መሪ ሐሰተኛ ትምህርቶችን ሊከላከልና የእምነትን እውነት ሊጠብቅ ይገባዋል (1ኛ ጢሞ. 4፡1-16)

ብዙውን ጊዜ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች እንዴት መልካም መሪዎች ሊሆኑ እንደሚችሉ ይሠለጥናሉ። ስለ ጊዜ አጠቃቀም፥ ኃላፊነትንና ሥልጣንን ለሌሎች ስለ መወከል፥ መልካም አደረጃጀትና ስለ መመሥረት፡ ግልጽ የሥራ ድርሻን መግለጫ ስለማዘጋጀትና ስለ ሌሎችም ተመሳሳይ ጉዳዮች ይማራሉ። እነዚህ ሁሉ የሥልጠና ሀሳቦች ጥሩዎች ናቸው። ይሁንና የትኞቹም የአመራርን ችግር ሊቀርፉ አይችሉም። መጽሐፍ ቅዱስ የአመራር መሠረቱ የሰው ልብ እንደሆነ ይናገራል። አንድ ሰው ጥሩ ልብ እስከሌለው ድረስ ምንም ያህል የአመራርና የአስተዳደር ችሎታ ቢኖረው፥ ፍጻሜው የእግዚአብሔርን ቤት ማፍረስ እንጂ መገንባት ሊሆን አይችልም። ነገር ግን ልቡ ከእግዚአብሔር ጋር ከተቃኘና እግዚአብሔርን የሚታዘዝ ሕይወት ካለው፥ ለውጤታማ አስተዳደር የሚያስፈልጉ ብቃቶች ሁሉ ባይኖሩትም እንኳን እግዚአብሔር ይህን ሰው ይጠቀምበታል። መጽሐፍ ቅዱስ በቀዳሚነት ልባችንና ባሕሪያችን ከእግዚአብሔር ጋር መስማማት እንዳለበት ያስተምረናል። ከዚያ በኋላ የአመራርን ችሎታ ልንማር እንችላለን። ወይም መልካም መሪዎችና ቤተ ክርስቲያንን የምንገነባ መሪዎች እንድንሆን ያስችለናል።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ስጦታ ኖሯቸው መንፈሳዊነት የጎደላቸው ሰዎች ቤተ ክርስቲያንን ሲጎዱ የተመለከትክበትን ሁኔታ ግለጽ። ለ) ብዙም የመሪነት ስጦታ የሌለውና ለእግዚአብሔር በመገዛቱ ምክንያት ቤተ ክርስቲያንና ለመገንባት በመሣሪያነት ያገለገለ መሪ አጋጥሞህ ያውቃል? ሁኔታውን ግለጽ። ሐ) መጽሐፍ ቅዱስ የጊዜ አጠቃቀም፥ ኃላፊነትና ሥልጣንን መወከል፥ ወዘተ… ካሉት የአመራር ጉዳዮች በላይ በመንፈሳዊነት፥ ከቅድስና፥ በትሕትና፥ ራስን በመቆጣጠርና እነዚህን በመሳሰሉት ባሕርያት ላይ ትኩረት የሚያደርገው ለምን ይመስልሃል?

ሐዋርያው ጳውሎስ ጢሞቴዎስ በኤፌሶን ቤተ ክርስቲያን ውስጥ መንፈሳዊ መሪዎችን ስለሚመርጥበት ሁኔታ ምክር እየሰጠው ነበር። ጳውሎስ እንደ የቤተ ክርስቲያን መሪ ሊያከናውናቸው የሚገባውን የሥራ ዝርዝሮች አላሰፈረም። ነገር ግን መሪነት ከልብ እንደሚመነጭ መሪዎችን በመምረጡ ረገድ እጅግ አስፈላጊው ነገር ልባቸውና ባሕሪያቸው ትክክል መሆኑን ማረጋገጥ መሆኑን ያስረዳል። መሪዎች መንፈሳዊነትን የተላበሱ፥ በእምነታቸው የበሰሉ፥ የተቀደሱና ከሌሎች ሰዎች ጋር አብረው እንዲሠሩ የሚያስችል ባህሪ ያላቸው ሊሆኑ ይገባል። ነገር ግን ጳውሎስ ቤተ ክርስቲያን እግዚአብሔርን የምታስከብር ተቋም ትሆን ዘንድ መሪዎች ሊኖሩዋቸው የሚገቧቸውን የተለያዩ ነገሮች ዘርዝሯል። ጳውሎስ ጢሞቴዎስ የመሪነትን ባህሪ ስለሚያንጸባርቅበት ሁኔታ ሲያስተምር፥ እግዚአብሔር ከሌሎች መሪዎች ምን እንደሚጠብቅ እግረ መንገዱን ማስተማሩ ነበር። ጳውሎስ ካነሣቸው ነጥቦች መካከል የሚከተሉት ይገኙባቸዋል።

ከኋለኛው ዘመን ባሕርያት እንዱ የሐሰት አስተማሪዎች መብዛት እንደሚሆንና ይህም ብዙ አማኞች እምነታቸውን እንዲተዉ የሚያደርግ መሆኑን መንፈስ ቅዱስ ለጳውሎስ ገልጾለት ነበር። በአዲስ ኪዳን ውስጥ፥ የኋለኛው ዘመን የሚለው ሐረግ ከክርስቶስ የመጀመሪያው መምጣት ጀምሮ ዳግም እስከሚመለስበት ጊዜ ድረስ ያለውን ያጠቃልላል። ስለሆነም ጳውሎስም ሆነ እኛ በዚሁ የኋለኛ ዘመን ውስጥ እንኖራለን።

ከመጀመሪያው ጀምሮ የቤተ ክርስቲያን ራስ ምታት ከሆኑት ነገሮች መካከል በዋናነት የሐሰት ትምህርት ይጠቀሳል። ጳውሎስ መልካምና መንፈሳዊ መስለው ከሚቀርቡት ከእነዚህ የሐሰት ትምህርቶች በስተጀርባ አሳሳች መናፍስቶችና የአጋንንት ትምህርቶች መኖራችውን ገልፆአል። በእያንዳንዱ ትውልድ ውስጥ ሰይጣን እውነትን የሚያዛቡትን አስመሳይ ክርስቲያኖች ይጠቀማል። ጳውሎስ እነዚህ የሐሰት አስተማሪዎች መንፈሳዊያን መስለው ቢቀርቡም፥ ሕሊናቸው እንደጠፋና የሰይጣንን ውሸቶች እንደሚያሰራጩ አስረድቷል። ስለሆነም ጳውሎስ ጢሞቴዎስና በየትውልዱ የሚገኙ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች እውነትን ለይተው በማወቅ የሐሰት ትምህርቶችን እንዲከላከሉ ያስጠነቅቃቸዋል።

በጳውሎስ ዘመን፥ በስፋት የሚታየው ዋንኛው የሐሰት ትምህርት ሰዎች ድነትን (ደኅንነት) ለማግኘት ወይም ለበለጠ መንፈሳዊነትን ለመላበስ የተወሰኑ ሕግጋትን መጠበቅ እንዳለባቸው የሚያስተምር ነበር። እነዚህ ሕግጋት ብሉይ ኪዳንንና ሌሎችም ሕጎችን ከሚያስተምሩ አይሁዶች ወይም ከሌሎች አስተማሪዎች መምጣታቸው አልተገለጸም። ምናልባትም እነዚህ ትምህርቶች በዓለም ውስጥ የሚገኙ ነገሮች ክፉዎች እንደሆኑ በማስተማር ሰዎች ሥጋቸውን በመጨቆን የተወሰኑ ምግቦችን እንዳይመገቡ፥ ብዙም ቁሳዊ ምቾቶችን እንዳይጠቀሙ፥ እንዳይጋቡ፥ ወዘተ.. ከሚከለክሉ አሕዛብ የመጡ ሊሆኑ ይችላሉ። ሰይጣን እነዚህን የሐሰት አስተማሪዎች በመጠቀም፥ ሰዎች እውነተኛ መንፈሳዊነትን በማያስገኙ ነገሮች ላይ እንዲያተኩሩ ያደርግ ነበር። ሰዎች በፍቅር፥ ቅድስና፥ ትሕትናን፥ ታዛዥነት፥ ወዘተ… ላይ እንዲያተኩሩ ከማድረግ ይልቅ፥ እነዚህ የሐሰት አስተማሪዎች በውጫዊ ሕግጋት ላይ ያተኩሩ ነበር። ከእነዚህ ሕግጋት መካከል አንዳንዶቹ በእግዚአብሔር የተፈቀዱ ቢሆኑም እውነተኛ መንፈሳዊነትን የማያንጸባርቁ ነበሩ። ለምሳሌ፥ ያህል፥ ወሲብን መፈጸም ትክክል እንዳልሆነና ለክርስቶስ ሳያገቡ መኖር እንደሚሻል በማሰብ፥ መጋባት ተገቢ አይደለም ብለው ያስተምሩ ነበር። ሰዎች እንደ ሥጋ ያሉትን የተወሰኑ ምግቦች እንዳይመገቡ ይከላከሉ ነበር። ምናልባት እነዚህ ሰዎች የከለከሉት ብሉይ ኪዳን ሰዎች እንዳይመገቡ የከለከለውን ሥጋ ሳይሆን አይቀርም። ጳውሎስ ግን እግዚአብሔር አንዳንድ ልምምድ እስካልከለከለ ድረስ፥ በትክክለኛ አነሣሽ ምክንያት፥ እግዚአብሔርን እያመሰገኑ ይህንኑ ልምምድ ማከናወን እንደሚቻል ገልጾአል። የእነዚህ ሰዎች ትምህርት በእግዚአብሔር ጸጋ፥ ክርስቲያን ለእግዚአብሔር ባለው ፍቅር፥ እንዲሁም በመንፈሳዊ ባሕርይ ላይ አያተኩርም ነበር። ይህ ዛሬ ብዙ ሰዎች ለእግዚአብሔርና ለሰዎች ከሚኖረን ፍቅር ይልቅ ስላላመጠጣን ወይም ስላለመደነስ አጽንኦት ሰጥተው ከሚያስተምሩበት ሁኔታ ጋር ተመሳሳይ ነው።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) በአዲስ ኪዳን ውስጥ በግልጽ ያልተከለከሉና ኢትዮጵያውያን የማያደርጓቸው ነገሮች ወይም የማይመገቧቸው ምግቦች ምን ምንድን ናቸው? ለ) እነዚህ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያልሆኑ ነገሮች በመንፈሳዊነት ላይ የሚያስከትሉት ተጽዕኖ ምንድን ነው? ሐ) በእነዚህ ውጫዊ ነገሮች ላይ ትኩረት መስጠቱ እግዚአብሔርና ሰዎችን እንደ ማፍቀር ካሉት እጅግ ጠቃሚ ነገሮች የሚያርቀን እንዴት ነው? መ) ብዙ ሰዎች በቤተ ክርስቲያንህ ውስጥ ከልባቸው ይልቅ በውጫዊ ነገሮች ላይ ስለሚያተኩሩባቸው ሁኔታዎች ግለጽ።

አንድ መሪ እነዚህን የሐሰት ትምህርቶች በሚመለከትበት ጊዜ ያለው ኃላፊነት ምንድን ነው? ጳውሎስ መሪዎች ሊያደርጓቸው ይገባል የሚላቸውን አያሌ ነጥቦች ዘርዝሯል።

ሀ) መሪዎች ሐሰተኛ የሆነውን ነገር በሚሰሙበት ጊዜ ለይተው ለማወቅ ይችሉ ዘንድ እውነትን ማወቅ አለባቸው፡፡ ከዚያ በኋላ ለምእመኖቻቸው በመጽሐፍ ቅዱስ አስተምህሮ መሠረት የተሳሳተው ነገር ምን እንደሆነ ሊያብራሩ ይችላሉ። ከቤተ ክርስቲያን መሪዎች ዐበይት ተግባራት መካከል አንዱ የወንጌሉን እውነት መጠበቅ ነው። መሪዎች ቤተ ክርስቲያንን ከሐሰት ትምህርቶች መከላከል አለባቸው። ይህንንም ማድረግ የሚቻልበት ብቸኛው መንገድ እውነትን በማወቅ ነው። እግዚአብሔር በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያስተማረውን እውነት ካላወቅንና ስሕተት የሆነውን ነገር ለይቶ ከሚያሳየን መንፈስ ቅዱስ ጋር በቅርብ ተጣምረን ካልተመላለስን፥ እውነትን ልንጠብቅ አንችልም። ከዚህም የተነሣ ብዙውን ጊዜ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት የተቀላቀለበትን የሰይጣንን ውሸት እናምናለን።

የቤተ ክርስቲያን መሪዎች አንድን አዲስ ትምህርት በሚሰሙበት ጊዜ ሊያደርጓቸው የሚገቧቸው ሦስት አማራጮች አሉ። በመጀመሪያ፥ ከዚህ በፊት ሰምተው የማያውቁት በመሆኑ ምክንያት ሊቃወሙት ይችላሉ። ብዙ መሪዎች በባህላዊ ግንዛቤያቸው ላይ በመንተራስ አዲስ የሆነውን ሁሉ ይቃወማሉ። ይህ ቤተ ክርስቲያኒቱን ከሐሰተኛ ትምህርት ቢከላከልም፥ መንፈስ ቅዱስ ወደ ቤተ ክርስቲያኒቱ ለማምጣት የሚፈልገውን አዲስ እውነትም የሚከላከል በመሆኑ ተመራጭነት አይኖረውም። ይህም አባሎቻቸው መጽሐፍ ቅዱስ በሚያስተምረው እውነት ሥር ነፃ ሆነው እንዳይመላለሱና ሰው ሠራሽ ሕግጋትን እንዲከተሉ ያደርጋል። ሁለተኛ፥ የመጣውን አዲስ ትምህርትም የሚቀበሉ የቤተ ክርስቲያን መሪዎችም አሉ። አዲስና ሰዎችን የሚያስደስት እስከሆነ ድረስ፥ ትክክል መሆን አለበት ብለው ያስባሉ። ከዚህም የተነሣ፥ ብዙ የሐሰት ትምህርቶች ወደ እነዚሁ አብያተ ክርስቲያናት እየጎረፉ በመምጣት ሰዎችን ከእውነት ያስታሉ። ሦስተኛ፥ ብቸኛው መጽሐፍ ቅዱሳዊ አማራጭ ያቀረበውን ትምህርት በመጽሐፍ ቅዱስ እውነት መገምገም ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቱን የሚደግፍ ከሆነ፥ በአዲስ መንገድ ቢቀርብም እንኳን ልንቀበለው ይገባል። ነገር ግን መጽሐፍ ቅዱስ ከሚደግፈው ውጪ ከሆነ፥ መቀበል የለብንም። ሰዎች ሐሰተኛ ትምህርት እንዳይቀበሉ መናገር ብቻ ሳይሆን መቀበል የለባቸውም የምንልባቸውን ምክንያቶችም ማብራራት አለብን። ይህም ማለት የሐሰት ትምህርቶችን ነቅለን ለማውጣትና እግዚአብሔር የሰጠንን መንጋ ለመጠበቅ እንድንችል በማይለወጠው የእግዚአብሔር ቃል እያደግን መሄድ አለብን ማለት ነው።

የውይይት ጥያቄ፡- በቅርቡ ወደ ቤተ ክርስቲያንህ የመጣ አዲስ ትምህርት ምንድን ነው? ሀ) ይህ ትምህርት ከላይ በቀረቡ ሦስት መንገዶች ሊስተናገድ የሚችልበትን ሁኔታ ግለጽ። ለ) የቤተ ክርስቲያንህ መሪዎች አዳዲስ ትምህርቶችን ወይም የአምልኮ ልምምዶችን ስለሚያስተናግዱበት ሁኔታ ምን ትመክራቸዋለህ?

ለ) የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ጎጂ የሆነውንና ሊወገድ የሚገባውን፥ እንዲሁም ጉዳት የሚያስከትለውንና ጠቃሚ ያልሆነውን ትምህርት ለይተው ማውጣት ይኖርባቸዋል። ጳውሎስ ጢሞቴዎስ ዘላለማዊ ምልከታዎች የሌሏቸውን ትምህርቶች ከመከታተል እንዲቆጠብ ይመክረዋል። እነዚህ ትምህርቶች የሰው ልጅ እእምሮ የፈጠራቸው ከንቱ አሳቦች ብቻ ናቸው። ጳውሎስ እነዚህን ተረትና መጨረሻ የሌለው የትውልድ ታሪክ ሲል ይጠራል።

ሐ) የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ደክመው በኃጢአት እንዳይወድቁ ባለማቋረጥ መንፈሳዊ ሕይወታቸውን ማጠናከር ይኖርባቸዋል። ጳውሎስ ይህንን እውነት በስፖርታዊ ምሳሌ ያብራራዋል። እንድ ሰው የሩጫ ውድድር ከማካሄዱ በፊት፥ ሰውነቱን ለማጠናከር ብርቱ ልምምድ ማድረግ ይኖርበታል። የማሸነፍ ዕድል የሚኖረው ከዚህ በኋላ ብቻ ይሆናል። ሰውነትን ለመቆጣጠር መማሩ አስፈላጊ ይሆናል። ይህ ግን እንደ መንፈሳዊነት፥ ጸሎት፥ ጾም፥ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን በቃል ማጥናት፥ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፥ ምስክርነት የሚሰጡትን ያህል መንፈሳዊ በረከት የሚያስገኝ አይደለም። እነዚህ ነገሮች አንድ መንፈሳዊ መሪ በሕይወቱ እንዲጠናከርና ውጤታማ እንዲሆን በማድረግ በሐሰተኛ ትምህርት እንዳይታለል ይረዱታል። በመሆኑም በከርስቶስ የፍርድ ወንበር በሚቀርብበት ጊዜ መሪው ለኀፍረት አይዳረግም። ብዙውን ጊዜ አንድ መሪ ለሐሰት ትምህርት፥ የወሲብ ኃጢአት፥ ወይም ለሌላ ኃጢአት የሚሸነፈው ከመንፈሳዊ ልምምዶች በሚርቅበት ጊዜ ነው።

መ) አንድ መሪ በቃሉ ብቻ ሳይሆን በምሳሌነቱ ጭምር መምራት አለበት። ጳውሎስ ጢሞቴዎስ በንግግር፥ በሕይወት፥ በፍቅር፥ በእምነትና በንጽህና ለምእመናን ምሳሌ እንዲሆንላቸው አሳስቦታል። ብዙውን ጊዜ ቤተ ክርስቲያን መሪዎች የሚያስተምሩትን ሕይወት አይኖሩም። ምእመናን የጸሎት ሰዎች እንዲሆኑ እያስተማሩ፥ እነርሱ ራሳቸው ብዙም አይጸልዩም። ምእመናን ለእግዚአብሔር አሥራት እንዲሰጡ እያስተማሩ፥ ራሳቸው ግን አሥራት አይከፍሉም። የአንድ መሪ ትልቁ ስብከት የሚናገረው ሳይሆን በሕይወቱ ኖሮ የሚያሳየው ነው። ብዙ ሰዎች የመሪን ምሳሌነት ይከተላሉ። እርሱ በቅድስና የሚመላለስ ከሆነ እነርሱም በቅድስና ይመላለሳሉ። መሪው ለመንፈሳዊ ሕይወቱ ግድ የለሽ ከሆነ፥ እነርሱም ለከርስቶስ የቆራጥነት ሕይወት አይኖሩም።

ሠ) የቤተ ክርስቲያን መሪ በእግዚአብሔር ቃል ላይ እንጂ በራሱ ሐሳብ ላይ ትኩረት መስጠት የለበትም። ጳውሎስ ጢሞቴዎስ ቅዱሳት መጻሕፍትን በማንበብ፥ በመስበክና በማስተማር እንዲተጋ መክሮታል። ብዙውን ጊዜ መሪዎች የገዛ ሐሳባቸውን ይሰብካሉ። ከመድረክ የሚሰበከው ቃል ደግሞ ተያያዥነት የለውም። የተለያዩ መሪዎች በሚወዷቸው ርእሰ ጉዳዮች ላይ ይሰብካሉ። በየሰንበቱ የሚጋበዙ አገልጋዮች ተመሳሳይ እውነቶችን ይናገራሉ። ከዚህም የተነሣ ምእመናን ስለ እግዚአብሔር ቃል የሚኖራቸው ዕውቀት የተወሰነ ይሆናል። ይህንን ለማስወገድ፥ ጳውሎስ ጢሞቴዎስ መጽሐፍ ቅዱስን ባለማቋረጥ እንዲያጠናና ይሄኑ ለምእመናን እንዲያስተምር ነግሮታል። የእግዚአብሔርን ቃል ሙሉ በሙሉ ካላወቅን የሐሰተኛ ሐሳቦችን ለማሸነፍና እግዚአብሔር የሚፈልግብንን ዓይነት ክርስቲያኖች ለመሆን አንችልም። የእግዚአብሔር ቃል በሙላት የምናውቀው ደግሞ መሪዎች በጥንቃቄ ተዘጋጅተው የእግዚአብሔርን ቃል ከዳር እስከ ዳር ሲያስተምሩን ነው።

ረ) መሪዎች የገዛ የራሳቸውን ሕይወት በጥንቃቄ መጠበቅ አለባቸው። ሰይጣን አንድን መሪ በሐሰተኛ ትምህርት ወይም በወሲብ ኃጢአት ለመጣል ከቻለ፥ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ብዙ ችግሮችን ሊፈጥር እንደሚችል ያውቃል። ስለሆነም መሪዎች ከምእመናን የበለጠ የሰይጣን ፈተናዎችና ጥቃቶች ዒላማዎች ናቸው። በመሆኑም መሪዎች በኃጢአት እንዳይወድቁና ለክርስቶስ ለመኖር መልካም ምሳሌዎች ይሆኑ ዘንድ ሕይወታቸውን በጥንቃቄ መጠበቅ ይኖርባቸዋል። በዚህም ጊዜ የራሳቸውን ሕይወት መጠበቅ ብቻ ሳይሆን፥ የቤተ ክርስቲያናቸው ምእመናን እግዚአብሔርን በሚያስከብር መንገድ እንዲኖሩ ይረዷቸዋል።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ጳውሎስ ከሰጣቸው ምክሮች መካከል በተለይ ለቤተ ክርስቲያን መሪዎች አስፈላጊ የሆኑት የትኞቹ ናቸው? ለ) ለማሸነፍ ከባድ የሆኑብህ የትኞቹ ነጥቦች ናቸው? ሐ) መሪዎቻችን የጳውሎስን ትምህርቶች ተቀብለው ቢለወጡ በአብያተ ክርስቲያኖቻችን ውስጥ ምን ዓይነት ለውጥ ይከሰታል?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: