መግቢያና ሰላምታ (ፊልሞና 1-7)
ከቀድሞይቱ ቤተ ክርስቲያን አስገራሚ ባሕርያት አንዱ በአማኞች መካከል የነበረው ፍቅርና መተሳሰብ ነበር። በተራራቁ ስፍራዎች የነበሩት ብዙም የማይታወቁ አማኞች ሳይቀር ከልባቸው ይዋደዱ ነበር። ጳውሎስ የሚኖረው ሮም ውስጥ ሲሆን ፊልሞና ደግሞ በቆላስይስ ውስጥ ይኖር ነበር። ይህም በመካከላቸው ከ1200 ኪሎ ሜትሮች በላይ ርቀት መኖሩን ያመለክታል። ጳውሎስ ቀደም ብሎም ከፊልሞና ጋር አብሮ ያሳለፈ አይመስልም። ይሁንና ለፊልሞና የጻፈው መልእክት ጥልቅ የወዳጅነት መንፈስ የሚታይበት ነበር። በተጨማሪም ጳውሎስ በቀላሉ የሰውን ስሜት ሊነኩ ስለሚችሉ አንዳንድ ጉዳዮች የፊልሞናን እርዳታ ለመጠየቅ ሲደፍር እንመለከታለን። ጳውሎስ አማኞች ሁሉ የእግዚአብሔር ቤተሰብ አካላት ናቸው የሚለውን እውነት ተግባራዊ እያደረገ ነበር። በመሆኑም፥ ጣልቃ እንደገባን ወይም ሌላውን ሰው ለራሳችን ዓላማ እንደተጠቀምንበት ሳናስብ ከክርስቲያን ወገኖች እርዳታ ልንጠይቅና አንዳችን ለሌላችን ልንጸልይ እንደምንችል ከዚህ መልእክት ውስጥ መረዳት ይቻላል።
ጳውሎስ ይህንን አጭር መልእክት የጻፈው ለፊልሞና፥ ለአፍብያ (ምናልባትም የፊልሞና ባለቤት) እና አርክጳ ነበር። አንዳንድ ሰዎች አርክጳ የፊልሞና ልጅና በፊልሞና ቤት ውስጥ የምትሰባሰብ ቤተ ክርስቲያን መሪ እንደነበረ ያስባሉ።
ጳውሎስ እስረኛ የነበረ ቢሆንም፥ ከእስረኛነቱ ችግሮች ባሻገር ስለ ሌሎች ያስብ ነበር። ጸሎቶቹ ያተኮሩት በግል ራሱ ስለሚባረክበት መንገድ አልነበረም። ይልቁንም ጳውሎስ ለሌሎቹ ሲማልድ እንመለከታለን። ጳውሎስ ስለ ፊልሞናና ስለ ቤተሰቡ ለእግዚአብሔር እንደሚጸልይ ይናገራል። ጳውሎስ ፊልሞና በክርስቶስ ላይ ጠንካራ እምነት እንደነበረውና ቅዱሳንን ሁሉ እንደሚወድ በመስማቱ፥ ጸሎቱ በምስጋና የተሞላ ነበር። ፊልሞና የራሱን ቤተሰብ፥ የራሱን ጎሳ ወይም የራሱን ቤተ ክርስቲያን ብቻ የሚወድ ሰው አልነበረም። ፊልሞና አማኞችን ሁሉ በመውደዱ የታወቀ ሰው ነበር። ጳውሎስ የፊልሞና ፍቅር እንደ ንጹሕ የምንጭ ውኃ እንደነበር ይናገራል። ይህም ፊልሞና የሚያጋጥመውን ሰው ሁሉ በመንፈሳዊ ሕይወቱ የሚያነቃቃ መልካም አገልጋይ እንደነበረ ያመለክታል።
የውይይት ጥያቄ፡- ከፍቅራቸው ትኩስነት የተነሣ ሌሎችን አማኞች የሚያነቃቁትን ክርስቲያኖች አይተህ ታውቃለህ? እንዲህ ዓይነቱ ሰው በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚፈለገው ለምንድን ነው? አንድ ሰው ለሌሎች የዚህ ዓይነት ፍቅር እንዲኖረው ምን ማድረግ ይኖርበታል?
ጳውሎስ ከምስጋናው በተጨማሪ ፊልሞና በክርስቶስ ላይ ያለውን እምነት ለሌሎች በድፍረት ማካፈል እንዲችል ይጸልይለታል። ጳውሎስ «እኛ ዘንድ ያለውን በጎ ነገር ሁሉ በማወቅ» የሚለውን አሳብ ከምስክርነት ጋር ማያያዙ አስገራሚ ነው። እምነታችንን ለሌሎች በምናካፍልበት ጊዜ መንፈስ ቅዱስ ለእግዚአብሔር ያለን እውቀት እንዲያድግ ይረዳናል። እንዲሁም የእግዚአብሔር ልጆች እንደ መሆናችን ልዩ ዕድሎች እንዳሉን እንድንረዳ ያስችለናል።
ጳውሎስ ፊልሞና አናሲሞስን ይቅር እንዲለውና እንዲቀበለው ይጠይቀዋል (ፊልሞና 8-22)
ጳውሎስ እዚህ ላይ የመልእክቱን ዓላማ ያብራራል። ጳውሎስ ፊልሞና አናሲሞስ ወደ እርሱ በሚመለስበት ጊዜ በፍቅር እንዲቀበለው ይለምነዋል። የስሙ ትርጉም «ጠቃሚ» የሆነው እናሲሞስ ቀደም ሲል ከፊልሞና በመኮብለሉ ሳይጠቅመው ቀርቶ ነበር። አሁን ግን አናሲሞስ የተለወጠና እንደ ፊልሞና በክርስቶስ የሚያምን ሰው ሆኖ ስለሚመለስ ለፊልሞናም ሆነ ለጳውሎስ «ጠቃሚ» ነበር። ጳውሎስ አናሲሞስን «ልጄ» ይለዋል። ይህም ምናልባትም ጳውሎስ አናሲሞስን ወደ ጌታ እንዳመጣውና አብረው በቆዩባቸው ጊዜያት በጣም ተዋድደው እንደ ነበር ያሳያል።
አናሲሞስ በክርስቶስ ካመነ በኋላ እስረኛ የነበረውን ጳውሎስን ሲያገለግለው ቆይቷል። በመሆኑም እዚያ ቆይቶ ቢረዳው ይወድ እንደ ነበር አስረድቷል። ነገር ግን ያለባለቤቱ ፈቃድ አንድን ነገር መውሰዱ ትክክል አለመሆኑን ያውቃል። ስለሆነም ጳውሎስ አናሲሞስን ወደ ፊልሞና መለሰው። ፊልሞና አናሲሞስን መልሶ ለጳውሎስ ለመስጠት ቢፈልግ ውሳኔው የራሱ ነበር። ፊልሞናም ወደ ክርስቶስ የመጣው በጳውሎስ ምስክርነት በመሆኑ የጳውሎስ ውለታ ነበረበት።
ጳውሎስ ከአናሲሞስ አሳዛኝ ሕይወት፥ ጳውሎስን በማግኘቱና በክርስቶስ በማመኑ ውስጥ የእግዚአብሔር ታላቅ እጅ እንደ ነበረበት ተገንዝቧል። የአናሲሞስን መኮብለል ጨምሮ እግዚአብሔር ሁኔታዎችን በሙሉ ይቆጣጠር ነበር። አሁን አናሲሞስ ለመታዘዝ የማይፈልግ ባሪያ ሆኖ አልነበረም ወደ ፊልሞና የተመለሰው። ነገር ግን በጌታ የተወደደ ወንድም ሆኖ ነበር የተመለሰው። አናሲሞስ ለጳውሎስም ሆነ ለፊልሞና የተወደደው ወንድም ነበር። ምክንያቱም አሁን ሁሉም የእግዚአብሔር ቤተሰቦች ናቸውና። ጳውሎስ ፊልሞናን የክርስቶስ አካል እናሲሞስ እንዲቀጣ ከሚፈቅደው የአገሪቱ ሕግ በላይ አስፈላጊ መሆኑን ያስገነዝበዋል። አሁን በክርስቶስ ወንድሞች በመሆናቸው፥ ፊልሞና አናሲሞስን በጌታ ወንድሙ አድርጎ እንዲቀበለውና ይቅርታን እንዲያደርግላት ይጠይቀዋል።
የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ሀብታሙ ፊልሞናና ባሪያው እናሲሞስ አሁን የእግዚአብሔር ቤተሰብ አካላት ሆነዋል። አናሲሞስ ወደ ቤቱ ከተመለሰ በኋላ ፊልሞና እንዴት ሊያስተናግደው ይገባል ትላለህ? ለ) ይህ ባህላዊውን የጌታና ባሪያ ግንኙነት እንዴት የሚያናጋው ይመስልሃል? ሐ) በቤተ ክርስቲያንህ ውስጥ የሚገኙትን አንዳንድ ማኅበረሰቡ ያገለላቸውን የኅብረተሰብ ክፍሎች ዘርዝር። የአንድ መንፈሳዊ ቤተሰብ አካል መሆናቸው ቀደም ሲል ይንቋቸው ከነበሩት ሰዎች ጋር የሚኖራቸውን ግንኙነት እንዴት እንደሚለውጥ ግለጽ። መ) እነዚህ የተገለሉ ሰዎች በክርስቶስ ወንድሞችና እኅቶች መሆናቸውን ለማሳየት ፍቅርህን እንዴት ትገልጽላቸዋለህ? ለእነዚህ ሰዎች ፍቅርህንና አቀባበልህን ለማሳየት በዚህ ሳምንት ምን ልታደርግ እንደምትችል ግለጽ።
አናሲሞስ ምናልባትም ከፊልሞና ንብረት ዘርፎ ይሆናል የሄደው። ይህ በፊልሞና ልብ ውስጥ መራርነት እንዳይፈጥር ሲል ጳውሎስ በአናሲሞስ ላይ ያለውን ዕዳ ራሱ ለመክፈል ዝግጁ መሆኑን ገለጸ። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ፥ እርቅ ይቅርታ መጠየቅን ብቻ ሳይሆን ከተቻለ የተሰረቀውን ንብረት መመለስን ወይም በሌላው ሰው ላይ የፈጸምነውን ጥፋት ማስተካከል ይጨምራል። ጳውሎስ በአናሲሞስ ምትክ ይህንን ለማድረግ ፈቃደኛ ነበር።
የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ጳውሎስ አናሲሞስ የሰረቀውን ንብረት ዋጋ ለመከፈል የፈለገው ለምን ይመስልሃል? ለ) ይህ ይቅርታ በምንጠይቅበት ጊዜ በተግባራችን ወይም ያጠፋነውን በማስተካከል ልንፈጽመው ስለሚገባው ተግባር ምን ያስተምረናል? ሐ) ብዙ ክርስቲያኖች ከሰረቁት ገንዘብ ይቅርታ ከጠየቁ ገንዘቡን የመመለስ ግዴታ እንደሌለባቸው የሚያስቡት ለምንድን ነው? ይህ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ይመስልሃል? ለምን?
ጳውሎስ በቅርቡ ከእስር ቤት እንደሚወጣ ያስባል። በዚህም ጊዜ በቆላስይስና ሎዶቅያ አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ እያገለገለ የተወሰነ ጊዜ ለመቆየት ዐቅዷል። ስለሆነም ጳውሎስ ፊልሞና በቤቱ ውስጥ እንዲቆይ ይፈቅድለት ዘንድ ይጠይቀዋል። ጳውሎስ ለብቻው የእንግዳ ክፍል ተዘጋጅቶለት ለመቆየት ይፈልጋል።
የመዝጊያ አሳቦች (ፊልሞና 23-25)
የውይይት ጥያቄ፡- ቆላ. 4፡12-14 እንብብ። የቆላስይስና የፊልሞና መልእክቶች አጨራረስ ተመሳሳይ የሚሆነው እንዴት ነው? በሁለቱም መልእክቶች ውስጥ የተጠቀሱትን ስሞች ዘርዝር።
ጳውሎስ የኤጳፍራን ሰላምታ በማቅረብ ይህንን ደብዳቤ ይደመድማል። ኤጳፍራ የቆላስይስ ክርስቲያኖች በሚገባ የሚያውቁትና በዚህ ጊዜ ከጳውሎስ ጋር ታስሮ የሚገኝ የቤተ ክርስቲያን መሪ ነበር። ጳውሎስ በተጨማሪም የማርቆስን፥ የአርስጥሮኮስን፥ የዴማስና የሉቃስንም ሰላምታ አስተላልፎአል። እነዚህ ሁሉ ስሞች በቆላስይስም መልእክት ውስጥ ይገኛሉ። ይህም ሁለቱም መልእክቶች በተመሳሳይ ጊዜ መጻፋቸውን ያመለክታል።
የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ማኅበረሰቡ ላገለላቸው ሰዎች ስለሚኖረን አመለካከት ከፊልሞና መልእክት ምን እንማራለን? ለ) ማኅበረሰቡ ካገለላቸው ሰዎች፥ በተለይም ከክርስቲያኖች ጋር ስለሚኖረን ግንኙነት እግዚአብሔር ከእኛ ምን ይጠብቃል?
(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)