የ2ኛ ጴጥሮስ ልዩ ባሕርያት፣ መዋቅር፣ እና አስተዋጽኦ

፩. የ2ኛ ጴጥሮስ ልዩ ባሕርያት

  1. ብዙ ምሁራን የይሁዳን መልእክት ከ2ኛ ጴጥሮስ 2፡1-22 ጋር ያነጻጽራሉ። እንዲያውም ከይሁዳ መልእክት 25 ጥቅሶች መካከል 19ኙ ከ2ኛ ጴጥሮስ ጋር ተመሳሳይ ናቸው። ይህ ማለት ጴጥሮስ የይሁዳን መልእክት ወይም ይሁዳ የ2ኛ ጴጥሮስን መልእክት ማንበቡን ወይም፥ ሁለቱም በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የተሰጠው አንድ ትምህርት በማጣቀሻነት መጠቀማቸውን ሊያመለክት ይችላል። ትክክለኛው ሁኔታ የትኛው እንደነበረ ግን ማወቁ አስቸጋሪ ነው። ሌላው አስተሳሰብ ጴጥሮስና ይሁዳ ሁለቱም ሌላ ሰው የጻፈውን ሰነድ በማጣቀሻነት ተጠቅመዋል የሚል ነው።
  2. የዚህ መልእክት ቋንቋ የአጻጻፉ ስልት ከ1ኛ ጴጥሮስ የተለየ ነው። ይህም አንዳንድ ምሁራን ጴጥሮስ ይህን መልእክት አልጻፈው ይሆናል ብለው እንዲጠራጠሩ አድርጓቸዋል። ይሁንና ጴጥሮስ በ1ኛ ጴጥሮስ እንዳደረገው ሲላስን በጸሐፊነት ከመጠቀም ይልቅ እራሱ መልእክቱን እንደ ጻፈ ወይም ሌላ ጸሐፊ እንደ ተጠቀመ መገመት ይቻላል። የመልእክቶቹ ፍሬ አሳብ የተለያየ በመሆኑ የተለያየ የአጻጻፍ ስልት ተጠቅሞ ሊሆን ይችላል።
  3. ጴጥሮስ የጳውሎስን መልእክቶች እንደ ቅዱሳት መጻሕፍት ይጠቅሳቸዋል (2ኛ ጴጥ. 3፡15-16)። ይህም ጳውሎስ መልእክቶቹን ከጻፈ በኋላ የቀድሞዎቹ ክርስቲያኖች መልእክቶቹ ተራ የሰው ሥራዎች ሳይሆኑ የመንፈስ ቅዱስ ኃይል ያረፈባቸው መሆኑን እንደተገነዘቡ ያሳያል። በመሆኑም የጳውሎስን መልእክቶች ማሰባሰብና ማንበብ ጀምረው እንደነበር እንረዳለን።”

፪. የ2ኛ ጴጥሮስ መዋቅር

የ2ኛ ጴጥሮስ መልእክት የተዋቀረው በመጽሐፉ ውስጥ በሚገኙት ሦስት ዐበይት ትምህርቶች መሠረት ነው።

  1. ጴጥሮስ ክርስቲያኖች በእምነታቸው እና በእግዚአብሔር ቃል እውቀት እንዲያድጉ ይመክራቸዋል (2ኛ ጴጥ. 1)። የመንፈሳዊ እድገት ቁልፍ ቁም ነገር ከመንፈስ ቅዱስ የሚመጣ የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት ነው።
  2. ጴጥሮስ ክርስቲያኖች መጽሐፍ ቅዱስን ከሚበርዙ ሐሰተኛ ትምህርቶች እንዲጠበቁ ያስጠነቅቃል (2ኛ ጴጥ. 2)። እነዚህ አስተማሪዎች በትዕቢት፥ በራስ ወዳድነት እና ግብረገባዊነት በጎደላቸው አኗኗሮች የሚታወቁ ነበሩ።
  3. ጴጥሮስ ክርስቶስ ተመልሶ አይመጣም የሚለውን እሳብ ፉርሽ በማድረግ ተገቢውን ምላሽ ይሰጣል (2ኛ ጴጥ. 3)። ጴጥሮስ ክርስቶስ ዳግም ተመልሶ እንደሚመጣና ዳሩ ግን እግዚአብሔር እንደ እኛ በጊዜ የተገደበ አምላክ አለመሆኑን ያስረዳል። ለእግዚአብሔር አጭር የሆነ ጊዜ ለእኛ ረጅም ሊሆን ይችላል። ክርስቶስ በቶሎ ያልተመለሰበት አንደኛው ምክንያት ከጸጋው የተነሣ መሆኑን ይናገራል። እግዚአብሔር ሰዎች ንስሐ ገብተው ክርስቶስ በሚመጣበት ጊዜ ከሚገለጸው የእግዚአብሔር ፍርድ እንዲተርፍ ይፈልጋል። በዚያን ጊዜ ዛሬ የምናውቃት ዓለም ሙሉ በሙሉ ትወድምና አዲስ ምድርና አዲስ ሰማይ ይፈጠራሉ።

፫. የ2ኛ ጴጥሮስ አስተዋጽኦ

  1. ጴጥሮስ አማኞች በእምነታቸውና በእግዚአብሔር ቃል እውቀት እንዲያድጉ ይመክራቸዋል (2ኛ ጴጥ. 1)።

ሀ) መግቢያ (2ኛ ጴጥ. 1፡1-2)

ለ) አማኞች በእግዚአብሔር ላይ ያላቸውን እምነት ለማረጋገጥ በመንፈሳዊ ባህሪ ማደግ አለባቸው (2ኛ ጴጥ. 1፡3–11)

ሐ) አማኞች ከመንፈስ ቅዱስ የመጣውን የእግዚአብሔርን ቃል እውነቶች ማስታወስ አለባቸው (2ኛ ጴጥ. 1፡12-21)።

  1. ጴጥሮስ አማኞች መጽሐፍ ቅዱስን ከሚበርዙ ሐሰተኛ አስተማሪዎች እንዲጠነቀቁ ያሳስባል (2ኛ ጴጥ. 2)።
  2. ጴጥሮስ ክርስቶስ እንደ ተስፋ ቃሉ አይመለስም የሚለውን አስተሳሰብ ፉርሽ ያደርጋል (2ኛ ጴጥ. 3)።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: