እውነትን ማስተማር በሁሉም የቤተ ክርስቲያን መሪ የብቃት መመዘኛዎች ዝርዝር ውስጥ ሰፍሮ ይገኛል። አንድ የቤተ ክርስቲያን መሪ እውነትን እንዲያስተምር ከተፈለገ አራት ነገሮች ያስፈልጉታል።
- መሪው ራሱ እውነትን ማወቅ ይኖርበታል። የወንጌሉን መሠረታዊ እውነቶች የማያውቅ መሪ ለቤተ ክርስቲያን አመራር ከሚያስፈልጉ ወሳኝ መመዘኛዎች አንዱ ይጎድለዋል። በግል የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፥ መጻሕፍትን በማንበብ፥ በቡድን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች፥ ወይም በመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ገብቶ በመማር፥ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች እውነትን ማወቅ ይኖርባቸዋል።
- መሪ እውነትን በሚያንጸባርቅ መልኩ መመላለስ አለበት። መጽሐፍ ቅዱስን የምናጠናው የአእምሮ ዕውቀት ለማግኘት ብቻ አይደለም። ነገር ግን የምንማራቸውን እውነቶች በዕለት ተዕለት ሕይወታችን ተግባራዊ ማድረግ ይኖርብናል።
- መሪ ለማስተማር የሚችል መሆን አለበት። አንዳንድ ሰዎች እውነተኛና መንፈሳዊ የሆነውን ነገር ቢያውቁም፥ ለሌሎች የማስተማር ብቃት የላቸውም፥ ጳውሎስ ዋና አገልግሎት በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ማስተማር እስከሆነ ድረስ፥ መሪ የማስተማር ስጦታ ሊኖረው እንደሚገባ ያስገነዝባል። ለዚህም ነው መጽሐፍ ቅዱስ ከዐበይት መንፈሳዊ ስጦታዎች አንዱ ማስተማር እንደሆነ የሚያብራራው (1ኛ ቆሮ. 12፡28 አንብብ)።
- መሪ ለማስተማር ጊዜ መውሰድ አለበት። ብዙ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ሌሎች ተግባራትን በማከናወን ራሳቸውን ስለሚያባክኑ ለማስተማሪያ የሚሆን ጊዜ የላቸውም። በዛሬው ዘመን ብዙ ሰዎች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በአግባቡ ትምህርት አያገኙም። ይህም ሆኖ በእያንዳንዱ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ አምስት ወይም ከዚያ የሚበልጡ ሽማግሌዎች አሉ። እነዚህ ሽማግሌዎች ለአባሎቻቸው እውነትን የሚያስተምሩበትን መንገድ ማግኘት ይኖርባቸዋል። መሪዎች ምእመኖቻቸውን ማስተማር ካላስፈለጋቸው፥ እግዚአብሔር የማስተማር ብቃት እንዲኖራቸው የሚጠይቀው ለምን ይሆን? የሚያሳዝነው በቤተ ክርስቲያን ውስጥ አብዛኞቹ ሽማግሌዎች በማስተማር አገልግሎት ላይ የማይሳተፉ መሆናቸው ነው። ወይም ደግሞ የሚያስተምሩት እሑድ ጧት ብቻ ይሆናል። ጳውሎስ ቲቶ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ለተለያዩ ቡድኖች ትኩረት በመስጠት ፍላጎታቸውን የሚያሟላ ትምህርት እንዲሰጣቸው ያብራራል።
የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) የቤተ ክርስቲያንህ መሪዎች የማስተማርን አገልግሎት በአግባቡ የማይወጡት በቀዳሚነት ከእነዚህ አራት ምክንያቶች ከየትኛው የተነሣ ነው? ለ) ይህን ሁኔታ ለመለወጥ ምን ሊደረግ ይገባል?
- አረጋውያንን ማስተማር (ቲቶ 2፡1-2)። ጳውሎስ ቲቶ ጤናማ ትምህርትን እንዲያስተምር ያሳስበዋል። ጳውሎስ ይህን ሊል የመጽሐፍ ቅዱስን ዐበይት እውነቶች ማለቱ ነው። ጳውሎስ ቲቶ ለአረጋውያን አማኞች የማይለወጠውን የእግዚአብሔርን ቃል እውነት ማስተማር እንዳለበት ያስገነዝበዋል። ለመሆኑ አረጋውያን የሚማሩት ለምንድን ነው? ጳውሎስ አረጋውያን ባሕሪያቸውን ለመለወጥ የእግዚአብሔርን ቃል መማር እንዳለባቸው ያስረዳሉ። ውሸታሞች፥ የማይታመኑና ሰነፎች ከመሆን ይልቅ ጭምቶች፥ ሊከበሩ የሚገባቸው፥ ራሳቸውን የሚገዙ፥ በእምነት፥ በፍቅርና በትዕግሥት የተሞሉ መሆን ያስፈልጋቸው ነበር። እነዚህ አረጋውያን በባህላቸው ከታወቀው ሁኔታ የተለየ ሕይወት መምራት ያስፈልጋቸው ነበር።
- አሮጊቶች (ቲቶ 2፡3-5)። ቲቶ አሮጊቶችንም ማስተማር ያስፈልገው ነበር። አሁንም ጳውሎስ ትኩረት ያደረገው በባሕሪና ተግባር ለውጥ ላይ ነው። በአሉታዊ ጎኑ፥ አሮጊት ሴቶች አንደበታቸውን በመግዛት ሰዎችን ከመሳደብ ወይም ከማማት መቆጠብ ያስፈልጋቸው ነበር። ለስካር እንዳይጋለጡ የሚጠጡትን መጠን መወሰን ያስፈልጋቸው ነበር። በአዎንታዊ ጎኑ፥ በአኗኗራቸው እግዚአብሔርን ማስከበር ያስፈልጋቸዋል። በአኗኗራቸውና በትምህርታቸው ለወጣት ሴቶች አዎንታዊ ተጽዕኖ ማሳደር ያስፈልጋቸዋል። አሮጊቶች ወጣት ሴቶች ራሳቸውን እንዲገዙ፥ ንጹሕ ሕይወት እንዲመሩ፥ ደጎች እንዲሆኑና መንፈሳዊ ቤቶች እንዲኖሯቸው፥ እንዲሁም ባሎቻቸውን እንዲያከብሩ ማስተማር ያስፈልጋቸዋል። ይህም በተለወጠ ሕይወታቸው እግዚአብሔርን ከማሰደብ ይልቅ እንዲያስከብሩ ያስችላቸዋል።
- ወጣት ወንዶች (ቲቶ 2፡6-8)። ቲቶ እንደ ጢሞቴዎስ ወጣት የነበረ ይመስላል። የቤተ ክርስቲያን መሪ እንደ መሆኑ መጠን፥ የዕድሜ እኩያዎቹ ለሆኑት ሰዎችም ኃላፊነት ነበረበት። ለእነዚህ ወጣት ወንዶች የሚያስተምረው ዋንኛ ባሕሪ ራስን ስለመግዛት ነበር። ወጣቶች ምኞታቸው፥ አሳባቸውና ፍላጎታቸው እንዲቆጣጠራቸው ከመፍቀድ ይልቅ በእግዚአብሔር ፈቃድ መመላለስ ያስፈልጋቸው ነበር። ለመሆኑ ወጣቶችንና ሌሎችንም የሚያስተምረው እንዴት ነው? በእነዚህ ርእሰ ጉዳዮች ላይ የክፍል ውስጥ ትምህርት በመስጠት ይሆን? አይደለም። ጳውሎስ ጢሞቴዎስ በሁሉም የዕድሜ ክልል ላሉት ሰዎች በመንፈሳዊ ሕይወቱ ምሳሌ በመሆን እንዲያስተምራቸው ያሳስባል። ሕይወቱ እውነተኛነትን፥ ተገቢ ንግግርን፥ መንፈሳዊነትን፥ ወዘተ… ማሳየት ነበረበት።
የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ጳውሎስ በዚህ የአረጋውያን፥ የአሮጊቶች፥ የወጣቶች ዝርዝር ውስጥ ቢያንስ ሦስት ጊዜ ራስን ስለመግዛት ገልጾአል። ይህ ባሕሪ ለሁሉም የዕድሜ ክፍሎች አስፈላጊ የሆነው ለምን ይመስልሃል? ጳውሎስ ቲቶ መንፈሳዊ ባሕሪን በሞዴልነት ለሰዎች እንዲያሳይ የጠየቀው ለምንድን ነው? ሐ) በሕይወትህ የሚያስቸግሩህ ባሕርያት የትኞቹ ናቸው? እነዚህ ባሕርያት በሕይወትህ ውስጥ እንዲታዩ ምን እያደረግክ ነው? መ) በቤተ ክርስቲያንህ እነዚህን እውነቶች እንዴት እያስተማርክ ነው?
- ባሮች (ቲቶ 2፡9-10።) ጳውሎስ በመጨረሻ ፥ ለባሮችም (ሠራተኞች) የእግዚአብሔርን ቃል ማስተማር እንደሚያስፈልግ ይናገራል። በጌቶቻቸው ሥር የሚተዳደሩ አማኝ ባሮች በአግባቡ ባይያዙም ምሳሌያዊ ሕይወት መኖር ያስፈልጋቸው ነበር። ጌቶቻቸውን ለመታዘዝና ለማስደሰት መጣር፥ ታማኞችና እምነት የሚጣልባቸው መሆን ያስፈልጋቸው ነበር። ይህ ክርስትናን ያስከብር ነበር። አጭበርባሪዎች፥ ሰነፎች፥ ሌቦች፥ የማይታዘዙ ወይም ተጨቃጫቂዎች የሆኑ እንደሆነ የክርስቶስን ስም ያሰድባሉ።
(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)