ጳውሎስ ስለ ተሰሎንቄ አማኞች እግዚአብሔርን ያመሰግናል (1ኛ ተሰ. 1:1-10)

ገብረ እግዚአብሔር በክርስቶስ ካመነ ብዙም ሳይቆይ እናቱ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየች። እናቱም እንደ እርሱ አዲስ አማኝ ነበረች። ገብረ እግዚአብሔር እናቱን ከልቡ ይወዳት ስለነበር ልቡ በኀዘን ቆሰለ። አሁን ምን ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ይሆን ያለችው ሲል አሰበ። በሥቃይ ርዶ ድምፁን ጮክ አድርጎ አለቀሰ። ሌላ ክርስቲያን ሲያለቅስ ሰምቶት ክርስቲያኖች ሊያለቅሱ አይገባም ሲል በብርቱ ገሠጸው። የገብረ እግዚአብሔር ዘመዶች በአብዛኛው ክርስቲያኖች ባለመሆናቸው እናቱ ጥንታዊ ልማዶች በሚጠይቁት መንገድ እንድትቀበር የግድ አሉ። ምንም እንኳን ገብረ እግዚአብሔር እናቱ በክርስቲያናዊ መንገድ እንድትቀበር ቢፈልግም፥ ለዘመዶቹ ሲል በባህላዊ መንገድ እንድትቀበር አደረገ። ይህም ባህላዊ የአቀባበር ሥርዓት ድምፅን ጮክ አድርጎ ማልቀስን፡ ደረት መምታትንና፥ ከፊት ላይ ጭቃ መለጠፍን እና ሌሎችንም ተመሳሳይ ተግባራትን ይጨምር ነበር።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ለክርስቲያኖች የምንወዳቸው ሰዎች በሚሞቱበት ጊዜ ምን ዓይነት ምላሽ መስጠት እንዳለብን እግዚአብሔር ከእኛ የሚጠብቀውን ነገር ማወቁ ለምን ያስፈልጋል? ለ) እግዚአብሔር ለክርስቲያኖች እንደ አማኞች በምንሞትበት ጊዜ የምናገኘውን ተስፋ ማወቁ ለምን ያስፈልጋል? ሐ) አንድ ሰው በሚሞትበት ጊዜ በማልቀስ (ክርስቶስ እንዳደረገው ዮሐ 11፡35 አንብብ) እና ዛሬ ብዙ ሰዎች እንደሚያደርጉት በከንቱ በመጮህ መካከል ያለው ልዩነት ምንድን ነው?

ሞት ለአማኞችም ሆነ ለማያምኑ ሰዎች የማይቀር ነገር ነው። ሞት ወደዚህ ዓለም የመጣው አዳምና ሔዋን መጀመሪያ ኃጢአት በሠሩበት ጊዜ ሲሆን እስከ መጨረሻው ዘመን ድረስ የሚቀጥል ይሆናል። የኋላ ኋላ ግን ክርስቶስ ሞትን ያስወግደዋል (ራእ. 21፡4)። ክርስቲያኖችና ክርስቲያን ያልሆኑ ሰዎች በሚሞቱበት ጊዜ ምን እንደሚከሠት ማወቁ ለአማኞች በጣም አስፈላጊ ነው። ጳውሎስ ከተሰሎንቄ አማኞች ጋር ጥቂት ጊዜ ብቻ እንዳሳለፈ ስደት በመከሠቱ ስፍራውን ለቅቆ ለመሄድ ተገድዶ ነበር። የተሰሎንቄ አማኞች ካልተማሯቸው ነገሮች አንዱ የአማኞች ሞትና ያም ሞት ከክርስቶስ መመለስ ጋር የሚዛመድበት ሁኔታ ነበር። ጳውሎስ ከተሰሎንቄ ከተሰናበተ በኋላ አንዳንድ ክርስቲያኖች በሞት የተለዩ ይመስላል። በዚህን ጊዜ የተሰሎንቄ አማኞች «የምንወዳቸውን ወገኖች እንደገና እናያቸው ይሆን? ከሞት በኋላ ተስፋና ሕይወት አለን? የሞቱት አማኞች የክርስቶስን ክብርና የንግሥና በረከት አያገኙም ማለት ነውን? የሞቱ ወገኖቻችንን በምንቀብርበት ጊዜ ጥንታዊውን ባህል መከተል አለብን ወይስ የተለየ ነገር ማድረግ አለብን?» እነዚህና ሌሎችም ጥያቄዎች የተሰሎንቄን አማኞች ያስጨንቋቸው ነበር። ጳውሎስ ሞት ለአማኞች የተለየ ነገር መሆኑን ይናገራል። ከኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ የተነሣ አማኞች ከሞት እንደሚነሡ ዋስትና ተሰጥቷቸዋል። ስለሆነም ሞትን መፍራት የለብንም። መሞት ወይም ከሥጋ መለየት ማለት ከጌታ ጋር መሆን ማለት ነውና። በሞት የተለዩን ወንድሞቻችን የክርስቶስን የንግሥና በረከት ሳያገኙ ይቀሩ ይሆን? ለሚለው የተሰሎንቄ አማኞች ፍርሃት ጳውሎስ አጥጋቢ ምላሽ ሰጥቷል። ጳውሎስ እንዳብራራው የሞቱት አማኞች በሕይወት ያሉት አማኞች ከመለወጣቸው አስቀድመው ከሞት እንደሚነሡና በቀዳሚነት የበረከቱ ተካፋዮች እንደሚሆኑ አስረድቷል። ከዚህም ተስፋ የተነሣ የክርስቲያኖች የቀብር ሥነ ሥርዓት ተስፋ ቢስነት የሚታይበት ጊዜ ሊሆን አይገባም። ይህ ጊዜ የክርስቶስን የትንሣኤ ተስፋ የሚፈነጥቅ ሊሆን ይገባል። ለዚህ ነው ጳውሎስ ተስፋ እንደሌላቸው ዓለማውያን አናዝንም የሚለው። የምናለቅሰው ለጊዜው ከወገኖቻችን በመለየታችን ብቻ ነው። ይህም አንድ ሰው ወደ አሜሪካ ወይም ወደ ሌላ ቦታ በሚሄድበት ጊዜ እንደምናዝን ማለት ነው።

ሁለቱም የተሰሎንቄ መልእክቶች የሚጀምሩት በሦስት የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ሰላምታ ነው። እነዚህም መሪዎች ከሦስት ወራት በፊት ወደ ተሰሎንቄ የክርስቶስን ወንጌል ያመጡ አገልጋዮች ነበሩ። የመልእክቱ ጸሐፊ ጳውሎስ ሲሆን፥ ሲላስና ጢሞቴዎስም አብረውት በቆሮንቶስ ነበሩ። ሁሉም አገልጋዮች ለሚወዷቸው አማኞች ሰላምታቸውን ልከዋል።

ጳውሎስ ከተሰሎንቄ አማኞች ጋር ያሳለፈው የአንድ ወር ወይም የስድስት ሳምንታት ጊዜ ሊዘነጋ የማይችል ነበር። ጳውሎስ ስለ ደኅንነታቸውና በስደት ውስጥ ለክርስቶስ ታማኞች ሆነው ስለ መጽናታቸው ከጢሞቴዎስ ሲሰማ ልቡ በምስጋና ተሞላ። በዚህም ምክንያት እግዚአብሔርን ያመሰግናሉ። በመሆኑም ጳውሎስ እነዚህን አዳዲስ አማኞች በእምነታቸው ለማበረታታት ሲል መልእክቶቹን ጽፎአል።

ሀ) ጳውሎስ በሕይወታቸው ስለ ተከሠቱት ለውጦች የሰማውን አሳብ በመግለጽ አማኞቹን ያበረታታል። በተለይም በአማኞቹ ሕይወት ውስጥ የተከሠቱትን ሦስት ቀዳማይ ጉዳዮች ይዘረዝራል።

በመጀመሪያ፡- ከእምነት የተገኘ የሥራ ፍሬ ነበራቸው። ምንም እንኳ የሚያድነን በኢየሱስ ክርስቶስ ሞት ማመናችን ቢሆንም፥ እግዚአብሔር እምነታችን ፍሬ እንዲያፈራ ይፈልጋል። እምነታችን አኗኗራችንን፥ አስተሳሰባችንንና አተገባበራችንን ይለውጠዋል። እምነታቸው የአእምሮ እውቀት ብቻ ሳይሆን፥ አኗኗራቸውን፥ በችግር ውስጥ ያሉትን ሰዎች የሚረዱበትን መንገድ፥ ወንጌሉን የሚመሰከሩበትን ሁኔታ፥ ወዘተ… ተቆጣጥሯል።

ሁለተኛ፡- የተሰሎንቄ አማኞች ተግባራቸውን ያከናወኑት በፍቅር ነበር። እነዚህ ሰዎች እግዚአብሔርን ይወዱትና እርስ በርሳቸውም ይዋደዱ ነበር። ፍቅር ስሜት ሳይሆን ተግባር ነው። ከዚህም ፍቅር የተነሣ የተሰሎንቄ አማኞች ለእግዚአብሔር ክብር ተግተው ሠርተዋል። በችግር ጊዜ በተለይም በከባድ ስደት ውስጥ በሚያልፉበት ጊዜ እርስ በርሳቸው ተረዳድተዋል።

ሦስተኛ፡- በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ከማመናቸው የመነጩ የተስፋ ጽናት ነበራቸው። በክርስቶስ እንዳመኑ ስደት ሲደርስባቸው በታማኝነት ጸንተው እንዲቆዩ ያደረጋቸው ምን ነበር? ተስፋቸው ነበር። ይህም ክርስቶስ ዳግም እንደሚመጣና እንደሚሸልማቸው መገንዘባቸው ነበር። ከዚህም የተነሣ የተሰሎንቄ አማኞች ስደትንና የተለያዩ ችግሮችን በታማኝነት ተጋፍጠዋል።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) እነዚህ ሦስት ነገሮች ለእያንዳንዱ ክርስቲያን ለምን አስፈላጊዎች እንደሚሆኑ አብራራ። ለ) በሕይወትህ እነዚህ ሦስቱ ባሕርያት የሚገኙት እንዴት ነው?

ጳውሎስ የተሰሎንቄ አማኞች የተለወጠ ሕይወት፥ ከጣኦት አምልኮ የተመለሱበት ሁኔታና ኢየሱስ ክርስቶስን በማገልገል ምጽአቱን መጠበቃቸው በመቄዶኒያ ብቻ ሳይሆን ከአካይያ ጭምር እንደታወቀ ያስረዳል። አካይያ ጳውሎስ በዚህ ጊዜ ወንጌሉን በሚሰብክበት በቆሮንቶስ ከተማ አካባቢ የምትገኝ ስፍራ ነበረች። ይህ ክርስቶስን ካወቁ የስድስት ወራት ዕድሜ ለነበራቸው አማኞች ምንኛ ታላቅ ምስክርነት ነው።

ለ) ጳውሎስ ከእግዚአብሔር ጋር ስለነበራቸው ልዩ ግንኙነት በመመስከር አማኞችን ያበረታታል። ጳውሎስ የመረጣቸው እግዚአብሔር የተሰሎንቄን አማኞች እንደሚወዳቸው ገልጾአል። ከደረሰባቸው ስደትና ችግር ባሻገር፥ እግዚአብሔር ምን ያህል እንደሚወዳቸው ማስታወስ ያስፈልጋቸው ነበር።

ወንጌል መጀመሪያ ወደ ተሰሎንቄ ሲመጣ ከእግዚአብሔር የመነጨ እንጂ ከንቱ ተስፋ እንዳልሆነ በሚያረጋግጥ መልኩ በታላቅ ኃይል ነበር የተገለጠው። ወንጌል ወደ ተሰሎንቄ አማኞች የመጣው በቃላት ብቻ አይደለም። ጳውሎስ በመካከላቸው ወንጌሉን በመኖር መልካም ምሳሌ ሆኗቸው ነበር። ይህ ማለት ግን ክርስቶስን ለመከተል የደረሱበት ውሳኔ ቀላል ነበር ማለት አይደለም። አይሁዶች በጳውሎስ ላይ ስደትን እንዳደረሱ ሁሉ በተሰሎንቄ አማኞች ላይም አይሁዶችና አሕዛብ ከፍተኛ ስደት በማስከተል ላይ ነበሩ። ነገር ግን በቶሎ ይመጣል ብለው በሚያምኑት በክርስቶስ ላይ ጽኑ እምነት ስለነበራቸው በእምነታቸው ጸንተው ቆመዋል።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

Discover more from

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading