ክርስቲያኖች የተቀደሰ ሕይወት መምራት ይኖርባቸዋል (1ኛ ጴጥ. 4፡1-6)።
በመከራ ውስጥ በማለፍ ክርስቶስ ድልን ተቀዳጅቷል። እግዚአብሔር ክርስቶስን በማክበር ከሁሉም በላይ ሥልጣን ሰጥቶታል። ክርስቲያኖች መከራ በሚቀበሉበት ጊዜ የክርስቶስን ምሳሌነት ቢከተሉ ድል ነሺዎች ይሆናሉ። ብንሠቃይም፥ በኃጢአት ተፈጥሮአችን ላይ ድልን እንቀዳጃለን። መከራ ክርስቲያኖች በክርስቶስ ላይ እንዲደገፉ ይረዳቸዋል። ከዘላለም ዘመን አንጻር አስፈላጊው ነገር ምን እንደሆነ ለይተው እንዲያውቁ ያግዛቸዋል። በሕይወታችን ውስጥ ያለውን ኃጢአት ተመልክተን እግዚአብሔርን ይቅርታ እንድንጠይቅ ያግዘናል። በስደት የሚሠቃዩት ሰዎች በአመዛኙ የዓለማውያንን ፈሪሃ እግዚአብሔር የጎደለበት ሕይወት አይጋሩም። እምነታቸውን ክደው ወይም ደብቀው ከዓለማውያን ጋር ይተባበራሉ ወይም መከራን ከሚቀበሉ አማኞች ጋር ሆነው የተቀደሰ ሕይወት ይመራሉ። ነገር ግን ክርስቲያኖች መከራ የሚያደርሱባቸው ሰዎች የሚቀጡበት ጊዜ እንደሚመጣ ማስታወስ ይኖርባቸዋል። በክርስቶስ ለሚያምኑ ክርስቲያኖች፥ የዘላለም ሕይወት ተዘጋጅቶላቸዋል። በክርስቶስ የማያምኑ ሰዎች ግን የዘላለም ሞት ይጠብቃቸዋል። ዛሬ እምነታችንን ክደን ጊዜያዊውን መከራ ልናመልጥ ብንችልም፥ ይህ ለዘላለማዊ ፍርድ የሚያጋልጠን በመሆኑ አደገኛ ነው። ይልቁንም ጊዜያዊውን መከራ ተጋፍጦ ወደ ዘላለማዊ ሕይወት መሻገሩ አስተዋይነት ነው።
የእግዚአብሔር ሕዝብ ሌሎች አማኞችን ከልባቸው መወደድ ይኖርባቸዋል (1ኛ ጴጥ. 4፡7-11)።
ጴጥሮስ ስለ ጸሎት በማካፈል ማብራሪያውን ይጀምራል። በሚያስገርም ሁኔታ እንደ ባለ አእምሮ ማሰብንና ራስን መቆጣጠርን ከጸሎት ጋር ያዛምደዋል። ጸሎት ስለ አንዳንድ ነገሮች ስናስብ የምናነበንበው ልማድ መሆን የለበትም። እንዲሁም ጸሎታችን በራስ ወዳድነት ወይም በፍርሃት ላይ መመሥረት የለበትም። ይልቁንም ጸሎታችን አስፈላጊና ዘላለማዊ በሆኑት ነገሮች ላይ መመሥረት ይኖርበታል። እነዚህም ነገሮች በእግዚአብሔር ቃል ውስጥ የተገለጡና የእግዚአብሔርን ዓላማዎች የሚያንጸባርቁ ናቸው። ይህም የእግዚአብሔር ዓላማዎች በስደታችን ውስጥ ጭምር የሚገለጡ ናቸው። መከራ በምንቀበልበት ጊዜ፥ «ይህን መከራ ከእኔ አስወግድ» የሚለው ጸሎት ወደ ልባችን መምጣቱ የማይቀር ነው። ነገር ግን ጴጥሮስ በመከራ ውስጥ የሚገለጹትን አንዳንድ የእግዚአብሔር ዓላማዎችንና ክርስቶስም በቅርብ ጊዜ እንደሚመለስ ከተረዳን ጸሎታችን እንደሚቀየር ይናገራል። በመከራችን ውስጥ ክርስቶስን ለማስከበር የምንችልበትን ኃይል እንድናገኝ መጸለይ እንጀምራለን፡፡ ለሚያሳድዱን ሰዎች ተገቢውን ምላሽ ለመስጠት እንድንችል የእግዚአብሔርን ኃይል እንጠይቃለን። እግዚአብሔር ሕይወታችንን እንዲቀድሰው እንጠይቀዋለን። ደፍረን ለመመስከር እንድንችልም እንጸልያለን።
በስደት ጊዜ ልናደርጋቸው ከሚገቡን ጉዳዮች አንዱ አማኞች እርስ በርሳችን በጥልቅ ፍቅር መዋደዳችን ነው። በስደት ጊዜ የተሳሳተ ግንዛቤ መያዝና በኃጢአት መውደቅ ሊከሰት ይችላል። ነገር ግን ስለ አንድ ሰው መጥፎውን ከማሰብ ወይም እርስ በርስ ከመጋጨት ወይም ቤተሰባዊ መሥመሮችን ተከትሎ ከመከፋፈል ይልቅ፥ አማኞች እርስ በርሳቸው ለመዋደድ መቁረጥ አለባቸው። ለእርስ በርሳችን ፍቅር ልናሳይ የምንችልባቸው አያሌ መንገዶች አሉ።
ፍቅራችን ሌሎች ኃጢአት በሚሠሩበት ጊዜ ቁጣችንን በመሸፈን፥ በስሜት መጎዳትና መከፋፈል እንዳይከሰት ያደርጋል።
- ስደት የደረሰባቸው ክርስቲያኖች ለሌሎች ክርስቲያኖች ማበረታቻ መስጠት አለባቸው። መተጨማሪም በእንግድነት ሊቀበሏቸው ይገባል።
- እግዚአብሔር ለእያንዳንዱ አማኝ የተለያዩ መንፈሳዊ ስጦታዎችን ሰጥቷል። እነዚህን ስጦታዎች እርስ በርሳችን ለማገልገል እና ለእግዚአብሔር ክብር ለማዋል ልንጠቀምባቸው ይገባል። መንፈሳዊ ስጦታዎች የሥልጣን ስፍራ እንድናገኝ ወይም ከሰዎች ክብርን እንድንቀበል፥ እንዲሁም ለማንኛውም የግል ጥቅም የምንገለገልባቸው አይደሉም (ጴጥሮስ ከጸጋ ስጦታዎች መካከል መናገርንና ማገልገልን በምሳሌነት ገልጾአል።) መንፈስ ቅዱስ እነዚህን ስጦታዎች የሚሰጠን አንዳችን ሌላችንን ለማገልገል እንድንችል ነው። ቁልፉ ነገር ስጦታውን መጠቀማችን ሳይሆን፥ ስጦታውን ስንጠቀም ሊኖረን የሚገባው አስተሳሰባችን ነው። ዋናው ነገር መንፈሳዊ ስጦታዎችን መጠቀማችን ብቻ ሳይሆን፥ እግዚአብሔር የሰጠንን ስጦታዎች የምንጠቀምበት ባህሪም ወሳኝ ነው። መንፈሳዊ ስጦታችን ታላቅ መሆኑ እግዚአብሔርን አያስደንቀውም። ምክንያቱም የመንፈሳዊ ስጦታውን ደረጃ የወሰነው እርሱ ነው። ነገር ግን እግዚአብሔርን በዋናነት የሚያሳስበው ስጦታችንን በታማኝነት መጠቀማችን ነው። ክርስቶስ ሽልማትን የሚሰጠን እርሱ የሰጠንን ስጦታ በታማኝነት መጠቀማችንን በመመርመር እንጂ እርሱ በሰጠን የስጦታ ደረጃ አይደለም።
ክርስቲያኖች ስደትን በደስታ መቀበል አለባቸው (1ኛ ጴጥ. 4፡12-19)።
ጴጥሮስ አሁንም ወደ መጽሐፉ ዋነኛው ጉዳይ ይመለሳል። ይኸውም በዘመኑ የነበሩት ክርስቲያኖች የሚጋፈጡት ስደትና መከራ ነው። በዚህ ጊዜ ጴጥሮስ ለስደት የሚያቀርበውን ትምህርት አንድ ደረጃ ወደፊት ያልቀዋል። ጴጥሮስ መከራን እንድንቀበል ብቻ ሳይሆን መከራን በምንቀበልበት ጊዜ አጸፋውን እንዳንመልስም ጭምር ነው የሚያስተምረን፡፡ ክርስቲያኖች መከራን መቀበል ወይም መከራ የሚያደርሱባቸውን ሰዎች አለመበቀል ብቻ ሳይሆን፥ ስደትን እንደ ዕድል መቁጠር ይኖርባቸዋል። ይህም ደስ እንድንሰኝ ያደርገናል። የምንደሰተው በመሰደዳችን ሳይሆን፥ የክርስቶስ መከራ የመቀበል ዕድል ስለገጠመን ነው። በምንሰደድበትም ጊዜ ስለ እኛ መከራ ከተቀበለው ክርስቶስ ጋር እንተባበራለን። ለክርስቶስ መከራ መቀበል ደግሞ እግዚአብሔር እንደሚተማመንበትና እንደሚያከብረን የሚያመለክት ማስረጃ ነው። መሰደድ መንፈስ ቅዱስ በሕይወታችን ውስጥ መኖሩን ያሳያል። ክርስቶስ በክብሩ በሚመለስበት ጊዜ ሽልማትን እንደምናገኝ እናውቃለን።
(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)