የፊልሞና ዓላማ፣ ልዩ ባሕሪያት እና አስተዋጽኦ

የፊልሞና ዓላማ

የመጀመሪያ ዓላማ፡- ፊልሞና የኮበለለ ባሪያውን አናሲሞስን እንዲቀበል ለማግባባት። በሆነ ምክንያት ባሪያው አናሲሞስ ከፊልሞና ኮብልሎ ነበር። ምናልባትም የሆነ ነገር ሰርቆ ሊሆን ይችላል የኮበለለው። አናሲሞስ ነጻነቱን ፍለጋ ብዙ ርቀት ተጉዞ ወደ ሮም ሄደ። ሮም ከአንድ ሚሊዮን የሚበዛ ሕዝብ የነበረባት በመሆኗ በቀላሉ ሊደበቅባት ይችል ነበር። በጥንት ዘመን፥ ከጌቶቻቸው የኮበለሉ ባሮች በጭካኔ ይቀጡ ነበር። ድንገት ቢያዙ በጋለ ብረት የማን ንብረት መሆናቸውን የሚያመለክት ምልክት ሰውነታቸው ላይ ይደረግ ነበር። በተጨማሪም በእሳት ይቃጠሉ፥ አንገታቸው ይቀላ ወይም ይገደሉ ነበር። ይህ ጭካኔ የተሞላበት ቅጣት የሚፈጸመው ሌሎች ባሪያዎች እንዳይኮበልሉ ለማስጠንቀቅ ነበር። እግዚአብሔር አናሲሞስን ወደ ጳውሎስ በመምራቱ ወንጌልን ሊሰማ ችሏል። አናሲሞስ በወንጌል አምኖ ከዳነ በኋላ ለአጭር ጊዜ እስረኛውን ጳውሎስን ሲረዳው ቆየ (የሐዋ. 28፡17–31 አንብብ።) አናሲሞስ የተመለሰው በጳውሎስ ገፋፊነት ወይም ራሱ አናሲሞስ ወደ ጌታውና አሁን ደግሞ በክርስቶስ ወንድሙ ወደ ሆነው ፊልሞና ተመልሶ ራሱን ማስገዛት እንዳለበት በመገንዘቡ ይሆን የምናውቀው ነገር የለም። በሮም ሕግ መሠረት፥ ጳውሎስ አናሲሞስን ወደ ጌታው የመመለስ ግዴታ ነበረበት። ጳውሎስ ፊልሞና በዘመኑ ልምድ አናሲሞስን በሞት እንዳያስቀጣውና ዳሩ ግን እንደ ክርስቲያን ወንድም እንዲቆጥረው በመጠየቅ ይህን ደብዳቤ ላከለት። አንዳንድ ምሁራን ጳውሎስ ፊልሞና ለወንጌል መልእክተኝነት አገልግሎቱ ይረዳው ዘንድ አናሲሞስን መልሶ እንዲልክለት እየጠየቀው ነበር ይላሉ (ፊልሞና 14)። ሌሎች ደግሞ ጳውሎስ በፊልሞና 21 ላይ «ከምልህ ይልቅ አብልጠህ እንድታደርግ አውቄ» ሲል፥ ፊልሞና አናሲሞስን ነፃ እንዲያወጣው መጠየቁ ነው ይላሉ። በዚህ ጊዜ ሁለቱም በክርስቶስ አንድ ናቸውና። ይህ እጭር መልእክት በአዲስ ኪዳን ውስጥ መካተቱ፥ ምናልባትም ፊልሞና እግዚአብሔር ሰዎችን ሁሉ በእኩል ደረጃ እንደሚወድና በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ባሪያዎችና ነፃ ሰዎችም እኩል መሆናቸውን እንደተገነዘበ ያመለክታል። ምናልባትም አናሲሞስ ነፃ ወጥቶ ሊሆን ይችላል።

ሁለተኛ ዓላማ፡- ጳውሎስ በቅርቡ ተፈትቶ ወደ ቆላስይስ ለመምጣት እንደሚፈልግ ለፊልሞና ለመግለጽ ነው። ጳውሎስ በፊልሞና ቤት ውስጥ ማረፍ ይችል እንደሆነም ጠይቋል። ጳውሎስ በአካባቢው የአገልግሎት ጣቢያ አድርጎ ሊጠቀምበት የሚችለውን ልዩ የእንግዳ ክፍል እንዲያዘጋጅለት ይፈልጋል።

ሦስተኛ ዓላማ፡- ሌሎች ክርስቲያን ባሪያ አሳዳሪዎች ባሪያዎቻቸውን፥ በተለይም ክርስቲያን ባሪያዎቻቸውን እንዴት ማስተናገድ እንዳለባቸው ለመምከር፡፡ በዚያን ዘመን በሮም ከተማ ውስጥ ይኖሩ ከነበሩት ሰዎች ግማሾቹ፥ በአቴና ከነበሩት ደግሞ ሦስት አራተኞቹ ባሪያዎች እንደነበሩ ይገመታል። ይህም በመጀመሪያው ምእተ ዓመት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ባሮች እንደነበሩ ያመለክታል። እነዚህ ባሮች ምንም ዓይነት መብት ያልነበራቸውና እንደ ንብረት የሚቆጠሩ ነበሩ። ከእነዚህ ባሪያዎች ብዙዎቹ በክርስቶስ አምነው ነበር።

እንዲያውም በብዙ አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ የባሪያዎች ቁጥር ከነፃ ሰዎች ይበልጥ ነበር። ወንጌሉ እየተስፋፋ ሲሄድ፥ ቤተ ክርስቲያን ይህንን ክፉ ልምምድ (ባሪያ ፍንገላ) ምን ማድረግ እንዳለባት መወሰን ነበረባት። ክርስቲያን የባሪያ አሳዳሪዎችና ክርስቲያን ባሪያዎች ክርስቶስ ከእነርሱ የሚጠብቀው ምን እንደሆነ ማወቅ ያስፈልጋቸው ነበር። አዲስ ኪዳን ይህንን ክፉ የባሪያ ፍንገላ ልምምድ በግልጽ ሲቃወም እንመለከትም። ባሪያዎች እንዲያምጹ ወይም እንዲኮበልሉ አይመክርም። ባሪያ አሳዳሪዎችም ባሪያዎቻቸውን ነፃ እንዲያወጡ አይጠይቅም። ችሎቶች ወይም የፖለቲካ አስተዳደሮች ለዚህ ችግር መፍትሔ እንዲፈልጉ አላሰቡም።

ልክ ውኃ ቀስ ብሎ ልብሳችንን እንደሚያጸዳ ሁሉ፥ አዲስ ኪዳንም የባርነትን መጥፎነት በርጋታ ያሳያል። በዚህም ረገድ አያሌ ነጥቦች ተጠቅሰው እንመለከታለን። በመጀመሪያ፥ አዲስ ኪዳን ባሪያዎች እንስሳት ሳይሆኑ፥ በእግዚአብሔር አምሳል የተፈጠሩ ሰዎች መሆናቸውን ያስረዳል። ሁለተኛ፥ በእግዚአብሔር ዓይን ፊት ሰዎች በምድር ላይ ባሪያዎች ይሁኑም አይሁኑም እኩል መሆናቸውን ያስረዳል። ሦስተኛ፥ እንደ ጳውሎስ ያሉ ጸሐፊዎች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የባሪያዎቹ ጌቶችና ባሪያዎች አንድ መሆናቸውን ይገልጻሉ። ባሪያ ወይም ጨዋ የሚባል ነገር የለም (ገላ. 3፡28)። ይህም አንዱ አስፈላጊ ሌላው የተናቀ ተደርጎ የሚቆጠርበት ሁኔታ እንደሌለ ያመለክታል። በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ካለው ከእንዲህ ዓይነቱ አንድነት የተነሣ ጳውሎስ አናሲሞስ ከእንግዲህ ባሪያ ብቻ ሳይሆን በጌታ ወንድም መሆኑን ገልጾአል ( ፊልሞና 16)። ይህ ባሪያዎች ጌቶቻቸው የሚጠቀሙባቸው መሣሪያዎች ናቸው ብሎ የሚያስበውን የባሪያ አሳዳሪነት ሥርዓት ከመሠረቱ አናግቷል። በመሆኑም፥ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በባሪያዎችና በጌቶቻቸው መካከል ፍጹም አዲስ ግንኙነት መመሥረቱ አስፈላጊ ነበር። አራተኛ፥ ጳውሎስ የባሪያ አሳዳሪዎች ባሪያዎቻቸውን በፍትሕ እንዲያስተዳድሩ ይጠይቃል። ምክንያቱም እርስ በርሳችን ፍትሕ የሰፈነበት ግንኙነት እንዲኖረን በሚጠይቀው በእግዚአብሔር ፊት አድልዎ የለምና (ቆላ. 4፡1፥ ኤፌ. 6፡9)። አምስተኛ፥ ጳውሎስ ክርስቲያን ባሪያዎች ነፃ ለመውጣት እንዳይታገሉና ወንጌሉን በሚያስከብር መንገድ አገልግሎታቸውን እንዲያበረክቱ ጠይቋል (ቆላ. 3፡22-25)።

ምናልባትም ቀደምት የቤተ ክርስቲያን አባቶች በመንፈስ ቅዱስ ተመርተው የፊልሞና መልእክት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንዲያስቀምጡ ያደረጋቸው በባርነት ላይ የተሰጠው ይህ ድነትን (ደኅንነትን) የሚያንጸባርቅ ትምህርት ሳይሆን አይቀርም።

አራተኛ ዓላማ፡- ቤተ ክርስቲያን ማኅበረሰቡ ላገለላቸው ሰዎች መራራት እንዳለበት ለማሳየት፡፡ ክርስቶስ በምድር ላይ በነበረበት ጊዜ በአብዛኛው የኃጢአተኞች፥ የቀራጮችና የአመንዝራዎች ወዳጅ በመሆኑ ምክንያት ወቀሳ ይሰነዘርበት ነበር (ማቴ. 11፡19)፡፡ እነዚህ ማኅበረሰቡ ያገለላቸው ሰዎች እግዚአብሔር እንደሚወዳቸው የሚያመለክተውን ወንጌል መስማት ያስፈልጋቸው ነበር። ሁሉም በእኩልና ተወዳጅ ወደሚሆኑበት የቤተ ክርስቲያን ቤተሰብነት መምጣት ያስፈልጋቸው ነበር።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) በኢትዮጵያ ውስጥ ማኅበረሰቡ የሚያገልላቸውን ቡድኖች ዘርዝር። ለ) ክርስቶስ በኢትዮጵያ ውስጥ ቢኖር ኖሮ ከእነዚህ የሕዝብ ቡድኖች ጋር ምን ዓይነት ግንኙነት የሚያደርግ ይመስልሃል? እንዴት የሚያስተናግዳቸው ይመስልሃል? ሐ) ክርስቶስ ሕዝቡ (ቤተ ክርስቲያን) እነዚህን ሰዎች እንዴት እንዲያስተናግዱ የሚፈልግ ይመስልሃል? መ) ቤተ ክርስቲያን እነዚህን ሰዎች ያስተናገደበትን ሁኔታ ክርስቶስ እንድናስተናግዳቸው ከሚፈልገው መንገድ ጋር አነጻጽር። ይበልጥ ክርስቶስ የሚፈልገውን ለማድረግ እንደሚችል ዛሬ በቤተ ክርስቲያን ግንዛቤ ልምምድ ውስጥ ሊከሰቱ የሚገባቸው ለውጦች ምን ምንድን ናቸው?

የፊልሞና ልዩ ባሕርያት

  1. በዚህ መልእክት ውስጥ ዐቢይ አስተምህሮ ወይም የቤተ ክርስቲያን ጉዳይ አልተነሣም። ነገር ግን ፊልሞና የግል ጉዳይ የሚመስለውን አጀንዳ ሲያንጸባርቅ እንመለከታለን። ይህም ቀደም ሲል የኮበለለውንና አሁን ወደ ጌታው የሚመለሰውን ባሪያ የሚመለከት ነበር።
  2. ፊልሞና ጳውሎስ የኮበለለውን ባሪያ በሚመለከተው አስቸጋሪ ጉዳይ ውስጥ በምን እጁን እንዳስገባ ሊጠይቅ ስለሚችል፥ ጳውሎስ መልእክቱን የጻፈው በጥንቃቄና በዘዴ ነበር። ጳውሎስ ፊልሞናን ሳያስቀይም ጥያቄውን ለማቅረብ ይፈልጋል። ምሁራን ጳውሎስን ጥንታዊ የግሪክና የሮም ጸሐፊዎች የሚከተሉትን የደብዳቤ አጻጻፍ እንደተከተለ ያስባሉ። ከፊልሞና ጋር ግንኙነት ለመመሥረት በመሻት ደብዳቤውን ሲጀምር እንመለከታለን (ፊልሞና 4-10)። ከዚያ በኋላ ፊልሞና ለአናሲሞስ የነበረውን አመለካከት ለመቀየር ይሞክራል (ፊልሞና 11፡19)። ከዚያም የፊልሞናን ልብ ለመንካት ይፈልጋል (ፊልሞና 20-21)። በዚህ ዓይነት ጳውሎስ ፊልሞና እግዚአብሔር ለአናሲሞስ እንዲያደርግ የፈለገውን ለማድረግ ወደሚችልበት ደረጃ ሲመራው እንመለከታለን።
  3. ጳውሎስ መልእክቱን ለፊልሞና ለማስተላለፍ የቃላት ጨዋታን ይጠቀማል። የአናሲሞስ የስሙ ትርጉም ጠቃሚ ማለት ነው። ጳውሎስ በመንፈሳዊ አነጋገር ያልዳነና የኮበለለ ባሪያ በመሆኑ አናሲሞስ ቀደም ሲል ለፊልሞና እንዳልጠቀመ ይናገራል። አሁን ግን ወደ ጌታው ስለተመለሰና ከሁሉም በላይ የፊልሞና መንፈሳዊ ወንድም በመሆኑ፥ አናሲሞስ ጠቃሚ ሰው ሆኖ መገኘቱን ያስረዳል (ፊልሞና 11)።

የፊልሞና አስተዋጽኦ

  1. መግቢያና ሰላምታ (ፊልሞና 1-7)
  2. ጳውሎስ ፊልሞና አናሲሞስን ይቅር ብሎ እንዲቀበለው ይጠይቀዋል (ፊልሞና 8–22)።
  3. የማጠቃለያ አሳቦች (ፊልሞና 23-25)

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

1 thought on “የፊልሞና ዓላማ፣ ልዩ ባሕሪያት እና አስተዋጽኦ”

Leave a Reply

%d bloggers like this: