ብቃት ያላቸውን የቤተ ክርስቲያን መሪዎች መሾም (ቲቶ 1፡1-16)

ጥሩ ወጥ ለመሥራት ጥራት ያላቸውን ቅመሞች በተገቢው መጠን መጨመር እንደሚያስፈልግ ሁሉ፥ ጤናማ ቤተ ክርስቲያን ለመመሥረትም አንዳንድ ነገሮች ሊካተቱ ይገባል። ቲቶ የሚያገለግላትና በቀርጤስ ደሴት የምትገኝ ቤተ ክርስቲያን አዲስና ብዙም መንፈሳዊነት የማይታይባት ነበረች። ጳውሎስ ቲቶ ይህቺን ያልበሰለች ቤተ ክርስቲያን ክርስቶስን ወደምታስከብር በሳል ቤተ ክርስቲያንነት እንዲለውጥ አደፋፍሮታል። ጳውሎስ ለዚህ ተግባር የሚከተሉትን ነገሮች እንዲያደርግ ያበረታታዋል። ሀ) መንፈሳዊ አመራር፥ ለ) የሐሰት ትምህርቶችን መከላከል፥ ሐ) በሁሉም የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ሰዎች ባሕሪያቸውንና አኗኗራቸውን የሚለውጥ የትምህርት ፕሮግራም መከታተልና መ) ወንጌሉን በግልጽ መረዳት። ድነት (ደኅንነት) የሚገኘው በኢየሱስ ክርስቶስ ሞት በማመን መሆኑንና የዳኑ ሰዎች ግን እግዚአብሔርን በሚያስከብር መንገድ መመላለስ እንዳለባቸው ማወቅ ያስፈልጋቸው ነበር።

መግቢያ (ቲቶ 1፡1-4)

ሐዋርያው ጳውሎስ እግዚአብሔር ከእርሱ የሚፈልገውን ነገር በትክክል ያውቅ ነበር። ጳውሎስ ሕይወቱን በሙሉ እግዚአብሔር በሚፈልገው መንገድ የሚኖር ባሪያ ነበር። ምንም እንኳ ይህ እስራትና ሞትን ቢያስከትልበትም፥ ጳውሎስ የእግዚአብሔርን ፈቃድ ለማድረግ የቆረጠ አገልጋይ ነበር። እንዲሁም ኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌሉን እንዲሰብክ የሾመው ሐዋርያ ነበር። ወንጌሉ እግዚአብሔር ለጳውሎስ የገለጸውን የማይለወጥ እውነት የያዘ ነበር። ሰዎች የዘላለምን ሕይወት የሚያገኙት እግዚአብሔር የገለጠው እውነት ሲሰበክና ይህንኑ እውነት ሲያምኑ ነው። ነገር ግን ሕይወትን የማይለወጥ እውነት መስበኩ ብቻ በቂ አይደለም። ወንጌሉ የተለወጠ ሕይወት በማስከተል ሰዎች መንፈሳዊ አኗኗር እንዲከተሉ ያደርጋልና። ወንጌሉ የሚቀርበው በሚከተለው ቅደም ተከተል ነው። ) የእግዚአብሔር እውነት ይሰበካል፥ 2) ሰዎች በኢየሱስ ክርስቶስ ያምናሉ፥ 3) ወንጌሉን የሚያንጸባርቅ ሕይወት ይኖሩ ዘንድ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል አማኞች አኗኗራቸውን ይቀይራሉ። ይህንን ቅደም ተከተል ስንቀይርና በቀዳሚነት ሰዎች ከድነት (ደኅንነት) በኋላ ሊያሳዩ በሚገቧቸው ለውጦች ላይ ስናተኩር፥ ብዙውን ጊዜ ወንጌሉ ይለወጥና ሰዎች ድነት (ደኅንነትን) ለማግኘት መልካም ተግባር ማከናወን እንዳለባቸው ያስባሉ።

በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ተገቢውን አመራር ማደራጀት (ቲቶ 1፡5-9)

ምናልባትም ጠንካራ ቤተ ክርስቲያን እንድትመሠረት የሚያደርገው እጅግ ወሳኙ ነገር ትክክለኛ መሪዎች መመረጣቸው ይሆናል። ብዙውን ጊዜ ቤተ ክርስቲያን ደካማ የምትሆነው ሀ) መሪዎች በእምነታቸው ደካማ ሲሆኑ፥ ለ) የመንፈሳዊነት ሞዴሎች ሆነው ባለመመለሳቸው፥ ወይም ሐ) አማኞችን በትክክል ባለማስተማራቸው ሊሆን ይችላል።

የውይይት ጥያቄ፡- እነዚህ ሦስት ነገሮች የቤተ ክርስቲያንን ዕድገት ሲገድሉ የተመለከትከበትን ሁኔታ ግለጽ።

ጳውሎስ ቲቶ በአዲሲቷ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንዲያደርግ የፈለገው የመጀመሪያው ነገር ትክክለኛ መሪዎችን መሾም ነበር። ቲቶ በዚህች አዲስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ መሪዎችን ለመምረጥ ምን ዓይነት የመሪነት ብቃቶችን መመዘኛ አድርጎ መጠቀም ያስፈልገው ነበር? ጳውሎስ ለቲቶ የዘረዘራቸው የብቃት መመዘኛዎች በአብዛኛው ለጢሞቴዎስ የዘረዘራቸው ናቸው (1ኛ ጢሞ. 3፡1-13)። ለመሪዎች የሚያስፈልጉ የብቃት መመዘኛዎች የሚከተሉትን ያካትታሉ።

  1. ነቀፋ የሌለበት ይህም በባሕሪው፥ ከሰዎች ጋር ባለው ግንኙነትና ከገንዘብ ጋር ባለው ግንኙነት፥ ወዘተ… ያጠቃልላል።
  2. የአንዲት ሚስት ባል፥ ብዙ ሚስቶች የሌሉት
  3. የሚያምኑ ልጆችና በሥርዓት የተያዘ ቤተሰብ ያለው መሪ ክርስቲያናዊ ቤተሰብ ምን መምሰል እንዳለበት በሞዴልነት የሚያሳይ አገልጋይ ነው። መሪነቱን የማስተማር ብቃቱ በልጆቹ ባሕሪና ተግባር መታየት ይኖርበታል።
  4. ከሰዎች ጋር ባለው ግንኙነት ተገቢውን ባሕሪ ማንጸባረቅ አለበት። የማይጠጣ፥ የማይበሳጭ፥ የማይጣላና እንግዳ ተቀባይ መሆን ይኖርበታል።
  5. የአልኮል መጠጦች ቁራኛ ያልሆነ
  6. ለሀብትና ገንዘብ ትክክለኛ አመለካከት ያለው
  7. መንፈሳዊ ባሕሪ ያለው፥ ራሱን የሚገዛ፥ ቀጥተኛ ሥነ ምግባራዊ ሕይወት የሚኖርና የተቀደሰ
  8. እውነትን የሚያውቅ፥ የሚጠብቅና የሚያስተምር

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ብዙ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች የሚወድቁባቸው ብቃቶች የትኞቹ ናቸው? ለ) እነዚህ ብቃቶች በቤተ ክርስቲያን መሪዎች ሕይወት ውስጥ መንጸባረቃቸው አስፈላጊ የሚሆነው ለምንድን ነው? ሐ) በእነዚህ በቲቶ መልእክት ውስጥ ከተገለጡት በተጨማሪ ዛሬ ትኩረት የምንሰጣቸው ሌሎች የብቃት መመዘኛዎች የትኞቹ ናቸው?

በ1ኛ ጢሞቴዎስ ውስጥ እንደተመለከትነው፥ ጳውሎስ አጽንኦት የሚሰጥባቸው ዐበይት የብቃት መመዘኛዎች የግለሰቡ ባሕሪና መንፈሳዊነት፥ ቤተሰባዊ ሕይወቱ፥ ከሌሎች ሰዎች ጋር ያለው ግንኙነትና እውነትን የማስተማር ብቃቱ ናቸው። ጳውሎስ ዛሬ አስፈላጊ ናቸው ብለን የምናስባቸውን እንደ የትምህርት ደረጃ ፥ የጎሳ ሥረ መሠረት፥ ሀብት፥ ወዘተ… አይጠቅስም። በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ችግሮች በሚኖሩበት ጊዜ፥ በአመዛኙ የችግሩ ምንጭ የሚውለው ከመሪዎች ላይ ነው። በመሪዎች መካከል ችግሮች የሚከሰቱት ደግሞ በአብዛኛው ጳውሎስ መሪዎችን ለመምረጥ መሠረታዊ አድርጎ የሚጠቅሳቸው ባሕርያት ስለሌሉአቸው ነው። ብዙውን ጊዜ በመሪዎች ላይ የምናጉረመርም ከሆነ ምናልባትም ችግሮቹ ራሳችን እንሆናለን። የምናገኘው የምንመርጠውን ነው። ምርጫችን በተሳሳተ መመዘኛ ላይ የተመሠረተ ከሆነ፥ የሚጨቁኑንን ወይም እንደ ፖለቲካ መሪዎች የሚያጉላሉንን መሪዎች እናጭዳለን። ነገር ግን በመጽሐፍ ቅዱሳዊ መመዘኛዎች ላይ ተመሥርተን ከመረጥን፥ እግዚአብሔርን የምታስከብር ቤተ ክርስቲያን ትኖረናለች።

ሐሰተኛ ትምህርቶችን መከላከል (ቲቶ 1፡10-16)

የቀድሞይቱ ቤተ ክርስቲያን እኛ እንደምናስበው ፍጹም አልነበረችም። ምክንያቱም ልክ እንደ እኛው አብያተ ክርስቲያናቱ ከሐሰት ትምህርት ጋር ግብግብ ይፈጥሩ ነበር። በየትኛውም ዘመን ውስጥ በምትኖር ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ችግሮች፥ ክፍፍሎችና ሐሰተኛ ትምህርቶች ከውስጥ ሊመነጩ፥ ከውጭ ደግሞ ስደት ሊመጣ ይችላል። ጳውሎስ ቲቶ ስለ ሐሰተኛ ትምህርት ጥንቃቄ እንዲያደርግ ያሳስበዋል። ቀርጤስ አዲስ ቤተ ክርስቲያን ብትሆንም፥ ሐሰተኛ አስተማሪዎች ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር የማይዛመዱ ትምህርቶች በማቅረብ ላይ ነበሩ። እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ሲያጋጥም መሪዎች ምን ማድረግ ይኖርባቸዋል? እውነትን በማስተማር ሐሰተኛ አስተማሪዎችን ዝም ማሰኘት ይኖርባቸዋል። በጳውሎስ ዘመን፥ ዋንኛው የሐሰት ትምህርት የመነጨው ክርስቲያኖች ነን ከሚሉ አይሁዶች ነበር። እነዚህ ሰዎች ክርስቲያኖችን በእምነት ከሚገኝ ድነት (ደኅንነት) በሥራ ወደሚገኝ ድነት (ግርዘት፥ የብሉይ ኪዳንን ሕግጋት መጠበቅ፥ ወዘተ…) ለመለወጥ ፈልገው ነበር። አሁንም ከቤተ ክርስቲያን መሪዎች ዐበይት ኃላፊነቶች አንዱ ቤተ ክርስቲያንን ከሐሰተኛ አስተማሪዎች መጠበቅ መሆኑን እንመለከታለን። ይህንንም ለማድረግ፥ እውነትን ማወቅ ይኖርባቸዋል።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: