የሕይወት እንጀራ

ወደ ቲቶ

የጸጋው ወንጌል የተለወጠ አኗኗርን እንደሚያካትት ማስተማር (ቲቶ 2፡11-3፡15)

ወንጌል አማኞች መንፈሳዊ ያልሆኑትን ነገሮች እንዳያደርጉ ያስተምራል (ቲቶ 2፡11-3፡8)። ለመንፈሳዊ ጉዞ ቁልፉ ሚዛናዊነት ነው። ብዙውን ጊዜ ሐሰተኛ ትምህርት ክርስቲያኖች በእምነታችንና በተግባራችን ሚዛናዊነት የጎደለው እርምጃ እንድንወስድ ይገፋፋናል። የሚዛናዊነት መዛባትና የተሳሳተ ትምህርት ወደ ቤተ ክርስቲያን ከሚገቡባቸው መንገዶች አንዱ ድነት (ደኅንነትን) ባገኘንበትና በምንመላለስበት መንገድ መካከል ባለው ግንኙነት ነው። የአዲስ ኪዳን ዋነኛ ትምህርት በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን መዳናችንን መግለጽ ነው። እርሱ ከጸጋው የተነሣ በነፃ የዘላለም ሕይወት ይሰጠናል። ምንም እንኳ ሰይጣን ሁልጊዜም ድነት (ደኅንነትን) ለማግኘት ወይም ያገኘነውን ድነት (ደኅንነት) ጠብቀን ለማቆየት መልካም መሆን ወይም መልካም ሥራ መሥራት እንዳለብን ለማሳሰብ ቢፈልግም፥ መጽሐፍ ቅዱስ ድነት (ደኅንነት) ክርስቶስ በመስቀል ላይ ስለ እኛ ኃጢአት መሞቱን ባመንንበት ጊዜ በነፃ የምናገኘው ስጦታ መሆኑን ይናገራል። ነገር ግን ይህም ትምህርት ሚዛናዊነቱን ሊያጣ ይችላል። የቀርጤስ አማኞች፥ «ድነት (ደኅንነት) የሚገኘው በእምነት ብቻ ከሆነ፥ በክርስቶስ ካመንን በኋላ እንደፈለግን ልንኖር እንችላለን» የሚሉ ይመስላል። ስለሆነም ጳውሎስ ምንም እንኳን ድነት የሥራችን ውጤት ባይሆንም፥ እግዚአብሔር እኛን ካዳነባቸው ዓላማዎች አንዱ ሕይወታችንን መለወጥ እንደሆነ ይናገራል። «ሰዎችን ሁሉ የሚያድን የእግዚአብሔር ጸጋ ተገልጧልና ይህም ጸጋ ኃጢአተኝነትንና ዓለማዊን ምኞት ክደን ራሳችንን በመግዛትና በጽድቅ እግዚአብሔርን በመምሰል በአሁኑ ዘመን እንድንኖር ያስተምረናል»። እግዚአብሔርን በሚያስከብር መንገድ የማይመላለስ ሰው አንድም ከልቡ አላመነም (የአእምሮ እውቀት ብቻ አለው) ወይም ወንጌሉ ምን እንደሆነ በትክክል አልተገነዘበም ማለት ነው። ወይም ደግሞ በእግዚአብሔር ላይ በማመጽ እየተመላለሰ በመሆኑ ለፍርድ ራሱን ያጋልጣል። ክርስቶስ እኛን ከኃጢአት በማዳኑ፥ ለንጹሕ ሕይወትና መልካም ሥራ  አድኖናል። እግዚአብሔርን የሚያስከብር ሕይወት ለመኖር ልንለወጥባቸው የሚገቡ አንዳንድ መንገዶች ምን ምንድን ናቸው? በቤተ ክርስቲያንም ሆነ በማኅበረሰብ ውስጥ መሪዎችን በመታዘዝ፡፡ ሌሎችን በፍቅር በመርዳት፡፡ ስለሌሎች ክፉ እንዳንናገር (እንዳንሳደብ) አንደበታችንን በመግዛት። 4 ከሌሎች ጋር በሰላም በመኖርና ለሌሎች በማሰብ። የራሳችንን መንገድ ወይም የግል ክብር ከመሻት ይልቅ እግዚአብሔርን በትሕትና በማገልገል። የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) በቤተ ክርስቲያንህ ውስጥ ከሚገኙት ምእመናን አብዛኞቹ በእነዚህ አምስት መንገዶች እግዚአብሔርን ለማስከበር ቢሹ፣ በቤተ ክርስቲያንህና በማኅበረሰብህ ውስጥ ምን ዓይነት ለውጦች የሚከሰቱ ይመስልሃል? ለ) ብዙ ከርስቲያኖች በዚህ መንገድ የማይመላለሱት ለምን ይመስልሃል? የቤተ ክርስቲያን መሪ ከሐሰተኛ አስተማሪዎች ጋር የማያባራ ሙግት መግጠም የለበትም (ቲቶ 3፡9-11)። ሐሰተኛ ትምህርት ወደ ቤተ ክርስቲያን ሾልኮ በሚገባበት ጊዜ፥ የቤተ ክርስቲያን መሪ በቀላሉ በማያቋርጥ ክርክሮች ሊጠመድ ይችላል። ከእነዚህ ሐሰተኛ ትምህርቶች አብዛኞቹ የሞኝነት ነገሮች ሲሆኑ፥ ሌሎች ደግሞ አደገኞች ናቸው። የቤተ ክርስቲያን መሪ የሞኝነት ሐሳቦችን ማራቅ ይኖርበታል። አደገኛ የሆኑትን ሐሰተኛ ትምህርቶች ግን መዋጋት አለበት። የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ከክርስቶስ ያገኙትን ሥልጣን በመጠቀም ሐሰተኛ ትምህርት የሚያስተምሩትንና የሚያምኑትን ሰዎች መገሠጽ አለባቸው። እንዲህ ዓይነቱ እርምጃ በመሪው አሳቦች ወይም ምርጫዎች ላይ ሳይሆን፣ በእግዚአብሔር ቃል ላይ መመሥረት እንዳለባቸው ቀደም ብለን ተመልክተናል። ሐሰተኛ ትምህርቶችን የሚከተል የቤተ ክርስቲያን መሪ የመሪዎችን ምክር በማይሰማበት ጊዜ በተደጋጋሚ ማስጠንቀቁ ተገቢ ነው፡፡ ነገር ግን የዐመጻኝነት መንፈሱ የማይፈወስ ከሆነ፥ ቤተ ክርስቲያን ግለሰቡን መቅጣት አለባት። መደምደሚያ (ቲቶ 3፡12-15) ጳውሎስ መልእክቱን ሲደመድም ለቲቶ አንዳንድ ግላዊ ትእዛዛትን ይሰጣል። ጳውሎስ አጢሞን ወይም ቲኪቆስ ቲቶን መጥተው እንደሚተኩት ይናገራል። በዚህ ጊዜ ቲቶ ወደ ኒቃፖሊስ መጥቶ ከጳውሎስ ጋር ይገናኛል። ዜማስና አጵሎስ ምናልባትም ለቲቶ የጳውሎስን መልእክት ያደረሱ ሰዎች ሳይሆኑ አይቀሩም። ከዚያ በኋላ ጳውሎስ መልእክቱን በሰላምታ ይደመድማል። የውይይት ጥያቄ፡- ከቲቶ መጽሐፍ ስለ አመራር ወይም እግዚአብሔርን በሚያስከብር መንገድ ስለመመላለስ የተማርካቸውን አንዳንድ ጠቃሚ እውነቶች ዘርዝር። (ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የጸጋው ወንጌል የተለወጠ አኗኗርን እንደሚያካትት ማስተማር (ቲቶ 2፡11-3፡15) Read More »

ሁሉንም የዕድሜ ክፍሎች በማስተማር ቤተ ክርስቲያንን ማጠናከር (ቲቶ 2፡1-10)

እውነትን ማስተማር በሁሉም የቤተ ክርስቲያን መሪ የብቃት መመዘኛዎች ዝርዝር ውስጥ ሰፍሮ ይገኛል። አንድ የቤተ ክርስቲያን መሪ እውነትን እንዲያስተምር ከተፈለገ አራት ነገሮች ያስፈልጉታል። መሪው ራሱ እውነትን ማወቅ ይኖርበታል። የወንጌሉን መሠረታዊ እውነቶች የማያውቅ መሪ ለቤተ ክርስቲያን አመራር ከሚያስፈልጉ ወሳኝ መመዘኛዎች አንዱ ይጎድለዋል። በግል የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፥ መጻሕፍትን በማንበብ፥ በቡድን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች፥ ወይም በመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ገብቶ በመማር፥ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች እውነትን ማወቅ ይኖርባቸዋል። መሪ እውነትን በሚያንጸባርቅ መልኩ መመላለስ አለበት። መጽሐፍ ቅዱስን የምናጠናው የአእምሮ ዕውቀት ለማግኘት ብቻ አይደለም። ነገር ግን የምንማራቸውን እውነቶች በዕለት ተዕለት ሕይወታችን ተግባራዊ ማድረግ ይኖርብናል። መሪ ለማስተማር የሚችል መሆን አለበት። አንዳንድ ሰዎች እውነተኛና መንፈሳዊ የሆነውን ነገር ቢያውቁም፥ ለሌሎች የማስተማር ብቃት የላቸውም፥ ጳውሎስ ዋና አገልግሎት በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ማስተማር እስከሆነ ድረስ፥ መሪ የማስተማር ስጦታ ሊኖረው እንደሚገባ ያስገነዝባል። ለዚህም ነው መጽሐፍ ቅዱስ ከዐበይት መንፈሳዊ ስጦታዎች አንዱ ማስተማር እንደሆነ የሚያብራራው (1ኛ ቆሮ. 12፡28 አንብብ)። መሪ ለማስተማር ጊዜ መውሰድ አለበት። ብዙ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ሌሎች ተግባራትን በማከናወን ራሳቸውን ስለሚያባክኑ ለማስተማሪያ የሚሆን ጊዜ የላቸውም። በዛሬው ዘመን ብዙ ሰዎች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በአግባቡ ትምህርት አያገኙም። ይህም ሆኖ በእያንዳንዱ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ አምስት ወይም ከዚያ የሚበልጡ ሽማግሌዎች አሉ። እነዚህ ሽማግሌዎች ለአባሎቻቸው እውነትን የሚያስተምሩበትን መንገድ ማግኘት ይኖርባቸዋል። መሪዎች ምእመኖቻቸውን ማስተማር ካላስፈለጋቸው፥ እግዚአብሔር የማስተማር ብቃት እንዲኖራቸው የሚጠይቀው ለምን ይሆን? የሚያሳዝነው በቤተ ክርስቲያን ውስጥ አብዛኞቹ ሽማግሌዎች በማስተማር አገልግሎት ላይ የማይሳተፉ መሆናቸው ነው። ወይም ደግሞ የሚያስተምሩት እሑድ ጧት ብቻ ይሆናል። ጳውሎስ ቲቶ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ለተለያዩ ቡድኖች ትኩረት በመስጠት ፍላጎታቸውን የሚያሟላ ትምህርት እንዲሰጣቸው ያብራራል። የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) የቤተ ክርስቲያንህ መሪዎች የማስተማርን አገልግሎት በአግባቡ የማይወጡት በቀዳሚነት ከእነዚህ አራት ምክንያቶች ከየትኛው የተነሣ ነው? ለ) ይህን ሁኔታ ለመለወጥ ምን ሊደረግ ይገባል? አረጋውያንን ማስተማር (ቲቶ 2፡1-2)። ጳውሎስ ቲቶ ጤናማ ትምህርትን እንዲያስተምር ያሳስበዋል። ጳውሎስ ይህን ሊል የመጽሐፍ ቅዱስን ዐበይት እውነቶች ማለቱ ነው። ጳውሎስ ቲቶ ለአረጋውያን አማኞች የማይለወጠውን የእግዚአብሔርን ቃል እውነት ማስተማር እንዳለበት ያስገነዝበዋል። ለመሆኑ አረጋውያን የሚማሩት ለምንድን ነው? ጳውሎስ አረጋውያን ባሕሪያቸውን ለመለወጥ የእግዚአብሔርን ቃል መማር እንዳለባቸው ያስረዳሉ። ውሸታሞች፥ የማይታመኑና ሰነፎች ከመሆን ይልቅ ጭምቶች፥ ሊከበሩ የሚገባቸው፥ ራሳቸውን የሚገዙ፥ በእምነት፥ በፍቅርና በትዕግሥት የተሞሉ መሆን ያስፈልጋቸው ነበር። እነዚህ አረጋውያን በባህላቸው ከታወቀው ሁኔታ የተለየ ሕይወት መምራት ያስፈልጋቸው ነበር። አሮጊቶች (ቲቶ 2፡3-5)። ቲቶ አሮጊቶችንም ማስተማር ያስፈልገው ነበር። አሁንም ጳውሎስ ትኩረት ያደረገው በባሕሪና ተግባር ለውጥ ላይ ነው። በአሉታዊ ጎኑ፥ አሮጊት ሴቶች አንደበታቸውን በመግዛት ሰዎችን ከመሳደብ ወይም ከማማት መቆጠብ ያስፈልጋቸው ነበር። ለስካር እንዳይጋለጡ የሚጠጡትን መጠን መወሰን ያስፈልጋቸው ነበር። በአዎንታዊ ጎኑ፥ በአኗኗራቸው እግዚአብሔርን ማስከበር ያስፈልጋቸዋል። በአኗኗራቸውና በትምህርታቸው ለወጣት ሴቶች አዎንታዊ ተጽዕኖ ማሳደር ያስፈልጋቸዋል። አሮጊቶች ወጣት ሴቶች ራሳቸውን እንዲገዙ፥ ንጹሕ ሕይወት እንዲመሩ፥ ደጎች እንዲሆኑና መንፈሳዊ ቤቶች እንዲኖሯቸው፥ እንዲሁም ባሎቻቸውን እንዲያከብሩ ማስተማር ያስፈልጋቸዋል። ይህም በተለወጠ ሕይወታቸው እግዚአብሔርን ከማሰደብ ይልቅ እንዲያስከብሩ ያስችላቸዋል። ወጣት ወንዶች (ቲቶ 2፡6-8)። ቲቶ እንደ ጢሞቴዎስ ወጣት የነበረ ይመስላል። የቤተ ክርስቲያን መሪ እንደ መሆኑ መጠን፥ የዕድሜ እኩያዎቹ ለሆኑት ሰዎችም ኃላፊነት ነበረበት። ለእነዚህ ወጣት ወንዶች የሚያስተምረው ዋንኛ ባሕሪ ራስን ስለመግዛት ነበር። ወጣቶች ምኞታቸው፥ አሳባቸውና ፍላጎታቸው እንዲቆጣጠራቸው ከመፍቀድ ይልቅ በእግዚአብሔር ፈቃድ መመላለስ ያስፈልጋቸው ነበር። ለመሆኑ ወጣቶችንና ሌሎችንም የሚያስተምረው እንዴት ነው? በእነዚህ ርእሰ ጉዳዮች ላይ የክፍል ውስጥ ትምህርት በመስጠት ይሆን? አይደለም። ጳውሎስ ጢሞቴዎስ በሁሉም የዕድሜ ክልል ላሉት ሰዎች በመንፈሳዊ ሕይወቱ ምሳሌ በመሆን እንዲያስተምራቸው ያሳስባል። ሕይወቱ እውነተኛነትን፥ ተገቢ ንግግርን፥ መንፈሳዊነትን፥ ወዘተ… ማሳየት ነበረበት። የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ጳውሎስ በዚህ የአረጋውያን፥ የአሮጊቶች፥ የወጣቶች ዝርዝር ውስጥ ቢያንስ ሦስት ጊዜ ራስን ስለመግዛት ገልጾአል። ይህ ባሕሪ ለሁሉም የዕድሜ ክፍሎች አስፈላጊ የሆነው ለምን ይመስልሃል? ጳውሎስ ቲቶ መንፈሳዊ ባሕሪን በሞዴልነት ለሰዎች እንዲያሳይ የጠየቀው ለምንድን ነው? ሐ) በሕይወትህ የሚያስቸግሩህ ባሕርያት የትኞቹ ናቸው? እነዚህ ባሕርያት በሕይወትህ ውስጥ እንዲታዩ ምን እያደረግክ ነው? መ) በቤተ ክርስቲያንህ እነዚህን እውነቶች እንዴት እያስተማርክ ነው? ባሮች (ቲቶ 2፡9-10።) ጳውሎስ በመጨረሻ ፥ ለባሮችም (ሠራተኞች) የእግዚአብሔርን ቃል ማስተማር እንደሚያስፈልግ ይናገራል። በጌቶቻቸው ሥር የሚተዳደሩ አማኝ ባሮች በአግባቡ ባይያዙም ምሳሌያዊ ሕይወት መኖር ያስፈልጋቸው ነበር። ጌቶቻቸውን ለመታዘዝና ለማስደሰት መጣር፥ ታማኞችና እምነት የሚጣልባቸው መሆን ያስፈልጋቸው ነበር። ይህ ክርስትናን ያስከብር ነበር። አጭበርባሪዎች፥ ሰነፎች፥ ሌቦች፥ የማይታዘዙ ወይም ተጨቃጫቂዎች የሆኑ እንደሆነ የክርስቶስን ስም ያሰድባሉ። (ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

ሁሉንም የዕድሜ ክፍሎች በማስተማር ቤተ ክርስቲያንን ማጠናከር (ቲቶ 2፡1-10) Read More »

ብቃት ያላቸውን የቤተ ክርስቲያን መሪዎች መሾም (ቲቶ 1፡1-16)

ጥሩ ወጥ ለመሥራት ጥራት ያላቸውን ቅመሞች በተገቢው መጠን መጨመር እንደሚያስፈልግ ሁሉ፥ ጤናማ ቤተ ክርስቲያን ለመመሥረትም አንዳንድ ነገሮች ሊካተቱ ይገባል። ቲቶ የሚያገለግላትና በቀርጤስ ደሴት የምትገኝ ቤተ ክርስቲያን አዲስና ብዙም መንፈሳዊነት የማይታይባት ነበረች። ጳውሎስ ቲቶ ይህቺን ያልበሰለች ቤተ ክርስቲያን ክርስቶስን ወደምታስከብር በሳል ቤተ ክርስቲያንነት እንዲለውጥ አደፋፍሮታል። ጳውሎስ ለዚህ ተግባር የሚከተሉትን ነገሮች እንዲያደርግ ያበረታታዋል። ሀ) መንፈሳዊ አመራር፥ ለ) የሐሰት ትምህርቶችን መከላከል፥ ሐ) በሁሉም የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ሰዎች ባሕሪያቸውንና አኗኗራቸውን የሚለውጥ የትምህርት ፕሮግራም መከታተልና መ) ወንጌሉን በግልጽ መረዳት። ድነት (ደኅንነት) የሚገኘው በኢየሱስ ክርስቶስ ሞት በማመን መሆኑንና የዳኑ ሰዎች ግን እግዚአብሔርን በሚያስከብር መንገድ መመላለስ እንዳለባቸው ማወቅ ያስፈልጋቸው ነበር። መግቢያ (ቲቶ 1፡1-4) ሐዋርያው ጳውሎስ እግዚአብሔር ከእርሱ የሚፈልገውን ነገር በትክክል ያውቅ ነበር። ጳውሎስ ሕይወቱን በሙሉ እግዚአብሔር በሚፈልገው መንገድ የሚኖር ባሪያ ነበር። ምንም እንኳ ይህ እስራትና ሞትን ቢያስከትልበትም፥ ጳውሎስ የእግዚአብሔርን ፈቃድ ለማድረግ የቆረጠ አገልጋይ ነበር። እንዲሁም ኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌሉን እንዲሰብክ የሾመው ሐዋርያ ነበር። ወንጌሉ እግዚአብሔር ለጳውሎስ የገለጸውን የማይለወጥ እውነት የያዘ ነበር። ሰዎች የዘላለምን ሕይወት የሚያገኙት እግዚአብሔር የገለጠው እውነት ሲሰበክና ይህንኑ እውነት ሲያምኑ ነው። ነገር ግን ሕይወትን የማይለወጥ እውነት መስበኩ ብቻ በቂ አይደለም። ወንጌሉ የተለወጠ ሕይወት በማስከተል ሰዎች መንፈሳዊ አኗኗር እንዲከተሉ ያደርጋልና። ወንጌሉ የሚቀርበው በሚከተለው ቅደም ተከተል ነው። ) የእግዚአብሔር እውነት ይሰበካል፥ 2) ሰዎች በኢየሱስ ክርስቶስ ያምናሉ፥ 3) ወንጌሉን የሚያንጸባርቅ ሕይወት ይኖሩ ዘንድ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል አማኞች አኗኗራቸውን ይቀይራሉ። ይህንን ቅደም ተከተል ስንቀይርና በቀዳሚነት ሰዎች ከድነት (ደኅንነት) በኋላ ሊያሳዩ በሚገቧቸው ለውጦች ላይ ስናተኩር፥ ብዙውን ጊዜ ወንጌሉ ይለወጥና ሰዎች ድነት (ደኅንነትን) ለማግኘት መልካም ተግባር ማከናወን እንዳለባቸው ያስባሉ። በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ተገቢውን አመራር ማደራጀት (ቲቶ 1፡5-9) ምናልባትም ጠንካራ ቤተ ክርስቲያን እንድትመሠረት የሚያደርገው እጅግ ወሳኙ ነገር ትክክለኛ መሪዎች መመረጣቸው ይሆናል። ብዙውን ጊዜ ቤተ ክርስቲያን ደካማ የምትሆነው ሀ) መሪዎች በእምነታቸው ደካማ ሲሆኑ፥ ለ) የመንፈሳዊነት ሞዴሎች ሆነው ባለመመለሳቸው፥ ወይም ሐ) አማኞችን በትክክል ባለማስተማራቸው ሊሆን ይችላል። የውይይት ጥያቄ፡- እነዚህ ሦስት ነገሮች የቤተ ክርስቲያንን ዕድገት ሲገድሉ የተመለከትከበትን ሁኔታ ግለጽ። ጳውሎስ ቲቶ በአዲሲቷ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንዲያደርግ የፈለገው የመጀመሪያው ነገር ትክክለኛ መሪዎችን መሾም ነበር። ቲቶ በዚህች አዲስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ መሪዎችን ለመምረጥ ምን ዓይነት የመሪነት ብቃቶችን መመዘኛ አድርጎ መጠቀም ያስፈልገው ነበር? ጳውሎስ ለቲቶ የዘረዘራቸው የብቃት መመዘኛዎች በአብዛኛው ለጢሞቴዎስ የዘረዘራቸው ናቸው (1ኛ ጢሞ. 3፡1-13)። ለመሪዎች የሚያስፈልጉ የብቃት መመዘኛዎች የሚከተሉትን ያካትታሉ። ነቀፋ የሌለበት ይህም በባሕሪው፥ ከሰዎች ጋር ባለው ግንኙነትና ከገንዘብ ጋር ባለው ግንኙነት፥ ወዘተ… ያጠቃልላል። የአንዲት ሚስት ባል፥ ብዙ ሚስቶች የሌሉት የሚያምኑ ልጆችና በሥርዓት የተያዘ ቤተሰብ ያለው መሪ ክርስቲያናዊ ቤተሰብ ምን መምሰል እንዳለበት በሞዴልነት የሚያሳይ አገልጋይ ነው። መሪነቱን የማስተማር ብቃቱ በልጆቹ ባሕሪና ተግባር መታየት ይኖርበታል። ከሰዎች ጋር ባለው ግንኙነት ተገቢውን ባሕሪ ማንጸባረቅ አለበት። የማይጠጣ፥ የማይበሳጭ፥ የማይጣላና እንግዳ ተቀባይ መሆን ይኖርበታል። የአልኮል መጠጦች ቁራኛ ያልሆነ ለሀብትና ገንዘብ ትክክለኛ አመለካከት ያለው መንፈሳዊ ባሕሪ ያለው፥ ራሱን የሚገዛ፥ ቀጥተኛ ሥነ ምግባራዊ ሕይወት የሚኖርና የተቀደሰ እውነትን የሚያውቅ፥ የሚጠብቅና የሚያስተምር የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ብዙ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች የሚወድቁባቸው ብቃቶች የትኞቹ ናቸው? ለ) እነዚህ ብቃቶች በቤተ ክርስቲያን መሪዎች ሕይወት ውስጥ መንጸባረቃቸው አስፈላጊ የሚሆነው ለምንድን ነው? ሐ) በእነዚህ በቲቶ መልእክት ውስጥ ከተገለጡት በተጨማሪ ዛሬ ትኩረት የምንሰጣቸው ሌሎች የብቃት መመዘኛዎች የትኞቹ ናቸው? በ1ኛ ጢሞቴዎስ ውስጥ እንደተመለከትነው፥ ጳውሎስ አጽንኦት የሚሰጥባቸው ዐበይት የብቃት መመዘኛዎች የግለሰቡ ባሕሪና መንፈሳዊነት፥ ቤተሰባዊ ሕይወቱ፥ ከሌሎች ሰዎች ጋር ያለው ግንኙነትና እውነትን የማስተማር ብቃቱ ናቸው። ጳውሎስ ዛሬ አስፈላጊ ናቸው ብለን የምናስባቸውን እንደ የትምህርት ደረጃ ፥ የጎሳ ሥረ መሠረት፥ ሀብት፥ ወዘተ… አይጠቅስም። በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ችግሮች በሚኖሩበት ጊዜ፥ በአመዛኙ የችግሩ ምንጭ የሚውለው ከመሪዎች ላይ ነው። በመሪዎች መካከል ችግሮች የሚከሰቱት ደግሞ በአብዛኛው ጳውሎስ መሪዎችን ለመምረጥ መሠረታዊ አድርጎ የሚጠቅሳቸው ባሕርያት ስለሌሉአቸው ነው። ብዙውን ጊዜ በመሪዎች ላይ የምናጉረመርም ከሆነ ምናልባትም ችግሮቹ ራሳችን እንሆናለን። የምናገኘው የምንመርጠውን ነው። ምርጫችን በተሳሳተ መመዘኛ ላይ የተመሠረተ ከሆነ፥ የሚጨቁኑንን ወይም እንደ ፖለቲካ መሪዎች የሚያጉላሉንን መሪዎች እናጭዳለን። ነገር ግን በመጽሐፍ ቅዱሳዊ መመዘኛዎች ላይ ተመሥርተን ከመረጥን፥ እግዚአብሔርን የምታስከብር ቤተ ክርስቲያን ትኖረናለች። ሐሰተኛ ትምህርቶችን መከላከል (ቲቶ 1፡10-16) የቀድሞይቱ ቤተ ክርስቲያን እኛ እንደምናስበው ፍጹም አልነበረችም። ምክንያቱም ልክ እንደ እኛው አብያተ ክርስቲያናቱ ከሐሰት ትምህርት ጋር ግብግብ ይፈጥሩ ነበር። በየትኛውም ዘመን ውስጥ በምትኖር ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ችግሮች፥ ክፍፍሎችና ሐሰተኛ ትምህርቶች ከውስጥ ሊመነጩ፥ ከውጭ ደግሞ ስደት ሊመጣ ይችላል። ጳውሎስ ቲቶ ስለ ሐሰተኛ ትምህርት ጥንቃቄ እንዲያደርግ ያሳስበዋል። ቀርጤስ አዲስ ቤተ ክርስቲያን ብትሆንም፥ ሐሰተኛ አስተማሪዎች ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር የማይዛመዱ ትምህርቶች በማቅረብ ላይ ነበሩ። እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ሲያጋጥም መሪዎች ምን ማድረግ ይኖርባቸዋል? እውነትን በማስተማር ሐሰተኛ አስተማሪዎችን ዝም ማሰኘት ይኖርባቸዋል። በጳውሎስ ዘመን፥ ዋንኛው የሐሰት ትምህርት የመነጨው ክርስቲያኖች ነን ከሚሉ አይሁዶች ነበር። እነዚህ ሰዎች ክርስቲያኖችን በእምነት ከሚገኝ ድነት (ደኅንነት) በሥራ ወደሚገኝ ድነት (ግርዘት፥ የብሉይ ኪዳንን ሕግጋት መጠበቅ፥ ወዘተ…) ለመለወጥ ፈልገው ነበር። አሁንም ከቤተ ክርስቲያን መሪዎች ዐበይት ኃላፊነቶች አንዱ ቤተ ክርስቲያንን ከሐሰተኛ አስተማሪዎች መጠበቅ መሆኑን እንመለከታለን። ይህንንም ለማድረግ፥ እውነትን ማወቅ ይኖርባቸዋል። (ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

ብቃት ያላቸውን የቤተ ክርስቲያን መሪዎች መሾም (ቲቶ 1፡1-16) Read More »

የቲቶ መልዕክት ልዩ ባሕርያት እና አስተዋጽኦ

የቲቶ ልዩ ባሕርያት 1) ቲቶ ስለ ክርስቶስ አምላክነት ግልጽ የሆነ ትምህርት ያቀርባል። በቲቶ መልእክት ውስጥ ክርስቶስ ታላቅ አምላክና አዳኝ ተብሎ ተጠቅሷል። ይህም ብዙውን ጊዜ ለእግዚአብሔር አብ የሚያገለግል ስያሜ ነው (ቲቶ 2፡13)። 2) የቲቶ መጽሐፍ በ1ኛ ጢሞቴዎስ ውስጥ የሚገኙትን አብዛኞቹን ጉዳዮች ይዳስሳል። የሽማግሌዎች ምርጫ፥ የሴቶችና የባሪያዎች ሚና፥ እንዲሁም ሐሰተኛ ትምህርቶችን መከላከል የሚሉ ዐቢይ ነጥቦች በሁለቱም መጻሕፍት ውስጥ ይገኛሉ። 3) ቲቶ ከማናቸውም የጳውሎስ መልእክቶች በላይ በተገቢው እምነትና መንፈሳዊ ባሕሪ መካከል ያለውን ግንኙነት በግልጽ ያሳያል። ከተገለጹት ሐረጎች መካከል «መልካም ባሕሪ» የሚለው ይገኝበታል። ይህም የክርስቶስን ስም የሚጠሩ ሰዎች እንደ እግዚአብሔር ልጆች ሊመላለሱ እንደሚገባ ያሳያል። 4) ቲቶ ወንጌል ምን እንደሆነ ጠቅለል አድርጎ ያቀርባል። በቲቶ 2፡11-13 የጸጋው ወንጌል ምን ዓይነት ውጤቶችን እንደሚያስከትል ተገልጾአል። ወንጌል፥ መንፈሳዊ ያልሆኑትን ባሕሪዎች እንዳንከተልና መንፈሳዊ አኗኗርን እንድንሻ ያደርገናል። በቲቶ 3፡4-8፥ ጳውሎስ መንፈስ ቅዱስ በክርስቶስ ወደሚያምኑት ሕይወት ስለሚያመጣቸው እንደ ምሕረት፥ ድነት (ደኅንነት) እና ተሐድሶ በመሳሰሉት ነገሮች ላይ ያተኩራል። አሁንም ጳውሎስ ትክክለኛ እምነት እንዴት ወደ መንፈሳዊ አኗኗር እንደሚመራ አጽንኦት ሰጥቶ ገልጾአል። የቲቶ አስተዋጽኦ ይህ የቲቶ መልእክት አንድ የቤተ ክርስቲያን መሪ በአዲስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሊያደራጃቸው ስለሚገቡ የተለያዩ ነገሮች የሚናገር ተግባራዊ መልእክት ነው። በመሆኑም፥ እነዚህ ነገሮች መሪዎች ጤናማ ቤተ ክርስቲያን ለመመሥረት የሚጠቀሙባቸውን መሠረታዊ እውነቶች ያቀርባሉ። ጳውሎስ ጢሞቴዎስ አዲሷን ቤተ ክርስቲያን እንዴት እንደሚያደራጅ በሚመክርበት ጊዜ ግልጽ አስተዋጽኦ ከመከተል ይልቅ ከርእሰ ጉዳይ ወደ ርእሰ ጉዳይ እያለፈ የተለያዩ ትምህርቶችን ያቀርባል። የቲቶ መልእክት አጠቃላይ መዋቅር የሚከተለውን ይመስላል፡ ብቃት ያላቸውን መሪዎች መሾም (ቲቶ 1፡1-9) ሀ) መግቢያ (ቲቶ 1፡1-4) ለ) በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ተገቢውን አመራር መመሥረት (ቲቶ 1፡5-9)። የሐሰት ትምህርቶችን ስለመከላከል (ቲቶ 1፡10-16) ለሁሉም የዕድሜ ክፍሎች ግልጽ ትምህርት በማቅረብ ቤተ ክርስቲያንን ማጠናከር (ቲቶ 2፡1-10) ሀ) አረጋውያንን ማስተማር (ቲቶ 2፡1-2) ለ) አረጋውያን ሴቶችን ማስተማር (ቲቶ 2፡3-5) ሐ) ወጣት ወንዶችን ማስተማር (ቲቶ 2፡6-8) መ) ባሮችን ማስተማር (ቲቶ 2፡9-10) 4 የጸጋው ወንጌል የተለወጠ አኗኗርን እንደሚያስከትል ማስተማር (ቲቶ 2፡11-3፡5) ሀ) ወንጌል አማኞች መንፈሳዊ ያልሆኑትን ልምምዶች እንዳይከተሉ ያደርጋል (ቲቶ 2፡11-3፡8)፡፡ ለ) የቤተ ክርስቲያን መሪ ከሐሰተኛ አስተማሪዎች ጋር ማቆሚያ የሌለው ክርክር መግጠም የለበትም (ቲቶ 3፡9-11)፡፡ ሐ) ድምዳሜ (ቲቶ 3፡12-15) (ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የቲቶ መልዕክት ልዩ ባሕርያት እና አስተዋጽኦ Read More »

የቲቶ መጽሐፍ ዓላማ

የመጀመሪያው ዓላማ፡- ቲቶ በቀርጤስ ቤተ ክርስቲያን እንዴት እንደሚያደራጅ መግለጽ። ጳውሎስ ቲቶ መሪዎችን እንዲመርጥና አማኞች ደግሞ እምነታቸውን የሚያንጸባርቅ ሕይወት እንዲኖሩ ያበረታታቸው ዘንድ ይህን መልእክት ጽፎአል። ቲቶ ከጳውሎስ የተቀበለው አገልግሎት አስቸጋሪ ነበር። ቤተ ክርስቲያኒቱ በቅርብ ጊዜ የተመሠረተች አዲስ ነበረች። ይህ ጢሞቴዎስ በሚገባ በተደራጀች የኤፌሶን ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ከሚያበረክተው አገልግሎት የተለየ ነበር። የቀርጤስ ሰዎች ያልተማሩ። ውሸታሞች፥ የማይታመኑ፥ ለመብላት ብቻ የሚኖሩ፥ ሰነፎች፥ ወዘተ… በመሆናቸው ባሕሪያቸው በጣም አስቸጋሪ ነበር። ጳውሎስ በክርስቶስ ላይ ያለን እምነት ባሕሪያችንን መለወጥ እንዳለበት አጽንኦት ሰጥቶ የሚናገረው ለዚህ ሳይሆን አይቀርም። ይህ በተለይ ለመሪዎች እጅግ አስፈላጊ ነው። ይህም እግዚአብሔር የብሉይ ኪዳንን ሕዝብ የጸኑትን አይሁዶች ብቻ በወንጌል ለመለወጥ አለመፈለጉን ያሳያል። እንደ ግሪኮች ያሉትን የሠለጠኑ ሕዝቦች ብቻም አልነበረም የሚፈልገው፥ ላልተማሩና ብዙ ሕዝብ የማይስብ ባህል ላላቸው ሕዝቦችም ይገደዋል። እግዚአብሔር ለቀርጤስ ሕዝብ የሚገደው ከሆነ፥ ለዘላኖች፥ ሸክላ ሠሪዎች፥ ብረት ቀጥቃጮች፥ እንዲሁም በዓለም በየትኛውም ስፍራ ለሚኖር ሕዝብ እንደሚገደው ግልጽ ነው። ቤተ ክርስቲያን የተናቁ ናቸው ብላ የምታስባቸውን የሕዝብ ክፍሎች በወንጌል ለመድረስ በማትፈልግበት ጊዜ የምእመኖቿ የክርስቶስን ምሳሌነት እየተከተሉ አለመሆናቸውን መመልከት ይችላል። ለሰዎች ሁሉ የሚራራ የእግዚአብሔርም ልብ እንደሌላቸው ግልጽ ነው። ወንጌሉ የተለያየ ባህል ወዳሏቸው ሕዝቦች የሚደርስበት ጊዜ፥ አማኞቹ እግዚአብሔርን የማያስከብረውን የባህላቸውን ክፍል መከተል አይኖርባቸውም። ነገር ግን መጽሐፍ ቅዱስ የባህሎች ሁሉ ዳኛ ሆኖ መቀመጥ ይኖርበታል። የየትኛውም ባህል ተከታዮች የሆኑ ሕዝቦች እግዚአብሔር ከባህላቸው ውስጥ የትኛው እርሱን እንደማያስከብረው እንዲያሳያቸው ሊጠይቁትና ይህንኑ ባህሪ ሊለውጡት ይገባል። አንድ ባህል ውሸት፥ አለመተማመንና ስርቆት ተገቢ እንደሆነ ቢያስተምር፥ የእግዚአብሔር ቃል እነዚህን የባህሉን ክፍሎች አማኞች ሊለውጡ እንደሚገባ ያስገነዝባል። ነገር ግን ወንጌል ሊለውጠው የሚገባውን እንዳለ መተው የሚገባውን የባህል ክፍል በምንገመግምበት ጊዜ በጥንቃቄ ማድረግ ይኖርብናል። ጳውሎስ ያልሠለጠኑትን የቀርጤስ ሰዎች በሚያስተምርበት ጊዜ፥ በየትኛውም ስፍራ የግሪክን ባህል እንዲከተሉ፥ ትምህርት እንዲከታተሉ፥ የተወሰነ የአለባበስ ስልት እንዲይዙ ወይም የተወሰነ ቋንቋ እንዲማሩ አልጠየቃቸውም። ከቃሉ ጋር በግልጽ በሚጣረሱ አካባቢዎች ካልሆነ በስተቀር፥ እግዚአብሔር ሕዝቦች ባህላቸውን እንዲከተሉ ይፈቅዳል። አንዳንድ ጊዜ የእግዚአብሔር ልጆች በሙሉ በአንድ ቋንቋ እንደሚያመልኩ፥ የተወሰነ የአለባበስ ስልት እንደሚከተሉ፥ ኳየሮች እንደሚኖሩዋቸው፥ በቆርቆሮ ቤቶች ውስጥ እንደሚጸልዩ፥ እንደሚማሩ፥ የምዕራባውያንን ልብሶች እንደሚለብሱ፥ ወዘተ. እናስባለን። አንዳንድ ወንጌላውያን ዘላኖች ይህንኑ የባህላቸውን ክፍሎች እንዲቀይሩ በተሳሳተ መንገድ ያስተምራሉ። ወንጌላውያን የእግዚአብሔርን ቃል እንደ ማስተማር ሰዎች የገዛ ባህላቸውን ትተው የእነርሱን ባህሎች እንዲከተሉ ያስተምራሉ። ይህ ቅኝ ገዢዎች ኋላ ቀር ባህል ያላቸውን ሰዎች የባእድ አገሮችን ባህሎች እንዲከተሉ ካስገደዱበት መንገድ ጋር የሚመሳሰል የተሳሳተ አመለካከት ነው። ወንጌላውያን መቃወም ያለባቸው ከእግዚአብሔር ጋር የሚቃረኑትን ባህሎች ብቻ ነው። ይህንኑም የሚያደርጉት እንደ ጳውሎስ እግዚአብሔር ክርስቲያኖች የሚጠብቃቸውን አዎንታዊ የባህሪ ለውጦች በማመልከት ሊሆን ይገባል። ሰዎች እንዴት ሊለወጡ እንደሚገባ የሚዘረዝሩ ሕጎችን ልንሰጣቸው አንችልም። ይህ ወንጌሉን የሰናይ ምግባራት ሃይማኖት ከማድረጉም በላይ፥ ባህላችንን በሌሎች ሰዎች ባህል ላይ እንድንጭን ያበረታታናል። ጳውሎስ ለአይሁዶች ወንጌልን ለማካፈል በፈለገ ጊዜ አይሁዳዊ ሆኖ እንደቀረበ ገልጾአል። ይህንን ያደረገው እንደ ዕብራውያን ሰዎች በመልበስ፥ ቋንቋቸውን በመናገርና ልክ እንደ እነርሱ በማምለክ ነበር። ለአይሁዶች ወንጌልን በሰበከ ጊዜ የአይሁዶችን ባህል ተከትሏል። የግሪክን ቋንቋ በመጠቀም፥ እንደ ግሪኮች በመልበስና እንደ ግሪኮች በማምለክ አገልግሎቱን ተወጥቷል። (በዚህ ጊዜ ግን ጳውሎስ እግዚአብሔር በግልጽ የከለከለውን የጣዖት አምልኮ አልተከተለም።) አይሁዶች ግሪኮች እንዲሆኑ ወይም ግሪኮች አይሁዶች እንዲሆኑ ከማስገደድ ይልቅ፥ ወንጌሉ የሚሰሙትን ይማርክ ዘንድ መልእክቱን ከሰሚዎቹ ባህል ጋር በሚጣጣም መልኩ ለማቅረብ መጣሩ ተገቢ ይሆናል (1ኛ ቆሮ. 9፡19-23)። የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) የእግዚአብሔር ቃል ከሚያስተምረው በግልጽ የሚጣረሱትን የባህልህን ክፍሎች በምሳሌነት ዘርዝር። አብዛኞቹ አማኞች መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረውን ይከተላሉ ወይስ እንደ ዓለማውያን በመኖር ተግባራቸው የባህላቸው ውጤት መሆኑን ለማመሃኛነት ያቀርባሉ? ለ) ከእግዚአብሔር ጋር በግልጽ የሚቃረኑትን የሌሎች ባህሎች ገጽታዎች ዘርዝር። ብዙውን ጊዜ ከራሳችን ይልቅ የሌሎችን ባህሎች ችግሮች መመልከት የሚቀልለን ለምንድን ነው? ሐ) ሚሲዮናውያን ወይም ከሌሎች ባህሎች የመጡ ወንጌላውያን ሰዎች ክርስቲያን ለመሆን ከፈለጉ ባህላቸውን መለወጥ እንዳለባቸው የሚያስተምሩበትን ሁኔታ ግለጽ። መ) ይህ አደገኛና እግዚአብሔር ከሚፈልገው ሁኔታ ጋር የማይጣጣመው ለምንድን ነው? ሠ) በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉትን አንዳንድ የተናቁ ባህሎች ዘርዝር። ብዙ ሰዎች ለእነዚህ ባህሎች ምን ዓይነት አመለካከቶች አሏቸው? ለእነዚህ ሰዎች ወንጌሉን ለመመስከርና በእኩልነት ወደ ቤተ ክርስቲያን እንዲመጡ ለማድረግ እንተ፥ ቤተ ክርስቲያንህ ወይም ሌሎች አብያተ ክርስቲያናት ምን እያደረጉ ናቸው? ሁለተኛ ዓላማ፡- ጳውሎስ መልእክቱን የጻፈው ለቲቶ ቢሆንም፥ ዓላማው የቀርጤስ አማኞች እንደ እግዚአብሔር ልጆች እንዴት መመላለስ እንዳለባቸው ማስተማር ነው። ጳውሎስ ቲቶ የእርሱ ተወካይ እንደሆነና የሚሰጣቸውን መልእክት ሊቀበሉ እንደሚገባ ለአማኞቹ ያስረዳል። ሦስተኛ ዓላማ፡- እግዚአብሔርን የምታከብር ጠንካራ ቤተ ክርስቲያን ለማደራጀት ምን ዓይነት ዐበይት ነገሮች እንደሚያስፈልጉ ለጢሞቴዎስና ለሌሎችም የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ለማስተማር። ጠንካራ ቤተ ክርስቲያን የመገንባቱ ተግባር በድንገት የሚከሰት ሳይሆን፥ ሁሉንም የዕድሜ ክልሎች በጥልቀት ማስተማርን የሚጠይቅ ነው። አራተኛ ዓላማ፡- ጢሞቴዎስና የቀርጤስ ቤተ ክርስቲያን እንዴት ሐሰተኛ ትምህርቶች እንደሚቋቋሙ ለመምከር። በቀርጤስ ቤተ ክርስቲያን የነበረው ሐሰተኛ ትምህርት ጠቅላላ ቤተሰቦችን እያወከ ያለ ይመስላል (ቲቶ 1፡11)። ቤተ ክርስቲያኒቱን እያጠቃ ያለው ሐሰተኛ ትምህርት ከአይሁዳውያን ክርስቲያኖች የመጣ ነበር። (ከተገረዙት ወገን፥ ቲቶ 1፡10፣ 14)። እነዚህ ሰዎች እግዚአብሔርን እንደሚያውቁ በመግለጽ የብሉይ ኪዳንን ሕግ መጠበቅ አስፈላጊ መሆኑን አስተምሯል። ተግባራቸው ግን ጭራሽ እግዚአብሔርን የማያውቁ መሆናቸውን አጋልጧል (ቲቶ 1፡10-16፥ 3፡9)። አምስተኛ ዓላማ፡- በክርስቶስ ላይ የተጣለ እምነት በመልካም ባሕሪ ራሱን እንደሚገልጽ ለማሳየት። አማኞች በክርስቶስ አምናለሁ እያሉ አለማመናቸውን በሚያሳብቅ አኳኋን ሊመላለሱ ይችላሉ (ቲቶ 1፡16)። የአማኞች ባሕሪና ተግባር በክርስቶስ ማመን ሕይወታቸው ያመጣውን ለውጥ በሚያሳይ መልኩ መለወጥ አለበት። አዲስ ፍጥረት በተለወጠ ሕይወት ራሱን ያሳያል። የውይይት ጥያቄ፡– እነዚህ ትምህርቶች ዛሬ ለቤተ ክርስቲያን አስፈላጊ የሚሆኑት ለምንድን ነው? (ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የቲቶ መጽሐፍ ዓላማ Read More »

የቲቶ መልእክት በማን ተጻፈ፣ ለማን ተጻፈ፣ መቼና የት ተጻፈ

የቲቶ መልእክት ጸሐፊ የውይይት ጥያቄ፡ ቲቶ 1፡1-3 አንብብ። ሀ) የቲቶ መልእክት ጸሐፊ ማን ነው? ) ጸሐፊው ራሱን የገለጸው እንዴት ነው? ይህ በ1ኛ ጢሞ. 1፡1 ራሱን ከገለጸበት ሁኔታ ጋር የሚመሳሰለውና የሚለያየው እንዴት ነው? ይህ ጸሐፊው በዚህ መልእክት ውስጥ ስላተኮረበት አሳብ ምን ያሳያል? ጳውሎስ በዚህ መልእክት ውስጥ ባልተለመደ ሁኔታ ለቲቶ ረጅም መግቢያ ሰጥቷል። በተለመደው ስያሜው ራሱን «የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ» ብሎ ከመጥራቱ በተጨማሪ፥ ሁለተኛውንና በጣም የሚወደውን ስም «የእግዚአብሔር ባሪያ» የሚለውንም ይጠቀማል። ጳውሎስ በሐዋርያነቱና በሥልጣኑ ላይ በማተኮር ሊኩራራ ቢችልም፥ የሐዋርያነት ሥልጣኑን ከባሪያነት አመለካከት ጋር ሚዛናዊ አድርጎ ገልጾአል። ጳውሎስ ክርስቶስ የሚጠይቀውን ነገር ሁሉ ለማድረግ ፈቃደኛ ነበር። ይህም በቀዳሚነት ለሌሎች ክርስቲያኖች በሚያበረክተው አገልግሎት ተመልክቷል። ስለሆነም ጳውሎስ የቤተ ክርስቲያን ሁሉ መሪዎች ሊከተሉት የሚገባው መልካም ምሳሌ ነው። የሽማግሌነት ሥልጣን ቢኖረንም፥ አመለካከታችን ሌሎችን በማገልገልና እግዚአብሔርን በማገልገል ላይ የተመሠረተ ሊሆን ይገባል። ጳውሎስ በዚህ በቲቶ በጻፈው መልእክቱ መግቢያ ላይ በሁለት ቁልፍ ጉዳዮች ላይ ያተኩራል። በመጀመሪያ የአማኞች እምነት ስለተመሠረተበት እውነት ይናገራል። ጳውሎስ ይህ እውነት ከማይዋሽ አምላክ የመነጨ መሆኑን ያስረዳል። ይህም እግዚአብሔር በቃሉ ውስጥ ለሕዝቡ በሰጣቸው የተስፋ ቃሎች ላይ የተመሠረተ ነው። ይህም የተስፋ ቃል ድነት (ደኅንነትን) ብቻ ሳይሆን ለዘላለም ከእግዚአብሔር ጋር መኖርንም የሚያጠቃልል ነው። ሁለተኛ፥ ይህን እውነት ከማመን የሚመጣ መንፈሳዊነት አለ። እግዚአብሔር ሊያድነን የሚፈልገው ከሲኦል እንድናመልጥ ብቻ አይደለም። በባሕሪያችንና በተግባራችንም መንፈሳውያን እንድንሆን ይፈልጋል። የውይይት ጥያቄ፡– ሀ) እውነትና መንፈሳዊነት የሚሉት እነዚህ ሁለት ቃላት የአዲስ ኪዳን መልእክት ማጠቃለያ የሆነው የእምነት ውጤቶች መሆናቸውን ግለጽ። ለ) ቤተ ክርስቲያንህ ከእነዚህ ሁለት ነገሮች በየትኛው ላይ የበለጠ ታተኩራለች? ሐ) እግዚአብሔርን የሚያስከብር ሕይወት እንድንኖር እነዚህ ሁለት ነገሮች አስፈላጊ የሚሆኑት ለምንድን ነው? ጳውሎስ መልእክቱን የጻፈው ለማን ነው? ጳውሎስ ይህን መልእክት ለማን እንደላከ ሲገልጽ፥ «በኃይማኖት ኅብረት እውነተኛ ልጄ ለሚሆን ለቲቶ» ይላል። ቲቶ በሁላት ልዩ መንገዶች የጳውሎስ ልጅ ነበር። በመጀመሪያ፥ ቲቶ የጳውሎስ መንፈሳዊ ልጅ ነበር። ምናልባትም ቲቶ በክርስቶስ እንዲያምን በመሣሪያነት ያገለገለው ጳውሎስ ሳይሆን አይቀርም። ሁለተኛ፥ ቲቶ ከጳውሎስ፥ የቅርብ ጓደኞችና የጉዞ ባልደረቦች አንዱ በመሆኑ የጳውሎስ ልጅ ነበር። የውይይት ጥያቄ፡– እነዚህን ጥቅሶች በማንበብ በጳውሎስና ቲቶ መካከል የነበረውን ግንኙነት አብራራ። ገላ. 2፡1-3፡ 2ኛ ቆሮ. 2፡13፥ 7፡5-14፥ 8፡16-23፥ 2ኛ ጢሞ. 4፡10። ስለ ቲቶ ብዙ ነገር በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አልተጠቀሰም። ማንነቱ፥ የመጣበት አካባቢ፥ ወዘተ… በዝርዝር ሰፍሮ አንመለከትም። ምንም እንኳ በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ውስጥ ተጠቅሶ ባይገኝም፥ የጳውሎስ መልእክቶች እንደሚያሳዩት ቲቶ ከጳውሎስ የቅርብ ባልደረቦችና የወንጌል መልእክተኝነት ጉዞዎቹ አጋዦች አንዱ ሳይሆን አይቀርም። በመጀመሪያ ስለ ቲቶ የምናነበው ከገላትያ መልእክት ውስጥ ነው። በገላትያ መልእክት ውስጥ ቲቶ አሕዛብ ሲሆን፥ በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘት መገረዝ የሚያስፈልገው መልካም የአሕዛብ አማኝ ምሳሌ ሆኖ ተጠቅሷል። ይህ ከፊል አሕዛብና ከፊል አይሁዳዊ ሆኖ ሳለ ጳውሎስ ከገረዘው የጢሞቴዎስ ሁኔታ የተለየ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ ቲቶ ከገላትያ ወይም ከአንጾኪያ ቤተ ክርስቲያን መምጣቱን አይናገርም። በተጨማሪም ከመጀመሪያው የጳውሎስና የበርናባስ የወንጌል መልእክተኝነት ጉዞ ሰኋላ ማመን አለማመኑ አልተጠቀሰም። የአሕዛብ ክርስቲያኖች መገረዝ አለባቸው ወይም የለባቸውም የሚለው ክርክር በተጧጧፈበት ወቅት ጳውሎስና በርናባስ ቲቶን ወደ ኢየሩሳሌም ወሰዱት። ቲቶ የተመረጠው ምናልባትም ጥልቅ መንፈሳዊነት የነበረው ሰው በመሆኑ ሳይሆን አይቀርም። ጳውሎስና በርናባስ አሕዛብ ክርስቲያን መገረዝ ሳያስፈልገው በመንፈስ ቅዱስ ሊሞላና የእግዚአብሔር ሰው ሆኖ ሊመላለስ እንደሚችል ለአይሁድ ክርስቲያኖች ለማሳየት ፈልገው ነበር። የቲቶን መንፈሳዊነት መመልከታቸው የአይሁድ መሪዎች የአሕዛብ ክርስቲያኖች ድነት (ደኅንነትን) ለማግኘት መገረዝ አለባቸው በሚለው ክርክር ላይ ሚዛናዊ አመለካከት እንዲይዙ ሳይረዳቸው አልቀረም። የአይሁድ መሪዎች ቲቶ ባይገረዝም እንደ ክርስቲያን ሊቀበሉት ችለዋል። ቲቶ ከጳውሎስ የወንጌል መልእክተኝነት ጉዞዎች ውስጥ በምን ያህሎቹ ላይ አብሮ እንደተጓዘ አልተጠቀሰም። ነገር ግን ከጳውሎስ ጋር ለረጅም ጊዜ በማገልገሉ ምክንያት ለትላልቅ አገልግሎቶች እንደ ተሾመ እንመለከታለን። በጳውሎስ ሦስተኛው የወንጌል መልእክተኝነት ጉዞው ላይ፥ ቲቶ ከጳውሎስ ጋር በኤፌሶን ነበር። ጳውሎስ 1ኛ ቆሮንቶስን ከጻፈ በኋላ በእርሱና በቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን መካከል አለመግባባት ተፈጥሮ ነበር። ቲቶ መልካም የአስተዳዳሪነት ስጦታ የነበረውና እንደ ጢሞቴዎስ መጋፈጥን የሚፈራ ሰው አልነበረም። በመሆኑም ጳውሎስ በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ የነበሩትን ችግሮች በማስተካከል ለኢየሩሳሌም ክርስቲያኖች ገንዘብ የማሰባሰቡን ተግባር እንዲጀምሩ ያበረታታቸው ዘንድ ቲቶን ወደ ቆሮንቶስ ላከው። ምናልባትም የጠፋውንና 2ኛው የቆሮንቶስ መልእክት በመባል የሚታወቀውን ለክርስቲያኖች የወሰደው ቲቶ ሳይሆን አይቀርም። ቲቶ በቆሮንቶስ የነበረውን ሁኔታ በዘዴ ለማስተካከል ችሏል። ቲቶ በመቄዶኒያ ከጳውሎስ ጋር በተገናኘ ጊዜ፥ ክርስቲያኖች ለጳውሎስ የነበራቸውን አመለካከት ቀይረው ነበር። በዚህ ጊዜ ጳውሎስ 2ኛ ቆሮንቶስን ጽፎ በቲቶ በኩል ወደ ቆሮንቶስ ላከ። ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ፍቅር የነበረው ቲቶ ክርስቲያኖች የጳውሎስን መመሪያዎች በመከተል ለኢየሩሳሌም ክርስቲያኖች ገንዘብ የማሰባሰቡን ተግባር እንዲጀምሩ ሊረዳቸው ችሏል። ጳውሎስ ቲቶን እንደ ባልደረባውና የወንጌል አገልግሎት ተባባሪ አድርጎ ይቆጥረውና ያከብረው ነበር። ጳውሎስ ታስሮ በቆየባቸው ሁለት ዓመታት ውስጥ ቲቶ ስለደረሰበት ሁኔታ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ የሚለው የለውም። ጳውሎስ ከተፈታ በኋላ ቲቶ ከጳውሎስ ጋር በመተባበር አራተኛው የወንጌል መልእክተኝነት ጉዞው የሚባለውን አገልግሎት ያከናወነ ይመስላል። ጳውሎስና ቲቶ ወደ ቀርጤስ ከተማ ሲደርሱ፥ ጳውሎስ ቲቶ በዚያ ሆኖ ቤተ ክርስቲያኒቱን እንዲያደራጅ አደረገ። ከዚያ ጳውሎስ ወደ ኤፌሶንና መቄዶኒያ ተጓዘ። በዚህም ጊዜ ቲቶ የሚደርስበትን ተቃውሞ ለማሸነፍ ሥልጣኑን እንዲጠቀምና እውነትን እንዲያስተምር አሳስቧታል። በኋላ ግን ሌሎች መሪዎች በቲቶ እግር በመተካታቸው በኒቃፖሊስ ከጳውሎስ ጋር ሊገናኝ ችሏል። ኒቃፖሊስ ከግሪክ በምዕራባዊ ዳርቻ የምትገኝ ከተማ ነበረች። በኋላ በደልማጢያ (ያሁኗ ዩጎዝላቪያ) እንዲያገለግል የተጠየቀ ይመስላል። ጳውሎስ እስር ቤት ውስጥ ሆኖ ሁለተኛውን የጢሞቴዎስ መልእክት በጻፈበት ወቅት ቲቶ በዚያች ከተማ ውስጥ ያገለግል ነበር። አንድ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ እንደሚለው፥ ከዚያ በኋላ ቲቶ ወደ ቀርጤስ ተመልሶ ጳጳስ ሆኗል። በዚህም በደሴቲቱ ውስጥ ያሉትን አብያተ ክርስቲያናት የማስተባበሩን ተግባር አከናውኗል። የቀርጤስ ደሴት የምትገኘው ከግሪክ በስተደቡብ ነበር። ይህቺ ደሴት 350 ኪ.ሜትሮች ያህል ርዝመት ያላት ሰፊ ስፍራ ነበረች። ቤተ ክርስቲያን በዚህች ደሴት ውስጥ እንዴት እንደ ተመሠረተች የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ የገለጸው ነገር የለም። በበዐለ ኀምሳ በክርስቶስ ያመኑ አንዳንድ የቀርጤስ ሰዎች እንደነበሩ ይናገራል (የሐዋ. 2፡11)። ጳውሎስ እስረኛ ሆኖ ወደ ሮም በሚሄድበት ጊዜ የቀርጤስን ደሴት ጎብኝቷታል። በዚህ ጊዜ በዚህች ከተማ ውስጥ የስብከት አገልግሎት ለመስጠት የተፈቀደለት መሆኑ አልተገለጸም። ነገር ግን ይህን ለማድረግ ፈቃድ ያገኘ አይመስልም። ጳውሎስ ከመጀመሪያው የሮም እሥራት ከተፈታ በኋላ፥ ወደ ቀርጤስ ተመልሶ እገልግሏል። ሌሎችን አካባቢዎች ለመጎብኘት በፈለገ ጊዜ፥ ቲቶ በዚያ ሆኖ ቤተ ክርስቲያኒቱን እንዲያደራጅ አድርጓል። ስለሆነም ጳውሎስና ቲቶ ይህችን ቤተ ክርስቲያን በጋራ የመሠረታት ይመስላል። ቲቶ አመራሩን የማደራጀቱን ተግባር ለብቻው ተወጥቷል። ምናልባትም ቤተ ክርስቲያኒቱ አዲስና ብዙ ምእመናን ያልነበሯት በመሆኑ ይመስላል ዲያቆናትን መሾም አላስፈለገም። የቀርጤስ ሰዎች ወደ ደሴቲቱ ከመጡት ጥንታዊያን ቀርጤሳውያንና ግሪኮች የተወለዱ ነበሩ። (የብሉይ ኪዳን ፍልስጤሞች የመነጩት ከዚህ ነው።) የቀርጤስ ሰዎች የሠለጠኑ ሰዎች ሳይሆኑ፥ በጭካኔአቸው፥ ታማኞች ባለመሆናቸውና በስንፍናቸው ይታወቁ ነበር። በዚህ ስፍራ ወንጌልን በጽናት መመሥረቱና መሪዎችን ማስመረጡ የቲቶ ኃላፊነት ነበር። ጳውሎስ መንፈስ ቅዱስ የአማኞቹን ሕይወት ሊለውጥና የእግዚአብሔር ልጆች እንዴት ሊመላለሱ እንደሚገባ የሚያሳዩ ሞዴሎች ሊሆኑ እንደሚገባ አስረድቷል። ቲቶ የተጻፈበት ዘመንና ቦታ እንደ 1ኛ ጢሞቴዎስ ሁሉ የቲቶ መልእክት ስለተጻፈበትም ጊዜ ምሁራን የተለያዩ አመለካከቶች አሏቸው። ይህም ምሁራኑ ጳውሎስ ከሐዋርያት ሥራ 28 በኋላ ከእስራት ተፈትቷል ወይም አልተፈታም ለሚለው ጥያቄ በሚሰጡት መልስ ላይ የሚወሰን ነው። ጳውሎስ ከእስራት አልተፈታም የሚሉ ወገኖች የቲቶ መልእክት የተጻፈው ጳውሎስ በ64 ዓ.ም ከመሞቱ ጥቂት ቀደም ብሎ ነው ይላሉ። አንደኛው አመለካከት ጳውሎስ በሦስተኛው የወንጌል መልእክተኝነት ጉዞው መጨረሻ ላይ ወደ ኢየሩሳሌም በሚሄድበት ወቅት ቲቶን ወደ ቀርጤስ እንደላከው ያስረዳል። ጳውሎስ በ57 ዓ.ም አካባቢ ከኢየሩሳሌም ሆኖ የቲቶን መልእክት ጻፈ። በዚህም መልእክቱ ቲቶ

የቲቶ መልእክት በማን ተጻፈ፣ ለማን ተጻፈ፣ መቼና የት ተጻፈ Read More »

የቲቶ መልዕክት መግቢያ

«አንተ ግን ሕይወት ለሚገኝበት ትምህርት የሚገባውን ተናገር። ሽማግሌዎች ልክኞች፥ ጭምቶች፥ ራሳቸውን የሚገዙ፥ በእምነትና በፍቅር በመጽናትም ጤናሞች እንዲሆኑ ምከራቸው። እንዲሁም አሮጊቶች ሴቶች አካሄዳቸው ለቅዱስ አገልግሎት የሚገባ… አስተምራቸው። ጎበዞችም እንዲሁ ራሳቸውን እንዲገዙ ምከራቸው… ባሪያዎች…. ምከራቸው» (ቲቶ 2፡1-9)። አንድ ጊዜ አንድ ታዋቂ አፍሪካዊ ክርስቲያን በአፍሪካ ውስጥ ክርስትና ሁለት ኪሎ ሜትር ስፋትና ሁለት ሴንቲ ሜትር ጥልቀት አለው ሲል ተናግሮ ነበር። ይህን ሲል በአፍሪካ ውስጥ ክርስቲያኖች ነን የሚሉ ብዙ ሰዎች እንዳሉ መግለጹ ነበር። ነገር ግን እግዚአብሔርንና ቃሉን በማወቅ አላደጉም። ይህን ክርስቲያን ወንድም ያሳሰበው በአፍሪካ የሚገኙ ክርስቲያኖች መንፈሳዊ እውነትን አለመማራቸውና ተገቢውን ክርስቲያናዊ ሕይወት የማይኖሩና ለሐሰት ትምህርቶች የተጋለጡ መሆናቸው ነበር። ቲቶ ጳውሎስ አብያተ ክርስቲያናትን እንዲያደራጁ ከወከላቸው አገልጋዮች አንዱ ነበር። ጳውሎስ ለቲቶ በጻፈው መልእክቱ በማስተማር ተግባር እንዲተጋ በተደጋጋሚ አሳስቦታል። ልጆች፥ ወጣት ወንዶች፥ ወጣት ሴቶች፥ አረጋውያን ሴቶችንና አረጋውያን ወንዶችን ጨምሮ ሁሉም የዕድሜ ክልሎች፥ እንዲሁም ባሮችን ጨምሮ በሁሉም የኢኮኖሚ ደረጃ ላይ የሚገኙ ሰዎች የእግዚአብሔርን ቃል መማር እንዳለባቸው ጳውሎስ ለቲቶ አሳስቧል። እነዚህ ሰዎች በሁለት መንገዶች መማር ነበረባቸው። በመጀመሪያ፥ አማኞች የእግዚአብሔርን እውነቶች መማር ያስፈልጋቸው ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ እግዚአብሔር፥ ኢየሱስ ክርስቶስ፥ መንፈስ ቅዱስ፥ ድነት (ደኅንነት)፥ ወዘተ… የሚያስተምረውን ማወቅ ያስፈልጋቸዋል። ማንም ሰው ከእግዚአብሔር ቃል እነዚህን እውነቶች ሳያውቅ በእምነቱ ሥር ሊሰድ አይችልም። ትላልቅ ዛፎች በጥልቅ እንደሚሰዱት ሥር እነዚህ እውነቶች የሰው ሕይወት እንዲጸናና የሐሰተኛ አስተምህሮ ወይም የስደትን ነፋሳት እንዲቋቋም ያስችሉታል። ሁለተኛ፥ አማኞች ባሕሪያቸውን እንዲቀይሩ መማር አለባቸው። የቀርጤስ ሰዎች በሮም ግዛት ውስጥ በውሸተኝነታቸው፥ በክፋታቸው፥ እንዲሁም ሰነፎችና ሆዳሞች በመሆናቸው ይታወቁ ነበር (ቲቶ 1፡12)። እንዲህ ዓይነቱ ባህሪ በክርስቶስ ላይ ካለህ እምነትና በእግዚአብሔር መንግሥት ውስጥ አዲስ ፍጥረት ከመሆን ጋር የሚጣጣም አልነበረም። ይልቁንም ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር ባላቸው ግንኙነት መንፈስ ቅዱስ የማይበሳጩ፥ ክብር የሚገባቸው፥ ራሳቸውን የሚገዙ፥ ጤናማ እምነት ያላቸው፥ አፍቃሪዎችና ታጋሾች፥ የማይሰርቁ፥ ወዘተ. አድርጎ እንዲለውጣቸው መጣር ያስፈልጋቸው ነበር። የእግዚአብሔርን ቃል የምንማርበትና የምናስተምርበት ዋናው ዓላማ አዳዲስ እውነቶችን ማወቅ ብቻ አይደለም። (ለምሳሌ፥ የዳዊት አባት ማን እንደሆነ ማወቅ)። ነገር ግን ባህሪያችን እንዲለወጥና አኗኗራችንም የተስተካከለ እንዲሆን የእግዚአብሔርን ቃል እንማራለን። ጳውሎስ እንደ መጠጣት፥ ፊልም ማየት፥ አለባበስ በመሳሰሉት አንዳንድ ሕጎች ወይም ደንቦች ላይ አጽንኦት አለመስጠቱ ልብ ሊባል የሚገባው ነው። ነገር ግን የጳውሎስ ትምህርት በሰዎች ባሕሪ ላይ ያተኩራል፥ ምክንያቱም አተገባበራችንን የሚወስነው ባሕሪያችን ነውና። ጳውሎስ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ከሚያከናውኗቸው ተግባራት ዋናው ማስተማር እንደሆነ ለቲቶ ያስረዳል። ጤናማ የሆነች ቤተ ክርስቲያን ድነት (ደኅንነትን) ላላገኙ ሰዎች ብቻ ሳይሆን ላመኑት ክርስቲያኖችም እምነታቸውን የሚያጸና ትምህርት በማቅረብ ትተጋለች። በመንፈሳዊ ሕይወታቸው ያድጉ ዘንድ በሁሉም የዕድሜ ክልል ለሚገኙ ሰዎች ተዛማጅነት ያላቸው የሥልጠና ፕሮግራሞች ይሰጣሉ። የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) የቤተ ከርስቲያንህን የትምህርት ፕሮግራሞች መርምር። በሁሉም የዕድሜ ክልሎች የሚገኙ አማኞች ትምህርት እያገኙባቸው ያሉባቸውን መንገዶች ግለጽ። ለ) ትምህርቱ የሚያተኩረው የተወሰኑ መረጃዎችን፥ ደንቦችና ሕጎችን በማወቅ ላይ ነው? ወይስ የአኗኗር ለውጥን በሚያስከትለው ባሕሪ ላይ? ሐ) ቤተ ክርስቲያንህ ያልዳኑትን ሰዎች ወደ ክርስቶስ ለማምጣትና አማኞች በሕይወታቸው እንዲያድጉ ለማገዝ የምታቀርባቸውን ትምህርቶችና ስብከቶች ሚዛናዊ ታደርጋለች? መልስህን እብራራ። መ) ቤተ ክርስቲያንህ እንዴት የተጠናከረ የትምህርት ፕሮግራም ልትዘረጋ እንደምትችል የበኩልህን አስተያየት ስጥ። የቲቶ መልእክት ከመጋቢያዊ መልእክቶች አንዱ ሲሆን፥ ጳውሎስ ቲቶ የቤተ ክርስቲያንን አመራር ስለሚያደራጅበት መንገድ የሰጠውን ማብራሪያ ያካትታል። ምንም እንኳ የቲቶ መልእክት የተጻፈው የ1ኛና 2ኛ ጢሞቴዎስ መልእክቶች በተጻፉበት ጊዜ ቢሆንም፥ ቀደምት የእምነት አባቶች 2ኛ ጢሞቴዎስን ተከትሎ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንዲሰፍር አድርገውታል። ይህንንም ያደረጉት የ1ኛና የ2ኛ ጢሞቴዎስ መልእክቶች ጎን ለጎን እንዲቀመጡ በማሰብ ነው። የውይይት ጥያቄ፡– ስለ ቲቶ ከመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት አንብብ። ስለ ጸሐፊው፥ መልእክቱን ስለሚቀበሉት ሰዎችና ስለ መጽሐፉ የተሰጠውን ማብራሪያ ጠቅለል አድርገህ ጻፍ። (ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የቲቶ መልዕክት መግቢያ Read More »