የፊልሞና መግቢያ

ቤተልሔም ያደገችው ክርስቲያን ባልሆኑ ቤተሰቦች ዘንድ ነበር። አባቷ ሰካራም በመሆናቸውና እናቷም ቅስም ሰባሪ ቃላት ስለሚሰነዝሩባት፥ በ14 ዓመቷ የተሻለ ሕይወት ፍለጋ ወደ አዲስ አበባ ጠፍታ መጣች። አዲስ አበባ ደርሳ ከአውቶቡስ ስትወርድ ዙሪያዋን የከበቡትን ጸጉረ ልውጥ ሰዎች ተመልክታ ፈራች። ለአያሌ ቀናት በጎዳናዎች ላይ ላይ ታች እያለች ሥራ ስትፈልግ ቆየች። የኋላ ኋላ አንዲት አሮጊት ሴትዮ ከሆቴላቸው ውስጥ እንድትሠራ ቀጠሯት። ነገር ግን ክፍያው በጣም አነስተኛ በመሆኑ ልብስ ለመግዛት የሚያስችል ገንዘብ ልታገኝ አልቻለችም። አንድ ቀን የሆቴሉ ባለቤት የሆኑት አሮጊት ወደ ሆቴሉ ከሚመጡት እንግዶች ጋር አብራ ብትተኛ የተሻለ ገንዘብ ልታገኝ እንደምትችል ነገሯት። ይህን አሳብ ካልተቀበለች ደግሞ ከሥራ እንደሚያባርሯት አስጠነቀቋት። በመሆኑም በ14 ዓመት ዕድሜዋ ቤተልሔም ሴተኛ አዳሪ ሆነች። በዚህ ጊዜ ሕይወት መረራት። የሚተኟት ወንዶች አለአግባብ ያንገላቷት ነበር። ብዙውን ጊዜ ከተኟት በኋላ ገንዘብ አይሰጧትም። ከምታገኘውም ገንዘብ አብዛኛውን የሆቴሉ ባለቤት ይወስዱባታል። አንድ ቀን ሁኔታው በጣም ስለመረራት ራሷን ለመግደል ወሰነች። ራሷን ስለምታጠፋበት መንገድ እያሰላሰለች ስትሄድ ከአንዲት ትንሽ ቤት የሙዚቃ ድምጽ ተሰማት። ይህ በሆቴሉ ውስጥ ሁልጊዜ ከምትሰማው ሙዚቃ የተለየ በመሆኑ፥ ቀረብ ብላ ከግቢው ጥግ በመቀመጥ ታዳምጥ ጀመር። የቤቱ ባለቤት ቤተልሔምን ተመልክታ ቀረብ አለችና ስለ ክርስቶስ ወንጌል መሰከረችላት። በዚህ ጊዜ እርሷን ከመውደዱ የተነሣ ሕይወቱን ሊሰጥ የፈቀደ ሰው በመኖሩ እጅግ ተደነቀች። እግዚአብሔር ኃጢአትን ይቅር ለማለትና አዲስ ሕይወት ለመስጠት በመቻሉ ልቧ ራደ። በተሰበረ ልብ እንባዋን እያፈሰሰች ክርስቶስን የግል አዳኝዋ አድርጋ አመነች።

የውይይት ጥያቄ፡- ሉቃስ 5፡29-32 አንብብ። ክርስቶስ እንደ ሐኪም ሁሉ መንፈሳዊ በሽተኞች የሆኑትን ሰዎች ለመፈወስ እንደ መጣ ተናግሯል። ሀ) እግዚአብሔር እንደ ቤተልሔም ዓይነቷን ልጅ የመረጠው ለምን ይመስልሃል? ለ) እግዚእብሔር እንደ ቤተልሔም ያሉትን ሰዎች የሚወድና የሚያድን ከሆነ፥ ብዙ ክርስቲያኖች ማኅበረሰቡ ለሚንቃቸው ሰዎች ወንጌሉን ለመመስከር የማይፈልጉት ለምንድን ነው? ሐ) ማኅበረሰቡ ካገለላቸው ሰዎች ጋር ለመተባበር አለመፍቀዳችን ስለ ልባችን፥ ስለ ራሳችን፥ ስለ ኃጢአትና ስለ እግዚአብሔር ምን ዓይነት ግንዛቤ እንዳለን ያሳያል? ይህ በሉቃስ 5፡29-32 ከተገለጸው የክርስቶስ አመለካከት የሚለየው እንዴት ነው?

የፊልሞና መጽሐፍ እግዚአብሔር አንድን ባርያ በማዳን ያሳየውን አስደናቂ ጸጋ ይናገራል። አናሲሞስ የተባለ ባርያ ከቆላስይስ ኮብልሎ በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮች ተጉዞ ወደ ሮም ሄደ። ኑሮው በፍርሃት የተሞላ መሆኑ አያጠራጥርም። ባለሥልጣናት ቢያገኙት፥ ሊገደል ይችል ነበር። እሚኖርበት ቤትና ስፍራ ስላልነበረው፥ ምናልባትም ለምኖ እየበላ በጎዳናዎች ላይ ሳያድር አልቀረም። እግዚአብሔር ግን ይህን ባርያ አሰበው።

በሚያስገርም ሁኔታ እግዚአብሔር አናሲሞስን ወደ ጳውሎስ መራው። አናሲሞስ የክርስቶስን ወንጌል በሰማ ጊዜ በክርስቶስ አዳኝነት አመነ። በሕይወቱ ለመጀመሪያ ጊዜ አናሲሞስ በመንፈሱ ነፃ ሆነ። እንግዲህ አሁን ምን ማድረግ አለበት? ጳውሎስ አናሲሞስን ፊልሞና ወደሚባለው ጌታው እንዲመለስ ግድ አለው። ፊልሞና ነጻነቱን ቢሰጠው መልካም ይሆናል። ነገር ግን ለአናሲሞስ ከጌታው በመኮብለል ነጻነቱን ማግኘቱ ተገቢ አልነበረም። በመሆኑም ጳውሎስ አጭር ደብዳቤ ለፊልሞና ጽፎ አናሲሞስን ወደ ጌታው መለሰው። ጳውሎስ በዚህ ደብዳቤ ውስጥ ፊልሞና አናሲሞስን በክርስቶስ ወንድሙ አድርጎ እንዲቀበለውና በጥሩ ሁኔታ እንዲያስተናግደው ይጠይቀዋል። መንፈስ ቅዱስ ዝቅተኛ ለሆነው ባሪያ እግዚአብሔር ያሳየውን ፍቅር ለማመልከትና ሰዎች ከክርስቶስ ጋር ከመገናኘታቸው በፊት ምንም ዓይነት ጥፋት ቢፈጽሙ የእግዚአብሔር ቤተሰብ በጸጋ፥ በይቅርታና በአቀባበል የተሞላ እንዲሆን ሁላችንንም ለማስተማር ይችን አጭር ደብዳቤ ጠብቋታል።

የውይይት ጥያቄ፡- ከመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት ስለ ፊልሞና አንብብ። ስለ ጸሐፊው፥ ፊልሞና ማን እንደ ነበረ፥ አናሲሞስ ማን እንደ ነበረና የመልእክቱ ዓላማ ምን እንደሆነ ጠቅለል አድርገህ ግለጽ።

የፊልሞና ጸሐፊ

የውይይት ጥያቄ፡- ፊልሞና 1ን አንብብ። ሀ) ጸሐፊው ማን ነው? ራሱን እንዴት ገለጸው? ይህ በቲቶ መልእክት ውስጥ ራሱን ከገለጸበት ሁኔታ የሚለየው እንዴት ነው? ለ) መልእክቱ የተጻፈው ለማን ነው?

የፊልሞና መልእክት በአዲስ ኪዳን ውስጥ ከምናገኛቸው የጳውሎስ መልእክቶች በጣም አጭሩ ነው (ይህ መልእክት አንድ ምዕራፍ ብቻ ስላለው የፊልሞናን መልእክት በምንጠቅስበት ጊዜ ምዕራፉን ትተን ቁጥሩን ብቻ እንጽፋለን።) የፊልሞና መልእክት አጭርና በባህሪውም ግላዊ መልእክት ያዘለ መሆኑ፥ ቀደምት የቤተ ክርስቲያን አባቶች ከጳውሎስ መልእክቶች የመጨረሻው አድርገው አስቀምጠውታል። በጊዜ ቅደም ተከተል ይህ መልእክት የተጻፈው ሦስቱ የእስር ቤት መልእክቶች፥ ማለትም የኤፌሶን፥ የፊልጵስዩስ፥ የቆላስይስ መእክቶች በተጻፉበት ወቅት ነው። እነዚህ አራቱ መልእክቶች የተጻፉት በተመሳሳይ ጊዜ ጳውሎስ ሮም ውስጥ ታስሮ በነበረበት ወቅት ነው።

ጳውሎስ የዘመኑን የደብዳቤ አጻጻፍ ሥርዓት ተከትሎ በቀዳሚነት የደብዳቤው ጸሐፊ ራሱ መሆኑን በማስታወቅ ይጀምራል። ነገር ግን ጳውሎስ ራሱን የክርስቶስ እስረኛ በማለት በተለየ ሁኔታ ይገልጻል። በዚህ ስፍራ ሐዋርያ መሆኑን አልጠቀሰም። ሰሌሎች ስፍራዎች እንዳሰፈረው የእግዚአብሔር ባሪያ ነኝ ሲልም አልተናገረም። ጳውሎስ ራሱን እንደ እስረኛ ያስታወቀው በዚህኛው መልእክት ውስጥ ብቻ ነው። ጳውሎስ በዚህ መልእክት ውስጥ ሐዋርያነቱን ያልጠቀሰው እንደ ሌሎቹ መልእክቶች ለብዙ አንባቢዎች የማይቀርብ በመሆኑ ነው። ይህ መልእክት የሚነበበው በፊልሞና ቤተሰብ ብቻ ይሆናል። በመሆኑም በሐዋርያነት ሥልጣኑ ላይ ብዙም ትኩረት አልሰጠም። ይልቁንም ጳውሎስ ለፊልሞናና ቤተሰቡ የላከው በወዳጅነት መንፈስ የሚነበብ መልእክት ነበር። ጳውሎስ ስለመታሰሩ የገለጸው ስለ ወንጌሉ እየከፈለ ያለውን ዋጋ ለፊልሞና ለመግለጽ ነበር። በዚህም ውስጥ ፊልሞና በኮበለለው ባሪያው በአናሲሞስ በኩል ምን ያህል እንዳጽናናው መግለጽ ይፈልጋል።

ጳውሎስ ይህን መልእክት የጻፈው ለማን ነበር?

ጳውሎስ ይህን መልእክት፥ «ለተወደደውና አብሮን ለሚሠራ ለፊልሞና፥ ለእኅታችንም ለአፍብያ፥ ከእኛም ጋር አብሮ ወታደር ለሆነ ለአርክጳ፥ በቤትህም ላለች ቤተ ክርስቲያን» እንደላክ ይናገራል። ፊልሞናና አፍብያ ምናልባትም የኮበለለው ባሪያ የአናሲሞስ ጌቶችና ባልና ሚስት ሳይሆኑ አይቀሩም። አርክጳ ፊልሞና የነበራት የቆላስይስ ቤተ ክርስቲያን መሪ ነበር። አንዳንዶቹ አርክጳ የፊልሞናና የአፍብያ ልጅ ነበር ይላሉ።

ጳውሎስ ወደ ቆላስይስ ሄዶ እንደማያውቅ ታስታውሳላችሁ። ስለሆነም ከፊልሞናና ከአፍብያ ጋር የነበረው ግንኙነት ምናልባትም ስለዚሁ ቤተሰብ በሰማው መረጃ ላይ የተመሠረተ ሊሆን ይችላል። ወይም ጳውሎስ በኤፌሶን በሚያገለግልበት ወቅት ከፊልሞና ጋር ተገናኝቶ ይሆናል (የሐዋ. 19)። ጳውሎስ ምናልባትም ደግሞ ከእርክጳ ጋር በኤፌሶን ተገናኝቶ የቆላስይስን ቤተ ክርስቲያን እንዲያንጽ ሾሞት ይሆናል።

ስለ ፊልሞናና አፍብያ ብዙም የምናውቀው ነገር የለም። እነዚህ ሰዎች በቆላስይስ ከተማ የሚኖሩ አማኞች ነበሩ። ምናልባትም በክርስቶስ ያመኑት ጳውሎስ በሦስተኛው የወንጌል መእልክተኝነት ጉዞው ኤፌሶን ውስጥ በሚያገለግልበት ወቅት ሳይሆን አይቀርም። ጳውሎስ በሆነ መንገድ ለፊልሞና ድነት (ደኅንነት) አስተዋጽኦ እንዳበረከተ ይናገራል (ፊልሞና 19)። ምናልባትም ፊልሞና ሀብታም ነጋዴ ሳይሆን አይቀርም። ይህንንም የምናውቀው በሁለት ምክንያቶች ነው። በመጀመሪያ፥ ባሪያ ነበረው። ይህ ድሆች ሊያደርጉት የማይችሉት ነገር ነው። ሁለተኛ፥ በቆላስይስ አማኞች የሚሰባሰቡበት ትልቅ ቤት ነበረው።

ፊልሞና የተጻፈበት ጊዜና ስፍራ

ጳውሎስ ይህን መልእክት በጻፈበት ወቅት በሮም ታስሮ እንደነበር ግልጽ ነው። ግን ይሄ የትኛው እስራቱ እንደነበር ጳውሎስ በግልጽ አይናገርም። አንዳንድ የቤተ ክርስቲያን ምሁራን ጳውሎስ በኤፌሶን እንደታሰረ ይናገራሉ። ሌሎች ደግሞ በቂሳሪያ ታስሮ ነበር ይላሉ። ይሁንና ጳውሎስ በእነዚህ ሁለት ስፍራዎች የታሰረ አይመስልም። (የእስር ቤት መልእክቶች ስለተጻፉበት ጊዜ የቀረበውን መግቢያ በኤፌሶንና በፊልጵስዩስ መልእክት አንብብ።) በአመዛኙ ተቀባይነት ያለው አመለካከት ጳውሎስ በሮም ከተማ ታስሮ እንደነበር የሚያስረዳው ነው። ስለሆነም ይህ ፊልሞና መልእክት የተጻፈው የሐዋርያት ሥራ 28 እንደሚገልጸው ሳይሆን አይቀርም።

ፊልሞና የቆላስይስ መልእክት በተጻፈበት ጊዜ ነበር የተጻፈው። እንደዚህ ከሆነ ደግሞ፥ መልእክቱ የተጻፈው በ60 ዓ.ም አካባቢ ይሆናል። በቆላስይስ 4፡7-9 ጳውሎስ ቲኪቆስና አናሲሞስ መልእክቱን ወደ ቆላስይስ እንደሚያመጡ ይናገራል። በመሆኑም የቆላስይስና የፊልሞና መልእክቶች የተላኩት በእነዚህ ሁለት ሰዎች አማካኝነት እንደነበር እንገነዘባለን። ይኸው አክርጳ የተባለው ሽማግሌ በቆላስይስ ስሙ ተጠቅሷል (ቆላ. 4፡17)።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: