የቆላስይስ መጽሐፍ ዓላማ፣ ልዩ ባሕሪያት፣ መዋቅርና አስተዋጽኦ

፩. የቆላስይስ መጽሐፍ ዓላማ

የመጀመሪያው ዓላማ፡ በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ የተነሣውን የሐሰት ትምህርት መመከት። ጳውሎስ በኤፌሶን ካገለገለ ስምንት ዓመታት ያህል አልፈዋል። በዚህ ጊዜ በቆላስይስ ክርስቲያኖች እምነት ውስጥ መጠነኛ ለውጥ ተከስቷል። በክርስቶስ ላይ የነበራቸውን እምነት ባይክዱም፥ የይሁዲና በትንሹ እስያ የተለመዱ ፍልስፍናዎችን የቀየጡበት ይመስላል። ይህ የሌሎችን እምነቶች የመጨመር ተግባር ወንጌሉን ስለሚለውጥ አደገኛ ነው። ይህም የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የይሁዲነት እምነቶችን ከእምነቷ ላይ ከጨመረችበትና ብዙ የአፍሪካ ሃይማኖቶች በክርስትና እምነታቸው ላይ የአያት ቅድማያት ወይም የጥንቆላ ትምህርቶችን ከሚጨምሩበት ሁኔታ ጋር ተመሳሳይ ነው። የቆላስይስ አማኞች በእነዚህ ትምህርቶች ባይወሰዱም፥ ለቤተ ክርስቲያን አደገኛ ሊሆኑ የሚችሉትን ትምህርቶች መቀበል ጀምረው ነበር። ስለሆነም፥ ጳውሎስ የብዙ ሰዎች እምነት ከመበከሉ በፊት ይህንን የሐሰት ትምህርት መከላከሉ አስፈላጊ መሆኑን ተገነዘበ።

ጳውሎስ፥ ኤፌሶንን ከለቀቀ በኋላ ለሚከተሉት ስምንት ዓመታት፥ ሁለት ዓባይት የሐሰት ትምህርት ቡድኖች ቆላስይስን ሲያውኩ ነበር። ይህም የቆላስይስን ክርስቲያኖች ግራ አጋባቸው። የሐሰት አሰተማሪዎቹ የሚናገሩት ቀደም ሲል ጳውሎስ ያስተማረውን ዓይነት ትምህርት እንዳልሆነ ቢያውቁም እውነተኛው የትኛው እንደሆነ ለመረዳት አልቻሉም። በመሆኑም፥ አማኞቹ ስለዚህ ጉዳይ ከጳውሎስ ጋር እንዲነጋገር መሪያቸው የነበረውን ኤጳፍራን ወደ ሮም የሰደዱት ይመስላል። ጳውሎስም ሆነ ኤጳፍራ ወደ ቆላስይስ ተመልሰው የሐሰት ትምህርቱን በአካል ሊከላከሉ ስላልቻሉ፥ ጳውሎስ ይህንን መልእክት ለመጻፍ ተገደደ።

የቆላስይስን ቤተ ክርስቲያን ያውኩ የነበሩ የሐሰት ትምህርቶች ምን ምን ነበሩ? ጳውሎስ እነዚህን ትምህርቶች በስማቸው ባይጠቅስም አንዳንድ ትምህርቶቻቸውን ግን ገልጾአል። ጳውሎስ በዚህ መልእክቱ ሁለት ዓይነት የሐሰት ትምህርቶችን የሚጠቅስ ይመስላል። .

  1. ክርስቲያኖች የብሉይ ኪዳን ሕግጋትን እንዲከተሉ የፈለጉ አይሁዶች። ጳውሎስ እነዚህ አይሁዶች እንደ ምግብ፥ መጠጥ፥ የበዓል ቀናትን በመሳሰሉ ውጫዊ ደንቦች ላይ ያተኩሩ እንደነበረ ገልጾአል (ቆላ. 2፡16-17)። በግርዘት ላይም እንዲሁ አጽንኦት ይሰጡ ነበር (ቆላ. 2፡11)።
  2. የቀድሞውን የኖስቲሲዝም ትምህርት ይከተሉ የነበሩ አሕዛብ። ጳውሎስ የገለጻቸው የዚህ ፍልስፍና ትምህርቶች የሚከተሉትን ነገሮች ያካትታሉ።

ሀ. ከዓለም ነገሮች መራቅ (ቆላ. 2፡21-23)

ለ. መላእክትን ማምለክ (ቆላ. 2፡18)

ሐ. ክርስቶስ ፍጹም አምላክ እንዳልሆነ መገንዘብ (ቆላ. 1፡15-20፥2፡2-3፥ 9)

መ. መንፈሳዊ ሕይወት በሆነ ምሥጢራዊ እውቀት እንደሚገኝ የሚያስረዱ ትምህርቶች (ቆላ. 2፡18)

ሠ. በሰብአዊ ጥበብና ልማድ ላይ ማተኮር (ቆላ. 2፡4፥8)

ምሁራን የቆላስይስና የ1ኛ ዮሐንስ መልእክቶች ምን ያህል ኖስቲሲዝም ከተባለ የሐሰት ትምህርት ጋር እንደሚዛመዱ ይከራከራሉ። ኖስቲሲዝም ሐሰተኛ ትምህርት መሆኑ የታወቀው ከጳውሎስ ዘመን ከ100 ዓመታት በኋላ ነበር። ነገር ግን የኖስቲሲዝም መሠረታዊ ገጽታዎች የሆኑ አንዳንድ ነገሮች በጳውሎስና በዮሐንስ ዘመንም የነበሩ ይመስላል።

ኖስቲሲዝም የሚለው የግሪክ ቃል እውቀትን ያመለክታል። ይህም ለድነት (ደኅንነት) ልዩ እውቀት አስፈላጊ መሆኑን ያስተምራል። ይህ የሐሰት ትምህርት ሦስት ዐበይት ነገሮችን ያካትታል። እነዚህም፥ ሀ) የተፈጠረው ነገር ሁሉ ክፉ ነው። ለ) በክፉው ዓለምና በተቀደሰው አምላክ መሀል ምልጃን የሚያካሂዱ እንደ መላእክት ያሉ ልዩ ፍጥረታት አሉ። ሐ) ሰው የሚድነው በራሱ ልዩ እውቀት ነው የሚሉ ነበሩ።

ኖስቲኮች በእግዚአብሔርና በተፈጠረው ቁሳዊ ዓለም መካከል ብዙ ርቀት እንዳለ ያምናሉ። እግዚአብሔር ይህን ክፉ ዓለም አልፈጠረውም ይላሉ። ከዓለም ጋርም ምንም ዓይነት ቀጥተኛ ግንኙነት እያደርግም ሲሉ ያስተምራሉ። ነገር ግን ከእግዚአብሔር ሥራ ብዙ የመንፈሳዊ ፍጥረታት (መላእክት ወይም ትናንሽ አማልክት) ደረጃዎች እንዳሉና ከሁሉም አነስተኛ የሆነው መለኮታዊ አካል ከእግዚአብሔር ፈቃድ ውጭ ዓለምን እንደፈጠረ ያምናሉ። ስለሆነም ዓለምና በውስጧ ያለው ሁሉ ክፉ እንደሆኑ ያስባሉ። ሰው የዚህ ክፉ ዓለም አካል ነው። አንዳንድ ምሁራን ጳውሎስ «ዙፋናት፥ ጌትነት፥ አለቅነት፥ ሥልጣናት» ሲል እነዚህኑ መለኮታዊ አካላትን ማመልከቱ ነው ይላሉ (ቆላ. 1፡16፥ 2፡9፥ 15)።

ስለሆነም ኖስቲኮች ዓለምን ለሁለት ይከፍሏታል። የሚታየው የተፈጠረ ዓለም ክፉ ነው ይላሉ። መልካም የሆነው የመናፍስት ዓለም እንደሆነ ያምናሉ። የሰው ልጅ ከዚህ ክፉ የተፈጠረ ዓለም ወጥቶ ወደ መናፍስት ዓለም ሊገባ የሚችለው የግለሰቡ ነፍስ የመለኮታዊ ሕይወትን ብልጭታ ካገኘች ነው ይላሉ። ይህም የሚሆነው ሰውየው ልዩ ምሥጢራዊ እውቀት ሲያገኝ ነው። ይህ ምሁራዊ እውቀት አልነበረም። ነገር ግን ይህ አንድ ሰው ከእግዚአብሔር ጋር ግንኙነት ለማድረግ በሚሞክርበት ጊዜ የሚማረው እንደ ልዩ ስም ወይም ዜማ ያለ ነገር ነው። እንዲህ ዓይነት ልዩ እውቀት ያላቸው ሰዎች የምሥጢራዊ ማኅበራት አካል ነበሩ።

ኖስቲሲዝም በክርስትና ላይ በተጨመረ ጊዜ ትምህርቶቹ የወንጌልን እምነት በብዙ መንገዶች ጎድተዋል።

በመጀመሪያ፥ የክርስቶስን ደረጃ ዝቅ በማድረግ ሰዎች ከዚህ ክፉ ዓለም እንዲላቀቁ መንገድ እንደከፈተ አነስተኛ አምላክ ገልጾታል። ኖስቲኮች ክርስቶስ ከእግዚአብሔር አብና ከሌሎች ታላላቅ መንፈሳዊ አካላት ጋር እኩል እንዳልሆነ ያምናሉ። በእነርሱ ግምት እርሱ ከታናናሾቹ መለኮታዊ አካላት አንዱ ነው። ነገር ግን ክርስቶስ ዓለምን የፈጠሯት አነስተኛ አማልእክት የነበሯቸውን ዓይነት ክፉ ባሕርይ እንዳልያዘ ያስተምራሉ። ኖስቲኮች ክርስቶስ እውነተኛ ሰው ሆኖ እንደማያውቅ ይናገራሉ። ይህ ክፉ ያደርገው ነበር ይላሉ። ልክ እንደ መንፈስ ሰው መስሎ ታየ እንጂ እውነተኛ ሰው አልሆነም ይላሉ። አንዳንድ ኖስቲኮች ደግሞ የመለኮታዊ ክርስቶስ መንፈስ በጥምቀቱ ጊዜ ኢየሱስ በተባለው ሰው ላይ እንዳረፈና ከእምነቱ በፊት እንደተለየው ያስተምራሉ። ጳውሎስ ለዚህ ምላሽ ሲሰጥ ክርስቶስ ፍጹም አምላክና ከእግዚአብሔር አብ ጋር እኩል እንደሆነ አስረድቷል። ክርስቶስ ፍጹም ሰው እንደሆነም ገልጾአል (ቆላ. 1፡15፥ 19)።

ሁለተኛ፥ ኖስቲሲዝም በኃጢአትና በክርስቶስ የመስቀል ላይ ሞት አስፈላጊነት ላይ አጽንኦት አልሰጠም። ስለሆነም፥ የክርስቶስ ሞተ፥ መቀበርና መነሣት ጠቃሚ እውነቶች እንደሆኑ አይገነዘብም። የሚያስፈልገው ነገር ቢኖር የመለኮታዊ ሕይወት መሰጠትና ሰዎችን ከእስራት ያስለቀቀ «ምሥጢራዊ» እውቀት ብቻ ነበር። ጳውሎስ ግን ያዳነን የክርስቶስ የመስቀል ላይ ሞት እንጂ ልዩ እውቀት እንዳልሆነ አስረድቷል (ቆላ. 1፡13-14፥ 21-22፥ 2፡13-15)።

ሦስተኛ፥ አንዳንድ ኖስቲኮች የተፈጠረው ነገር ሁሉ ክፉ እስከሆነ ድረስ ከማኅበራዊ ሕይወት መራቅ እንደሚሻል ያስተምሩ ነበር። ስለሆነም ወደ ገዳማት መግባት፥ ብዙ አለመመገብ፥ በወለል ላይ መተኛት እና የመሳሰሉት ጠቃሚ እንደሆኑ ያስተምሩ ነበር። ይህም አንድ ሰው የክፉ ዓለምን ተጽዕኖ እንዲገድብ ይረዳዋል ተብሎ ይታሰባል። ሰውነታቸውን በመቅጣት ነፍሳቸውን ለማፋፋት ፈለጉ። ይህ ትምህርት በቆላስይስ ቤተ ክርስቲያን ላይ ተጽዕኖ እያደረሰ ነበር። ጳውሎስ እነዚህ ነገሮች የሰውን የኃጢአት ተፈጥሮ ሊያሸንፉ እንደማይችሉና ምንም ዓይነት ጠቀሜታ እንደሌላቸው አስረድቷል (ቆላ. 2፡20-23)።

አራተኛ፥ ሌሎች የኖስቲክ አስተማሪዎች እንደ ሰዎች በምናከናውናቸውና በመንፈሳዊ ባሕሪያት መካከል ምንም ዓይነት ግንኙነት እንደሌለ ያስተምሩ ነበር። ክርስቲያኖች እንዳሻቸው ሊኖሩ እንደሚችሉ ይናገሩ ነበር። ወሲባዊ ኃጢአት ውስጣዊ ሕይወታችውን ስለማይነካ ስሕተት እንዳልሆነ ያስተምሩ ነበር። የ1ኛ ዮሐንስ መልእክት ይህንን ትምህርት ያፋልሰዋል። በቆላስይስ 3፡5ም ስላለው ጉዳይ ፍንጭ ተሰጥቷል። ጳውሎስ ለዚህ ለአሮጌው ሕይወት እንደሞትንና አዲስ ባሕርይ እንደ ለበስን ገልጾአል። ይህም አዲስ ባሕርይ ወደ አዳዲስ ተግባራት የሚመራ ነው (ቆላ. 3፡1-17)።

አምስተኛ፥ በልዩ እውቀት ላይ የተደረገው አጽንኦት በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የመደብ ደረጃ አስከተለ። ልዩ እውቀት (ይህን ምሥጢራዊ ቃል ወይም ሐረግ) ያላቸው ሰዎች ከሌሎች የተሻልን ነን ብለው አሰቡ። ጳውሎስ ዋናው ምሥጢር አንድ ብቻ መሆኑን ያስረዳል። ይህም እግዚአብሔር ሰዎች በክርስቶስ በማመን ሊድኑ እንደሚችሉ በጳውሎስ በኩል ማስታወቁ ነበር። ምንም ተጨማሪ እውቀት አያስፈልግም። አንድ ሰው ለወንጌል ምላሽ መስጠቱ ብቻ ይበቃዋል። ሁሉም «ጥበብና እውቀት» የሚገኘው ከክርስቶስና ስለ እርሱ ከሚናገሩ ትምህርቶች ብቻ ነው (ቆላ. 1፡25-2፡4)።

ዛሬም የኖስቲኮች ዓይነት አስተሳሰብ በአንዳንድ ክርስቲያኖች ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል። ለምሳሌ፥ በአንዳንድ ክርስቲያናዊ ቡድኖች ጋብቻ እንደ ክፉ ነገር ይታያል። አንዳንዶች ደግሞ ከማኅበረሰቡ ተነጥለው በዋሻዎች ውስጥ ይኖራሉ። በቅርቡ ደግሞ ክርስቲያን በሥጋው የሚያደርገው ነገር ምንም ችግር እንደማያስከትል እየተነገረ ነው። አንድ ሰው ልቡን በአምልኮ እስካነጻ ድረስ የወሲብ፥ የስርቆት ወይም ሌላም ዓይነት ኃጢአት ቢፈጽም ምንም እንዳልሆነ ይናገራል። የይሖዋ ምስክሮች ስለ ክርስቶስ የሚያምኑትም ከኖስቲሲዝም ጋር ተመሳሳይነት አለው። ሕልሞችን፥ ራእዮችን ወይም በልሳን መናገርን አጥብቀው የሚከተሉ ሰዎችም «ልዩ እውቀት» ወይም «ልዩ ልምምድ» የመፈለግና የእነርሱ ዓይነት ልምምዶች የሌሏቸውን ሰዎች ዝቅ አድርጎ የመመልከት ዝንባሌ ይታይባቸዋል።

የውይይት ጥያቄ፡– ከኖስቲክ የመነጩትንና ዛሬ ተጽዕኖ እያደረሱ ያሉትን ሌሎች ትምህርቶች በምሳሌነት ጥቀስ።

የውይይት ጥያቄ፡- ቆላስይስ 1፡14-22 እንብብ። ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ የተነገሩትን ነገሮች በሙሉ ዘርዝር። እነዚህ እውነቶች በሕይወታችን ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድሩት እንዴት ነው?

ሁለተኛው ዓላማ፡- የቆላስይስ መጽሐፍ ክርስቶስ ማን እንደሆነ ያብራራል። የኖስቲክን የሐሰት ትምህርት ፉርሽ ለማድረግ የሚቻለው ስለ ክርስቶስ ማንነት ግልጽ ትምህርት በማቅረብ ነበር። ጳውሎስ ክርስቶስ ከአነስተኛ አምላክ በላይ መሆኑን ያስረዳል። እርሱ ፍጹም አምላክና ከአብ ጋር እኩል ነው። ጳውሎስ የክርስቶስን የከበረ ስፍራ በብዙ መንገዶች ያብራራል።

ሀ. ክርስቶስ የማይታይ አምላክ አምሳል ነው። ክርስቶስ በሁሉም ነገር ከእግዚአብሔር አብ ጋር አንድ ዓይነት ነው። እርሱ ከማይታየው አምላክ ጋር እኩል ነው (ቆላ. 2፡9)።

ለ. ክርስቶስ የፍጥረት ሁሉ በኩር ነው። ክርስቶስን ከፍጥረት ሁሉ በኩር ብሎ በመጥራቱ ጳውሎስ የክርስቶስን ሥጋዊ ልደት ሳይሆን ከማንኛውም ፍጡር የላቀውን የከበረ ስፍራውን እያመለከተ ነበር። እንዲያውም ጳውሎስ ክርስቶስ ሁሉንም ነገር እንደ ፈጠረና ፍጥረታት በሙሉ ሊያከብሩት እንደሚገባ አስረድቷል (ቆላ. 1፡15-16)።

ሐ. ክርስቶስ ሁሉንም እንዳያያዘም ተገልጾአል (ቆላ. 1፡17)። ክርስቶስ የአጽናፈ ዓለሙ ማጣበቂያ ነው። አጽናፈ ዓለሙ ጉዞውን እንዲቀጥል፥ ሕይወት ወደፊት እንዲገሠግሥ፥ ታሪክ ወደፊት እንዲሄድ፥ ፀሐይ ሁሌም እንድትወጣ፥ ወዘተ… የሚያደርገው እርሱ ነው።

መ. ክርስቶስ ለጠፋው ሰብአዊነት መፍትሔ ነው። ከጨለማችንና ከኃጢአታችን አውጥቶ በብርሃን መንግሥት ውስጥ የሚያስቀምጠን እርሱ ነው (ቆላ. 1፡13-14)።

ሠ. ክርስቶስ የቤተ ክርስቲያን ራስ ነው። የኤፌሶን መልእክት በክርስቶስ ራስነት ሥር ስለምትተዳደረው ቤተ ክርስቲያን ሲያስተምር፥ የቆላስይስ መልእክት ግን የቤተ ክርስቲያን ራስ በሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ያተኩራል።

ረ. ክርስቶስ በዩኒቨርስ ውስጥ ያለው ኃይልና ሥልጣን ሁሉ የበላይ ገዥ ነው (ቆላ. 2፡10)

ሰ. ክርስቶስ የጥበብና የእውቀት ሁሉ ምንጭ ነው (ቆላ. 2፡3)

ሸ. ክርስቶስ ክፉ ኃይላትን ሁሉ አሸንፎአል (ቆላ. 2፡15)።

ቀ. ክርስቶስ በአብ ቀኝ እየገዛ ነው (ቆላ. 3፡1)።

ሦስተኛ ዓላማ፡ ጳውሎስ ክርስቲያኖች ወደ ቀድሞው የአረማዊነት አኗኗራቸው እንዳይመለሱ (ቆላ. 3፡5) እና በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ያላቸውን እምነት በሚያንጸባርቅ መልኩ እንዲመላለሱ ያስጠነቅቃቸዋል።

የውይይት ጥያቄ፡– ዛሬ ክርስቲያኖች እነዚህን ትምህርቶች ማወቅና ከሕይወታችን ጋር ማዛመድ ያለብን ለምንድን ነው?

፪. የቆላስይስ ልዩ ባሕርያት

  1. ቆላስይስ ከኤፌሶን ጋር በጣም ይመሳሰላል። በቆላስይስ መልእክት ውስጥ ከሚገኙት ጥቅሶች ከግማሽ የሚበዙት ከኤፌሶን ጋር ተመሳሳይ ናቸው። ሁለቱንም መልእክቶች ያደረሳቸው ቲኪቆስ ነው (ኤፌ. 6፡21፤ ቆላ. 4፡7)። ሁለቱም እንደ ምሥጢር፥ ጥበብ፥ እውቀትና አለቅነት ዓይነት ቃላትን ይጠቀማሉ። ሁለቱም በክርስቶስ ማንነትና ከቤተ ክርስቲያን ጋር ባለው ግንኙነት ላይ ያተኩራሉ። ኤፌሶን ስለ ቤተ ክርስቲያንና ከክርስቶስ ጋር ስለተዛመደችበት ሁኔታ ሲያስተምር፥ ቆላስይስ ግን በክርስቶስና ከቤተ ክርስቲያን ጋር ስለተዛመደበት ሁኔታ ያብራራል። ሁለቱም መልእክቶች ከክርስቶስ ጋር ያለን ግንኙነት በማኅበረሰቡ ውስጥ ባለን ግንኙነት ላይ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር ያስተምራሉ።
  2. ቆላስይስ ብዙውን ጊዜ ከእግዚአብሔር ጥበብ ጋር በሚጋጩ የሰው ፍልስፍናዎችና ጥበብ ላይ እንዳናተኩር ያስጠነቅቃል (ቆላ. 2፡8)። ክርስቲያኖች ሁልጊዜም በትምህርት ቤት ውስጥ የሚማሩትን በእግዚአብሔር ቃል መገምገም አለባቸው። ግጭት በሚኖርበት ጊዜም የእግዚአብሔር ቃል የሚለውን እንጂ ትምህርት ወይም ባሕል የሚለውን ማመንና መከተል የለባቸውም።

፫. የቆላስይስ መዋቅር

እንደ ሌሎች የጳውሎስ መልእክቶች ሁሉ ቆላስይስ በሁለት ዐበይት ክፍሎች ተካፍሏል። የመጀመሪያው ክፍል (ቆላ. 1-2) አስተምህሯዊ ሲሆን፥ ስለ ክርስቶስ ማንነት ይናገራል። ጳውሎስ የክርስቶስን ታላቅነት ካሳየ በኋላ (ቆላ. 1፡13-27)፥ ስለ ክርስቶስና እርሱን ስለ መከተል የሚያወሳውን እውነት ስለሚያጣምሙ የሐሰት አስተማሪዎች ይናገራል (ቆላ. 2፡8-23)።

ሁለተኛው ክፍል (ቆላ. 3-4)። የክርስቶስ ተከታዮች እንዴት እግዚአብሔርን በሚያስከብር መልኩ ሊኖሩ እንደሚገባቸው ያስተምራል። በግለሰብ ደረጃም ሆነ እንደ ክርስቶስ አካላት ከኃጢአት መለየት አለብን። እንዲሁም፥ ክርስቶስ ራሳችን መሆኑን በሚያሳይ መልኩ በቤታችንና በማኅበረሰቡ ውስጥ እርስ በርሳችን መዛመድ አለብን።

፬. የቆላስይስ አስተዋጽኦ

  1. መግቢያ (ቆላ. 1፡1-14)
  2. ጳውሎስ ለክርስቲያኖች ስለ ክርስቶስ ያስተምራል (ቆላ. 1፡15-2፡23)።

ሀ. ክርስቶስ እንደ አብ ሁሉ ከተፈጠሩት ነገሮች የበለጠ ነው (ቆላ.1፡15-23)

ለ. ክርስቶስ ጳውሎስ ያስተማረው የወንጌል እምብርት ነው (ቆላ. 1፡24-2፡5)።

ሐ. አማኞች ከንቱ የሆነውን የሰው ትምህርት ከመከተል ይልቅ በክርስቶስ ላይ ማተኮር አለባቸው (ቆላ. 2፡6-23)።

  1. ጳውሎስ ክርስቲያኖች እንዴት ለክርስቶስ ሊኖሩ እንደሚገባቸው ያስተምራል (ቆላ. 3፡1-4፡6)።

ሀ. እንዴት የተቀደሰ ሕይወት እንደሚኖሩ (ቆላ. 3፡1-17)

ለ. በቤትና በሥራ ቦታ እንዴት መንፈሳዊ ግንኙነቶችን እንደሚያደርጉ (ቆላ. 3፡18–4፡1)

ሐ. እግዚአብሔርን እንዴት ማስደሰት እንደሚቻል የሚያስረዳ የመጨረሻ ትእዛዝ (ቆላ. 4፡2-6)

  1. ማጠቃላያ (ቆላ. 4፡7-18)

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: