ጳውሎስ ጢሞቴዎስ ለወንጌሉ በቆራጥነት እንዲቆም ያበረታታዋል (2ኛ ጢሞ 1፡1-14)
ከአርባ ለሚበልጡ ዓመታት ገብረ እግዚአብሔር እግዚአብሔርን በታማኝነት ሲከተል ቆይቷል። በግል ሕይወቱ፥ እግዚአብሔርን በሙሉ ልቡ ለመውደድና በመንፈሳዊ ሕይወቱ ለማደግ ሲሻ ቆይቷል። በአደባባይ ሕይወቱም እንዲሁ፥ ገብረ እግዚአብሔር በምስክርነትና በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የተለያዩ እርዳታዎችን በማድረግ እግዚአብሔርን ለማገልገል ጥሯል። ምንም እንኳን የቤተ ክርስቲያኒቱ ሽማግሌ ሆኖ ባይመረጥም፥ በየሳምንቱ በማለዳ ወደ ቤተ ክርስቲያን ይመጣል። ይህንንም የሚያደርገው ቤተ ክርስቲያኒቱን ለአምልኮ ለማሰናዳት ነበር። የቤተ ክርስቲያን የሥራ ቀን በሚታወጅበት ጊዜ፥ ሁልጊዜም ገብሬ ከሰዎች ቀድሞ ይመጣና ዘግይቶ ከቦታው ይሄዳል። በየቀኑ ሰፊ ጊዜ በጸሎት ያሳልፋል። በተለይም ደግሞ ለቤተ ክርስቲያኒቱና ለመጋቢው አጥብቆ ይጸልያል። የጥበቃ ሠራተኛ የሆነው ገብረ እግዚአብሔር በታማኝነቱ የታወቀ ነበር። በጊዜ ወደ ሥራው በመምጣት፥ ሳያንቀላፋ ተግቶ በመቆየትና ተግባሩን በሚገባ በማከናወን አገልግሎቱን ያበረክታል። ገብሬ ከእርጅናው የተነሣ ሥራውን ለማከናወን ባልቻለ ጊዜ በጡረታ ተገለለ። ከዚያ በኋላ ብዙም ሳይቆይ በጠና ታሞ ሊሞት መቃረቡን ተገነዘበ። በዚህም ጊዜ የቤተ ክርስቲያኒቱ መጋቢ መጥቶ እንዲጠይቀው መልእክተኛ ላከበት። ወጣቱ መጋቢ ሊጸልይለት በመጣ ጊዜ፥ ገበሬ ምን ዓይነት ጸሎት ሊደረግለት እንደሚፈልግ ጠየቀው። ገብሬ ለዚህ ወጣት፥ «በጥሩ ሁኔታ ለመሞት እፈልጋለሁ። እስከ መጨረሻው ድረስ ለክርስቶስ ታማኝ መሆን አለብኝ። እርሱም መልካም አደረግህ ታማኝ ባሪያዬ እንዲለኝ እፈልጋለሁ (ማቴ. 25፡14-30)። ክርስቶስ እንደማያሳፍር መልካም ሠራተኛ እንዲያየኝ እፈልጋለሁ (2ኛ ጢሞ. 2፡15)። በክርስቶስ ካመንኩበት ዕለት ጀምሮ እርሱን በታማኝነት ለማገልገል ስሻ ኖሬአለሁ። ከፍተኛ ስጦታ አልነበረኝም፥ ትምህርት ቤት የመግባትም ዕድል አላገኘሁም። ነገር ግን እግዚአብሔር ያለኝን ሁሉ ለክብሩ እንዲጠቀምበት ፈልጌአለሁ። አሁን ሩጫዬን በመልካም ሁኔታ እንድፈጽም ጸልይልኝ።» ሲል ተናገረ።
የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) የገብረ እግዚአብሔር ባሕሪ እግዚአብሔር ከሁላችን የሚጠብቀው አመለካከት መሆኑን ግለጽ። ለ) ይህ ፍላጎት የገብሬን የዕለት ተዕለት ሕይወት እንዴት እንደ መራው አብራራ። ሐ) ለእግዚአብሔር ታማኝ መሆን በዓለም ከሚታወቀው ስኬት፥ ማለትም እንደ ትምህርት፥ ሀብት፥ ጥሩ ርስት፥ ወዘተ… ካሉት ነገሮች በላይ ለእግዚአብሔር አስፈላጊ የሚሆነው እንዴት ነው? መ) የራስህን ሕይወት ለመገምገም ጊዜ ውሰድ። አሁን ወደ መንግሥተ ሰማይ ብትሄድ እግዚአብሔር ታማኝ አገልጋይ ነበርህ የሚልህ ይመስልሃል? ካልሆነ ታማኝ አገልጋይ እንድትሆንና መንግሥተ ሰማይ በደረስህ ጊዜ መልካም አደረግህ እንድትባል ከባሕሪህና ከተግባርህ ሊለወጥ የሚገባው ምንድን ነው?
የ2ኛ ጢሞቴዎስ መጽሐፍ የተጻፈው ሐዋርያው ጳውሎስ ወደ ሕይወቱ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ ነበር። ሕይወቱን መለስ ብሎ በተመለከተ ጊዜ፥ ጳውሎስ ሕሊናው ንጹህ እንደነበረ ለመመስከር ችሏል (2ኛ ጢሞ. 1፡3)። መንፈሳዊ ሕይወቱንም በጥሩ ሁኔታ እንዳከናወነ ተረድቷል (2ኛ ጢሞ. 4፡6-8)። ያለምንም ጸጸት ከሚወደው ጌታው መልካም አደረግህ የሚሉትን ቃላት ለመስማት ወደ መንሥተ ሰማይ እየገሰገሰ ነበር። በዚህ መጽሐፍ ውስጥ፥ ጳውሎስ በሚሞትበት ጊዜ መልካም አደረግህ የሚሉትን እነዚሁኑ ቃላት ለመስማት የሚያስችሉትን ወሳኝ መንፈሳዊ እውነቶች ያብራራል። በዚህ አዛውንቱ ጳውሎስ ለወጣት መንፈሳዊ ልጁ በጻፈው መልእክቱ፥ እግዚአብሔርን አስከብሮ ስለመኖር የሚናገሩ ጠቃሚ እውነቶችን ዘርዝሯል።
ስደት በሚነሣበት ጊዜ ብዙ ክርስቲያኖች በፍርሃት ይናጣሉ። በመሆኑም ብዙዎቹ መመስከር ያቆማሉ። አማኞች መሆናቸውም እንዳይታወቅ ጥረት ያደርጋሉ። አንዳንድ ፈሪ እማኞች አካባቢውን ለቅቀው ሰዎች ወደማያውቋቸው አካባቢዎች ይፈልሳሉ። ሌሎች ግን በሚታሰሩበት ጊዜ እምነታቸውን ይክዳሉ። ይህ ፍርሃት ተፈጥሯዊ ነው። እንደውም ስደትን መፍራት ወይም ሌሎች መሪዎች ምን ይሉኝ ይሆን የሚለው አስተሳሰብ ከጳውሎስ ጋር ከ15 ዓመታት ለሚበዙ ጊዜያት ያገለገለውን ጢሞቴዎስን እየተፈታተነው ነበር። ይህም የጢሞቴዎስን አገልግሎት አደናቅፎታል። ስለሆነም ሐዋርያው ጳውሎስ የ2ኛ ጢሞቴዎስ መልእክቱን የጀመረው ወጣት የሥራ ጓደኛው ፍርሃቱን ተቋቁሞ እግዚአብሔርን በድፍረት እንዲያገለግል በማበረታታት ነበር። ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ በጻፈው ምክር የሚከተሉትን ነጥቦች ይጠቅሳል፡-
ሀ) ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ የነበረውን ጥልቅ ፍቅር በመግለጽ እንደሚጸልይለትና እንደገና ሊያየው እንደሚናፍቅ ይገልጽለታል።
ለ) ጳውሎስ የጢሞቴዎስን የቤተሰባዊ ውርስ፥ እንዲሁም የእናቱንና የአያቱን ጠንካራ እምነት ያስገነዝበዋል። በተጨማሪም ጢሞቴዎስ ከእግዚአብሔር ስለተቀበለው ስጦታና ጥሪ ያሳስበዋል። ምናልባትም ከሁለተኛው የወንጌል መልእክተኝነት ጉዞው በኋላ፥ ጳውሎስ ለወጣቱ ጢሞቴዎስ በሚጸልይበት ጊዜ እግዚአብሔር እንደ ጢሞቴዎስ ልዩ መንፈሳዊ ስጦታ የሰጠው ይመስላል። ጳውሎስ የሚናገረው ስለምን ዓይነቱ ስጦታ እንደሆነ አልተጠቀሰም። ምናልባትም በ1ኛ ጢሞ. 4፡14 ላይ የተጠቀሰው የትንቢት ስጦታ ሳይሆን አይቀርም። ምናልባትም ጢሞቴዎስ ሰዎችንና ሐሰተኛ አስተማሪዎችን በመፍራቱ ምክንያት፥ የእግዚአብሔርን ቃል ለሌሎች የማካፈሉን ስጦታ ከመጠቀም ሳይቆጠብ አልቀረም። ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ ፍርሃት ከእግዚአብሔር እንዳልሆነ ነግሮታል። ምንም እንኳን ጢሞቴዎስ ዓይናፋርና ፈሪ ቢሆንም፥ እግዚአብሔር ስጦታውን በሰዎች ፊት እንዲጠቀም ኃይልን ይሰጠዋል። እንዲሁም እግዚአብሔር ሰዎችን በሚያስፈርስ ሳይሆን በሚያንጽ መንገድ ስጦታውን እንዲጠቀም ፍቅርን ይሞላበታል። በተጨማሪም የራሳችንን መንፈሳዊ ሕይወት ከመገንባቱ በተጨማሪ፣ ጥራት ያለውን አገልግሎት የምንሰጥባትን ራስን የመግዛት ችሎታ ያላብሰናል። ይህም አገልግሎታችን በተከፈለ ልብ እንዳናከናውን ይረዳናል። ይህ ጥቅስ እያንዳንዱ ክርስቲያን መንፈሳዊ ስጦታውን በማሳደግ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ከፍተኛ ውጤት ማምጣት እንዳለበት ያሳያል።
የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) መንፈሳዊ ስጦታዎችህ ምን ምንድን ናቸው? ለ) እነዚህን ስጦታዎች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ለመጠቀም ምን እያደረግህ ነው? ሐ) በበለጠ ውጤታማነት ትገለገልባቸው ዘንድ እነዚህን ስጦታዎች እያሳደግህ ያለኸው እንዴት ነው?
ሐ) ጳውሎስ ጢሞቴዎስ የስደትና የሥቃይ ፍርሃቱን እንዲያሸንፍ ይነግረዋል። ሀ) በማያምኑ ሰዎች ፊት ስለ ክርስቶስ በድፍረት ለመመስከር፥ ለ) በእስር ቤት ውስጥ በሚገኘው ጳውሎስ ምክንያት ኀፍረት እንዳይሰማው ያስጠነቅቀዋል። ጢሞቴዎስ ስደትን ከመፍራቱ የተነሣ ከጳውሎስ የራቀ ይመስላል። ጳውሎስ ጢሞቴዎስ መከራንና ስደትን ከእግዚአብሔር የተቀበለው ጥሪ አካል አድርጎ እንዲቀበል ያሳስበዋል። ጳውሎስ ስለ ወንጌሉ የነበረው ግንዛቤ ስደትን፥ መከራንና ሞትን ያለ ፍርሃት እንዲቀበል አስችሎታል። ወንጌል የጳውሎስን አገልግሎት ብቻ ሳይሆን ሞትን የሚጋፈጥበት መንገድ ጭምር የሚለውጥ ነበር። ክርስቶስ ሞትን እንዳሸነፈውና በወንጌሉ አማካኝነት ሕይወትንና ዘላለማዊነትን እንዳመጣ ማመኑ ሞትን እንዳይፈራ እድርጎታል። ጳውሎስ፥ «ያመንሁትን አቃለሁና የሰጠሁትንም አደራ እስከዚያ ቀን ድረስ ለመጠበቅ እንዲችል ተረድቻለሁ» ሲል ተናግሯል። ክርስቶስ ሞትን እንዳሸነፈና የዘላለም ሕይወት ተስፋ እንደሰጠን ካመንን፥ ያ የተስፋ ቃል እውነት እንዳልሆነ በመግለጽ ሞትን እየፈራን መኖር የለብንም።
መ) ጳውሎስ ጢሞቴዎስ የተሰጠውን መልካሙን አደራ እንዲጠብቅ አጽንኦት ሰጥቶ ይመክረዋል። ጳውሎስ እያረጀ ሲሄድ፥ ወንጌልን በጥንቃቄ በመጠበቁ ላይ ማለትም በጤናማ ትምህርት ላይ ሲያተኩር እንመለከተዋለን። ይህንንም ያደረገው የሐሰተኛ አስተማሪዎች እንዳይበርዙት በማሰብ ነው። ጳውሎስ ወንጌሉን፥ ማለትም የክርስቶስ ኢየሱስን ሕይወትና ሞት የሚያመለክተውን እውነት እንደ ማይለወጥ እውነት ይገልጸዋል። ይህ ለባንክ ቤት ብዙ ገንዘብ በአደራ እንደ ማስረከብ ነበር። ገንዘቡ ውድ ዋጋ ስላለው በጥንቃቄ መጠበቅ አለበት። ወንጌልንም በተመለከተ እንዲህ ዓይነት እርምጃ መውሰዱ ተገቢ ነው። ወንጌሉ እንዲለወጥ ማድረጉ ወይም ሐሰተኛ እውነቶች ወደ ቤተ ክርስቲያን ዘልቀው እንዲገቡ መፍቀድ ዘራፊ ባንክ ቤት ውስጥ ገብቶ የተከማቸውን ሁሉ ከሚዘርፍበት ሁኔታ የከፋ ነው። ጢሞቴዎስ እውነትን ብቻውን ሊጠብቅ አይችልም ነበር። ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ እውነትን እንዲጠብቅ ሊያበረታታው ይገባ ነበር።
የውይይት ጥያቄ፡- ለቤተ ክርስቲያን መሪዎች የማይለወጠውን የወንጌል እውነት ማወቅና በጥንቃቄ መጠበቅ የሚያስፈልገው ለምን ይመስልሃል?
እግዚአብሔር የቤተ ክርስቲያን መሪዎች እውነትን እንዲያውቁና እንዲጠብቁ ይፈልጋል። ወንጌሉ በሐሰተኛ ትምህርት እንዲበረዝና እንዲለወጥ ከፈቀዱ፣ መሪዎቹ የሰዎችን ሕይወት ዘላለማዊ ዕጣ ፈንታ ለአደጋ አጋልጠዋል ማለት ነው። ዋናው ነገር ክርስቲያን የሚለወጥ ስም እንደ ታፔላ ለጥፎ መዞሩ አይደለም። ድነት (ደኅንነት) እና የዘላለም ሕይወት የሚገኙት አንድ ሰው ስለ ክርስቶስና ስለ ሞቱ ትክክለኛ እውነቶችን ሲያውቅና ክርስቶስ የሞተው በእርሱ ምትክ መሆኑን በግሉ አምኖ ሲቀበል ብቻ ነው። በዘመናችን አንድነትን ለማምጣት ስንል እውነትን እንዳንሠዋ መጠንቀቅ ይኖርብናል።
በተጨማሪም ጳውሎስ ልንከላከል እንደሚገባንና እንደማይገባን ስለሚናገራቸው ነገሮች መገንዘቡ ጠቃሚ ነው። ጳውሎስ የተወሰነ የአምልኮ ስልትን ጠብቀን ለማቆየት እንድንሞክር አላዘዘንም። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በግልጽ ያልተቀመጠውን እውነትም እንድንጠብቅ አላስተማረም። አንዱን ቤተ እምነት በመደገፍ ሌላውን እንድንቃወምም አላዘዘንም። ይልቁንም ጤናማውን ትምህርት ወይም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተቀመጡትን መሠረታዊ የአስተምህሮ እውነቶች እንድንጠብቅ አዞናል። ይህንን ለማድረግ ደግሞ የቤተ እምነታችን አጽንኦት የሆነውንና የምንመርጠውን የአምልኮ ወይም የአኗኗር ስልት ከወንጌሉ አስኳል ለይተን መመልከት መቻል አለብን። ንጹህን ወንጌል ጠብቀን ለማቆየት መጣር አለብን። ነገር ግን እርስ በርሳችን ክርስቲያናዊ ፍቅርና መቻቻልን በማዳበር ቤተ እምነታዊ ልዩነቶችን ከመራገብ መቆጠብ ይኖርብናል። እነዚህ ቤተ እምነታዊ ልዩነቶች የአምልኮ ስልትን ወይም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በግልጽ ያልተቀመጡትን እውነቶች የሚመለከቱ ናቸው። (ስለ መጨረሻው ዘመን ያለን አመለካከት ለዚህ ለቤተ እምነታዊ ልዩነቶች እንደ አብነት የሚጠቀስ ነው።)
ጳውሎስ ከሄኔሲፎሩ በስተቀር ሁሉም እንደተዉት ይናገራል (2ኛ ጢሞ. 1፡15-18)
የስደቱ ውጥረት በሮም ግዛት ሁሉ በተለይም በሮም ከተማ ያየለ ይመስላል። ኔሮ የክርስቶስ ተከታይ ነን የሚሉትን ብዙ ሰዎች ገድሎ ነበር። ሮማውያን የክርስትና መሪዎች ናቸው ብለው የሚያስቧቸው ጴጥሮስና ጳውሎስ ወኅኒ ቤት ታስረው ለእምነታቸው ሊሠዉ ተዘጋጅተው ነበር። ይህ ለክርስቲያኖች ፈታኝ ጊዜ ነበር። እንደ አለመታደል ሆኖ የቤተ ክርስቲያን መሪዎችን ጨምሮ ብዙ ክርስቲያኖች ለእምነታቸው ለመሞት ዝግጁ አልነበሩም። በመሆኑም እምነታቸውን በመደበቅ፥ ወይም እንደ ጳውሎስ ካሉት ሰዎች ጋር የነበራቸውን ግንኙነት ለሰዎች ላለማሳወቅ ጥረት አድርገዋል። ጳውሎስ ከዚሁ የስደት ፍርሃት የተነሣ በእስያ ከሚገኙት አማኞች ብዙዎቹ ከእርሱ ጋር ለመተባበር እንዳልፈለጉ ገልጾአል። እስያ ኤፌሶንና በራእይ ውስጥ የተጠቀሱት ሰባቱ አብያተ ክርስቲያን የሚገኙባት የሮም አውራጃ ነበረች። ጳውሎስ በዚህ መልእክት መጨረሻ ላይ ከጻፈው አሳብ ለመረዳት እንደሚቻለው፥ በእምነታቸው ጸንተው የቆሙ አንዳንድ ክርስቲያኖች ነበሩ። ነገር ግን ከስደት ፍርሐት የተነሣ ብዙዎቹ እምነታቸውን ደብቀዋል።
ጳውሎስ የፊሎጎስንና የሄርዋጌኔስን ፍርሃት ከሄኔሲፎሩ ድፍረት ጋር ያነጻጽራል። እነዚህ ሰዎች በጥንቷ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የታወቁ መሪዎች ነበሩ። ሄኔሲፎሩ ምናልባትም የኤፌሶን ክርስቲያን ሳይሆን አይቀርም። እርሱና ቤተሰቦቹ እምነታቸውን ወይም ከጳውሎስ ጋር የነበራቸውን ግንኙነት ለመደበቅ አልፈለጉም። እንዲያውም ጳውሎስን ለማበረታታት ሲል ሄኔሲፎሩ ወደ ሮም ተጉዟል። በዚያም ጳውሎስን እስኪያገኝ ድረስ ከተማ ለከተማ እየዞረ ፈልጎታል።
ጳውሎስ ይህን ሁኔታ በመጠቀም ሞትም የሚያስከትልብን ቢሆንም እንኳን፥ በስደት ጊዜ ምን ማድረግ እንዳለብን ያስረዳል። በክርስቶስ ያለንን እምነት መደበቅ የለብንም። እንዲሁም ለእምነታቸው የታሰሩትን ሰዎች ከመርዳትና ከእነርሱ ጋር ከመተባበር ወደ ኋላ ማለት የለብንም። ለወንጌሉና ለእርስ በርሳችን ሕይወታችንን አሳልፈን ልንሰጥ ይገባል። ምክንያቱም ለወንጌል መሞት አማኝን ከክርስቶስ ጋር ወደሚኖርበት ዘላለማዊ ቤት የሚያደርስ በር እንደሆነ ያስተምራል። ፍርሃት ሕይወታችንን እንዲቆጣጠር መፍቀድ የለብንም።
የውይይት ጥያቄ፡- በኮሚኒዝም ዘመን ለእምነቱ የታሰረ አማኝ አነጋግር። ሀ) እምነቱንና ከሌሎች ጋር የነበረውን ግንኙነት ለመደበቅ የተፈተነበት ሁኔታ እንዳለ ጠይቀው። ለ) ከዚህ ይልቅ ምን ለማድረግ መረጠ? ሐ) እግዚአብሔር በዚያ አስቸጋሪ ጊዜ ውስጥ እንዴት እንዳበረታታው አብራራ። መ) በእስር ቤት ውስጥ ለክርስቶስ ያላቸውን ምስክርነት መጠበቃቸው፥ በእስር ቤት ውስጥ ከአማኞች ጋር ኅብረት ማድረጋቸው አስፈላጊ የሚሆነው ለምንድን ነው? ሠ) ይህ እውነተኛ እምነት ያላቸውን ሰዎች እምነት የሚያጸናው እንዴት ነው?
(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)