የጸጋው ወንጌል የተለወጠ አኗኗርን እንደሚያካትት ማስተማር (ቲቶ 2፡11-3፡15)

ወንጌል አማኞች መንፈሳዊ ያልሆኑትን ነገሮች እንዳያደርጉ ያስተምራል (ቲቶ 2፡11-3፡8)።

ለመንፈሳዊ ጉዞ ቁልፉ ሚዛናዊነት ነው። ብዙውን ጊዜ ሐሰተኛ ትምህርት ክርስቲያኖች በእምነታችንና በተግባራችን ሚዛናዊነት የጎደለው እርምጃ እንድንወስድ ይገፋፋናል። የሚዛናዊነት መዛባትና የተሳሳተ ትምህርት ወደ ቤተ ክርስቲያን ከሚገቡባቸው መንገዶች አንዱ ድነት (ደኅንነትን) ባገኘንበትና በምንመላለስበት መንገድ መካከል ባለው ግንኙነት ነው። የአዲስ ኪዳን ዋነኛ ትምህርት በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን መዳናችንን መግለጽ ነው። እርሱ ከጸጋው የተነሣ በነፃ የዘላለም ሕይወት ይሰጠናል። ምንም እንኳ ሰይጣን ሁልጊዜም ድነት (ደኅንነትን) ለማግኘት ወይም ያገኘነውን ድነት (ደኅንነት) ጠብቀን ለማቆየት መልካም መሆን ወይም መልካም ሥራ መሥራት እንዳለብን ለማሳሰብ ቢፈልግም፥ መጽሐፍ ቅዱስ ድነት (ደኅንነት) ክርስቶስ በመስቀል ላይ ስለ እኛ ኃጢአት መሞቱን ባመንንበት ጊዜ በነፃ የምናገኘው ስጦታ መሆኑን ይናገራል።

ነገር ግን ይህም ትምህርት ሚዛናዊነቱን ሊያጣ ይችላል። የቀርጤስ አማኞች፥ «ድነት (ደኅንነት) የሚገኘው በእምነት ብቻ ከሆነ፥ በክርስቶስ ካመንን በኋላ እንደፈለግን ልንኖር እንችላለን» የሚሉ ይመስላል። ስለሆነም ጳውሎስ ምንም እንኳን ድነት የሥራችን ውጤት ባይሆንም፥ እግዚአብሔር እኛን ካዳነባቸው ዓላማዎች አንዱ ሕይወታችንን መለወጥ እንደሆነ ይናገራል። «ሰዎችን ሁሉ የሚያድን የእግዚአብሔር ጸጋ ተገልጧልና ይህም ጸጋ ኃጢአተኝነትንና ዓለማዊን ምኞት ክደን ራሳችንን በመግዛትና በጽድቅ እግዚአብሔርን በመምሰል በአሁኑ ዘመን እንድንኖር ያስተምረናል»። እግዚአብሔርን በሚያስከብር መንገድ የማይመላለስ ሰው አንድም ከልቡ አላመነም (የአእምሮ እውቀት ብቻ አለው) ወይም ወንጌሉ ምን እንደሆነ በትክክል አልተገነዘበም ማለት ነው። ወይም ደግሞ በእግዚአብሔር ላይ በማመጽ እየተመላለሰ በመሆኑ ለፍርድ ራሱን ያጋልጣል። ክርስቶስ እኛን ከኃጢአት በማዳኑ፥ ለንጹሕ ሕይወትና መልካም ሥራ  አድኖናል።

እግዚአብሔርን የሚያስከብር ሕይወት ለመኖር ልንለወጥባቸው የሚገቡ አንዳንድ መንገዶች ምን ምንድን ናቸው?

  1. በቤተ ክርስቲያንም ሆነ በማኅበረሰብ ውስጥ መሪዎችን በመታዘዝ፡፡
  2. ሌሎችን በፍቅር በመርዳት፡፡
  3. ስለሌሎች ክፉ እንዳንናገር (እንዳንሳደብ) አንደበታችንን በመግዛት።

4 ከሌሎች ጋር በሰላም በመኖርና ለሌሎች በማሰብ።

  1. የራሳችንን መንገድ ወይም የግል ክብር ከመሻት ይልቅ እግዚአብሔርን በትሕትና በማገልገል።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) በቤተ ክርስቲያንህ ውስጥ ከሚገኙት ምእመናን አብዛኞቹ በእነዚህ አምስት መንገዶች እግዚአብሔርን ለማስከበር ቢሹ፣ በቤተ ክርስቲያንህና በማኅበረሰብህ ውስጥ ምን ዓይነት ለውጦች የሚከሰቱ ይመስልሃል? ለ) ብዙ ከርስቲያኖች በዚህ መንገድ የማይመላለሱት ለምን ይመስልሃል?

የቤተ ክርስቲያን መሪ ከሐሰተኛ አስተማሪዎች ጋር የማያባራ ሙግት መግጠም የለበትም (ቲቶ 3፡9-11)።

ሐሰተኛ ትምህርት ወደ ቤተ ክርስቲያን ሾልኮ በሚገባበት ጊዜ፥ የቤተ ክርስቲያን መሪ በቀላሉ በማያቋርጥ ክርክሮች ሊጠመድ ይችላል። ከእነዚህ ሐሰተኛ ትምህርቶች አብዛኞቹ የሞኝነት ነገሮች ሲሆኑ፥ ሌሎች ደግሞ አደገኞች ናቸው። የቤተ ክርስቲያን መሪ የሞኝነት ሐሳቦችን ማራቅ ይኖርበታል። አደገኛ የሆኑትን ሐሰተኛ ትምህርቶች ግን መዋጋት አለበት። የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ከክርስቶስ ያገኙትን ሥልጣን በመጠቀም ሐሰተኛ ትምህርት የሚያስተምሩትንና የሚያምኑትን ሰዎች መገሠጽ አለባቸው። እንዲህ ዓይነቱ እርምጃ በመሪው አሳቦች ወይም ምርጫዎች ላይ ሳይሆን፣ በእግዚአብሔር ቃል ላይ መመሥረት እንዳለባቸው ቀደም ብለን ተመልክተናል። ሐሰተኛ ትምህርቶችን የሚከተል የቤተ ክርስቲያን መሪ የመሪዎችን ምክር በማይሰማበት ጊዜ በተደጋጋሚ ማስጠንቀቁ ተገቢ ነው፡፡ ነገር ግን የዐመጻኝነት መንፈሱ የማይፈወስ ከሆነ፥ ቤተ ክርስቲያን ግለሰቡን መቅጣት አለባት።

መደምደሚያ (ቲቶ 3፡12-15)

ጳውሎስ መልእክቱን ሲደመድም ለቲቶ አንዳንድ ግላዊ ትእዛዛትን ይሰጣል። ጳውሎስ አጢሞን ወይም ቲኪቆስ ቲቶን መጥተው እንደሚተኩት ይናገራል። በዚህ ጊዜ ቲቶ ወደ ኒቃፖሊስ መጥቶ ከጳውሎስ ጋር ይገናኛል። ዜማስና አጵሎስ ምናልባትም ለቲቶ የጳውሎስን መልእክት ያደረሱ ሰዎች ሳይሆኑ አይቀሩም። ከዚያ በኋላ ጳውሎስ መልእክቱን በሰላምታ ይደመድማል።

የውይይት ጥያቄ፡- ከቲቶ መጽሐፍ ስለ አመራር ወይም እግዚአብሔርን በሚያስከብር መንገድ ስለመመላለስ የተማርካቸውን አንዳንድ ጠቃሚ እውነቶች ዘርዝር።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: