የቲቶ መጽሐፍ ዓላማ

የመጀመሪያው ዓላማ፡- ቲቶ በቀርጤስ ቤተ ክርስቲያን እንዴት እንደሚያደራጅ መግለጽ። ጳውሎስ ቲቶ መሪዎችን እንዲመርጥና አማኞች ደግሞ እምነታቸውን የሚያንጸባርቅ ሕይወት እንዲኖሩ ያበረታታቸው ዘንድ ይህን መልእክት ጽፎአል። ቲቶ ከጳውሎስ የተቀበለው አገልግሎት አስቸጋሪ ነበር። ቤተ ክርስቲያኒቱ በቅርብ ጊዜ የተመሠረተች አዲስ ነበረች። ይህ ጢሞቴዎስ በሚገባ በተደራጀች የኤፌሶን ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ከሚያበረክተው አገልግሎት የተለየ ነበር። የቀርጤስ ሰዎች ያልተማሩ። ውሸታሞች፥ የማይታመኑ፥ ለመብላት ብቻ የሚኖሩ፥ ሰነፎች፥ ወዘተ… በመሆናቸው ባሕሪያቸው በጣም አስቸጋሪ ነበር። ጳውሎስ በክርስቶስ ላይ ያለን እምነት ባሕሪያችንን መለወጥ እንዳለበት አጽንኦት ሰጥቶ የሚናገረው ለዚህ ሳይሆን አይቀርም። ይህ በተለይ ለመሪዎች እጅግ አስፈላጊ ነው።

ይህም እግዚአብሔር የብሉይ ኪዳንን ሕዝብ የጸኑትን አይሁዶች ብቻ በወንጌል ለመለወጥ አለመፈለጉን ያሳያል። እንደ ግሪኮች ያሉትን የሠለጠኑ ሕዝቦች ብቻም አልነበረም የሚፈልገው፥ ላልተማሩና ብዙ ሕዝብ የማይስብ ባህል ላላቸው ሕዝቦችም ይገደዋል። እግዚአብሔር ለቀርጤስ ሕዝብ የሚገደው ከሆነ፥ ለዘላኖች፥ ሸክላ ሠሪዎች፥ ብረት ቀጥቃጮች፥ እንዲሁም በዓለም በየትኛውም ስፍራ ለሚኖር ሕዝብ እንደሚገደው ግልጽ ነው። ቤተ ክርስቲያን የተናቁ ናቸው ብላ የምታስባቸውን የሕዝብ ክፍሎች በወንጌል ለመድረስ በማትፈልግበት ጊዜ የምእመኖቿ የክርስቶስን ምሳሌነት እየተከተሉ አለመሆናቸውን መመልከት ይችላል። ለሰዎች ሁሉ የሚራራ የእግዚአብሔርም ልብ እንደሌላቸው ግልጽ ነው።

ወንጌሉ የተለያየ ባህል ወዳሏቸው ሕዝቦች የሚደርስበት ጊዜ፥ አማኞቹ እግዚአብሔርን የማያስከብረውን የባህላቸውን ክፍል መከተል አይኖርባቸውም። ነገር ግን መጽሐፍ ቅዱስ የባህሎች ሁሉ ዳኛ ሆኖ መቀመጥ ይኖርበታል። የየትኛውም ባህል ተከታዮች የሆኑ ሕዝቦች እግዚአብሔር ከባህላቸው ውስጥ የትኛው እርሱን እንደማያስከብረው እንዲያሳያቸው ሊጠይቁትና ይህንኑ ባህሪ ሊለውጡት ይገባል። አንድ ባህል ውሸት፥ አለመተማመንና ስርቆት ተገቢ እንደሆነ ቢያስተምር፥ የእግዚአብሔር ቃል እነዚህን የባህሉን ክፍሎች አማኞች ሊለውጡ እንደሚገባ ያስገነዝባል።

ነገር ግን ወንጌል ሊለውጠው የሚገባውን እንዳለ መተው የሚገባውን የባህል ክፍል በምንገመግምበት ጊዜ በጥንቃቄ ማድረግ ይኖርብናል። ጳውሎስ ያልሠለጠኑትን የቀርጤስ ሰዎች በሚያስተምርበት ጊዜ፥ በየትኛውም ስፍራ የግሪክን ባህል እንዲከተሉ፥ ትምህርት እንዲከታተሉ፥ የተወሰነ የአለባበስ ስልት እንዲይዙ ወይም የተወሰነ ቋንቋ እንዲማሩ አልጠየቃቸውም። ከቃሉ ጋር በግልጽ በሚጣረሱ አካባቢዎች ካልሆነ በስተቀር፥ እግዚአብሔር ሕዝቦች ባህላቸውን እንዲከተሉ ይፈቅዳል። አንዳንድ ጊዜ የእግዚአብሔር ልጆች በሙሉ በአንድ ቋንቋ እንደሚያመልኩ፥ የተወሰነ የአለባበስ ስልት እንደሚከተሉ፥ ኳየሮች እንደሚኖሩዋቸው፥ በቆርቆሮ ቤቶች ውስጥ እንደሚጸልዩ፥ እንደሚማሩ፥ የምዕራባውያንን ልብሶች እንደሚለብሱ፥ ወዘተ. እናስባለን። አንዳንድ ወንጌላውያን ዘላኖች ይህንኑ የባህላቸውን ክፍሎች እንዲቀይሩ በተሳሳተ መንገድ ያስተምራሉ። ወንጌላውያን የእግዚአብሔርን ቃል እንደ ማስተማር ሰዎች የገዛ ባህላቸውን ትተው የእነርሱን ባህሎች እንዲከተሉ ያስተምራሉ። ይህ ቅኝ ገዢዎች ኋላ ቀር ባህል ያላቸውን ሰዎች የባእድ አገሮችን ባህሎች እንዲከተሉ ካስገደዱበት መንገድ ጋር የሚመሳሰል የተሳሳተ አመለካከት ነው። ወንጌላውያን መቃወም ያለባቸው ከእግዚአብሔር ጋር የሚቃረኑትን ባህሎች ብቻ ነው። ይህንኑም የሚያደርጉት እንደ ጳውሎስ እግዚአብሔር ክርስቲያኖች የሚጠብቃቸውን አዎንታዊ የባህሪ ለውጦች በማመልከት ሊሆን ይገባል። ሰዎች እንዴት ሊለወጡ እንደሚገባ የሚዘረዝሩ ሕጎችን ልንሰጣቸው አንችልም። ይህ ወንጌሉን የሰናይ ምግባራት ሃይማኖት ከማድረጉም በላይ፥ ባህላችንን በሌሎች ሰዎች ባህል ላይ እንድንጭን ያበረታታናል።

ጳውሎስ ለአይሁዶች ወንጌልን ለማካፈል በፈለገ ጊዜ አይሁዳዊ ሆኖ እንደቀረበ ገልጾአል። ይህንን ያደረገው እንደ ዕብራውያን ሰዎች በመልበስ፥ ቋንቋቸውን በመናገርና ልክ እንደ እነርሱ በማምለክ ነበር። ለአይሁዶች ወንጌልን በሰበከ ጊዜ የአይሁዶችን ባህል ተከትሏል። የግሪክን ቋንቋ በመጠቀም፥ እንደ ግሪኮች በመልበስና እንደ ግሪኮች በማምለክ አገልግሎቱን ተወጥቷል። (በዚህ ጊዜ ግን ጳውሎስ እግዚአብሔር በግልጽ የከለከለውን የጣዖት አምልኮ አልተከተለም።) አይሁዶች ግሪኮች እንዲሆኑ ወይም ግሪኮች አይሁዶች እንዲሆኑ ከማስገደድ ይልቅ፥ ወንጌሉ የሚሰሙትን ይማርክ ዘንድ መልእክቱን ከሰሚዎቹ ባህል ጋር በሚጣጣም መልኩ ለማቅረብ መጣሩ ተገቢ ይሆናል (1ኛ ቆሮ. 9፡19-23)።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) የእግዚአብሔር ቃል ከሚያስተምረው በግልጽ የሚጣረሱትን የባህልህን ክፍሎች በምሳሌነት ዘርዝር። አብዛኞቹ አማኞች መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረውን ይከተላሉ ወይስ እንደ ዓለማውያን በመኖር ተግባራቸው የባህላቸው ውጤት መሆኑን ለማመሃኛነት ያቀርባሉ? ለ) ከእግዚአብሔር ጋር በግልጽ የሚቃረኑትን የሌሎች ባህሎች ገጽታዎች ዘርዝር። ብዙውን ጊዜ ከራሳችን ይልቅ የሌሎችን ባህሎች ችግሮች መመልከት የሚቀልለን ለምንድን ነው? ሐ) ሚሲዮናውያን ወይም ከሌሎች ባህሎች የመጡ ወንጌላውያን ሰዎች ክርስቲያን ለመሆን ከፈለጉ ባህላቸውን መለወጥ እንዳለባቸው የሚያስተምሩበትን ሁኔታ ግለጽ። መ) ይህ አደገኛና እግዚአብሔር ከሚፈልገው ሁኔታ ጋር የማይጣጣመው ለምንድን ነው? ሠ) በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉትን አንዳንድ የተናቁ ባህሎች ዘርዝር። ብዙ ሰዎች ለእነዚህ ባህሎች ምን ዓይነት አመለካከቶች አሏቸው? ለእነዚህ ሰዎች ወንጌሉን ለመመስከርና በእኩልነት ወደ ቤተ ክርስቲያን እንዲመጡ ለማድረግ እንተ፥ ቤተ ክርስቲያንህ ወይም ሌሎች አብያተ ክርስቲያናት ምን እያደረጉ ናቸው?

ሁለተኛ ዓላማ፡- ጳውሎስ መልእክቱን የጻፈው ለቲቶ ቢሆንም፥ ዓላማው የቀርጤስ አማኞች እንደ እግዚአብሔር ልጆች እንዴት መመላለስ እንዳለባቸው ማስተማር ነው። ጳውሎስ ቲቶ የእርሱ ተወካይ እንደሆነና የሚሰጣቸውን መልእክት ሊቀበሉ እንደሚገባ ለአማኞቹ ያስረዳል።

ሦስተኛ ዓላማ፡- እግዚአብሔርን የምታከብር ጠንካራ ቤተ ክርስቲያን ለማደራጀት ምን ዓይነት ዐበይት ነገሮች እንደሚያስፈልጉ ለጢሞቴዎስና ለሌሎችም የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ለማስተማር። ጠንካራ ቤተ ክርስቲያን የመገንባቱ ተግባር በድንገት የሚከሰት ሳይሆን፥ ሁሉንም የዕድሜ ክልሎች በጥልቀት ማስተማርን የሚጠይቅ ነው።

አራተኛ ዓላማ፡- ጢሞቴዎስና የቀርጤስ ቤተ ክርስቲያን እንዴት ሐሰተኛ ትምህርቶች እንደሚቋቋሙ ለመምከር። በቀርጤስ ቤተ ክርስቲያን የነበረው ሐሰተኛ ትምህርት ጠቅላላ ቤተሰቦችን እያወከ ያለ ይመስላል (ቲቶ 1፡11)። ቤተ ክርስቲያኒቱን እያጠቃ ያለው ሐሰተኛ ትምህርት ከአይሁዳውያን ክርስቲያኖች የመጣ ነበር። (ከተገረዙት ወገን፥ ቲቶ 1፡10፣ 14)። እነዚህ ሰዎች እግዚአብሔርን እንደሚያውቁ በመግለጽ የብሉይ ኪዳንን ሕግ መጠበቅ አስፈላጊ መሆኑን አስተምሯል። ተግባራቸው ግን ጭራሽ እግዚአብሔርን የማያውቁ መሆናቸውን አጋልጧል (ቲቶ 1፡10-16፥ 3፡9)።

አምስተኛ ዓላማ፡- በክርስቶስ ላይ የተጣለ እምነት በመልካም ባሕሪ ራሱን እንደሚገልጽ ለማሳየት። አማኞች በክርስቶስ አምናለሁ እያሉ አለማመናቸውን በሚያሳብቅ አኳኋን ሊመላለሱ ይችላሉ (ቲቶ 1፡16)። የአማኞች ባሕሪና ተግባር በክርስቶስ ማመን ሕይወታቸው ያመጣውን ለውጥ በሚያሳይ መልኩ መለወጥ አለበት። አዲስ ፍጥረት በተለወጠ ሕይወት ራሱን ያሳያል።

የውይይት ጥያቄ፡– እነዚህ ትምህርቶች ዛሬ ለቤተ ክርስቲያን አስፈላጊ የሚሆኑት ለምንድን ነው?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: