ክርስቶስ የሚበልጥ የእግዚአብሔር መገለጥ ነው (ዕብ. 1፡1-3)

ታረቀች ያደገችው በጠንካራ የኦርቶዶክስ አማኞች ቤተሰብ ውስጥ ነበር። ከትንሽነቷ ጀምሮ የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት በጥንቃቄ መከተል እንዳለባት ተምራለች። በአብዛኛው ተአምረ ማርያም ወይም የኦርቶዶክስን እምነት የሚያጠናክሩትን ሌሎች መጻሕፍት እንድታነብ ትመከር ነበር። ታረቀች በተጨማሪም፥ ክርስቶስ በቀዳሚነት አምላክ እንጂ ሰው እንዳልሆነ፥ እርሱ ታላቅ አምላክ በመሆኑ ምክንያት ሰዎች በቀጥታ ወደ እርሱ ሊደርሱ እንደማይችሉ ተምራለች። በመላእክት ወይም የክርስቶስ እናት በሆነችው ድንግል ማርያም በኩል ልትጸልይ እንደምትችል ተነግሯታል። በማርያም በኩል ከጸለየች እርሷ ጥያቄዋን ለክርስቶስ እንደምታቀርብላት ተረድታለች። ምክንያቱም ጥሩ ልጆች ሁሉ እናቶቻቸውን ይታዘዛሉ። ታረቀች እግዚአብሔር ከእርሷ የሚፈልገው በተወሰኑ ቀናት እንድትጾምና በበዓል ቀናት ወደ ቤተ ክርስቲያን እየሄደች መላእክትን እንድታገኝ፥ ቅዱሳንንና ድንግል ማርያምን እንድታከብር መሆኑን አመነች። በመሆኑም እነዚህን ልምምዶች ጠንቀቅ ታደርግ ጀመር።

አንድ ቀን ታረቀች የኦርቶዶከስ የተሐድሶ ቡድን አባል ከሆነች አማኝ ጋር ተገናኘች። በዚህም ጊዜ ታረቀች የተሐድሶ ቡድን አባል የሆነችው አማኝ ለየት ያለ የንግግር፥ የጸሎትና የአምልኮ ዘይቤ እንደምትከተል ተገነዘበች። ልዩነቱ ከምን እንደ መጣ ስትጠይቅ፥ ይህች የተሐድሶ አባል የክርስትና እምነት አስኳሉ ክርስቶስ እንደሆነ ገለጸችላት። ማምለክ፥ መጸለይ፥ መዘመርና ማክበር ያለብን ክርስቶስን ነው ስትል ገለጸችላት፡፡ ክርስቶስ ፍጹም አምላክ ከመሆኑ በተጨማሪም ፍጹም ሰውና ሊቀ ካህናችን በመሆኑ ሩቅና የማይደረስበት ሳይሆን፥ በቀጥታ ልንጸልይለት የምንችለው አምላክ ነው አለቻት። ድነት (ደኅንነት) በኦርቶዶክስ ቤተሰብ ውስጥ በመወለድ፥ ለድሆች በመመጽወት፥ ለቅድስት ማርያም ወይም ለመላእክት በመጸለይ፥ ሃይማኖታዊ በዓላት ላይ በመገኘት፥ ወዘተ.. እንደማይገኝ አብራራችላት። ድነት (ደኅንነት) ክርስቶስ ለኃጢአቷ መሥዋዕት ሆኖ እንደ ሞተ በማመን የምታገኘው የግላዊ ውሳኔ ውጤት እንደሆነም ገለጸችላት። ይህም ክርስቶስን የመከተልና ከእርሱ ጋር ኅብረት የማድረግን ፍላጎት እንደሚያሳድር አስረዳቻት።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ብዙ የኦርቶዶክስ አማኞች ከክርስቶስ ጋር የግል ግንኙነት ላመመሥረት የሚቸገሩት ለምንድን ነው? ከክርስቶስ ይልቅ ከቅዱሳን፥ ከመላእክት፥ ከድንግል ማርያም ጋር መዛመድ የሚቀላቸው ለምንድን ነው? ሐ) ከቅዱሳን፥ ከመላእክት፥ ወይም ከድንግል ማርያም ይልቅ በክርስቶስ ላይ ማተኮር ለምን እንደሚያስፈልግ ግለጽ።

የዕብራውያን መልእክት እንደ ኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች በመልካም ነገሮች ላይ ዓይኖቻቸውን ላሳረፉ አይሁዶች የተጻፈ መልእክት ነው። እነዚህ መልካም ነገሮች ግን እጅግ አስፈላጊዎች አልነበሩም። የአይሁድ አማኞች የብሉይ ኪዳን ጽሑፎችን፥ የእንስሳት መሥዋዕቶችን፥ ካህኖቻቸውን ወይም እንደ ሙሴ ያሉትን የብሉይ ኪዳን ቅዱሳን ማክበርን፥ እንዲሁም የቤተ መቅደሱን ሕንጻ ወሳኝ አድርገው ይቆጥሩ ነበር። እነዚህ መልካም ነገሮች ላይ በማተኮር፥ እግዚአብሔር ከሰዎች ጋር በቀጥታ ለመገናኘት የሚፈልግ መሆኑን ዘነጉ። እግዚአብሔር በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ሥጋ ለብሶ ሲመጣ አይሁዶች የብሉይ ኪዳን የተስፋ ቃሎች ፍጻሜ አድርገው ሊቀበሉት አልፈለጉም። እግዚአብሔር አዲስ ነገር እንዳደረገ ሳያውቁ ባህላዊ እምነቶቻቸውንና ልምምዶቻቸውን መከተላቸውን ቀጠሉ።

በኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ተመሳሳይ ዝንባሌ ይታያል። መልካም አስተሳሰብ ያላቸው ብዙ ሰዎች በቤተ ክርስቲያን ሕንጻዎቻቸው በካህኖቻቸው፥ በታቦት፥ በሃይማኖታዊ ባርነት ወይም በጾም ላይ ያተኩራሉ። ቅዱሳንን፥ መላእክትንና ድንግል ማርያምን በጥንቃቄ ያከብራሉ። ይህን በማድረጋቸው ግን እግዚአብሔር በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን እንደ ልጆቹ በቀጥታ ከእርሱ ጋር እንዲገናኙ የሚፈልግ መሆኑን ለማየት ታውረዋል። ክርስቶስ በሞተበት ጊዜ ሰውንና እግዚአብሔርን ይለይ የነበረው የቤተ መቅደስ መጋረጃ ተቀዷል። አሁን ኢየሱስ ክርስቶስ የግል ኃጢአታቸው መሥዋዕት እንደሆነ የሚያምኑ ሰዎች በሙሉ በድፍረትና በልበ ሙሉነት እግዚአብሔር ወደሚገኝበት የጸጋው ዙፋን ሊቀርቡ ይችላሉ። በዚህም ጊዜ ከሚወዳቸውና ከሚንከባከባቸው ሰማያዊ አባታቸው ጋር እንደሚነጋገሩ ይረዳሉ።

የዕብራውያን ጸሐፊ ይህንን ታላቅ መጽሐፍ የጻፈው እግዚአብሔር በክርስቶስ ኢየሱስ በኩል ያከናወነውን ተግባር ቸል እያሉ በትውፊቶችና ውጫዊ ነገሮች ላይ ማተኮሩ ስሕተት መሆኑን ለማመልከት ነው። ይህ መጽሐፍ ከውጫዊ ነገሮች ወይም ከትውፊቶቻችን በላይ የእምነታችን ጀማሪና ራስ በሆነው (ዕብ 12፡2-3) በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ዓይናችንን እንድንተክል ያሳስበናል። ይህ መልእክት አይሁዶች በብሉይ ኪዳን አምልኮ ውስጥ እጅግ ከሚያከብሯቸው ነገሮች ሁሉ ክርስቶስ እንደሚበልጥ በጥንቃቄ ያሳያል። ጸሐፊው አይሁዶች ወደ ታሪካዊና ትውፊታዊ አምልኳቸው በመመለስ ክርስቶስ እንዳልሞተላቸው ሁሉ የቀድሞ አኗኗራቸውን እንዳይቀጥሉ በጽኑ ያስጠነቅቃቸዋል። ዛሬ እኛ እንደ ካህናትና ዝነኛ ሰባኪዎች በመሳሰሉት ሰዎች ትኩረት እንዳናደርግ ያስጠነቅቀናል። እንደ ማርያም ወይም መላእክት ያሉትን አማላጆችን መጠቀም የለብንም። እንዲህ የምናደርግ ከሆነ በክርስቶስ ኢየሱስ በኩል ከእግዚአብሔር ጋር ግንኙነት ማድረጉ በቂ እንዳልሆነ መግለጻችን ነው። ከእግዚአብሔር ጋር ያለንን ግንኙነት ለመለካት የቤተ ክርስቲያን አባልነት፥ ለደሃ መመጽወት፥ የአንድ ቤተ እምነት አባል መሆን፥ በልሳን መናገር ወይም ፈውሶች በመሳሰሉት ውጫዊ ነገሮች ላይ ማተኮር የለብንም። ይልቁንም መንፈሳዊ ዓይኖቻችን በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ሊያርፉና ከእርሱ ጋር ያለማቋረጥ ግንኙነት ልንፈጥር ይገባል።

ልክ እንደኛው አይሁዶችም የሃይማኖታቸው ሁሉ መሠረት ቅዱሳት መጻሕፍት (ብሉይ ኪዳን) መሆናቸውን ያምኑ ነበር። እግዚአብሔር ለግለሰቦች እራሱን ለመግለጡ እነርሱም በመንፈስ ቅዱስ ተመርተው የእግዚአብሔርን ቃላት ለመጻፍ በቅተዋል። አይሁዶች ቅዱሳት መጻሕፍትንና እግዚአብሔር መልእክቱን ለመጻፍ የተጠቀመባቸውን አገልጋዮች እጅግ ያከብሩአቸዋል። አይሁዶች ብሉይ ኪዳን እግዚአብሔር ለሰው ልጅ የገለጠው በእስትንፋሰ እግዚአብሔር የተጻፈ መልእክት እንደሆነና ይህም በቀዳሚነት ክርስቶስን ለሰዎች የሚገልጥ እንደሆነ ያምኑ ነበር። የሚገርመው ግን አይሁዶች አካላዊውን መጽሐፍ እጅግ እያከበሩት (የእግዚአብሔርን ቃል ለማክበር ብራናውን ይስሙት ነበር።)፤ የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት እጽንኦት የሰጡበትን ክርስቶስን ለማወቅ አልቻሉም። የዕብራውያን መልእክት ጸሐፊ የእግዚአብሔር የመጨረሻው መገለጥ የሆነው ክርስቶስ በብሉይ ኪዳን ውስት ከታዩት መገለጦች ሁሉ እንደሚበልጥ ለመግለጽ ማብራሪያውን ይጀምራል።

ጸሐፊው ታሪክን በሁለት ይከፍላል። እነዚህም ከጥንት ጀምሮ እና በዚህ ዘመን መጨረሻ የሚሉ ናቸው። ጥንት ወይም በብሉይ ኪዳን ዘመን፥ እግዚአብሔር ራሱን ገልጦ ለአይሁዶች ተናግሯል። እግዚአብሔር ራሱን ለነቢያት ለመግለጥ የተለያዩ መንገዶችን ተጠቅሟል። አንዳንዶች ራእዮችን አይተዋል። ሌሎች ደግሞ ሕልም አልመዋል። ሌሎች ቃሉን በሚጽፉበት ጊዜ መንፈስ ቅዱስ በልባቸው ላይ ሲንቀሳቀስ ይሰማቸው ነበር። እንዲሁም የእግዚአብሔርን ድምጽ ከመስማታቸው የተነሣ የጻፉ ነቢያትም ነበሩ። መልእክቱ የመጣበት መንገድ ወሳኝ አልነበረም። ዋናው ከእግዚአብሔር ዘንድ መምጣቱ እና የእግዚአብሔር ቃል መሆኑ ብቻ ነበር።

ክርስቶስ በመጣ ጊዜ፥ እግዚአብሔር ራሱንና ፈቃዱን ከብሉይ ኪዳን እጅግ በጠራ መንገድ ገልጧል። በሌላ ሰው በኩል ከመናገር ይልቅ ራሱ እግዚአብሔር በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ወደ ምድር መጣ። በዚህ ጊዜ በመናገር ብቻ ሳይሆን፥ ለሰዎች በሚታይ መልኩ የእግዚአብሔርን ባህሪ እና ፈቃድ በግልጽ አሳይቷል። ጸሐፊው ክርስቶስ መልካም ሰው፥ ወይም በብሉይ ኪዳን ዘመን የነበሩትን ነቢያት የሚመስል ሰው ብቻ እንዳልሆነ ይናገራል። ይልቁንም እርሱ ራሱ አምላክ ነበር። እግዚአብሔር በክርስቶስ በኩል ያስተላለፈው መገለጥ ከሌሎች የሚበልጠው የእግዚአብሔርን ፈቃድ የገለጠው ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ ከሰብአዊ ነቢያት የሚበልጥ በመሆኑ ምክንያት ነው። እርሱ በብሉይ ኪዳን ዘመን የእግዚአብሔርን ቃል ከተቀበሉትና እግዚአብሔር ራሱን አያሌ ጊዜያት ከገለጠባቸው ሰዎች ሁሉ በላይ ነው።

ሀ) የእግዚአብሔር መንግሥት ወራሽ የሆነውና እግዚአብሔር ወደ ዓለም የሚያመጣቸውን በረከቶች ሁሉ የሚቀበለው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። እርሱ ዙፋን ወራሽና አይሁዶች የሚጠብቁት መሢሕ ነው።

ለ) እግዚአብሔር አብ ነገሮችን ሁሉ ለመፍጠር ክርስቶስን ሾሟል።

ሐ) ክርስቶስ ሰው ብቻ ሳይሆን አምላክም ነው። እርሱም ከእግዚአብሔር አብ ጋር እኩል የሆነ ክብር አለው። የክብሩ መንጸባረቅና የባሕሪው ምሳሌ በመሆኑ በሕልውናው፥ በባሕሪውና በተግባራቱ ልክ እንደ እግዚአብሔር አብ ነው።

መ) ክርስቶስ «ሁሉን በሥልጣኑ ቃል እየደገፈ» አጽናፈ ዓለሙን ጠብቆ ያኖረዋል።

ሠ) ኃጢአታችንን የሚያነጻው ክርስቶስ ነው።

ረ) ክርስቶስ «በሰማያት በግርማው ቀኝ ተቀምጧል።» ይህም የክብር ስፍራ ነው። በጥንታዊ ባህሎች፥ አንድ ንጉሥ በአዛዥነት ከእርሱ ቀጥሎ ያለውን ባለሥልጣን (ብዙውን ጊዜ የራሱን ልጅ ወይም እንደ ጠቅላይ ሚኒስቴር ያለውን ባለ ሥልጣን) ከቀኙ ያስቀምጠው ነበር። ምንም እንኳን በዋንኛው ሰማያዊ ዙፋን ላይ የሚቀመጠው እግዚአብሔር አብ ቢሆንም፥ የዚህ መልእክት ጸሐፊ ክርስቶስ ከሌሎች ኃይሎች ሁሉ ከፍ ብሎ በእግዚአብሔር አብ የሥልጣንና የአገዛዝ ቀኝ እንደሚቀመጥ ይናገራል።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) እነዚህ ጥቅሶች ክርስቶስ ሙሉ በሙሉ አምላክ እንደሆነ የሚያሳዩበትን ሁኔታ አብራራ። ለ) ክርስቶስ ከእግዚአብሔር አብ ጋር እኩልና ዳሩ ግን የተለየ መሆኑን የሚያሳዩት እንዴት ነው? ሐ) እነዚህ ጥቅሶች እግዚአብሔር አብና ኢየሱስ ክርስቶስ አንድ እንጂ የተለያዩ የሥላሴ አካላት አለመሆናቸውን የሚያስረዳውን «የኢየሱስ ብቻ» ተከታዮች ትምህርት የሚያፈርሱት እንዴት ነው?

በአመዛኙ እንደ ሙሴና ሕዝቅኤል እግዚአብሔርን ለማየት በቻልን ብለን እናስባለን። ነገር ግን የዕብራውያን መልእክት ጸሐፊ ክርስቶስ በምድር ላይ በነበረበት ጊዜ ሙሴ ወይም ሕዝቅኤል ካዩበት በበለጠ እግዚአብሔርን በተሟላ መልኩ እንደገለጠው ያብራራል። ክርስቶስ ለደቀ መዛሙርቱ፥ «እኔን ያየ አብን አይቷል፤ እኔና አብ አንድ ነን» (ዮሐ 14፡9-10) ብሏል። አሁን ክርስቶስን በሥጋዊ ዓይናችን ልናየው አንችልም። ነገር ግን እግዚአብሔር አብ ክርስቶስን በወንጌላት ውስጥ ገልጦልናል። የሚያሳዝነው ብዙ ሰዎች በወንጌላት ውስጥ የእግዚአብሔር እጅግ የተሟላ መገለጥ በሆነው በክርስቶስ በኩል እግዚአብሔርን እያዩትም። ብዙዎቻችን ሰዎች ስለ ክርስቶስ ሲያወሩ ወይም ሰዎች በክርስቶስ ስም ተአምራትን ሲሠሩ ለማየት እንፈልጋለን። ወንጌላትን በጥንቃቄ የማናጠና ከሆነ በተግባራችን ለእግዚአብሔር አብ፥ «በእርግጥ በአንተ ደስተኞች አይደለንም፥ ግን አንተንና ባህሪህን፥ ፍቃድህን ለማወቅ አንፈልግም፥ ምክንያቱም ጊዜ ወስደን ልጅህ ኢየሱስ ክርስቶስን በቃልህ ውስጥ በተገለጠበት መልኩ ለማወቅ አንሻም» ማለታችን ነው።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስን በማጥናት እግዚአብሔር አብን በበለጠ ለማወቅ ምን እያደረግክ ነው? ለ) እግዚአብሔር አብና ወልድን በበለጠ ለማወቅ ልታደርግ የምትችላቸው ነገሮች ምን ምንድን ናቸው?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: