ጳውሎስ ስለ አፍሮዲጡ መመለስና የጢሞቴዎስ መምጣት ይናገራል (ፊልጵ. 2፡19-30)

ጳውሎስ በምርመራው መሃል የሚገኝ ይመስላል። በቅርቡ በነፃ እንደሚያሰናብቱትና የፊልጵስዩስን ሰዎች እንደሚጎበኝ ተስፋ ያደርጋል። ነገር ግን ከቤተ ክርስቲያኒቱ ጋር ግንኙነት ለማድረግ ስለፈለገ፥ የቅርብ ጓደኛውና ረዳቱ የነበረውን ጢሞቴዎስን እንደሚልክላቸው ይናገራል። ጢሞቴዎስ ለቤተ ክርስቲያን ምሥረታና ለወንጌል መስፋፋት የበኩሉን አስተዋጽኦ በማድረግ ከ12 ዓመታት በላይ ከጳውሎስ ጋር ሠርቷል። ጳውሎስ የፊልጵስዩስን ቤተ ክርስቲያን ሁኔታ ለማወቅ ስለፈለገ ጢሞቴዎስ አይቷቸው እንዲመጣና እንዲነግረው ፈለገ።

ጳውሎስ የፊልጵስዩስን መልእክት ከጻፈባቸው ምክንያቶች አንዱ አፍሮዲጡ ነበር። አፍሮዲጡ የፊልጵስዩስ አማኝ ሲሆን፥ ቤተ ክርስቲያኒቱ የጳውሎስን መታሠር በሰማች ጊዜ ይህንኑ ወንድም ነበረ መጀመሪያ ወደ ሮም የላከችው። እፍሮዲጡ ሮም ተቀምጦ ጳውሎስን በሚገባ አገለገለው። ብዙም ሳይቆይ ግን ለሞት እስኪያሰጋው ድረስ በጠና ታመመ። ጳውሎስም የፊልጵስዩስን ክርስቲያኖች ጭንቀት ለማርገብ ሲል ወደዚያው መልሶ ሰደደው። አፍሮዲጡ ባይታሠርም፥ ከጳውሎስ ጋር ሆኖ እሥራቱን ለመካፈል ፈቅዶ ነበር። ጳውሎስን ለማበረታታት ሲል የደረሰበትንም በሽታ ታግሦአል። «ስለሆነም፥ ጳውሎስ ክርስቲያኖች አፍሮዲጡንና ለወንጌሉ ሲል ራሳቸውን ለአደጋ የሚያጋልጡትን ሁሉ እንዲያከብሩ ጠይቋቸው ነበር።

ይህ አጋጣሚ ስለ ፈውስ አንድ ጠቃሚ ትምህርት ያስተላልፋል። እግዚአብሔር ብዙ ሰዎችን ለመፈወስ በጳውሎስ ተጠቅሟል (የሐዋ. 20፡712፥ 28፡8-10)። ይህ ማለት ግን ሁልጊዜም የመፈወስ ኃይል አለው ማለት አይደለም። ራሱን እንኳን ለማዳን አልቻለም ነበር (2ኛ ቆሮ. 12፡7-10፤ ገላ. 4፡13-14)። በዚህ ስፍራ አፍሮዲጡ ሊሞት ሲቃረብም፥ ጳውሎስ ሊያድነው አልቻለም። አፍሮዲጡ ለረዥም ጊዜያት ታሞ የሰነበተ ይመስላል። ምክንያቱም ከሮም ወደ ፊልጵስዩስ ተጉዞ ስለ ሕመሙ ለመናገር ቢያንስ አንድ ወር ይፈጃል። ይህ ፈውስ በእግዚአብሔር እንጂ በሰው ፈቃድ ብቻ እንደማይመጣ ያስረዳል። እግዚአብሔር አንድ ሰው ሌላውን ለመፈወስ መሣሪያው እንደሚሆን በሚናገርበት ጊዜ ፈውሱ በጸሎት አማካኝነት ተግባራዊ ይሆናል። ነገር ግን እግዚአብሔርን ፈቃዱን ባልገለጠ ጊዜ እግዚአብሔር እንዲፈውሰው ብንጠይቅም ውጤቱን የሚያውቀው እርሱ ብቻ ነው። ከዚያ በኋላ እግዚአብሔር የሚያደርገውን እንጠብቃለን። እንዳንድ ጊዜ እግዚአብሔር ፈውስን ያወርዳል። ሌላ ጊዜ ደግሞ ታማሚውን ወደ ራሱ ይወስዳል። እግዚአብሔር አንድን ነገር እንዲያደርግ ልናዝዘው አንችልም። እግዚአብሔር ሰዎችን ለመፈወስ የተጠቀመባቸው ወገኖች ሁልጊዜም የታመሙትን እንደሚፈውሱ ወይም የጸለዩለትን ሰው ሁሉ እንደሚፈወስ ማሰብ የለባቸውም። እግዚአብሔር በግልጽ እስካልነገረን ድረስ ለምንጸልይለት ሰው «ጌታ ይፈውስሃል» ማለት የለብንም። ይህ ካልሆነ፥ እግዚአብሔር ሳይነግረን የውሸት መልእክት በማስተላለፍ የዚያን ግለሰብ ተስፋ በከንቱ እናለመልማለን።

የውይይት ጥያቄ፡– ሀ) እግዚአብሔር ጳውሎስ አፍሮዲጡን እንዲፈውስ ያልፈቀደለት ለምን ይመስልሃል? ለ) ከዚህ ስለ ፈውስ አገልግሎትና አገልጋዮች ምን እንማራለን?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: