መሪ አድልዎ በሌለው ሁኔታ በሚያገለግልበት ጊዜ የቤተ ክርስቲያኒቱ አባላት ሊያከብሩት ይገባል (1ኛ ጢሞ. 5፡17-25)

የቤተ ክርስቲያን መሪነት ከባድ አገልግሎት ነው። ደመወዙ በጣም ዝቅተኛ ከመሆኑም በላይ፥ ብዙ የቤተ ክርስቲያን ምእመናን ፍላጎታቸው በማይሟላበት ጊዜ ያጉረመርማሉ። መሪው በአማኞች መካከል የሚከሰቱትን ስሜትን የሚጎዱ ነገሮችና ፀቦች የማስተካከል ኃላፊነት አለበት። ከቤተሰቡ ጋር የሚያሳልፈው በቂ ጊዜም አይኖረውም። ጳውሎስ በማስተማርና በመስበክ የሚተጉ መሪዎች እጥፍ ክብር እንደሚገባቸው ገልጾአል። የቤተ ክርስቲያን ምእመናን መሪዎቻቸውን በማክበር አገልግሎታቸውን ቀለል ሊያደርጉላቸው ይገባል። በተጨማሪም ጳውሎስ ለጠቅላላው ቡድን ጥቅም በመሥዋዕትነት ለሚያገለግሉት መሪዎች ምእመናን የገንዘብ ድጋፍ ሊያደርጉ እንደሚገባም ያስተምራል። መሪው በሚገባ ለመምራት፥ ለመስበክና ለማስተማር የሚችለው ለአገልግሎቱ በቂ ጊዜ ሲሰጥ ነው። ብዙ ጊዜ ሌላ ሥራ ወይም ንግድ ከሌለው፥ የገንዘብ ችግር ይገጥመዋል። በመሆኑም አገልጋዩ ኑሮን ለመምራት ባለመቻሉ፥ ቤተሰቡን የሚያስተዳድርበት ገንዘብ በማጣቱ ተጨማሪ ሸክም እንዳያድርበት፥ ቤተ ክርስቲያን ደመወዝ ልትከፍለው ይገባል። አገልጋዩ በቂ ደመወዝ የሚያገኝ ከሆነ፥ ስለ ገንዘብ ከማሰብ ተላቅቆ በአገልግሎቱ ላይ ሊያተኩር ይችላል። ለመሪነት፥ ለስብከትና ለማስተማር አገልግሎት ሙሉ ጊዜያቸውን ለሚሰጡት ሰዎች በቂ ደመወዝ የማትከፍል ቤተ ክርስቲያን፥ የመጽሐፍ ቅዱስን ትእዛዝ ትጥሳለች። ደመወዝ ሳይከፍሉ መሪዎች በነፃ ጊዜያቸውን እንዲሰጡ የሚያደርጉ አብያተ ክርስቲያናት ብዙውን ጊዜ የኋላ ኋላ ቤተ ክርስቲያኒቱን ይጎዳሉ። ቁልፍ መሪዎች ለመተዳደሪያ የሚያስፈልጋቸውን ገንዘብ ለማግኘት ወዲያ ወዲህ ለማለት የሚገደዱ ከሆነ፥ ሙሉ ለሙሉ ራሳቸውን ለአገልግሎት ሊሰጡ አይችሉም። ተገቢው አሠራር ለአብያተ ክርስቲያናት ለመሪዎች ደመወዝ መክፈል ቢሆንም፥ መሪዎች እንደ ጳውሎስ ጊዜያቸውን በነፃ ለመለገስ የሚፈቅዱባቸው አጋጣሚዎችም ሊኖሩ ይችላሉ (1ኛ ቆሮ. 9፡6-18)። ይሁንና፥ ይህ የአገልጋዩ የግል ምርጫ እንጂ ቤተ ክርስቲያን በግዳጅ የምታስፈጽመው ሊሆን አይችልም።

ጳውሎስ ጢሞቴዎስ ቤተ ክርስቲያንን ስለሚመራበት ሁኔታ አንዳንድ የምክር ቃሎችን ሰጥቷል፡–

ሀ) ምእመናን ወይም መሪዎች የፈጸሟቸውና በጠቅላላው የቤተ ክርስቲያን ማኅበረሰብ ላይ ተጽዕኖ ያስከተሉ ታላላቅ ኃጢአቶች በምእመናን ሁሉ ፊት ቀርበው እልባት ሊያገኙ ይገባል። ይህም ቤተ ክርስቲያኒቱን በንጽሕና ለመጠበቅ ይረዳል። ጳውሎስ አንድ ሰው እንደ ክፉ አሳብ ያሉ ድብቅ ኃጢአቶች በሚኖሩት ጊዜ ሁሉ ቤተ ክርስቲያን ፊት እየተነሣ ኃጢአቱን መናዘዝ አለበት ማለቱ አይደለም። ነገር ግን በአንድ አማኝ ወይም መሪ ሕይወት ውስጥ የዐመፅ መንፈስ ሲኖርና ይህም ዐመፅ ያስከተለው ኃጢአት በአማኞች ሁሉ ዘንድ በሚታወቅበት ጊዜ፥ መፍትሔውም ምእመናንን ባሳተፈ መልኩ እልባት ማግኘት እንዳለበት ይናገራል። የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ግለሰቡን በይፋ ሊገልጹት ይገባል። በመሆኑም በምእመናን ፊት ቀርቦ ንስሐ መግባት አለበት። ንስሐ ካልገባ፥ ውሳኔው የቤተ ክርስቲያኒቱ ምእመናን የሚሰጡት ይሆናል። እንዲህ ዓይነቱን ኃጢአት በዚህ ዓይነት መንገድ ማስተናገዱ፥ ሦስት ዐበይት ውጤቶችን ያስከትላል።

በመጀመሪያ፥ ቤተ ክርስቲያን በቤተሰብ ወይም በጓደኛሞች የአስተሳሰብ መሥመር አትከፋፈልም። ነገሮች በምሥጢር በሚያዙበት ጊዜ፥ የቤተ ክርስቲያን አባላት የተሳሳተ መረጃ ይደርሳቸዋል። ይህም እንደ ተሳሳተ ውሳኔ ይቆጠራል። በይፋ በሚታይበት ጊዜ ግን ክፍፍልን መፍጠር አዝማሚያው አናሳ ይሆናል።

ሁለተኛ፡ ግለሰቡ የኃጢአትን አደገኛነት እንዲገነዘብና ራሱን ዝቅ አድርጎ ንስሐ እንዲገባ ይረዳዋል።

ሦስተኛ፥ ሰዎች ለኃጢአት ፍትሐዊና ግልጽ እልባት እንደሚሰጥ ሲገነዘቡ በግድየለሽነት የኃጢአትን አመለካከት ከመያዝ ይቆጠባሉ። ምንም እንኳን በብዙ ባህሎች ውስጥ ኃጢአቱን በማጋለጥ አንድን ሰው ማሳፈሩ ትክክል ባይሆንም፥ መጽሐፍ ቅዱሳዊው መንገድ ግልጽ ተጋፍጦና ኑዛዜ የሚካተትበት ነው። ይህም ኃጢአትን ትኩረት ሰጥቶ ለማስወገድና በክርስቶስ አካል ውስጥ ቅድስናን ለማስፈን ይረዳል። ዛሬ በቤተ ክርስቲያናችን ውስጥ ኃጢአት የበረከተው በግልጽ ለመጋፈጥና ለመናዘዝ ባለመፈለጋችን ይሆን?

(ማስታወሻ፡ ይህ መመሪያ በማቴዎስ 18፡15-17 የቀረቡትን በቅድሚያ ከተከተልን በኋላ ልንከተለው የሚገባ ቀጣይ እርምጃ ነው።)

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) በቅርብ ጊዜ በቤተ ክርስቲያንህ ይፋዊ ተግሣጽ፥ ይፋዊ ኑዛዜ ወይም ውሳኔ የተሰጠው መቼ ነው? ለ) በቤተ ክርስቲያንህ ውስጥ ብዙ ኃጢአቶች በግልጽ የማይታዩት ለምን ይመስልሃል? ሐ) በቤተ ክርስቲያን ላይ ተጽዕኖ ያስከተለው ኃጢአት ከመደበቅና ይፋዊ እልባት ካለመስጠት የመነጩት አሉታዊ ነገሮች ምን ምንድን ናቸው? መ) አንድ የቤተ ክርስቲያንህ አባል በባህላችን እንዲህ ዓይነት ነገር አናደርግም ቢል ምን ዓይነት ምላሽ ትሰጠዋለህ? መጽሐፍ ቅዱሳዊ ዕገዳዎች ከባህል የበለጠ አስፈላጊነት የሚኖራቸው ይመስልሃል? ለምን? ሠ) እግዚአብሔር በሰዎች ሕይወት ውስጥ በከፍተኛ ደረጃ በመሥራት ምእመናን ንስሐ እንዲገቡና ለጽድቅ እንዲጠሙ ያሳስባቸው ዘንድ በጸሎት ጠይቅ።

ለ) የቤተ ክርስቲያን መሪ አድልዎ በሌለበት ሁኔታ አገልግሎቱን ማካሄድ አለበት። አንድ ሰው መሪ በሚሆንበት ጊዜ፥ ቤተሰቡ ጠቅላላው የቤተ ክርስቲያን ምእመናን የሚገኙበት ቡድን ይሆናል። ስለሆነም ጓደኞቹን፥ ሥጋዊ ቤተሰቡን፥ የጎሳውን አባላት የሚያስተናግድበትን መንገድ የቤተ ክርስቲያን አባላት በእኩልነት እንደሚያይ የሚያንጸባርቅ መሆን አለበት። የቤተ ክርስቲያን መሪዎች አድልዎ በማስፈጸም ለቤተሰቦቻቸው፥ ለወዳጆቻቸውና ለጎሳቸው አባላት የተለየ ጥቅማ ጥቅም በሚያስገኙበት ወቅት በእግዚአብሔር ቤተሰብ ውስጥ ከፍተኛ ችግር ይፈጠራል። መሪዎች ልጆቻቸውን የቤተ ክርስቲያን ኳየር ውስጥ በማስገባት፥ ወዳጆቻቸውን ቤተ ክርስቲያን እስፖንሰር ወደምታደርገው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት በመላክ ወይም የጎሳ አባሎቻቸውን ለሽምግልና በማስመረጥ አድልዎ ሊፈጽሙ ይችላሉ። በዚህም ረገድ ከባህላችን ይልቅ መጽሐፍ ቅዱሳዊው አሠራር ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል።

ሐ) የቤተ ክርስቲያን መሪ በችኮላ የመሪነትን ኃላፊነት ለሰዎች መስጠት የለበትም። የቀድሞዋ ቤተ ክርስቲያን በሰዎች ላይ መቼ እጇን እንደምትጭንና ይህም ምን እንደሚያመለክት አልተገለጸም። አንዳንድ ምሁራን እንደሚያስቡት ይህ የሚሆነው አንድ ሽማግሌ ንስሐ ገብቶ ወደ ቤተ ክርስቲያን ኅብረት በሚመለስበት ጊዜ ነው ይላሉ። በዚህ ጊዜ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ከራሱ ላይ እጆቻቸውን ጭነው በመጸለይ ወደ ቤተ ክርስቲያን ኅብረት ይመልሱታል። ጳውሎስ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ኃጢአት የፈጸመውን ሰው አመራር ከመመለሳቸው በፊት ንስሐ መግባቱን ማረጋገጥ እንዳለባቸው ያሳስባል። ንስሐ የልብንና የተግባርን ለውጥ የሚያመለክት እንጂ፥ በቀላሉ ይቅርታ መጠየቅን ብቻ የሚያመለክት መሆን የለበትም።

ይሁንና፥ እጅን መጫን አንድን መሪ ወይም ሽማግሌ ለአገልግሎት የማቆምን ልምምድ ይመስላል። ለምሳሌ ጳውሎስና በርናባስ ለወንጌል መልእክተኝነት አገልግሎት በተለዩ ጊዜ መሪዎች እጆቻቸውን ጭነው ጸልየውላቸዋል (የሐዋ. 13፡3)። ጳውሎስ ጢሞቴዎስ ሰዎችን በችኮላ ለመሪነት እንዳይቀበል የሚያሳስበው ይመስላል። ይህ አንድን ሰው ለመሪነት ከመወከሉ በፊት፥ ሕይወቱን መመርመርና መንፈሳዊነቱ፥ ብስለቱና ንጽሕናው ለመሪነት የሚያበቃው መሆኑን ማረጋገጥ አስፈላጊ ነው። ይህ መሪም ለአገልግሎት መሾም የሚጀምረው ሰዎች ለአዲሱ ሽማግሌ እንዲጸልዩና እጆቻቸውን እንዲጭኑበት በማድረግ ነበር። እንደ ጢሞቴዎስ ያለ መሪ በአዲሱ መሪ ላይ እጁን በሚጭንበት ጊዜ የግለሰቡ ሕይወት ተጨምሮ ለዚሁ አገልግሎት ብቁ ሆኖ መገኘቱን ማረጋገጡ ነበር። ይህንን በችኮላ ማከናወኑ ትክክለኛ ያልሆኑ መሪዎችን ወደ ቤተ ክርስቲያን አገልግሎት መጋበዝ ይሆናል። አንድን ሰው በችኮላ መሾም ወይም በኃጢአት ውስጥ የሚኖር ግለሰብን ለመሪነት አገልግሎት መቀበል ማለት ቤተ ክርስቲያንን ወደ ኃጢአት መምራት ማለት ነው። ይህ ማለት ደግሞ የግለሰቡ ክፉ አመራርና ኃጢአት ተካፋይ መሆን ነው። እግዚአብሔር እጁን በመጫን የሾመውን ግለሰብ ቤተ ክርስቲያንን ባለመጠበቁ በኃላፊነት ይጠይቀዋል።

የውይይት ጥያቄ፡- እነዚህን የጳውሎስ ማስጠንቀቂያዎች አብያተ ክርስቲያናት ሊያጤኗቸውና ተግባራዊ ሊያደርጓቸው የሚገባው ለምንድን ነው?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: