ጳውሎስ ከሐሰተኛ አስተማሪዎች እንዲጠበቁ ያስጠነቅቃቸዋል (ፊልጵ. 3፡1-21)

ዘሪሁን ከታወቀ የሥነ መለኮት ኮሌጅ በማስትሬት ዲግሪ ተመረቀ። መጽሐፍ ቅዱሳዊ እውነቶችን ለመረዳት ለብዙ ጊዜያት ሲያጠና ነበር የሰነበተው። ዲግሪውን ከተቀበለ በኋላ ወደ አገሩ ተመለሰ። ሰዎች ጴጥሮስን «ሊቅ» አድርገው ቆጠሩት። እርሱም የሚያነሡአቸውን ጥያቄዎች ሁሉ በልበ ሙሉነት መለሰ። በቤተ ክርስቲያንም ውስጥ የሥልጣን ስፍራ ተሰጠው። ሥራው ፋታ ስለነሣው የእግዚአብሔርን ቃል ለማጥናት ጊዜ አላገኘም። «ሁሉም የማውቀው ነው» ሲልም አሰበ። ብዙም ሳይቆይ መንፈሳዊ ሕይወቱ ባለበት በመርገጡ በወሲብ ኃጢአት ወድቆ ከቤተ ክርስቲያን መሪነቱ ለቀቀ።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) በተለይ ልዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ሥልጠና ከወሰድን በኋላ በቀላሉ በመንፈሳዊ ሕይወታችን ማደግን የምናቆመው ለምን ይመስልሃል? ለ) ፊልጵስዩስ 3፡12-15 አንብብ። ጳውሎስ ስለ ሕይወቱና መንፈሳዊ ዕድገቱን ስለቀጠለበት ሁኔታ ምን ይላል? ሐ) አንድ ሰው በእምነቱ ሳያቋርጥ ለማደግ ምን ሊያደርግ ይችላል? መ) መንፈሳዊ፥ ማኅበራዊ፥ የእውቀት፥ ወዘተ… ዕድገት ለማግኘት በግልህ ምን እያደረግህ ነው? ሠ) ፊልጵስዩስ 3-4 አንብብ። ጳውሎስ እግዚአብሔርን በሚያስደስት መንገድ ስለመኖር ያስተማራቸውን ጠቃሚ እውነቶች ዘርዝር።

እንዳለመታደል ሆኖ ብዙ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች መንፈሳዊ እድገታቸውን ያቋርጣሉ። መጽሐፍ ቅዱስን እያጠኑ በእግዚአብሔር ቃል እውቀት አያድጉም። እንደ መጾም፥ መጸለይ፥ መስጠት፥ ቃሉን ማካፈል፥ ባሉት መንፈሳዊ ነገሮች አያድጉም። ስላገኘናቸው ዲግሪዎች ብዙ ማውራቱ ቀላል ነው። ነገር ግን የክርስትና ሕይወት በሁሉም የሕይወት ክፍሎች የማያቋርጥ ዕድገት የሚከሠትበት ሊሆን ይገባል። አዳዲስ ነገሮችን እየሞከርን ሥራችንን በበለጠ ልናውቅ ይገባል። በመንፈሳዊ ልምምድ የጸሎትና የጾም ሕይወታችንም ማደግ አለብን። ወደ መንግሥተ ሰማይ እስክንደርስ ድረስ ዕድገታችን መቋረጥ የለበትም። ጳውሎስ ይህንን ስለተገነዘበ፥ እግዚአብሔር በከፍተኛ ደረጃ እየተጠቀመበት ቢሆንም ወደ ኋላ እየተመለከተ ገድሉን ለመተረክ አልፈለገም። ይልቁንም ለማደግ መጣሩን ቀጠለ። ጳውሎስ በሕይወት እስካለ ድረስ ሁልጊዜም ለመሻሻልና ለማደግ ስፍራ እንዳለው ያውቅ ነበር። ስለሆነም፥ ወደፊት መጓዙን ቀጠለ። ጳውሎስ እንዳለው፥ በእምነታቸው ለመብሰል የሚፈልጉ ሰዎች ዕድገታቸው እንዳይቋረጥም መሻት አለባቸው።

ጳውሎስ በፊልጵስዩስ ክርስቲያኖች ላይ የብሉይ ኪዳን ሕግጋትን የሚጭኑትን አይሁዳውያን ክርስቲያኖች ያስጠነቅቃቸዋል። ጳውሎስ እነዚህን አይሁዶች አስመልክቶ ሲናገር የፊልጵስዩስን አማኞች፥ «ከውሾች ተጠበቁ ከሐሰተኛም መገረዝ ተጠበቁ» ይላቸዋል። አይሁዶች በራሳቸውና የእግዚአብሔር ምርጥ ሕዝብ በመሆናቸው ይመኩ ነበር። አሕዛብን «ውሾች» እያሉ ይጠሩ ነበር። ጳውሎስ ግን ራሳቸውን ውሾች ይላቸዋል። በእግዚአብሔር ዓይን እውነተኞቹ የእግዚአብሔር ምርጥ ሕዝብ በክርስቶስ የሚያምኑት ሲሆኑ፥ ውሾቹ ደግሞ እነርሱ ነበሩ። በግርዘታቸው የተመኩት አይሁዶች ያልተገረዙ ሲሆኑ፥ ክርስቲያኖች ግን የተገረዙ ሆኑ። እግዚአብሔር የሚመለከተው የብልትን መቆረጥ ሳይሆን፥ በክርስቶስ የሚያምነውን ውስጣዊ ልብ ነውና።

ከዚያም ጳውሎስ እንደ አይሁዳውያን ያሉ ሰዎች ስለሚመኩባቸው ውጫዊ ነገሮች የተረዳውን ያካፍላል። አይሁዶች የእግዚአብሔር ምርጥ ሕዝብ፥ የአብርሃም ልጆች፥ የብሉይ ኪዳንና ፈሪሳውያን የሚከተሏቸውን ልማዶች በመከተላቸው ይመኩ ነበር። ጳውሎስ ከክርስቶስ ጋር ከመገናኘቱ በፊት እነዚህ ነገሮች ሁሉ እንደነበሩት ይናገራል። እርሱ ከቢንያም ነገድ የተወለደ አይሁዳዊ ነበር። የቢንያም ነገድ በጣም ከተከበሩት ነገዶች አንዱ ነበር። በዚህ ጊዜ ብዙ አይሁዶች ከየትኛው ነገድ እንደተወለዱ ባያውቁም፥ ጳውሎስ ግን ያውቅ ነበር።) እርሱ ከዕብራዊም ዕብራዊ ነበር። ይህም ጳውሎስ የግሪክን ባሕልና ቋንቋ ለመከተል ያልፈለገ አይሁዳዊ መሆኑን ያሳያል። ጳውሎስ ከብሉይ ኪዳን ሕግጋት በተጨማሪ የሃይማኖት መሪዎች ያወጡትን ሕግጋት ጠንቅቆ የጠበቀ ፈሪሳዊ ነበር። በአይሁዶችም እንከን እንደሌለው ሰው ይቆጠር ነበር። ጳውሎስ ቀጥተኛ አይሁዳዊ በመሆኑ ቤተ ክርስቲያንን ያሳድድ ነበር። ጳውሎስ ከክርስቶስ ጋር ከመገናኘቱ በፊት ተወዳዳሪ የሌለው ቆፍጣና አይሁዳዊ ነበር። (ይህ በእኛ ዘመን ከተከበረ ጎሳ እንደ መወለድ፥ የታዋቂ ወንጌላዊ ልጅ እንደ መሆን፥ የታላቅ ቤተ ክርስቲያን አባል እንደ መሆንና ከዝነኛ የምዕራባውያን ሴሚናሪ የሥነ መለኮት ዲግሪ እንደ ማግኘት ነበር።)

ከእነዚህ ነገሮች የትኞቹም ለጳውሎስ ድነት (ደኅንነትን) አላስገኙለትም። በዘላለሙ መንግሥት፥ የተወለደበት ጎሳም ሆነ ሌሎች ውጫዊ ነገሮች ምንም ጥቅም አይኖራቸውም። ዋናው ነገር ከክርስቶስ ጋር ያለው ግንኙነት ነበር። ስለሆነም ጳውሎስ በክርስቶስ እውቀት በማደግ፥ በመዳኑ ደስ በመሰኘትና በክርስቶስ ከማመን ባገኘው ጽድቅ መርካትን መረጠ። ጳውሎስ ክርስቶስን ከሙታን ያስነሣውን ኃይል ለመለማመድ፥ ለወንጌል በመሠቃየት ክርስቶስን ለመምሰል፥ በእምነት ለመጽናትና እንደ ክርስቶስ ከሞት ለመነሣት ነበር የፈለገው።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) መንፈሳዊ ጠቀሜታ የሌሏቸውና አንዳንድ ጊዜ ክርስቲያኖች የሚመኩባቸው ሥጋዊ ነገሮች ምን ምንድን ናቸው? ለ) ጳውሎስ ያተኮረባቸው ነገሮች ለዘላለማዊ ሕይወት እጅግ ጠቃሚዎች የሚሆኑት እንዴት ነው? ሐ) የተመካህባቸው አንዳንድ ውጫዊ ነገሮች ምን ምንድን ናቸው? መ) እነዚህ ነገሮች በሕይወትህ እውን ይሆኑ ዘንድ ምን ልታደርግ ትችላለህ?

እንደ ጳውሎስ ያሉ ታላላቅ መሪዎች ፍጹማን ናቸው ማለት ሊዳዳን ይችላል። እኛ ምን ያህል ደካሞች እንደሆንን እናውቃለን። የኃጢአት ተፈጥሯችን እንደ ጎሳችን፥ ቤተሰባዊ ውርሳችን፥ ትምህርታችን፥ ሀብታችን፥ ወዘተ… ካሉት ውጫዊ ነገሮች ክብርን ሊያገኝ እንደሚሻ እንረዳለን። ሁኔታዎች በማይመቻቹበት ጊዜ እድገታችንን ለማቋረጥም እንፈቅዳለን። ስለሆነም ጳውሎስ እርሱም እንደ እነርሱው መሆኑን ለፊልጵስዩስ ክርስቲያኖች ገልጾላቸዋል። ፍጹም ባይሆንም እድገቱን ለመቀጠል ይጥር ነበር። የሕይወቱን ዓላማ አካፍሏቸዋል። ባለው መንፈሳዊ ይዞታ ሳይረካ ለማደግ የሚፈልግ ሰው ነበር። ጳውሎስ የግሪክን የአትሌቲክስ ውድድሮች ምሳሌነት በመጠቀም የሕይወቱን ውስጣዊ ፍላጎት ገልጾላቸዋል። ይህ ለጳውሎስ ቀላል ባይሆንም ሩጫውን ለማሸነፍ እንደሚፈልግ ተወዳዳሪ ወደ ፊት ሊገሰግስ ፈለገ። «ስለ እርሱ በክርስቶስ ኢየሱስ የተያዝሁትን ያን ደግሞ እይዛለሁ ብዬ እፈጥናለሁ።» ይህን ሲል ጳውሎስ ክርስቶስ የሚፈልግብኝን ሁሉ እሆናለሁ ማለቱ ነበር።

ጳውሎስ ቀደም ሲል ብዙ አብያተ ክርስቲያናትን በተከለባቸው ድሎቹና ከመዳኑ በፊት ብዙ ክርስቲያኖችን በገደለባቸው ጸጸቶች ላይ ከማተኮር ይልቅ ወደፊት አሻግሮ በመመልከት ክርስቶስ እንዲሆን የሚፈልገውን ስለመሆን ያልማል። ይህም «መዘርጋት» እና «መፍጠን» ሲል የገለጻቸውን ታላላቅ ጥረቶች ጠይቆታል። ጳውሎስ የፈለገው የሕይወትን ሩጫ በሚገባ ለመሮጥና በመንግሥተ ሰማይ ክርስቶስ የሚሰጠውን ሽልማት ለመቀበል ነበር። ጳውሎስ በሕይወቱ መጨረሻ ላይ፥ «መልካሙን ገድል ተጋድዬአለሁ፤ ሩጫውን ጨርሼአለሁ፤ ሃይማኖትን ጠብቄአለሁ። ወደፊት የጽድቅ አክሊል ተዘጋጅቶልኛል። ይህንም ጻድቅ ፈራጅ የሆነው ጌታ ያን ቀን ለእኔ ያስረክባል። ደግሞም መገለጡን ለሚወዱ ሁሉ እንጂ ለእኔ ብቻ አይደለም» ሊል ችሏል (2ኛ ጢሞ. 4፡7-8)።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) እግዚአብሔር የሕይወትህ ዓላማ ምን እንደሆነ እንዲያሳይህ በጸሎት ጠይቅ። በልብህ ከምንም ነገር በላይ የምትፈልገው ምንድን ነው? ያንተ የሕይወት ዓላማ ከጳውሎስ ጋር ሲነጻጸር ምን ይመስላል? ለ) የሕይወትህ ዓላማ ምን እንዲሆን እንደምትፈልግ በጥቂት ዓረፍተ ነገሮች ግለጽ። (ለመሆንና ለማድረግ የምትፈልጋቸው ነገሮች ምን ምንድን ናቸው?) ሐ) ከዚያ ግብ ላይ ለመድረስ ልትወስዳቸው የሚገቡ ዝርዝር እርምጃዎች ምን ምንድን ናቸው? መ) ግብህ ተግባራዊ ይሆን ዘንድ በሕይወትህ ውስጥ ልታካሂዳቸው የሚገቡህ ለውጦች ምን ምንድን ናቸው?

ሰዎች ምሳሌዎችን (ሞዴሎችን) ይፈልጋሉ። ወጣቶች የስፖርት፥ የፊልም ወይም የሙዚቃ ከዋክብትን ያዩና እንደ እነርሱው ለመሆን ይፈልጋሉ። የእነዚህ ወጣቶች እሴቶች በሚያደንቋቸው ሰዎች ተጽዕኖ ሥር ይወድቃሉ። እግዚአብሔር የሚፈልገን ዓይነት ሰዎች ሆነን ለማደግ የሕይወትን ሩጫ ለማካሄድ መልካም ምሳሌዎች የሚሆኑንን ሰዎች መከተል ይኖርብናል። እዚህ ላይ መልካም ምሳሌዎችን መምረጡ አስፈላጊ ነው። የፊልጵስዩስ አማኞች ክርስቲያኖች ነን የሚሉትን አይሁዳውያን ለምሳሌነት ቢመርጧቸው ኖሮ ጠቀሜታ በሌላቸው ውጫዊ ጉዳዮች ላይ ያተኩሩ ነበር። ነገር ግን ትክክለኛ ምሳሌዎችን ከመረጡ ክርስቶስን እንዴት ሊከተሉ እንደሚችሉ በተግባራዊ መንገድ ያያሉ። ስለሆነም ጳውሎስ ራሱንና ውድድሩን በጥሩ ሁኔታ የሚሮጡትን ሌሎች የቤተ ክርስቲያን መሪዎች እንዲከተሉ አበረታቷቸዋል።

ጳውሎስ ብዙ ክርስቲያኖች በጥሩ ሁኔታ ጀምረው በሚያሳዝን መልኩ የመስቀሉ ጠላቶች እንደሚሆኑ ያውቅ ነበር። እንደ መንፈሳዊ ባሕርይ፥ ክርስቶስን ማገልገል፥ በሕይወታቸው፥ በባሕሪያቸውና በተግባራቸው ለሚያስከብሩት ሰዎች ክርስቶስ በሚሰጣቸው ሽልማቶች ላይ እንደ ማተኮር፥ ዓለም እንደ መልካምና ስኬት አድርጋ የምትመለከታቸውን ነገሮች ይከተላሉ። ብዙ ሰዎች እንደ ዓለማዊ ዝና፥ ጥሩ ምግብ፥ ሀብት፥ ጥሩ ቤት ባሉና ለኃጢአት ተፈጥሯቸው በሚመቹ ነገሮች ይሳባሉ። ነገር ግን ፍጻሜያቸው ጥፋት ነው።

ጳውሎስ የፊልጵስዩስ አማኞች የእግዚአብሔር ልጆች እንደ መሆናቸው፥ ቀዳሚው ዜግነታቸውና ዘላለማዊው ቤታቸው መንግሥተ ሰማይ እንደሆነ ያስታውሳቸዋል። የሮም ዜግነት ሊኖራቸውና በሮም ከተማ ውስጥ ሊኖሩ ቢችሉም፥ ይህ ምድራዊ ሕይወት ጊዜያዊ በመሆኑ የሰማያዊ መንግሥት ዜግነትን ያህል ጠቃሚ አልነበረም። በዚህ ምድራዊ ሕይወት የኢትዮጵያ ዜጎች ሆነን ስንኖር፥ ሰውነታችን ቀስ በቀስ ይዳዳከምና ይሞታል። ነገር ግን ክርስቶስ ከሞት ሲያስነሣን ለሰማዩ ዘላለማዊ ቤት የሚስማማ የተለወጠ አካል ይኖረናል። ከዚያም ከሞት የተነሣውን የክርስቶስን አካል የሚመስል አካል እንለብሳለን።

የውይይት ጥያቄ፡– ክርስቲያኖች ከምድራዊ ቤታችንና ዜግነታችን በላይ ስለ ሰማያዊ ዜግነታችንና ቤታችን በይበልጥ ብናስብ፥ በሕይወታችን ውስጥ ምን ዓይነት ለውጦች ይፈጸማሉ?

ጳውሎስ ምድራዊ ዜግነታችንን በሚያንጸባርቁት ነገሮች ላይ እንዳንሳተፍ አለማዘዙን ማጤኑ መልካም ነው። እርሱ የሚለው ሁለት ዜግነቶች እንዳሉን ነው። እነዚህም ምድራዊና ሰማያዊ ዜግነቶች ናቸው። ለሁለቱም ዜግነቶች የምናሟላቸው ግዴታዎች አሉ። እግዚአብሔር እንተን ኢትዮጵያ ውስጥ አስቀምጦሃል። እዚህ ኢትዮጵያዊ ዜግነት አለህ። ስለሆነም የተወሰኑ ግዴታዎች አሉብህ። ቀረጥ የመክፈል (ሮሜ 13፡6-7)፥ በማኅበራዊ ሥራዎች ውስጥ የመሳተፍ፥ ለጥሩ ተመራጮች ድምፅ መስጠት፥ አገርህ መልካም ኢኮኖሚያዊና ፍትሐዊ አቋም እንዲኖራት የመሥራት ኃላፊነት አለብህ። ክርስቲያኖች እንደ ዮሴፍና ዳንኤል በአገራቸው ውስጥ ለውጥ ለማምጣት ተጠርተዋል። ነገር ግን ምድራዊ ዜግነታችን አስፈላጊ እንደሆነ ሁሉ፥ ሰማይ ዘላለማዊ ቤታችን እንደሆነ ማስታወስ ይኖርብናል። የምናደርገው ማንኛውም ነገር ይህንን ዜግነት ማንጸባረቅ አለበት።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: