ጳውሎስ የኋላ ኋላ አሳዳጆቻቸው ክርስቶስ በሚመለስበት ጊዜ ለፍርድ እንደሚጋለጡ በማሳሰብ በስደት ላይ ያሉትን አማኞች ያበረታታቸዋል (2ኛ ተሰ. 1:1-12 )

እንግዳ ወርቅ ተወልዶ ያደገው በገጠሪቱ ኢትዮጵያ ውስጥ ነበር። ቤተሰቦቹ ትምህርት ጠቃሚ መሆኑን በመገንዘባቸው ብዙ ጥረት አድርገው ትምህርት ቤት አስገቡት። ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ካጠናቀቀ በኋላ ሥራ መፈለግ ጀመረ። ያገኘው ሥራ ግን አነስተኛና ዝቅተኛ ክፍያ የሚከፈልበት ነበር። እርሱ ግን ይህ ለክብሬ የሚመጥን ሥራ አይደለም ብሎ በማሰቡ ቀኑን ሙሉ ሲንቀዋለል ቆሞ ይውል ጀመር። የግብርና ሥራ ለማከናወንም የትምህርት ደረጃው እንደማይፈቅለት አሰበ። ወላጆቹን ለመጎብኘት ወደ እገር ቤት በተመለሰ ጊዜ በእርሻ ፥ በአረምና በእንጨት ፈለጣ ዘመዶቹን ለመርዳት አልፈለገም። ነገር ግን ወላጆቹ የሚያስፈልጉትን ነገሮች እንዲያሟሉለት ጠበቀ። ቀኑን ሙሉ ከጓደኞቹ ጋር ሲነጋገርና ከቤት ወደ ቤት እየዞረ ቡና ሲጠጣ ይውላል። እንግዳ ወርቅ ምንም ሥራ ስላልነበረው ብዙ ትርፍ ሰዓታት ነበሩት። በዚህም ጊዜ ውስጥ መጥፎ ልማዶችን ያስተናግድ ጀመር። ሥራ ከመፈለግ ይልቅ በሱቆች አካባቢ መዋልን መረጠ። ከጥቂት ጊዜ በኋላ ጓደኞቹ ጫት መቃም አስለመዱት። ብዙም ሳይቆይ ወደ መጠጥ ቤቶችና ሴተኛ አዳሪዎች ዘንድ ጎራ ማለት ጀመረ። በመጨረሻም በኤድስ በሽታ ተይዞ ሞተ።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ. እንግዳ ወርቅ ለአነስተኛ ሥራዎች የነበረው አመለካከት ምን ዓይነት ነበር? ይህ መጽሐፍ ቅዱሳዊ አመለካከት ይመስልሃል? ለ) ሥራ በፈታ ጊዜ ምን ዓይነት አሳቦች ወደ አእምሮው መጡ? ሐ) ሥራ መፍታቱ ምን ዓይነት ውጤት አስከተለ?

ሐዋርያው ጳውሎስ ማንኛውም ሥራ ክቡር መሆኑን አስተምሯል። አንዳንድ ሥራ ለተማሩት ሰዎች የማይገባና ትናንሽ ሥራዎችን ከመሥራት ይልቅ ዝም ብሎ መቀመጡ ተገቢ እንደሆነ የሚያስተምረው ዲያብሎስ ነው። አንዳንድ የተሰሎንቄ አማኞች ሥራ አቁመው የክርስቶስን መምጣት በሚጠባበቁበት ጊዜ ጳውሎስ እያንዳንዱ ክርስቲያን እንዲሠራ አዟል። ጳውሎስ ታላቅ ሐዋርያ የሆነው ራሱ ሳይቀር የሌሎች ሸክም እንዳይሆን ቀንና ሌት ይሠራ እንደነበር ገልጾአል (2ኛ ተሰ. 3፡8)። ጳውሎስ ለዚህ ጉዳይ ትልቅ ትኩረት በመስጠቱ አንድ ሰው ለመሥራት ካልፈለገ መብላት እንደሌለበት አስረድቷል። ጳውሎስ በተጨማሪም እነዚህ ሊሠሩ የማይፈልጉ ክርስቲያኖች እንደ ዓለማውያን የሚቆጠሩ መሆናቸውን ገልጾአል። ሌሎች አማኞች ከእነዚህ ሥራ ከማይወዱ ሰዎች ጋር ኅብረት መፍጠር አያስፈልጋቸውም ነበር (2ኛ ተሰ. 3፡9-15)። ብዙም ለተማሩት ሰዎች የሚስማማ ሥራ በማይበዛበት በዚህ ዘመን ክርስቲያን ወጣቶች መሥራትን አቁመው በወላጆቻቸው ላይ ሊደገፉ ይችላሉ። ይህ ግን ለወንጌሉ እንቅፋት ነው። አነስተኛ ሥራዎችን መፈለግ ወይም ወደ ግብርና ተመልሶ ማረሱ በጣም ጠቃሚ ነው። በዚህ ጊዜ እግዚአብሔር ሥራቸውን በማክበር በጊዜው ሊያነሣቸውና የተሻለ ሥራ ሊሰጣቸው ይችላል።

ብዙውን ጊዜ ለክርስቲያኖች ስደትን በደስታ ተቀብሎ ማስተናገዱ ቀላል አይደለም። በመሆኑም እግዚአብሔር ሁኔታዎችን በመቆጣጠር ላይ ከሆነ እነዚህ ክፉ ሰዎች እንዲያሳድዱን የሚፈቅደው ለምንድን ነው ብለን እንጠይቃለን። ወይም እግዚአብሔር አፍቃሪ አምላክ ከሆነ እንዲህ ዓይነቱ ስደት እንዲደርስብን ለምን ይፈቅዳል? ለብዙ ክርስቲያኖች በተለይም ብዙ ስደት ላልደረሰባቸው የክርስቲያኖች ልጆች እግዚአብሔር ካአስቸጋሪ ሁኔታዎች ሁሉ ይጠብቀናል ብሎ ማመኑ ቀላል ነው። ነገር ግን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በየትኛውም ስፍራ እንዲህ ዓይነት የተስፋ ቃል አልተገባልንም። ይልቁንም በሁሉም የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት ውስጥ ማለት ይቻላል፥ እንደ እግዚአብሔር ልጆች ስደትንና መከራን እንደምንቀበል ተገልጾአል። ስለሆነም አስፈላጊው ነገር ከስደት ለመሸሽ መሞከሩ ሳይሆን በስደት ውስጥ ተገቢውን ባሕርይ መጎናጸፋችን ነው።

የተሰሎንቄ አማኞች ገና በመንፈሳዊ ሕይወታቸው ሳይጠነክሩ ለስደት ተጋልጠው ነበር። በክርስቶስ ካመኑበት ጊዜ ጀምሮ በአይሁዶች ወይም በአሕዛብ ሲሰደዱ ቆይተዋል። ጳውሎስ በስደቱ የደረሰባቸውን ተስፋ መቁረጥ ስለ ሰማ ሰላምታ ካቀረበላቸው በኋላ ስደትን የሚመለከት ትምህርት ያቀርብላቸዋል።

  1. ጳውሎስ አማኞቹን ለእድገታቸው ያበረታታቸዋል። በእምነት፥ እርስ በርሳቸው ላላቸው ፍቅርና በስደት ውስጥ እምነታቸውን ይዘው ለማቆየት በመቻላቸው ያመሰግናቸዋል፡፡ በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ በምንሆንበት ጊዜ በአመዛኙ ሁሉም ነገር መጥፎ ይሆናል ብለን እናስባለን። ነገር ግን ጳውሎስ እግዚአብሔር የመከራ ጊዜያትን በመጠቀም እንዴት መንፈሳዊ ሕይወታችንን እንዳሳደገው እንድናስታውስ ይፈልጋል።
  2. ጳውሎስ በመከራ ውስጥ ያሉት ክርስቲያኖች ወደፊት እንዲመለከቱና የመጨረሻውን ዘመን እንዲያስታውሱ በማድረግ ያበረታታቸዋል። ለአማኞች በስደት መጽናቱ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት በሚገቡበት ጊዜ ልማትና ክብርን ያስገኝላቸዋል። ክርስቶስ በሚመለስበት ጊዜ መከራን ለተቀበሉት እማኞች እፎይታን ያጎናጽፋቸዋል። ራእይ 21፡4 እንደሚያስረዳው በእግዚአብሔር ዘላለማዊ መንግሥት ውስጥ እንባዎች አይኖሩም። መከራም ሆነ ሞት በዚያ ስፍራ የላቸውም። ይህንኑ መጪ የእግዚአብሔር መንግሥት ካስታወስን አሁን የምንጋፈጠውን ጊዜያዊ ፈተና ልንታገሥ እንችላለን (2ኛ ቆሮ. 4፡16–18 አንብብ)። – በአንጻሩ በመጨረሻው ዘመን የሚያምኑ ሰዎችና ስደትን ለማምጣት ሰይጣን በመሣሪያነት የተጠቀመባቸው ሰዎች ለከፍተኛ ቅጣት ይጋለጣሉ። እግዚአብሔር ጻድቅ ስለሆነ ለሰዎች የሥራቸውን ይከፍላቸዋል። አማኞች የዘላለምን ሕይወት ሲያገኙ የማያምኑ ሰዎች ግን የዘላለም ጥፋት ይጠብቃቸዋል። እግዚአብሔር ካለበት ስፍራና ከግርማው ኃይል ይርቃሉ። ሲኦል የቅጣት ሥቃይ የሚታይባት ብቻ አይደለም። ይህ ሰዎች ለዘላለም ከእግዚአብሔርና ከእግዚአብሔር በረከቶች የሚለይበት ነው። በምድር ላይ የማያምኑ ሰዎች ከእግዚአብሔር በረከቶች አንዳንዶችን ያገኛሉ። ከእነዚህም መካከል ጤና፥ ምግብ፥ ዝናብና የመሳሰሉት ይገኙባቸዋል። በሲኦል ግን ከእነዚህ በረከቶች አንዳቸውንም ሊያገኙ አይችሉም።
  3. ጳውሎስ አማኞች ለእግዚአብሔር ጥሪ እንደሚገባ ይኖሩ ዘንድ የሚጸልይላቸው መሆኑን ይናገራል። እግዚአብሔር በሕይወታቸው ውስጥ ስደትንም ጨምሮ በኃይል እንዲሠራና ለእነርሱ የወጠናቸውን ዕቅዶች ሁሉ የሚፈጽሙበትን ኃይል እንዲሰጣቸው ይጸልያል።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) በሕይወትህ የደረሱብህን አንዳንድ መከራዎች ዘርዝር። በእነዚያ አስቸጋሪ ጊዜያት ውስጥ ሳይቀር እግዚአብሔር ታማኝነቱን የገለጸልህ እንዴት ነው? በሕይወትህ ውስጥ ምን ለውጦች ተከሰቱ? ችግሮች በሚያጋጥሙን ጊዜ እነዚህኑ በረከቶችና እድገት ማስታወሱ ለምን ይጠቅማል? ለ) ለክርስቲያኖች ከምድራዊ ሥቃይና ስደት ይልቅ በሰማያዊ የዘላለም በረከቶች ላይ አጽንኦት መስጠቱ አስፈላጊ የሚሆነው ለምንድን ነው? የወደፊት በረከቶችን በምንዘነጋበት ጊዜ ምን ይከሰታል? ከአሁኑ ቀላል ሕይወት ይልቅ ዓይኖቻችንን በዘላለማዊ መንግሥት ላይ በምንተክልበት ጊዜ ምን ይከሰታል? ሐ) ጳውሎስ ለጥሪያችን እንደሚገባ እንድንኖር ሲናገር ምን ማለቱ ነው? ለመጠራታችን እንደሚገባ የምንኖርባቸውን መንገዶች ዘርዝር።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: