የቲቶ መልዕክት መግቢያ

«አንተ ግን ሕይወት ለሚገኝበት ትምህርት የሚገባውን ተናገር። ሽማግሌዎች ልክኞች፥ ጭምቶች፥ ራሳቸውን የሚገዙ፥ በእምነትና በፍቅር በመጽናትም ጤናሞች እንዲሆኑ ምከራቸው። እንዲሁም አሮጊቶች ሴቶች አካሄዳቸው ለቅዱስ አገልግሎት የሚገባ… አስተምራቸው። ጎበዞችም እንዲሁ ራሳቸውን እንዲገዙ ምከራቸው… ባሪያዎች…. ምከራቸው» (ቲቶ 2፡1-9)።

አንድ ጊዜ አንድ ታዋቂ አፍሪካዊ ክርስቲያን በአፍሪካ ውስጥ ክርስትና ሁለት ኪሎ ሜትር ስፋትና ሁለት ሴንቲ ሜትር ጥልቀት አለው ሲል ተናግሮ ነበር። ይህን ሲል በአፍሪካ ውስጥ ክርስቲያኖች ነን የሚሉ ብዙ ሰዎች እንዳሉ መግለጹ ነበር። ነገር ግን እግዚአብሔርንና ቃሉን በማወቅ አላደጉም። ይህን ክርስቲያን ወንድም ያሳሰበው በአፍሪካ የሚገኙ ክርስቲያኖች መንፈሳዊ እውነትን አለመማራቸውና ተገቢውን ክርስቲያናዊ ሕይወት የማይኖሩና ለሐሰት ትምህርቶች የተጋለጡ መሆናቸው ነበር።

ቲቶ ጳውሎስ አብያተ ክርስቲያናትን እንዲያደራጁ ከወከላቸው አገልጋዮች አንዱ ነበር። ጳውሎስ ለቲቶ በጻፈው መልእክቱ በማስተማር ተግባር እንዲተጋ በተደጋጋሚ አሳስቦታል። ልጆች፥ ወጣት ወንዶች፥ ወጣት ሴቶች፥ አረጋውያን ሴቶችንና አረጋውያን ወንዶችን ጨምሮ ሁሉም የዕድሜ ክልሎች፥ እንዲሁም ባሮችን ጨምሮ በሁሉም የኢኮኖሚ ደረጃ ላይ የሚገኙ ሰዎች የእግዚአብሔርን ቃል መማር እንዳለባቸው ጳውሎስ ለቲቶ አሳስቧል። እነዚህ ሰዎች በሁለት መንገዶች መማር ነበረባቸው። በመጀመሪያ፥ አማኞች የእግዚአብሔርን እውነቶች መማር ያስፈልጋቸው ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ እግዚአብሔር፥ ኢየሱስ ክርስቶስ፥ መንፈስ ቅዱስ፥ ድነት (ደኅንነት)፥ ወዘተ… የሚያስተምረውን ማወቅ ያስፈልጋቸዋል። ማንም ሰው ከእግዚአብሔር ቃል እነዚህን እውነቶች ሳያውቅ በእምነቱ ሥር ሊሰድ አይችልም። ትላልቅ ዛፎች በጥልቅ እንደሚሰዱት ሥር እነዚህ እውነቶች የሰው ሕይወት እንዲጸናና የሐሰተኛ አስተምህሮ ወይም የስደትን ነፋሳት እንዲቋቋም ያስችሉታል።

ሁለተኛ፥ አማኞች ባሕሪያቸውን እንዲቀይሩ መማር አለባቸው። የቀርጤስ ሰዎች በሮም ግዛት ውስጥ በውሸተኝነታቸው፥ በክፋታቸው፥ እንዲሁም ሰነፎችና ሆዳሞች በመሆናቸው ይታወቁ ነበር (ቲቶ 1፡12)። እንዲህ ዓይነቱ ባህሪ በክርስቶስ ላይ ካለህ እምነትና በእግዚአብሔር መንግሥት ውስጥ አዲስ ፍጥረት ከመሆን ጋር የሚጣጣም አልነበረም። ይልቁንም ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር ባላቸው ግንኙነት መንፈስ ቅዱስ የማይበሳጩ፥ ክብር የሚገባቸው፥ ራሳቸውን የሚገዙ፥ ጤናማ እምነት ያላቸው፥ አፍቃሪዎችና ታጋሾች፥ የማይሰርቁ፥ ወዘተ. አድርጎ እንዲለውጣቸው መጣር ያስፈልጋቸው ነበር። የእግዚአብሔርን ቃል የምንማርበትና የምናስተምርበት ዋናው ዓላማ አዳዲስ እውነቶችን ማወቅ ብቻ አይደለም። (ለምሳሌ፥ የዳዊት አባት ማን እንደሆነ ማወቅ)። ነገር ግን ባህሪያችን እንዲለወጥና አኗኗራችንም የተስተካከለ እንዲሆን የእግዚአብሔርን ቃል እንማራለን። ጳውሎስ እንደ መጠጣት፥ ፊልም ማየት፥ አለባበስ በመሳሰሉት አንዳንድ ሕጎች ወይም ደንቦች ላይ አጽንኦት አለመስጠቱ ልብ ሊባል የሚገባው ነው። ነገር ግን የጳውሎስ ትምህርት በሰዎች ባሕሪ ላይ ያተኩራል፥ ምክንያቱም አተገባበራችንን የሚወስነው ባሕሪያችን ነውና።

ጳውሎስ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ከሚያከናውኗቸው ተግባራት ዋናው ማስተማር እንደሆነ ለቲቶ ያስረዳል። ጤናማ የሆነች ቤተ ክርስቲያን ድነት (ደኅንነትን) ላላገኙ ሰዎች ብቻ ሳይሆን ላመኑት ክርስቲያኖችም እምነታቸውን የሚያጸና ትምህርት በማቅረብ ትተጋለች። በመንፈሳዊ ሕይወታቸው ያድጉ ዘንድ በሁሉም የዕድሜ ክልል ለሚገኙ ሰዎች ተዛማጅነት ያላቸው የሥልጠና ፕሮግራሞች ይሰጣሉ።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) የቤተ ከርስቲያንህን የትምህርት ፕሮግራሞች መርምር። በሁሉም የዕድሜ ክልሎች የሚገኙ አማኞች ትምህርት እያገኙባቸው ያሉባቸውን መንገዶች ግለጽ። ለ) ትምህርቱ የሚያተኩረው የተወሰኑ መረጃዎችን፥ ደንቦችና ሕጎችን በማወቅ ላይ ነው? ወይስ የአኗኗር ለውጥን በሚያስከትለው ባሕሪ ላይ? ሐ) ቤተ ክርስቲያንህ ያልዳኑትን ሰዎች ወደ ክርስቶስ ለማምጣትና አማኞች በሕይወታቸው እንዲያድጉ ለማገዝ የምታቀርባቸውን ትምህርቶችና ስብከቶች ሚዛናዊ ታደርጋለች? መልስህን እብራራ። መ) ቤተ ክርስቲያንህ እንዴት የተጠናከረ የትምህርት ፕሮግራም ልትዘረጋ እንደምትችል የበኩልህን አስተያየት ስጥ።

የቲቶ መልእክት ከመጋቢያዊ መልእክቶች አንዱ ሲሆን፥ ጳውሎስ ቲቶ የቤተ ክርስቲያንን አመራር ስለሚያደራጅበት መንገድ የሰጠውን ማብራሪያ ያካትታል። ምንም እንኳ የቲቶ መልእክት የተጻፈው የ1ኛና 2ኛ ጢሞቴዎስ መልእክቶች በተጻፉበት ጊዜ ቢሆንም፥ ቀደምት የእምነት አባቶች 2ኛ ጢሞቴዎስን ተከትሎ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንዲሰፍር አድርገውታል። ይህንንም ያደረጉት የ1ኛና የ2ኛ ጢሞቴዎስ መልእክቶች ጎን ለጎን እንዲቀመጡ በማሰብ ነው።

የውይይት ጥያቄ፡– ስለ ቲቶ ከመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት አንብብ። ስለ ጸሐፊው፥ መልእክቱን ስለሚቀበሉት ሰዎችና ስለ መጽሐፉ የተሰጠውን ማብራሪያ ጠቅለል አድርገህ ጻፍ።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: