የነበሩትን ጥቅሞች ትቶ በሰብአዊ ሰውነት ውስጥ ተወሰነ። እንደዚሁም ለሌሎች ጥቅም የሚሠራ «ባሪያ» ሆነ።

መ. ይህ ውርደት ምን አስገኘለት፡- ለእናንተና ለእኔ የሞተበትን የመስቀል ላይ ሥቃይ። ትሕትና ሁልጊዜም በደል ለደረሰበት ሰው መጀመሪያ ሥቃይን ያስከትላል።

ሠ. ዘላለማዊው ውጤት ምን ነበር፡- እግዚአብሔር ከስሞች ሁሉ የበለጠ ስም በመስጠት ክርስቶስን አከበረው። ስለሆነም፥ በሁሉም ይከበራል።

ከዚህ ላይ ለእኛ የተሰጠው ምሳሌነትና የተስፋ ቃል ምንድን ነው? እግዚአብሔር እንዲያከብረንና ለዘላለሙ እንዲሸልመን ከፈለግን፥ ራስን የማዋረዱን የትሕትና መንገድ መከተል ይኖርብናል። ለእኛ ጠቃሚዎች የሚመስሉትን ነገሮች ትተን አሳቦቻችንንና ዕቅዶቻችንን በመጣል፥ ለሌሎች በጎነት ጊዜያችንንና ገንዘባችንን በመስጠት አንዳንድ ጊዜ ራስን ማዋረድ የሚያስከትለው ሥቃይ መቀበል ይኖርብናል። በሰብአዊ አስተሳሰብ ይህ የባርነት ደረጃ በመሆኑ ከሕይወት ውስጥ አስፈላጊ የሆነውን ሁሉ ማጣት ሊመስል ይችላል። በዘላለሙ መንግሥት ግን እግዚአብሔር ያስከብረናል።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) የክርስቶስ ዓይነት አስተሳሰብ ቢኖረን የማንስማማባቸውና የምንጣላባቸው አብዛኞቹ ነገሮች እንዴት ሊወገዱ እንደሚችሉ አብራራ። ለ) ከአንድ ሰው ጋር የነበረህን ያለመስማማት አስብ። የክርስቶስ ዓይነት አስተሳሰብ ያንን አለመስማማት እንዴት በፍጥነት ያስወግድ እንደነበር ግለጽ።

፪. በስደት መጽናት፡፡ ጳውሎስ እንደ ክርስቶስ ተከታዮች እንድንኖር ያስተማረበት ሁለተኛው መንገድ ስደት የማይቀር የክርስቲያን ሕይወት መንፈሳዊ ጉዞ አካል መሆኑን በማሳየት ነው። ይህ የደኅንነታችን ውጤት ነው። «ይህ ስለ ክርስቶስ ተሰጥቷችኋልና፤ ስለ እርሱ መከራ ደግሞ እንደትቀበሉ እንጂ በእርሱ ልታምኑ ብቻ አይደለም።» ስደት ክርስቶስን የመከተል አካል እስከሆነ ድረስ እንዲህ ዓይነት ሁኔታ በሚከሰትበት ጊዜ ልንደነግጥና ልንሸሽ አይገባም። ይህ ክፍል ስለ አንድነት በቀረበው ትምህርት ውስጥ የተቀመጠው ለሁነኛ ዓላማ ነው። በቆራጥነት ስደትን ልንጋፈጥ የምንችለው እንዴት ነው? የእግዚአብሔር ዐቢይ የማበረታቻ መንገድ ምንድን ነው? የክርስቶስ አካል ነው። ስለሆነም፥ በስደት ለመጽናት የሌሎች ክርስቲያኖች ድጋፍ ያስፈልገናል። በእምነታችን እንድንጸና የሚያግዙንን ወገኖች ለምን እንጠላቸዋለን?

፫. ለእግዚአብሔር ለመኖር መትጋት፡- ጳውሎስ – ለፊልጵስዩስ ክርስቲያኖች፥ «በፍርሃትና በመንቀጥቀጥ የራሳችሁን መዳን ፈጽሙ» ይላቸዋል። ድነት (ደኅንነትን) በሥራችን እንደማናገኝ አዲስ ኪዳን በግልጽ ያስተምራል። ድነት (ደኅንነት) በእምነት የምንቀበለው የእግዚአብሔር ስጦታ ነው (ኤፌ. 2፡8-9 አንብብ)። እንግዲህ ጳውሎስ ምን ማለቱ ነው? መዳን የሚለው ቃል ብዙ ፍችዎች አሉት። የዘላለምን ሕይወት በማግኘት የእግዚአብሔር ልጅ መሆን ማለት ይሆናል። አዲስ ኪዳን እንዲህ ዓይነቱ ድነት (ደኅንነት) የእግዚአብሔር ስጦታ እንደሆነ ያስረዳል። መዳን የሚለው ቃል በመንፈሳዊ ሕይወታችን በማደግ እግዚአብሔርን የሚያስደስት ሕይወት መምራታችንንም ሊያመለክት ይችላል። ጳውሎስ በዚህ የመንፈሳዊ ዕድገት መዳን ውስጥ ሰውም እግዚአብሔርም እንደሚሳተፉ ገልጾአል። ዝም ብለን በመቀመጥ «ምንም ማድረግ አያስፈልገኝም እግዚአብሔር ለእኔ ያደርግልኛል» ማለት የለብንም። ነገር ግን እግዚአብሔር ሀ) የማደግ ፍላጎትን እንደሚሰጠንና ለ) እርሱ እንደሚፈልገው እንድንኖር ኃይልን እንደሚሰጠን እናውቃለን። ነገር ግን ኃጢአታችንን ልንናዘዝ፥ በልባችን ትክክለኛ አመለካከት ልንይዝ፥ ለእግዚአብሔር ልንኖርና በሙሉ ኃይላችን ልናገለግለው ይገባል።

፬. የተቀደሰ ሕይወት እንኖር ዘንድ አመለካከታችን ትክክለኛ መሆን አለበት። በሰዎች ግንኙነቶች ውስጥ ችግሮችን የሚፈጥሩ ሁለት ነገሮች አሉ። እነዚህም ማማረርና መከራከር ናቸው። ክርስቲያኖች የክርስቶስን አካል አንድነት የሚያጠቁትን እነዚህን ነገሮች በሚያስወግዱበት ጊዜ፥ ቤተ ክርስቲያን በጨለመው ክፉ ዓለም ውስጥ ታላቅ ብርሃን ትሆናለች። በአንድነት በምንኖርበት ጊዜ ሰዎች ስብከታችንን ሊሰሙ ይፈቅዳሉ («የሕይወትን ቃል እያቀረባችሁ»)።

የውይይት ጥያቄ፡– ሕይወትህን ገምግም። ሀ) በሕይወትህ እነዚህ አራት ነገሮች የሚታዩት እንዴት ነው? ለ) በእምነት ጉዞህ ውስጥ ደከም ያሉት አካባቢዎች የትኞቹ ናቸው? ላመንኸው ወንጌል እንደሚገባ ለመኖር ምን ዓይነት ተግባራዊ እርምጃዎች ለመውሰድ ፈቅደሃል?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: