ጳውሎስ አማኞች የተቀደሰ፣ በፍቅር የተሞላና ሰላማዊ ሕይወት እንዲኖሩ ያበረታታቸዋል (1ኛ ተሰ. 4፡1-12)

ጢሞቴዎስ ለጳውሎስ ስለ ተሰሎንቄ አማኞች ጽናት በገለጸ ጊዜ፥ አንዳንድ አሳሳቢ ጉዳዮች እንደነበሩም መናገሩ አልቀረም። ጳውሎስ በዚህ የአንደኛ ተሰሎንቄ የመጨረሻ ክፍል ውስጥ እነዚህን ጉዳዮች ይዳስሳል። የጳውሎስ ቀዳማዊ ዓላማ አማኞች እግዚአብሔርን በሚያስደስት መልኩ እንዲኖሩ ነበር።

እግዚአብሔር ባዳነን ጊዜ ከኃጢአት ብቻ ነፃ አላወጣንም። እርሱ እንቀደስ ዘንድ አድኖናል።

የውይይት ጥያቄ፡- መቀደስ ማለት ምን ማለት ነው? ይህን ቃል ከመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት ውስጥ አንብብ።

የመቀደስ መሠረታዊ ፍች መለየት ማለት ነው። በክርስቶስ አምነን በምንድንበት ጊዜ እንደ ተቀደስን ቢገለጽም፥ እግዚአብሔር በልባችን ውስጥ የፈጸመውን ተግባር በሚያንጸባርቅ መልኩ የተቀደሰ ሕይወት እንድንኖር ይፈልጋል። ዛሬ እግዚአብሔር በሕይወታችን ውስጥ ከሚፈጽማቸው ነገሮች አንዱ ባለማቋረጥ እኛን ቅዱሳን ማድረግ ነው። የእግዚአብሔር የመጨረሻ ዓላማ ከክርስቶስ ጋር በምንገናኝበት ጊዜ እንድንከብርና የክርስቶስን ያህል ቅድስና እንዲኖረን ነው (1ኛ ዮሐ 3፡2)።

ጳውሎስ የተሰሎንቄ አማኞች አጽንኦት ሊሰጡ የሚገቧቸውን የተለያዩ የክርስቲያናዊ አኗኗር ገጽታዎች ይዳስሳል።

ሀ) ወሲባዊ ንጽሕና፡- ልክ እንደኛው የተሰሎንቄ አማኞችም ከወሲባዊ ንጽሕና ጋር የተያያዙ ችግሮች ነበሩባቸው። ቀደም ሲል በጣኦት አምልኳቸው ውስጥ ብዙውን ጊዜ ከሌሎች ሰዎች ጋር ወሲባዊ ግንኙነቶችን ይፈጽሙ ነበር። ወደ ክርስትና ሕይወት ሲመጡ ይህንኑ ልምምድ ማቆሙ ቀላል አልሆነላቸውም። ጳውሎስ ግን ሰውነታቸውን ለመቆጣጠርና በንጽሕና ለመመላለስ ቁርጥ ውሳኔ እንዲያደርጉ ያበረታታቸዋል። ዛሬ ይህንን ትምህርት የማይታዘዝና ሌሎችም ንጹሕ ሕይወት እንዳይኖሩ የሚያስተምር ማንም ቢሆን ከእግዚአብሔር ጋር ፊት ለፊት ተጋፍጧል። ይህም እግዚአብሔር ለእያንዳንዱ አማኝ የሰጠውን የመንፈስ ቅዱስ ድምጽ አለመስማትና አለማክበር ይሆናል። እግዚአብሔርን የሚያሳስበው ከግል ሕይወታችን ይልቅ እርሱን የምናመልክበት ሁኔታ ነው ብለን የምናስብ ከሆነ ተሳስተናል። አንዳንድ አማኞች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እንደሚያስተምሩት እግዚአብሔር ለወሲባዊ ንጽሕናችን ግድ እንደሌለው የሚያሳይ ሐሳብ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አይገኝም። ቅድስናና ንጽሕና በጣም አስፈላጊዎች ናቸው። ከጋብቻ ግንኙነት ውጪ የሚፈጸም ማንኛውም ወሲብ በእግዚአብሔር ላይ የሚፈጸም ኃጢአት ነው። የወሲቡን ተግባር የምናጋራውም ሰው የዚሁ በደል ተካፋይ ይሆናል።

ለ) የፍቅር ግንኙነቶች፡- የተሰሎንቄ አማኞች ቀደም ሲል ያደርጉ እንደነበረው ለእርስ በርሳቸው የነበራቸውን ፍቅርና መተሳሰብ አጽንተው  ሊይዙ ይገባ ነበር።

ሐ) ተግቶ መሥራት፡- አማኞች ተግተው ሊሠሩና የጭምትነት ሕይወት ሊኖሩ ይገባቸው ነበር። ይህም ለሌሎች የሚሆን ምሳሌያዊ ሕይወት ለመኖር ያስችላቸዋል። የተሰሎንቄ አማኞች ክርስቶስ ቶሎ ይመለሳል ብለው በማሰባቸው ይመስላል ተግተው ከመሥራት ይቆጠቡ ነበር። ከዚህም የተነሣ የኢኮኖሚ ችግሮችን ለመጋፈጥ ተገደዱ። ይህም ብቻ አልነበረም። እርስ በርሳቸው በተለያዩ ችግሮች ውስጥ ለመግባትና ኃጢአትን ለመሥራት ተገድደዋል። ስለሆነም ጳውሎስ ወደ ሥራቸው እንዲመለሱና ሰዎች ክርስቲያኖችን ያከብሯቸው ዘንድ ምሳሌያዊ ሕይወት እንዲኖሩ ያበረታታቸዋል። ብዙ ሰዎች ሥራ ክፉ ነው የሚል ባሕላዊ አመለካከት አላቸው። ስለሆነም ብዙ ወጣቶች ወደ ትምህርት ቤት መሄድ ከጀመሩ በኋላ በቤት ተገቢውን ሥራ ከማከናወን ይቆጠባሉ። የእርሻም ሆነ ሌሎች ማናቸውንም ሥራዎች ከማከናወን ይሰንፋሉ። ጳውሎስ ይህንን ሲል ከትምህርት ደረጃችሁ ጋር የሚመጣጠን ሥራ ካገኛችሁ ማለቱ አልነበረም። ይልቁንም ማንም ሰው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ያጠናቀቀም ቢሆን ያገኘውን ሥራ ማከናወን እንዳለበት ያስገነዝባል። ይህ ለሌሎች ጥሩ ምሳሌ በመሆኑ የክርስቶስን ስም ያስከብራል።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) እነዚህን ሦስት እውነቶች ለወጣቶች ማስተማር አስፈላጊ የሚሆነው ለምንድን ነው? ለ) ብዙ ወጣቶች ራሳቸውን ዝቅ አድርገው ትናንሽ ሥራዎችን የማይሠሩት ለምንድን ነው? ሐ) ዛሬ ጳውሎስ በኢትዮጵያ ላሉት ወጣቶች ደብዳቤ የሚጽፍ ቢሆን ኖሮ ክርስቶስን ስለሚያስከብር ሕይወት ምን ዓይነት ተግባራዊ ነጥቦችን ይጠቅስላቸው ነበር።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: