ከስደት ባሻገር ድነታችን (ደኅንነታችን) ትልቅ ሽልማት ያስገኝልናል (1ኛ ጴጥ. 1፡1-12)

ወርቅነሽ ተወልዳ ያደገችው በሰሜን ኢትዮጵያ ውስጥ ሲሆን፥ ቤተሰቦቿ ጠንካራ የኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች ነበሩ። አንድ ቀን አንድ ወንጌላዊ ወደ አካባቢያቸው መጥቶ ወርቅነሽ ከክርስቶስ ጋር የግል ግንኙነት ሊኖራት እንደሚገባ ነገራት። ከወንጌላዊው ጋር በምትወያይበት ጊዜ በክርስቲያን ቤተሰብ ውስጥ መወለዱ ወይም ክርስቶስ እንደ ሞተ ማመኗ ብቻ በቂ እንዳልሆነና ዳሩ ግን ክርስቶስ ድነትን (ደኅንነትን) የምታገኝበት ብቸኛው መንገድ እንደሆነ በማመን ልትከተለው እንደሚገባው ስለተገነዘበች፥ ክርስቶስን የግል አዳኝዋ አድርጋ አመነች። ወላጆቿ ስለ አዲሱ እምነቷ በሰሙ ጊዜ እጅግ ተቆጡ። «እንዲህ ዓይነት ሃይማኖት ለመከተል ምን መብት አለሽ? አዲሱ እምነትሽን ክደሽ ወደ ቀድሞው እምነትሽ ካልተመለስሽ አንድ አደገኛ ነገር ይደርስብሻል» ሲሉ አስፈራሯት። እምነቷን ለመካድ ባልፈለገች ጊዜ አባቷ ዱላ አንሥተው ይደበድቧት ጀመር። እራሷን ስታ እስክትወድቅ ድረስ ይህንኑ ድብደባቸውን ቀጠሉ። በየቀኑ ወንድሞቿ፥ እኅቶቿና ሌሎችም ዘመዶቿ ስሟን በመጥራት ይሳለቁባት ጀመር። ወላጆቿ ልብስ ሊገዙላት ወይም የትምህርት ቤት ክፍያ ሊከፍሉላት ፈቃደኞች ሳይሆኑ ቀሩ። የኋላ ኋላ በክርስቶስ ላይ ያላትን እምነት ለመካድ እንደማትፈልግ ሲገነዘቡ፥ ከቤታቸው አባረሯት። በዚህ ጊዜ ከኢኮኖሚያዊ ችግር ባሻገር፥ ከቤተሰቦቿ በመለየቷ ልቧ ቆሰለ። «ለመሆኑ ይህ ለእኔ የእግዚአብሔር ፈቃድ ነውን? እኔ ትክክል ከሆንኩ፥ ለምንድን ነው በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ የምሠቃየው?» ስትል ታስባለች።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ክርስቶስን ለመከተል በመወሰናቸው ከፍተኛ ሥቃይ የደረሰባቸውና በግል የምታውቃቸው ሰዎች ሁኔታ ምን እንደሚመስል ግለጽ። ለ) ወርቅነሽ ወደ አንተ መጥታ እግዚአብሔር ለምን በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ እንድትሠቃይ እንደሚፈቅድ ብትጠይቀህ፥ ምን መልስ ትሰጣታለህ?

እንደ ወርቅነሽ ሁሉ ከመቶዎች በሚቆጠሩ ዓመታት በፊት በትንሿ እስያ ውስጥ ተበትነው ይኖሩ የነበሩ አማኞች በክርስቶስ በማመናቸው ምክንያት ስደትን ይጋፈጡ ነበር። «እምነታችን እውነት ከሆነ፥ ትክክለኛ ምርጫ በመውሰዳችን የምንሠቃየው ለምንድን ነው? ከዚህ ስደት ለማምለጥ ስንል ወደ ጥንቱ የአምልኮ ሥርዓታችን መመለስ አለብን? በዚህ ዓይነት ሥቃይን እየተቀበልን ሳለ እግዚአብሔር ከእኛ ምን ይጠብቃል?» የሚሉ ጥያቄዎች በእነዚህ አማኞች አእምሮ ውስጥ ይጉላሉ እንደነበር አይጠረጠርም። የ1ኛ ጴጥሮስ መልእክት ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ይሰጣል። ጴጥሮስ ለእነዚህ ለተበተኑ አማኞች ሲጽፍ፥ ስደት በሚመጣባቸው ጊዜ በእምነታቸው ጸንተው እንዲቆሙ ያበረታታቸዋል። ስደት ለጴጥሮስ አዲስ ነገር አልነበረም። ብዙ ጊዜ የታሰረና የተደበደበ ሲሆን፥ በቅርቡም ለእምነቱ ሲል የሞት ቅጣት ይፈጸምበት ነበር።

ብዙዎቻችን በተለያዩ መንገዶች ስደትን እንጋፈጣለን። የ1ኛ ጴጥሮስ መልእክት ስደትን ለመቋቋም በሚያስችል መልኩ ብቻ ሳይሆን፥ በስደት ውስጥ እግዚአብሔርን በሚያስከብር መንገድ መኖር እንዳለብን ያስነዝበናል።

ሰይጣን በስደት ጊዜ ተስፋ ሊያስቆርጠን ከሚፈልግባቸው መንገዶች አንዱ ከክርስቶስና እርሱ ካዘጋጀልን ዘላለማዊ በረከቶች ላይ ዓይኖቻችንን እንድናርቅ ማድረግ ነው። ሰይጣን በስደት ላይ በማተኮር በራሳችን እንድናዝን ይፈልጋል። በመከራ ጊዜ ተስፋ ሊያስቆርጠን ሲሞክር ሰይጣንን ልንቃወም ከምንችልባቸው መንገዶች አንዱ በእግዚአብሔር እና ከእርሱ ጋር ባለን ግንኙነት ላይ ትኩረታችንን መልሶ ማሳረፍ ነው። ጴጥሮስም ያደረገው ይሄንኑ ነበር። በመግቢያው ላይ፥ ጴጥሮስ ወዲያውኑ የአማኞቹን ቀልብ ከእግዚአብሔር ጋር ወዳላቸው ግንኙነት ሲመልስ እንመለከተዋለን። ጴጥሮስ አማኞችን ምን ብሎ እንደሚጠራቸው አጢን፡-

  1. የእግዚአብሔር ምርጦች፡ እግዚአብሔር አብርሃምን፥ ሙሴን ዳዊትንና ሌሎችንም ሰዎች እንደ መረጠ ሁሉ፥ እያንዳንዱ አማኝ የእርሱ ልጅ እንዲሆን መርጦታል። ዓለም ከንቱዎችና ሞኞች አድርጋ ብትቆጥረንም፥ በዓለም ውስጥ ካሉት ሰዎች ሁሉ መካከል እግዚአብሔር እንደ መረጠን ልናስታውስ ይገባል። እርሱ ከልቡ ይወደናል።
  2. መጻተኞች፡- ስደት የሰውን ልብ ከሚያቆስልባቸው መንገዶች አንዱ ከምንፈልጋቸው ነገሮች የሚያራርቀን በመሆኑ ነው። ብዙውን ጊዜ ከቤተሰቦቻችን፥ ከዘመዶቻችን፥ ከማኅበረሰቡ፥ ወዘተ… ይለየናል። በዚህን ጊዜ ብቸኝነት ይሰማናል። ስደት አንዳንድ ጊዜም ከጥሩ አኗኗር፥ ከትምህርት፥ እንዲሁም ከሥራ ይለየናል። ጴጥሮስ ይህንን ብቸኝነት በመገንዘብ፥ ብቸኛ የሆንንበት እውነተኛ ምክንያት ገና ከቤታችን ስላልደረስን መሆኑን ይናገራል። ቤታችን በሰማይ ነው፡፡ እውነተኛ ቤተሰባችን ያለው እዚያው ነው። በስደት ውስጥ የሚያልፉ ክርስቲያኖች በዚህን ጊዜያዊ ሕይወት ውስጥ እያለፍን ወደ ዘላለማዊው ቤታችን እየሄድን መሆናችንን መገንዘብ ይኖርባቸዋል። ይህንን ካስታወስን፥ ስደትን መቀበሉ ቀላል ይሆንልናል።
  3. እግዚአብሔር አብ አስቀድሞ እንዳወቃቸው፡ ጴጥሮስ እያንዳንዱ የሥላሴ አካል በደኅንነታችን ውስጥ እንዴት እንደ ተሳተፈ ያሳያል። እግዚአብሔር አብ ልጆቹ እንድንሆን መረጠን። የእግዚአብሔር ልጆች የሆንነው በአጋጣሚ ወይም በክርስቲያን ቤተሰብ ውስጥ በመወለዳችን አይደለም። ነገር ግን እግዚአብሔር አብ ከፍቅሩ የተነሣ እኔንና እንተን መርጦ ልጆቹ አድርጎናል። ይህም የሚያስደንቅ ነገር ነው!
  4. በመንፈስ የመቀደስ ሥራ፡ የእግዚአብሔርን ጥሪ እንድንሰማና እንድናምን የሚያደርገን መንፈስ ቅዱስ ነው። እርሱ ይቀድሰናል ወይም ይለየናል። ይህም ማለት፡- ሀ) እኛን የእግዚአብሔር ልጆች ለማድረግ በዓለም ውስጥ ካሉት ሌሎች ሰዎች ይለየናል። ለ) በተቀደሰው አምላክ ፊት ቅዱሳንና ተቀባይነት ያለን ሰዎች ያደርገናል።
  5. ይታዘዙና በኢየሱስ ክርስቶስ ደም ይረጩ ዘንድ፡ እግዚአብሔር ያዳነን ከሲዖል እንድናመልጥ ብቻ አይደለም። ነገር ግን ኢየሱስ ክርስቶስን በመታዘዝ እንድናስከብረው አድኖናል። ክርስቶስ ባዳነን ጊዜ፥ ይህንን ያደረገው እንዳሻን እንሆን ዘንድ ሕይወታችንን ቀላል ለማድረግ አልነበረም። ይልቁንም የክርስቶስ ተከታዮች እንድንሆንና ለእግዚአብሔር እየታዘዝን እንድንኖር ነው። ብዙውን ጊዜ ይህ የታዛዥነት ጎዳና ወደ ስደት ይመራናል። ክርስቶስ ከሥቃዩ ባሻገር ለእርሱ ታማኞች ሆነን እንድንቀጥል ይጠይቀናል።

የውይይት ጥያቄ፡- በስደት ውስጥ ያሉ ክርስቲያኖች እነዚህን አምስት እውነቶች ማወቃቸው አስፈላጊ የሚሆነው ለምንድን ነው?

በስደትና መከራ ጊዜ ሊያበረታታን የሚገባ ሌላው ነገር ደግሞ እግዚአብሔር የሰጠንን ታላቅ ድነት (ደኅንነት) ማስታወስ ነው። ጴጥሮስ እግዚአብሔርን ስለዚሁ ታላቅ ተስፋ ያመሰግነዋል። ይህ ድነት (ደኅንነት) የተገኘው ከምርጫችን ወይም ካደረግነው አንዳች ተግባር ሳይሆን፥ ከታላቅ ምሕረቱ የተነሣ ነው። ይህም ድነት (ደኅንነት) አዲስ ልደትን ያስገኝልናል (የእግዚአብሔር ልጆች ያደርገናል)። እንዲሁም በኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ ምክንያት እኛም ከሞት እንደምንነሣ ያረጋግጥልናል። የእኛም ድነት (ደኅንነት) ማንም ሊነጥቅብን ወደማይችለው የዘላለም በረከቶች ውርስ ይመለከታል። ምንም እንኳን መከራዎች በአሁን ሰዓት ከፍተኛ ስጋት ቢያስከትሉብንም፥ እነዚህ በረከቶች በምድር ላይ የምንጋፈጣቸው መከራዎች ቀለል ብለው እንዲታዩን ያደርጋሉ። (2ኛ ቆሮ. 4፡16-18 አንብብ)።

ጴጥሮስ ለእነዚህ አማኞች ይህ ድነት (ደኅንነት) ምን ያህል ታላቅና ልዩ እንደሆነ ይናገራል። የብሉይ ኪዳን ነቢያት ስለዚሁ ልዩ መዳን የተነበዩ ሲሆን (ለምሳሌ፥ ኤር. 31-34)፥ እግዚአብሔር ይህንን ተግባር ከፍጻሜ የሚያደስበትን ሁኔታ ለመረዳት ናፍቀው ነበር። እነዚህ ነቢያት ስለ ክርስቶስ ሞት በመተንበይ ለአዲሱ ኪዳን ዘመን አማኞች እያገለገሉ ነበር። ታላላቅ የሰማይ መላእክት እንኳን እግዚአብሔር ለኃጢአተኛ ሰዎች የሰጠውን ድነት (ደኅንነት)፥ የሰጠውን ስጦታና የሰጠውን ፍቅር በመመልከት ተደንቀዋል። ይህም ሙሉ በሙሉ ሊረዱት የማይችሉት ነው።

እንደ እግዚአብሔር ልጆች በሰማይ ርስት አለን፥ ይህም ማንም የማይወስደው ነው። ከዚህም በላይ፥ እግዚአብሔር ዘላለማዊ መንግሥቱ እስኪመጣ ድረስ ይጠብቀናል። ይህ ጥበቃ ምንን እንደሚያካትት መገንዘቡ ጠቃሚ ነው። አንዳንድ ጊዜ እግዚአብሔር ልጆቹን በዚህ ምድር ላይ ከስደትና መከራ ይጠብቃቸዋል። ለምሳሌ ያህል፥ እግዚአብሔር የዳንኤልን 3 ጓደኞች ከእሳት አድኗቸዋል (ዳን. 3)። ብዙውን ጊዜ ግን እግዚአብሔር በመከራ ውስጥ ሆነን ይጠብቀናል። ለእምነታችን ጸንተን የምንቆምበትን ኃይል ይሰጠናል። በታማኝነት እንድንቆም የሚያደርገን እርሱ ነው። ወደ ዘላለማዊ ቤታችን እንድንደርስ ይጠብቀናል።

ነገር ግን እግዚአብሔር ብዙውን ጊዜ መከራ እንድንቀበል የሚፈቅደው ለምንድን ነው? (ጴጥሮስ ልዩ ልዩ መከራ፥ ስደትን ብቻ ሳይሆን፥ እንደ በሽታ፥ ድህነት፥ ሥራ ማጣት፥ የቤተሰብ አባላት ሞት፥ የተፈጥሮ አደጋ የመሳሰሉትን ነገሮች እንደሚያመለክት ለማሳየት ልዩ ልዩ ፈተና የሚለውን ሐረግ ይጠቀማል። እነዚህም መከራን የሚያመጡና እነዚህም በሕይወታችን ውስጥ ሥቃይን የሚያስከትሉና እግዚአብሔር በመሣሪያነት የሚጠቀምባቸው ናቸው።) መጽሐፍ ቅዱስ ለምን መከራ በሕይወታችን እንደሚመጣ ለማመልከት የሚያቀርባቸው አያሌ ምክንያቶች አሉ።

  1. ጴጥሮስ እሳት ወርቅ እንደሚያጠራ ሁሉ መከራም ሕይወታችንን እንደሚያጠራ ይናገራል። መከራ እምነታችንን በማጥራት በሂደቱ ውስጥ እየበሰለ እንዲሄድ ያደርጋል። በተጨማሪም መከራ እግዚአብሔር ኩራትን፥ ራስ ወዳድነትን፥ የዓለምን ፍቅር፥ ወዘተ… በማቃጠል ባህሪያችንን ለመቅረጽ የሚጠቀምበት ዐቢይ መሣሪያ ነው።
  2. የእግዚአብሔር ልጆች በመከራ ጊዜ ጸንተው መቆማቸው እግዚአብሔርን ያስከብራል። በክርስቶስ ላለን እምነት እጅግ ጠንካራ ምስክርነቶች ከሚሆኑት ነገሮች ሁሉም ነገር አልሳካ እያለን በእግዚአብሔር ላይ ያለንን እምነት አለመተዋችን ነው። ሰይጣን በኢዮብ ላይ ያቀረበውን ክስ ታስተውላለህ። ሰይጣን ለእግዚአብሔር ባቀረበው ክስ የኢዮብ እምነት ከእግዚአብሔር ላይ በሚያገኛቸው በረከቶች ላይ የተመሠረተ እንደሆነ ገልጾአል። ሰይጣን፥ «በረከቶቹን ብትወስድበት ኢዮብ በፊትህ ይሰድብሃል» ብሎ ነበር። ነገር ግን በረከቶቹ ሁሉ ከተወሰዱበት በኋላ፥ ኢዮብ፥ «እግዚአብሔር ሰጠ እግዚአብሔር ነሳ የእግዚአብሔር ስም የተመሰገነ ይሁን» (ኢዮብ 1፡20-22) ብሏል። በተመሳሳይ ሁኔታ፥ በታላቅ መከራ ውስጥ ሆነን በእግዚአብሔር ላይ ያለንን እምነት መጠበቃችን እግዚአብሔርን ለሰጠን በረከቶች ሳይሆን ለማንነቱ ብለን እንደምናምን ማረጋገጣችን ነው።
  3. መከራ ለእግዚአብሔር ፍቅር እንዳለን ያሳያል። እንደ ጴጥሮስ ክርስቶስን ባናየውም፥ እንወደዋለን፤ ከእርሱም ጋር የጠበቀ ግንኙነት አለን። ነገሮች መልካም በማይሆኑበት ጊዜ ሳይቀር በክርስቶስ ያለንን እምነት ስንጠብቅ፥ ይኸው ፍቅር ይበልጥ እየጠራ ይሄዳል።
  4. ጳውሎስ በመከራ ውስጥ ያሉትን ሰዎች ለማገልገል እንድንችል እግዚአብሔር የሚጠቀምበት መሣሪያ እንደሆነ ገልጾአል (2ኛ ቆሮ. 1:3-7)።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) አንድን መከራ የተጋፈጥክበትን ሁኔታ ግለጽ። ይህ መከራ ከላይ ከተጠቀሱት አራት ነገሮች ወይም ሌሎች ምክንያቶች በሕይወትህ ውስጥ የትኛውን የፈጸመ ይመስልሃል? ለ) ብዙ ክርስቲያኖች እግዚአብሔር ከወደደንና እምነት ካለን፥ መከራ፥ እንደማይደርስብን ይናገራሉ። ይህ እውነት ይመስልሃል? በአማኞች ላይ ስለሚደርስ መከራ ያለህን ግንዛቤ ለማስደገፍ የሚያግዙህ ጥቅሶች የትኞቹ ናቸው?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

1 thought on “ከስደት ባሻገር ድነታችን (ደኅንነታችን) ትልቅ ሽልማት ያስገኝልናል (1ኛ ጴጥ. 1፡1-12)”

  1. mekera sigetmen getan bemayet lersu yalenn fker ena emnet bemetebek yeseytanen shingela balemesmat degmom zelelemawina yemaytefa yemaybelash erst endalen bemaseb yemitayewu yegizewu yemaytayewu gen yezelalem endehone bemaseb betesefana bemnet lnesena yegebal

Leave a Reply

%d bloggers like this: