የሕይወት እንጀራ

2ኛ የጴጥሮስ መልእክት

ጴጥሮስ ክርስቶስ ቃል እንደገባው ተመልሶ አይመጣም የሚለውን አሳብ ፉርሽ ያደርገዋል (2ኛ ጴጥ. 3፡1-18)

በመቀጠልም ጴጥሮስ በአብያተ ቤተ ክርስቲያናት እየተሰራጩ ካሉት ሐሰተኛ ትምህርቶች የአንደኛውን አስተምህሮ ሲያፈርስ እንመለከታለን። የክርስቶስን ዳግም ምጽአት የተጠራጠሩ ሰዎች የነበሩ ይመስላል። «ሰዎች ሁልጊዜም ስለ ዓለም ፍጻሜ ሲተነብዩ ኖረዋል። ይሄ እስካሁን አልተከሰተም። ክርስቶስም በቶሎ እመለሳለሁ ብሎ ነበር። ነገር ግን ይኸው ከ30 ዓመታት በኋላም ብቅ አላለም። ይህም የክርስቶስ ዳግም ምጽአት የሚባል ነገር እንደሌለ ያሳያል» ይሉ ነበር። ጴጥሮስ ይህንን አሳብ የሚያፈርሱ ምላሾችን በሚከተለው መልክ አቅርቧል። ሀ. እንዲህ ዓይነት ነገር የሚናገሩ ሰዎች የጥፋት ውኃውን ትምህርት ዘንግተዋል። ይህ እግዚአብሔር ወደ ሰዎች ታሪክ በታላቅ ኃይል ገብቶ የማያምኑ ሰዎችን ያጠፋበትን ዘመን የሚያሳይ ነው። ከዚያ በኋላ እግዚአብሔር ዓለምን በጥፋት ውኃ እንደማያጠፋ ቃል ገብቷል። ይህ ማለት ግን እግዚአብሔር ዓለምን አያጠፋትም ማለት አይደለም። በቀጣዩ ጊዜ በእሳት ያጠፋታል። ለ. ብዙ ሰዎች የእግዚአብሔርን የጊዜ ጽንሰ አሳብ አይረዱም። እግዚአብሔር እንደ እኛ በጊዜ የታሰረ አምላክ አይደለም። ጊዜ አሁን እኛ በምናውቀው መልኩ የተጀመረው እግዚአብሔር ዓለምን ሲፈጥር ነው። ነገር ግን እግዚአብሔር ከፍጥረት በፊት ስለነበር፥ እርሱ ከጊዜ ውጪ ነው። በሰማይ ጊዜን ለቀን እና ለሌሊት በዓመታት፥ በወራት፥ በቀናት፥ በ24 ሰዓታት፥ በደቂቃዎች እና በሰኮንዶች የሚከፍሉ ጸሐይና ጨረቃ የሉም። እነዚህ በምድር ላይ ብቻ የምናያቸው ነገሮች ናቸው። ይህም ማለት ለእግዚአብሔር ቅርብ የሆነው ጊዜ በጊዜ ለተወሰኑት ሰዎች ሺህ ዓመት ሊሆን ይችላል። ለዘላለማዊ አምላካችን፥ ሺህ ዓመት አጭር ሊሆን ይችላል። ልክ እንደ አንድ ቀን ጥቂት ጊዜ ብቻ ሊሆን ይችላል። ሐ) ክርስቶስ ያልተመለሰበት ዋናው ምክንያት ከምሕረቱና ከትዕግሥቱ የተነሣ ብዙ ሰዎች እንዲያምኑ ዕድል ለመስጠት ነው። እርሱ ለማመን የማይፈልጉትን ሰዎች ለመቅጣት ደስ አይሰኝም። ስለሆነም ሕይወታቸውን ለውጠው በክርስቶስ እንዲያምኑ ይጠብቃል። መ) ምንም እንኳን ጊዜው ረጅም ቢመስልም፥ የእግዚአብሔርን ቃል ማመን አለብን። ክርስቶስ ዳግም እመለሳለሁ ብሏል። አሁን ያለችውን ምድር እንደሚያጠፋ እና አዲስ ሰማይን እና አዲስ ምድር ለመፍጠር ቃል ገብቷል (ኢሳ. 65፡17 አንብብ)። የጌታ ቀን በሚመጣበት ጊዜ የትዕግሥትና የምሕረት ወቅት ይመጣል። እግዚአብሔር በዘፍጥረት 1 የፈጠራቸውን ሰማያትና ምድር ያጠፋል። በእግዚአብሔር ላይ በማመጽ የማይመለሱ ሰዎች በጥፋት ውኃ ዘመን እንደ ነበሩ ሁሉ ይቀጣሉ (ይጠፋሉ)። ነገር ግን እርሱን በመምሰል የሚመላለሱ የእግዚአብሔር ልጆች ወደ ጽድቅ ቤታቸው ይሄዳሉ። ይህም አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር ነው። አማኞች በእግዚአብሔር የፍርድ እሳት ወደማይጠፋ ቤታችን ለመሄድ አሁን በሕይወታችን እግዚአብሔርን ለማስደሰት ልንወስን ይገባል። በእግዚአብሔር ፊት ነቀፋና እንከን የሌለን ሆነን ከእርሱ ጋር በሰላም ልንመላለስ ይገባል። ሐሰተኛ አስተማሪዎች የጳውሎስን መልእክቶች በተሳሳተ መንገድ እየጠቀሱ ክርስቲያኖችን ወደ ተሳሳተ አቅጣጫ የሚመሩ ይመስላል። ከመልእክቱ የየትኞቹን ክፍሎች እንደ ጠቀሱ አናውቅም። ምናልባትም ጳውሎስ ድነትን (ደኅንነትን) ያገኘነው ሕግን በመጠበቅ ሳይሆን በእምነት ነው ሲል ያስተማረውን ሊሆን ይችላል (ለምሳሌ፥ ገላ. 2፡14-21)። ከዚህም የተነሣ፥ እነዚህ ሐሰተኛ አስተማሪዎች ክርስቲያኖች የፈለጉትን ነገር ሊያደርጉ እንደሚችሉ ያስተምሩ ነበር። ኃጢአት ጭምር ሊሠሩ እንደሚችሉ በመግለጽ ይናገሩ ጀመር። ጴጥሮስ፥ «የተወደደ ወንድማችን ጳውሎስ» በማለት ለጳውሎስ የነበረውን ፍቅር ከገለጸ በኋላ፥ እነዚህ ሐሰተኞች የጳውሎስን መልእክቶች ብቻ ሳይሆን መጽሐፍ ቅዱስን ሁሉ በተሳሳተ መንገድ እየተረጎሙ በማስተማር ላይ መሆናቸውን አስረድቷል። ጴጥሮስ የጳውሎስ መልእክቶች ከብሉይ ኪዳን ቅዱሳት መጻሕፍት ጋር እኩል መሆናቸውን ገልጾአል። እርሱም ሆነ ሌሎች መንፈስ ቅዱስ የብሉይ ኪዳን ነቢያትን በተጠቀመበት መንገድ ጳውሎስና ሌሎችን ሥልጣን ባለው መንገድ የተጠቀመ መሆኑን ተገንዝበው ነበር (2ኛ ጴጥ. 1፡21)። ይህ ትምህርት ለአማኞች ጠንካራ ማስጠንቀቂያ ነው። አንድ ሰው ከመጽሐፍ ቅዱስ አንድ ወይም ሁለት ጥቅስ ጠቀሰ ማለት ትምህርቱ ትክክል ነው ማለት አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረውን ትምህርተ አሳብ በተሳሳተ መንገድ መተርጎም ወይም መጠቀም ተገቢ አይሆንም። ስለሆነም፥ እግዚአብሔር በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለማስተላለፍ የፈለገውን መልእክት በትክክል መረዳታችንን በጥንቃቄ ማረጋገጥ አለብን። ዛሬ አብያተ ክርስቲያናችንን ከሚያውኩት መናፍቃን አብዛኞቹ የፈለቁት ሐሰተኛ አስተማሪዎች የተወሰኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን ከዐውዳቸው ውጭ የትምህርታቸው መሠረት አድርገው በመጠቀማቸው ነው። የእግዚአብሔርን ቃል በይበልጥ ባጠናንና የመጽሐፍ ቅዱስን ዐበይት ትምህርቶች ባወቅን መጠን፥ የሚመጡትን ትምህርቶች ሁሉ መርምረን እውነተኛውን ከሐሰተኛው ለመለየት እንችላለን። የውይይት ጥያቄ፡- ጴጥሮስ የሐሰተኛ ትምህርት መድኃኒቱ መጽሐፍ ቅዱስን በአግባቡ መተርጎምና በሚገባ ማወቅ እንደሆነ ይናገራል። ሀ) ግንዛቤህና አስተምህሮህ መጽሐፍ ቅዱሳዊ እንዲሆን ምን እያደረግክ ነው? ለ) የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ሁሉንም የእግዚአብሔር ቃል በበለጠ ለማወቅ ምን እያደረጉ ናቸው? ሐ) ይህ ትምህርት፥ «መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት አያስፈልገኝም፥ መንፈስ ቅዱስ ትክክለኛውንና ትክክለኛ ያልሆነውን ለይቼ እንዳውቅ፥ እንዲሁም ምን ማለት እንዳለብኝ ያስተምረኛል» ለሚሉ ሰዎች ምላሽ እንድንሰጥ የሚያግዘን እንዴት ነው? ሽማግሌው የመጨረሻ ምክሩን ሰጥቷል። ይኸውም፥ «በእውቀት እደጉ (በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና እውቀት እደጉ)፥ የእግዚአብሔርን ቃል ተጠቀሙ፤ መጽሐፍ ቅዱስን አለአግባብ እየተጠቀሙ ከፊል እውነት የሚያስተምሩትን ሰዎች በጥንቃቄ ተመልከቱ» የሚል ነበር። ይህንን በምናደርግበት ጊዜ፥ ራሳችንን በሐሰተኛ ትምህርት ከመወሰድ እንጠብቃለን። ለአዳነን ለኢየሱስ ክርስቶስ ስም ክብርን እናመጣለን። ለክርስቶስ ክብርን እያመጣህ ነው? የውይይት ጥያቄ፡– ከ2ኛ ጴጥሮስ ያስገረመህን አንዳንድ እውነቶች ዘርዝር። መንፈስ ቅዱስ እነዚህን እውነቶች ከሕይወትህ ጋር እንድታዛምድ የሚፈልገው እንዴት ነው? (ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

ጴጥሮስ ክርስቶስ ቃል እንደገባው ተመልሶ አይመጣም የሚለውን አሳብ ፉርሽ ያደርገዋል (2ኛ ጴጥ. 3፡1-18) Read More »

ጴጥሮስ አማኞች መጽሐፍ ቅዱስን ከሚያዛቡ ሐሰተኛ አስተማሪዎች እንዲጠበቁ ያስጠነቅቃል (2ኛ ጴጥ. 2፡1-22)

አማኞች በእምነታቸው እና የእግዚአብሔርን ቃል በማወቅ የማያድጉ ከሆነ በአደገኛ ሁኔታ ላይ ይወድቃሉ። ሐሰተኛ ትምህርቶች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሊስፋፉ የሚችሉት በዚህ ጊዜ ነው። በጴጥሮስ ዘመን በአማኞች ሕይወት ውስጥ እየተከሰተ የነበረው ችግር ይህ ነበር። የ2ኛ ጴጥሮስ መልእክት ዋነኛ ትምህርት ክርስቲያኖችን ስለ ሐሰተኛ ትምህርትና አስተማሪዎች ማስጠንቀቅ ነበር። በብሉይ ኪዳን ዘመን እውነተኛ ነቢያት በተነሣ ቁጥር ሐሰተኛ ነቢያትም ይነሡ ነበር። ከእግዚአብሔር እውነትን የሚናገሩ ሰዎች በሚነሡበት ጊዜ ውሸትን ከራሳቸው አመንጭተው የሚናገሩ ሰዎችም ብቅ ይሉ ነበር። የእነዚህም ሰዎች እሳብ ዋነኛው ምንጭ ሰይጣን ነው። ጴጥሮስ ሰዎች የእግዚአብሔርን እውነት ስተው ውሸትን በሚከተሉባት ጊዜ ምን እንደሚከሰት ታሪካዊ ምሳሌዎችን ይጠቅሳል። ሀ. መላእክት፡- መላእክት ኃጢአት በሠሩ ጊዜ፥ እግዚአብሔር ወደ ገሃነም ጥሎ በጨለማ ጉድጓድ ለፍርድ ሊጠበቁ አሳልፎ ሰጥቷቸዋል። ምሁራን ይህ ሁለት ነገሮችን ሊያመለክት እንደሚችል ይናገራሉ። በመጀመሪያ፥ ይህ የመጀመሪያውን የሰይጣን ውድቀት እና እርሱን ተከትለው በኃጢአት የወደቁትን መላእክት ያመለክታል ይላሉ። ስለ እነዚህ ውድቀቶች መጽሐፍ ቅዱስ በኢሳ. 14፡12-15 እና በሕዝ. 28፡11-17 ላይ ይናገራል። ነገር ግን መጽሐፍ ቅዱስ በየትኛውም ስፍራ ሰይጣን ወደ ጉድጓድ እንደ ተጣለ አይናገርም። ይህ ወደፊት የሚመጣ ነገር ነው (ራእይ 20፡1-3)። ሁለተኛ፥ ሌሎች ምሁራን ጴጥሮስ በዘፍጥረት 6፡2 ስለተጠቀሱት የእግዚአብሔር ወንዶች ልጆች እየተናገረ ነው ይላሉ። በእነርሱ አስተሳሰብ እነዚህ መላእክት ከሰዎች ሴቶች ጋር ጋብቻ የፈጸሙ ናቸው። እግዚአብሔርን በፍርድ እነዚህን መላእክት ወደ እስር ቤት ልኳቸዋል። በመጨረሻው ፍርድ ሰይጣን እና መላእክቱ ሁሉ ፍርድን እስከሚቀበሉበት ጊዜ ድረስ ታስረው ይቆያሉ። እነዚህ መላእክት መቼ እንደ ወደቁ ባናውቅም፥ የተላለፈልን መልእክት ግልጽ ነው። ይኸውም በእግዚአብሔር ላይ ማመጽ ታላቅ ቅጣትን እንደሚያመጣ ያስረዳል። ለ) የኖኅ ዘመን ዓለም፡- በዚህ ጊዜ እግዚአብሔር የሰው ልጆችን (ዐመፀኞችን) ያወደመ የጥፋት ውኃ ሰድዷል። እግዚአብሔር ይህን ከማቅረቡ በፊት የጽድቅ ሰባኪ በሆነው በኖኅ በኩል ሲያስጠነቅቃቸው ቆይቶ ነበር። የእግዚአብሔርን ማስጠንቀቂያ ሰምተው የታዘዙት (ኖኅና ቤተሰቡ) ብቻ ከጥፋት ውኃው ሊተርፉ በቅተዋል። ወደፊትም እንዲህ ዓይነት ዓለም ዓቀፍ የፍርድ ቀን ይመጣል። አብዛኛውን ሰው ሳንከተል እንደ ኖኅና ቤተሰቡ የጽድቅ ሕይወት ለመኖር እንመርጥ ይሆን? ወይስ አብዛኛዎችን የጥፋት ሰለባዎች እንከተል ይሆን? ሐ) ሰዶምና ገሞራ፡- በአብርሃምና ሎጥ ዘመን እግዚአብሔር እነዚህን በክፋት የተሞሉትን ከተሞች ቀጥቷቸዋል። ከዚህ ቅጣት ያመለጡት ሎጥና ሴት ልጆቹ ብቻ ነበሩ። እነዚህ ምሳሌዎች እግዚአብሔር ጻድቃንና ለእርሱ በመታዘዝ የሚኖሩትን በዐመፀኛነት እንዳሻቸው ከሚኖሩት የሚለይ መሆኑን ያሳያል። እግዚአብሔር ጻድቃንን ከፍጻሜው ጥፋት ይታደጋቸዋል። ይህ ምናልባትም እግዚአብሔር በአሁኑ ዘመን በዓለም ላይ ከሚያመጣው ቅጣት መትረፍን ሊያመለክት ይችላል። እግዚአብሔር ሌሎች ከተጋፈጧቸው የመከራ ጊዜያት ልጆቹን እንደ ጠበቀ የሚያሳዩ ብዙ ምሳሌዎች አሉ። ነገር ግን ጴጥሮስ አጽንኦት የሰጠው ከዘላለማዊ ፍርድ እና ከሲዖል ስለ መዳን ነው። ኃጢአተኞች አንዳንድ ጊዜ በምድር ላይ የእግዚአብሔርን ፍርድ ይቀበላሉ። ነገር ግን በመጨረሻው ዘመን ዘላለማዊ ፍርድን እንደሚቀበሉ የተረጋገጠ ነው። ጴጥሮስ በእግዚአብሔር ላይ የሚያምጹትን ሰዎች ዐመፀኛነት በዚህ መልእክት ውስጥ ገልጾአል። እነዚህ ሰዎች ትእቢተኞች ሆነው በእግዚአብሔር ላይ ይሳለቃሉ። በወሲባዊ እርካታዎች ላይ ያተኩራሉ። ሁል ጊዜም ተጨማሪ ገንዘብ፥ እንዲሁም እርካታ ለማግኘት ይፍጨረጨራሉ። ይህም ገንዘብን ከመውደድ የተነሣ ነው። በእስራኤል ሕዝብ ላይ የእግዚአብሔር ፍርድ እንዲመጣ ያደረገውን እና የኋላ ኋላ ለሞት የተዳረገውን የበለዓምን ታሪክ የሚመስል ሕይወት እንዲኖሩ ያስገድዳቸዋል (ዘኁል 22-24)። ለሰዎች የራስ ወዳድነት ምኞቶች ማራኪ የሆኑትን ነገሮች ይናገራሉ። አማኞች መስለው ይቀርባሉ። ነገር ግን የኃጢአት ባሪያዎች መሆናቸውን በተግባራቸው ያሳያሉ። ወደ ኃጢአት ሕይወታቸው በሚመለሱበት ጊዜ ውስጣዊ የውሻነት ወይም የአሳማነት ባህሪያቸው ብቅ ይላል። ይህም ደግሞ ልደት ያልዳሰሰው አሮጌ ባህሪ ነው። : ጴጥሮስ ሊያስተላልፍ የፈለገው መልእክት በረጅም ጊዜ ቆይታ ሐሰተኛ አስተማሪዎችን ከአኗኗራቸው ለይተን ልናውቅ እንደምንችል ነው። ለጊዜው መንፈሳዊያን መስለው ሊያሳስቱ ይችላሉ። ትምህርታቸውና ተግባራቸው ሊያስገርመን እና ሊማርከን ይችላል። የኋላ ኋላ ግን እውነተኛ ባህሪያቸው ይታያል። ሐሰተኛ አስተማሪዎች ብዙውን ጊዜ የኋላ ኋላ በሥልጣን፥ በገንዘብ ፍቅር ወይም በወሲብ ኃጢአት ይወድቃሉ። ስለሆነም ማራኪ የሚመስሉንን ፈጥነን መከተል የለብንም። መጽሐፍ ቅዱስን በሚገባ አጥንተን በማወቅ ሰዎች የሚያስተምሯቸውን ከፊል እውነቶች ልንላይ ይገባል። በሐሰተኛ ትምህርት ከወደቅን እንደ እነዚያ መላእክት፥ በጥፋት ውኃው ዘመን፥ እንዲሁም በሰዶምና ገሞራ ከተሞች እንደነበሩት ሰዎች የእግዚአብሔርን ጽኑ ቁጣ እንቀምሳለን። ስለሆነም ጻድቃን መሆናችንና ለተገለጠው የእግዚአብሔር ፈቃድ ለመታዘዝ መመላለሳችንን ማረጋገጥ ይኖርብናል! የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) በጊዜ ብዛት በአንድ ሐሰተኛ አስተማሪ ሕይወት ውስጥ የተከሰቱትን ነገሮች በመመልከት ሐሰተኛነቱን ለማወቅ ስለቻልክበት ሁኔታ ግለጽ። ለ) ከዚህ ውጭ ሐሰተኛ አስተማሪዎችንና ሐሰተኛ ትምህርቶችን እንዴት ለይተን ልናውቅ እንችላለን? (ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

ጴጥሮስ አማኞች መጽሐፍ ቅዱስን ከሚያዛቡ ሐሰተኛ አስተማሪዎች እንዲጠበቁ ያስጠነቅቃል (2ኛ ጴጥ. 2፡1-22) Read More »

በእምነትና ስለ እግዚአብሔር ባል እውቀት ማደግ (2ኛ ጴጥ. 1፡1-21)

ስለሺ እግዚአብሔርን የሚወድ ወንድም ነበር። እግዚአብሔርም በቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ በሽምግልና አገልግሎት በብዙ መንገዶች ተጠቅሞበታል። ይሁንና፥ ስለሺ ሁልጊዜም ለእግዚአብሔር የሚቀና ሰው አልነበረም። ከአሥር ዓመታት አካባቢ በፊት፥ ለእግዚአብሔር የነበረው ፍቅር እየቀዘቀዘ እንዲሄድ አድርጓል። አንድ ሌሊት ከሚስቱ ጋር ብዙ ከተጨቃጨቁ በኋላ፥ ወደ ቡና ቤት ሄዶ ጠጥቶ ከሰከረ በኋላም እዚያው ከአንዲት ሴተኛ አዳሪ ጋር አብሮ አደረ። በኋላም መንፈስ ቅዱስ ስለፈጸመው ኃጢአት ስለ ወቀሰው ኃጢአቱን ለእግዚአብሔር እና ለሚስቱ ተናዝዞ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ሕይወቱን በጥንቃቄ ይመራ ጀመር። ከብዙ ዓመታት በኋላ ስለሺ ይታመም ጀመር። ሐኪም ባዘዘለት መድኃኒት ለጊዜው ሻል አለው። ከቆይታ በኋላ ግን በሽታው እያየለበት ሄደ። ክብደቱም እየቀነሰ ይሄድ ጀመር። አንድ ቀን ለምርመራ ወደ ሐኪም ቤት ሄዶ ከተመረመረ በኋላ ውጤቱን በመጠባበቅ ላይ ሳለ ከነርሶች አንዷ፥ «ይሄ ምስኪን ሰውዬ ኤድስ አለበት። ሞቱ ተቃርቧል ማለት ነው» ስትል ሰማ። ስለ እርሱ እንደምትናገር በተገነዘበ ጊዜ እጅግ ደነገጠ። ስለሺ እግዚአብሔር እንዲፈውሰው ቢጸልይም መልስ አላገኘም። የቤተ ክርስቲያን ሽማግሌዎች እንዲጸልዩለት ጠየቀ በተጨማሪም፥ ሰዎችን በመፈወስ ወደሚታወቅ አንድ አገልጋይ ሄዶ ተጸለየለት። እግዚአብሔር ግን አልፈወሰውም፡፡ አንድ ቀን መንፈስ ቅዱስ የአንድ ዓመት እድሜ ብቻ እንዳለው በመግለጽ አስጠነቀቀው። የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) አንተ በስለሺ ቦታ ብትሆን ኖሮ ራስህንና ቤተሰቦችህን ለሞት ለማዘጋጀት በመጨረሻው ዓመትህ በምን ምን ጉዳዮች ላይ ትኩረት ታደርግ ነበር? ለ) በቅርቡ እንደምትሞት ማወቅህ ለገንዘብ፥ ለጥሩ ቤትና ለመማር የሚኖርህን አመለካከት የሚቀይረው እንዴት ነው? እግዚአብሔር ብዙውን ጊዜ መቼ እንደምንሞት አይነግረንም። ነገር ግን አንድ ቀን እንደምንሞት እና እንደዚሁም በቂ ዝግጅት ማድረግ እንዳለብን ያስጠነቅቀናል። ሞት በሚቃረብበት ጊዜ ሰዎች ስለ ገንዘብ፥ ጥሩ ቤት ወይም መኪና ስለ መግዛት አያስቡም። ስለ ትምህርትም አያስቡም። ስለሺ ሊሞት እንደ ተቃረበ ሚስቱን እርሱ በሌለበት ዓለም ውስጥ ለመኖር እንዴት እንደሚያዘጋጃት ያስብ ጀመር። ለልጆቹ በሕይወት አስፈላጊ ስለሆኑት ጉዳዮች ሊያስተምራቸው ፈለገ። እንደ እርሱ በኤድስ ለታመሙት እና የዘላለምን ሕይወት ሳያገኙ ለሚሞቱ ሰዎች እንዴት ወንጌልን እንደሚያደርስላቸው አሰበ። በዚህ ጊዜ የዘላለም ሕይወት በዚህ ምድር ካለው ነገር ሁሉ በላይ ዋጋ ያለው መሆኑን ተገነዘበ። ጴጥሮስ ይህን የ2ኛ ጴጥሮስ መልእክት የጻፈበት ዓላማ ክርስቲያኖች ዓለም ከምታጋንናቸው ጊዜያዊ ነገር ርቀው ዘላለማዊ እሴት ባላቸው ነገሮች ላይ እንዲያተኩሩ ለማበረታታት ነው። ይህንንም ለማድረግ ጴጥሮስ የተጠቀመው ስለ ሞት መጻፍ ሳይሆን፥ በጌታ ቀን ላይ አጽንኦት መስጠት ነበር። «የጌታ ቀን ግን እንደ ሌባ ሆኖ ይመጣል» አለ። «በዚያም ቀን ሰማያት በታላቅ ድምጽ ያልፋሉ። የሰማይም ፍጥረት በትልቅ ትኩሳት ይቀልጣል። ምድርም በእርሷ ላይ የተደረገው ሁሉ ይቃጠላል። እንዲህ የሚቀልጥ ከሆነ፥ የእግዚአብሔርን ቀን መምጣት እየጠበቃችሁ እና እያስቸኮላችሁ በቅዱስ ኑሮ እግዚአብሔርን በመምሰል እንደምን ልትሆኑ ይገባችኋል» ማናችንም ክርስቶስ መቼ እንደሚመለስ አናውቅም። ነገር ግን በየትኛውም ጊዜ ሊመለስ እንደሚችል ከተገነዘብን፥ የዛሬውን አኗኗራችንን እንለውጣለን። ለክርስቶስ ዳግም ምጽአት ተዘጋጅተሃል? የውይይት ጥያቄ፡- 2ኛ ጴጥ. 1፡3 አንብብ። ሀ) ጴጥሮስ በመንፈሳዊ ጉዞአችን ስለማደግ ምን ይላል? እነዚህ ምዕራፎች ስለ ሐሰተኛ ትምህርትና ስለ ሐሰተኛ አስተማሪዎች ምን ይላሉ? ሐ) ጴጥሮስ ስለ መጨረሻው ዘመን እና ክርስቶስ በየትኛው ጊዜ ሊመለስ እንደሚችል እየተገነዘቡ ስለ መኖር ምን ይላል? ስለሺ ወደ ሞት በተቃረበ ጊዜ ስለ ልጆቹ መንፈሳዊ እድገት በጽኑ እንዳሰበ ሁሉ፥ ጴጥሮስም እንዲሁ ሞቱ ሲቃረብ ስለ መንፈሳዊ ልጆቹ እና መንፈሳዊ እድገታቸው በጥልቀት ያስብ ጀመር። በዚህ ሁለተኛ መልእክቱ በእምነታቸው ለመብሰል ምን ሊያደርጉ እንደሚገባ ይመክራቸዋል። ጴጥሮስን ያሳሰበው የመጀመሪያው ነገር በእውቀት እና በመንፈሳዊነት ማደግ መቀጠላቸው ነበር። ጴጥሮስ እነዚህ ሁለት ነገሮች አብረው እንደሚሄዱ ተገንዝቧል። አንድ ሰው በእውቀት ካላደገ በመንፈሳዊነትም ሊያድግ አይችልም። ሰዎች በእውቀት ማደግ የሚያስፈልጋቸው በመንፈሳዊነት እንዲያድጉ ነው። ይህ እውነት በ2ኛ ጴጥሮስ የመጀመሪያው ክፍል ውስጥ ተመልክቷል። መግቢያ (2ኛ ጴጥ. 1፡1-2) ጴጥሮስ በዚህ መግቢያው መንፈሳዊ ልጆቹ በሕይወታቸው እንዲያድጉ መፈለጉን ገልጾአል። ጴጥሮስ ከውድ እምነታቸው የተነሣ በጽድቅ የሚመላለሱ በመሆናቸው ደስ መሰኘቱን ከገለጸ በኋላ፥ ጸጋና ሰላም እንዲኖራቸው ይጸልያል። ለመሆኑ አማኝ ጸጋና ሰላምን የሚያገኘው እንዴት ነው? ጴጥሮስ እግዚአብሔርን እና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በማወቅ መሆኑን ይናገራል። ስለ እግዚአብሔር ባለን እውቀት እና ከክርስቶስ ጋር ባለን ቅርበት እያደግን ስንሄድ በሕይወታችን የእግዚአብሔርን ጸጋ እንለማመዳለን። በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥም ሳይቀር የእርሱ ሰላም አእምሯችንን ይሞላዋል። እማኞች በክርስቶስ ያላቸውን እምነት ለማረጋገጥ በመንፈሳዊ ባህሪ ማደግ ይኖርባቸዋል (2ኛ ጴጥ. 1፡3-11) ድነት (ደኅንነት) የሚጀምረው በእውቀት ነው። በክርስቶስ ልናምን የምንችለው ማንነቱን እና ለእኛ የሚያደርገውን ነገር ካወቅን በኋላ ብቻ ነው። ይህ ስለ ክርስቶስ ያለን እውቀት ወደ ግንኙነት፥ ወይም ክርስቶስን ወደ ማወቅ ያድጋል። ይህም ከጓደኞቻችን ጋር ብዙ ጊዜ ባሳለፍን እና ስለ እነርሱ ብዙ ባወቅን መጠን የጠለቀ ወዳጅነት እንደምንመሠርት ማለት ነው። ጴጥሮስ እግዚአብሔር አብን እና ኢየሱስ ክርስቶስን ከማወቃችን እና ግንኙነት ከመመሥረታችን የሚፈልቁትን አያሌ ውጤቶች ይዘረዝራል። በመጀመሪያ ድነት (ደኅንነት) በእግዚአብሔር እይታ መነጽር ምን እንደሆነ ይገልጻል። ከዚያም በክርስቶስ ባመንን ጊዜ እግዚአብሔር የሰጠንን ስጦታዎች ይዘረዝራል። እግዚአብሔር እርሱን በሚያስከብር መንገድ ለመኖር የማያስፈልጉንን ነገሮች ለእኛ ለማስተላለፍ መለኮታዊ ኃይሉን ይጠቀማል። ሀ) እግዚአብሔር መለኮታዊ ባህሪን ለመስጠት እርሱን እንድንመስል ያደርጋል። ለ) እግዚአብሔር በክፉ ምኞቶች ምክንያት በዓለም ከተከሰተው ጥፋት ነፃ እንድንሆን ያደርጋል። ከእንግዲህ ኃጢአትን ለማድረግ የኃጢአት ባህሪያችን እስረኞች አይደለንም። ነገር ግን ከክፉ ተመልሰን እግዚአብሔርን ለማገልገል ነፃ ወጥተናል። ጴጥሮስ በድነት (ደኅንነት) ጊዜ እግዚአብሔር ምን እንዳደረገልን ከገለጸልን በኋላ፥ ልጆቹ ከሆንን በኋላ ከእኛ ምን እንደሚፈልግ ያስረዳል። እግዚአብሔር በቀዳሚነት ከእኛ የሚፈልገው እንደ መጠጥ ማቆም፥ ፊልም አለማየት ወይም ሰዎች መንፈሳዊነትን ይገልጻሉ ብለው የሚያስቧቸውን ነገሮች ማድረጋችንን አይደለም። ነገር ግን ጴጥሮስ፥ ባሕሪያችን መለወጥ እንዳለበት ይናገራል። እንደ ጠንካራ ሰንሰለት መንፈሳዊ ባሕሪ ከብዙ የተለያዩ ባሕርያት የተገነባ ነው። ጴጥሮስ የዚህን ሰንሰለት የተለያዩ መገጣጠሚያዎች በመመልከት እያንዳንዱ መገጣጠሚያ ጠንካራ እና እያደገ የሚሄድ ሊሆን እንደሚገባ ያስጠነቅቃል። እነዚህም የመንፈሳዊ ባህሪ መገጣጠሚያዎች እምነት፥ በጎነት፥ እውቀት፥ ራስን መግዛት፥ ጽናት፥ እግዚአብሔርን መምሰል፥ የወንድማማች መዋደድና ፍቅር ናቸው። የእግዚአብሔር ባህሪ በውስጣችን ስላለ እና የእርሱ ልጆች ስለሆንን፥ እነዚህ ነገሮች የባህሪያችን መገለጫዎች ሊሆኑ ይገባል። የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) እነዚህ ስምንት ባሕርያት የክርስቲያን ሕይወት ክፍሎች መሆናቸው ለምን አስፈላጊ እንደሚሆን ግለጽ? ለ) ከእነዚህ ባሕርያት አንዱ ቢጓደል ወደ ሕይወታችን ወይም ወደ ቤተ ክርስቲያናችን ሊመጡ የሚችሉትን ችግሮች ዘርዝር። ሐ) ከእነዚህ ባሕርያት የግልህ ለማድረግ የሚያስቸግርህ የትኛው ነው? መ) በእነዚህ ስምንት ባሕርያት ለማደግ ምን እያደረግህ ነው? በእነዚህ ባሕርያት እያደገ የሚሄድ ሕይወት ውጤቱ ምን ይሆናል? ጴጥሮስ ሁለት ነገሮችን ይዘረዝራል። በመጀመሪያ፥ በመንፈሳዊ ሕይወታችን ውጤታማ ሰዎች እንደምንሆን ይናገራል። በሌላ አገላለጽ፥ ተግባራችንም ሆነ አኗኗራችን እግዚአብሔርን የሚያስደስትም ሆነ የሚያስከብር ይሆናል። ሁለተኛ፥ የእግዚአብሔር ልጆች መሆናችንን የሚያሳይ ውስጣዊ ማረጋገጫ ይኖረናል። በራሳችን ሕይወት ውስጥ የተከሰተውን ለውጥ በመመልከት እምነታችን እውነተኛ መሆኑን እና የእርሱን ባሕሪ የተላበስን የእግዚአብሔር ልጆች መሆናችንን እንረዳለን። ጴጥሮስ «መመረጣችሁን እና መጠራታችሁን ታጸኑ ዘንድ ከፊት ይልቅ ትጉ» ሲል ይህን ማለቱ ነበር። አማኞች ከመንፈስ ቅዱስ የሚመጡትን የእግዚአብሔር ቃል እውነቶች ማስታወስ አለባቸው (2ኛ ጴጥ. 1፡12-21) ሰዎች ድግግሞሽ የመማር ቁልፍ ነው ሲሉ እንሰማለን። ጴጥሮስ ሊሞት እንደተቃረበ ስለተገነዘበ ለእማኞች ቀደም ሲል የሰሟቸውን እውነቶች በድጋሚ ሊያሳስባቸው ይፈልጋል። ለአማኞች ብዙውን ጊዜ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር የሚቃረኑ ወይም የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረቶች የሚያዛቡትን አዳዲስ እና አስገራሚ አሳቦች መከተል ቀላል ነው። እነዚህ አዳዲስ አሳቦች ይመጣሉ ይሄዳሉ። (ለምሳሌ፡ በተወሰኑ መንፈሳዊ ስጦታዎች ላይ፥ ወይም በተወሰነ የአምልኮ ስልት ላይ ትኩረት ማድረግ፥ ወዘተ. . . )። ነገር ግን አማኞች በፍጹም የማይለወጠውን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ካላወቁና አጥብቀው ካልያዙ፥ ሕይወታቸው በውዝግብ የተሞላ ይሆናል። ለመሆኑ እውነት የሆነውን እና ያልሆነውን እንዴት ነው ማወቅ የምንችለው? በየጊዜው የተለያዩ ትምህርቶች ይመጣሉ። እነዚህ ትምህርቶች ከእግዚአብሔር መሆናቸውን የምንገመግመው እንዴት ነው?

በእምነትና ስለ እግዚአብሔር ባል እውቀት ማደግ (2ኛ ጴጥ. 1፡1-21) Read More »

የ2ኛ ጴጥሮስ ልዩ ባሕርያት፣ መዋቅር፣ እና አስተዋጽኦ

፩. የ2ኛ ጴጥሮስ ልዩ ባሕርያት ብዙ ምሁራን የይሁዳን መልእክት ከ2ኛ ጴጥሮስ 2፡1-22 ጋር ያነጻጽራሉ። እንዲያውም ከይሁዳ መልእክት 25 ጥቅሶች መካከል 19ኙ ከ2ኛ ጴጥሮስ ጋር ተመሳሳይ ናቸው። ይህ ማለት ጴጥሮስ የይሁዳን መልእክት ወይም ይሁዳ የ2ኛ ጴጥሮስን መልእክት ማንበቡን ወይም፥ ሁለቱም በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የተሰጠው አንድ ትምህርት በማጣቀሻነት መጠቀማቸውን ሊያመለክት ይችላል። ትክክለኛው ሁኔታ የትኛው እንደነበረ ግን ማወቁ አስቸጋሪ ነው። ሌላው አስተሳሰብ ጴጥሮስና ይሁዳ ሁለቱም ሌላ ሰው የጻፈውን ሰነድ በማጣቀሻነት ተጠቅመዋል የሚል ነው። የዚህ መልእክት ቋንቋ የአጻጻፉ ስልት ከ1ኛ ጴጥሮስ የተለየ ነው። ይህም አንዳንድ ምሁራን ጴጥሮስ ይህን መልእክት አልጻፈው ይሆናል ብለው እንዲጠራጠሩ አድርጓቸዋል። ይሁንና ጴጥሮስ በ1ኛ ጴጥሮስ እንዳደረገው ሲላስን በጸሐፊነት ከመጠቀም ይልቅ እራሱ መልእክቱን እንደ ጻፈ ወይም ሌላ ጸሐፊ እንደ ተጠቀመ መገመት ይቻላል። የመልእክቶቹ ፍሬ አሳብ የተለያየ በመሆኑ የተለያየ የአጻጻፍ ስልት ተጠቅሞ ሊሆን ይችላል። ጴጥሮስ የጳውሎስን መልእክቶች እንደ ቅዱሳት መጻሕፍት ይጠቅሳቸዋል (2ኛ ጴጥ. 3፡15-16)። ይህም ጳውሎስ መልእክቶቹን ከጻፈ በኋላ የቀድሞዎቹ ክርስቲያኖች መልእክቶቹ ተራ የሰው ሥራዎች ሳይሆኑ የመንፈስ ቅዱስ ኃይል ያረፈባቸው መሆኑን እንደተገነዘቡ ያሳያል። በመሆኑም የጳውሎስን መልእክቶች ማሰባሰብና ማንበብ ጀምረው እንደነበር እንረዳለን።” ፪. የ2ኛ ጴጥሮስ መዋቅር የ2ኛ ጴጥሮስ መልእክት የተዋቀረው በመጽሐፉ ውስጥ በሚገኙት ሦስት ዐበይት ትምህርቶች መሠረት ነው። ጴጥሮስ ክርስቲያኖች በእምነታቸው እና በእግዚአብሔር ቃል እውቀት እንዲያድጉ ይመክራቸዋል (2ኛ ጴጥ. 1)። የመንፈሳዊ እድገት ቁልፍ ቁም ነገር ከመንፈስ ቅዱስ የሚመጣ የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት ነው። ጴጥሮስ ክርስቲያኖች መጽሐፍ ቅዱስን ከሚበርዙ ሐሰተኛ ትምህርቶች እንዲጠበቁ ያስጠነቅቃል (2ኛ ጴጥ. 2)። እነዚህ አስተማሪዎች በትዕቢት፥ በራስ ወዳድነት እና ግብረገባዊነት በጎደላቸው አኗኗሮች የሚታወቁ ነበሩ። ጴጥሮስ ክርስቶስ ተመልሶ አይመጣም የሚለውን እሳብ ፉርሽ በማድረግ ተገቢውን ምላሽ ይሰጣል (2ኛ ጴጥ. 3)። ጴጥሮስ ክርስቶስ ዳግም ተመልሶ እንደሚመጣና ዳሩ ግን እግዚአብሔር እንደ እኛ በጊዜ የተገደበ አምላክ አለመሆኑን ያስረዳል። ለእግዚአብሔር አጭር የሆነ ጊዜ ለእኛ ረጅም ሊሆን ይችላል። ክርስቶስ በቶሎ ያልተመለሰበት አንደኛው ምክንያት ከጸጋው የተነሣ መሆኑን ይናገራል። እግዚአብሔር ሰዎች ንስሐ ገብተው ክርስቶስ በሚመጣበት ጊዜ ከሚገለጸው የእግዚአብሔር ፍርድ እንዲተርፍ ይፈልጋል። በዚያን ጊዜ ዛሬ የምናውቃት ዓለም ሙሉ በሙሉ ትወድምና አዲስ ምድርና አዲስ ሰማይ ይፈጠራሉ። ፫. የ2ኛ ጴጥሮስ አስተዋጽኦ ጴጥሮስ አማኞች በእምነታቸውና በእግዚአብሔር ቃል እውቀት እንዲያድጉ ይመክራቸዋል (2ኛ ጴጥ. 1)። ሀ) መግቢያ (2ኛ ጴጥ. 1፡1-2) ለ) አማኞች በእግዚአብሔር ላይ ያላቸውን እምነት ለማረጋገጥ በመንፈሳዊ ባህሪ ማደግ አለባቸው (2ኛ ጴጥ. 1፡3–11) ሐ) አማኞች ከመንፈስ ቅዱስ የመጣውን የእግዚአብሔርን ቃል እውነቶች ማስታወስ አለባቸው (2ኛ ጴጥ. 1፡12-21)። ጴጥሮስ አማኞች መጽሐፍ ቅዱስን ከሚበርዙ ሐሰተኛ አስተማሪዎች እንዲጠነቀቁ ያሳስባል (2ኛ ጴጥ. 2)። ጴጥሮስ ክርስቶስ እንደ ተስፋ ቃሉ አይመለስም የሚለውን አስተሳሰብ ፉርሽ ያደርጋል (2ኛ ጴጥ. 3)። (ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የ2ኛ ጴጥሮስ ልዩ ባሕርያት፣ መዋቅር፣ እና አስተዋጽኦ Read More »

የ2ኛ ጴጥሮስ ዓላማ

የመጀመሪያው ዓላማ፡ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሐሰት ትምህርት መስፋፋት ጴጥሮስን አሳስቦት ነበር። ስለሆነም፥ የዚህ መልእክት ቀዳማይ ዓላማ ክርስቲያኖች በሐሰተኛ ትምህርቶች እንዳይወሰዱ ለማስጠንቀቅ ነው። ጴጥሮስ እንደሚለው፥ በመጨረሻው ዘመን ከሚከሰቱት ዐበይት ነገሮች አንዱ በፍጥነት የሚራሱ ሐሰተኛ ትምህርቶች መኖራቸው ነው። ክርስቲያኖች እውነተኛ የሆነውንና ያልሆነውን እንዴት ለይተው ሊያውቁ ይችላሉ? ለዚህ መረጃ ቀዳማዊው ምንጭ መንፈስ ቅዱስ በሰዎች ልብ ውስጥ ከማደሩ የተነሣ አማኞች ከሐዋርያት የተላለፈውን መጽሐፍ ቅዱስ በጥንቃቄ መጠበቅ አለባቸው። ጴጥሮስ ክርስቶስን እንዳየና የእግዚአብሔርም ቃል «ልጄ» እያለ ሲጠራ እንደሰማ ይናገራል። እነዚህ የወንጌል እውነቶች ለአማኞች ተላልፈዋል። እኛም እነዚህን እውነቶች በጥንቃቄ መጠበቅ ይኖርብናል። 2ኛ ዓላማ፡ ጴጥሮስ አማኞች በእምነታቸው ማደጋቸውን እንዲቀጥሉ ለማበረታታት ይፈልጋል። መዳን ብቻ በቂ አይደለም። የእግዚአብሔር ዓላማ በባህሪ እንድናድግና ውጤታማ የተቀደሰ ሕይወት እንድንኖር ማስቻል ነው። አማኞችን ከሐሰተኛ ትምህርት የሚጠብቃቸው ትልቁ ነገር በእውቀትና በመንፈሳዊ ባህሪ ማደግ፥ እንዲሁም በእምነታችን መትጋት ነው። ስለሆነም ጴጥሮስ ይህን መልእክት፥ «በእግዚአብሔርና በጌታችን በኢየሱስ እውቀት» በሚሉ ቃላት ይጀምራል (2ኛ ጴጥ. 1፡2)። ሲደመድምም፥ «በጌታችንና በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና እውቀት እደጉ» ይላል (2ኛ ጴጥ. 3፡18)። 3ኛ ዓላማ፡ የእግዚአብሔር ቃልና የተስፋ ቃሎቹ ፍጹም እውነትና ልንደግፍ የምንችልባቸው መሆናቸውን ማስተማር። አብዛኞቹ ሐሰተኛ ትምህርቶች የእግዚአብሔርን ቃል የማጣመም ውጤቶች ናቸው። ስለሆነም ለአማኞች መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ቃል መሆኑን ማወቅ ብቻ ሳይሆን ሐሰተኛ ትምህርቶችን ለመመርመር መጽሐፍ ቅዱስን መጠቀሙ ጠቃሚ ነው። ጴጥሮስ ጳውሎስ የጻፋቸው መልእክቶችም የእግዚአብሔር ቃል በመሆናቸው አማኞች ሊከተሏቸው እንደሚገባ ይናገራል። ጴጥሮስ በተደጋጋሚ ክርስቲያኖች የእግዚአብሔርን ቃል እውነቶች እንዲያስታውሱ ይመክራቸዋል (2ኛ ጴጥ. 1፡12-15፤ 3፡1)። ለዛሬው ዘመን ክርስቲያኖች ጥሩና ጥሩ ያልሆነውን ነገር ከእግዚአብሔር ቃል ውጭ ባሉ ነገሮች ይገመግማሉ። ስለሆነም የመጽሐፍ ቅዱስ ተጨባጭ ዓላማ ዋጋ አጥቷል። ሰዎች የወደዱትን ነገር ይቀበላሉ። ክርስቲያኖችም ብዙውን ጊዜ አንድን ነገር ለመቀበል ወይም ላለመቀበል እነዚህን ሦስት ምንጮች ይጠቀማሉ። ሀ) ስሜት፡ አንድ ነገር ጥሩ ስሜት ከሰጠን ወይም ላሜታችንን ካነሣሣ፥ ብዙ ክርስቲያኖች ይከተሉታል። የሰዎችን ስሜት በከፍተኛ ደረጃ የሚያነቃቃ ነገር በመንፈስ ቅዱስ የተሞላ ነው ተብሎ ይታመናል። ምንም እንኳን መንፈስ ቅዱስ ስሜታችንን ሊያነሣሣ ቢችልም ሁልጊዜም የሚሠራው በእውነት ላይ ተመሥርቶ ነው። ለ) በአስደናቂ ነገሮች ላይ የሚመሠረቱ የሊቆች ትምህርቶች አሉ። ብዙ ሰዎች ብዙም መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት ሳይኖራቸው በአስደናቂ ነገሮች ላይ (ተአምራት፥ በመንፈስ መገንደስ፥ ወዘተ…) የሚያተኩሩትን የታዋቂ አገልጋዮች ጽሑፎች፥ ካሴቶች ወይም ቪዲዮዎች ይከታተላሉ። ሐ) ወደ ትውፊት (ልማድ) የሚያተኩሩ ሰዎችም አሉ። እነዚህ ሰዎች፥ «በቤተ ክርስቲያናችን ውስጥ ሁልጊዜም የምናደርገው እንደዚህ ነው። ሲወርድ ሲዋረድ ወደ እኛ የመጣው እንዲህ ነው» ይላሉ። ልማድ ለእምነታችን እርጋታን ሊሰጥ እይችልም። ነገር ግን ሁልጊዜም ልማድ ከመጽሐፍ ቅዱስ ሥልጣን ሥር መዋል አለበት። ጴጥሮስ የመናፍቅነትና ሐሰተኛ ትምህርት በተትረፈረፈበት ዘመን ውስጥ የምንኖር ሰዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ እንድናተኩር ሁሉንም ነገር በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ተመሥርተን እንድንመረምር ይመክረናል። እግዚአብሔር የተቀባይነት ፊርማውን ያኖረው በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ብቻ ነው። የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ቤተ ክርስቲያንህን ያወከውን ሐሰተኛ ትምህርት ጥቀስ። ለ) በዚህ ጊዜ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች የሰጡት ምላሽ ምን ነበር? ሁኔታውን እንዴት ተቋቋሙት? ሐ) ብዙ ወጣቶች ለእውነት አስፈላጊነት ደንታ የሌላቸው ለምንድን ነው? መ) እውነት የሆነውንና ያልሆነውን ለመለየት መጽሐፍ ቅዱስ ምን አስተዋጽኦ ያበረክታል? ሠ) ክርስቲያኖች አንድን ትምህርት ወይም አሳብ በስሜቶች፥ ልማድ፥ ወይም አስደናቂ ነገሮች ላይ በሚያተኩር አገልጋይ ቃላት ሊገመግሙ እንደሚችሉ በተመለከትካቸው ነገሮች ላይ ተመሥርተህ አብራራ። 4ኛ ዓላማ፡ ክርስቶስ ተስፋ እንደተገባው ለምን በፍጥነት አልተመለሰም? የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ፡፡ ክርስቲያኖች ከተቸገሩባቸው ነገሮች አንዱ የክርስቶስ በፍጥነት አለመመለስ ይመስላል። በቶሎ እንደሚመለስ ተስፋ የሰጠው ክርስቶስ ሠላሳ ዓመታት ካለፉ በኋላም ብቅ አላለም። በመሆኑም አንዳንድ ሰዎች ክርስቶስ የተናገረውን ስለማድረጉና አለማድረጉ መጠራጠር ጀመሩ። ጴጥሮስ ለዚህ ምላሽ በመስጠት፥ ሀ) የእግዚአብሔር የጊዜ አመለካከት ከሰዎች እንደሚለይ ያብራራል። ለእኛ ረጅም ጊዜ (ሺህ ዓመታት) ለእርሱ አጭር ነው (አንድ ቀን)። ለ) ክርስቶስ በፍጥነት ያልተመለሰበት ዋነኛው ምክንያት ብዙ ሰዎች ንስሐ ገብተው በክርስቶስ ለማመን ዕድል እንዲያገኙ ነው። ይህም ክርስቶስ በሚመለስበት ጊዜ ከሚመጣው የእግዚአብሔር ፍርድ እንዲያመልጡ ያስችላቸዋል። (ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የ2ኛ ጴጥሮስ ዓላማ Read More »

የ2ኛ ጴጥሮስ መግቢያ

ሸምገል ያለ ሰው ነበር። ከ30 ዓመት በፊት ነበር አንድ ክስተት ሕይወቱን የለወጠው፡፡ በአንድ ተራ ቀን ወንድሙ የእድሜ እኩያው ከሆነው ከክርስቶስ ጋር እንዲተዋወቅ ጠየቀው «መሲሁ ይሄ ነው» ሲል ነገረው። ለሚቀጥሉት ሦስት ተኩል ዓመታት ከመሢሑ ጋር በመጓዝ፥ በመነጋገር፥ ሕይወቱን በመመልከት፥ ሲሞትም እዛው በመገኘትና በትንሣኤውና በእርገቱ በመደነቅ አሳልፎአል። ይህን መልእክት በሚጽፍበት ጊዜ ብዙ ዘመናት ስላለፉ እርጅና ተጫጭኖታል። እናም እስር ቤት ባይገባም ክርስቶስ በቅርቡ እንደሚሞት ነግሮታል። ጴጥሮስ እንደ ጻፈው፥ «ሁልጊዜም በዚህ ማደሪያ ሳለሁ በማሳሰቤ ላነቃችሁ የሚገባኝ ይመስለኛል። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዳመለከተኝ ከዚህ ማደሪያዬ መለየቴ ፈጥኖ እንደሆነ አውቃለሁና» (2ኛ ጴጥ. 1፡13-14)። ብዙም ሳይቆይ ይህ አረጋዊ እንደ ጌታው በመስቀል ላይ ተሰቅሎ ሞቷል። ከመሞቱ በፊት ግን ጴጥሮስ እርሱን ያውቁትና ያከብሩት የነበሩ ክርስቲያኖች አንዳንድ ጠቃሚ እውነቶችን እንዲያውቁ ፈለገ። ከእነዚህም እውነቶች አንዱ ከክርስቶስ ጋር ባላቸው ሕይወት ክርስቲያኖች ማደግ እንዳለባቸው ነበር። ጴጥሮስ ክርስቶስ ወደ ሰማይ ባረገ ጊዜ ማደጉን አላቆመም። ነገር ግን በክርስቶስ እውቀትና ባህሪ ለማደግ ፈለገ «ስለዚህም ምክንያት ትጋትን ሁሉ እያሳያችሁ በእምነታችሁ በጎነትን ጨምሩ፥ በበጎነትም እውቀትን፥ በእውቀትም ራስን መግዛት፥ ራስንም በመግዛት መጽናትን፥ በመጽናትም እግዚአብሔርን መምሰል፥ እግዚአብሔርንም መምሰል የወንድማማችን መዋደድ፥ በወንድማማችም መዋደድ ፍቅርን ጨምሩ» (2ኛ ጴጥ. 1፡5-7)። የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) በክርስቶስ ካመንህ ምን ያህል ጊዜ ሆነህ? ለ) ጴጥሮስ በዘረዘራቸው ባሕርያት በእያንዳንዳቸው እንዴት እያደግህ እንደ መጣህ ግለጽ። ያላደግህበት ባህሪ ካለህ ምክንያቱ ምንድን ነው? መንፈስ ቅዱስ ጴጥሮስ እንደተናገረው በመንፈሳዊ ሕይወትህ እንዲረዳህ ጊዜ ወስደህ ጸልይ! የውይይት ጥያቄ፡– 2ኛ ጴጥሮስን ከመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት አንብብ። በመዝገበ ቃላት ውስጥ ስለ ጸሐፊው፥ ስለ እንባቢዎቹ፥ መልእክቱ ስለ ተጻፈበት ጊዜና ዓላማ ጠቅለል አድርገህ ጻፍ። የ2ኛ ጴጥሮስ ጸሐፊ የውይይት ጥያቄ፡- 2ኛ ጴጥ. 1፡1-2 አንብብ። ሀ) ጸሐፊው ራሱን የሚገልጸው እንዴት ነው? ለማን እንደሚጽፍ ይናገራል? የሁለተኛ ጴጥሮስ ጸሐፊ ራሱን፥ «የኢየሱስ ክርስቶስ ባሪያና ሐዋርያ የሆነ ስምዖን ጴጥሮስ» ሲል ይገልጻል። ምንም እንኳን በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ሁሉ ይህን መጽሐፍ ማን እንደ ጻፈው የሚጠራጠሩ ሰዎች ቢኖሩና አንዳንድ ምሁራን ደግሞ ጴጥሮስ ይህን መልእክት እንዳልጻፈው ቢናገሩም፥ ጸሐፊው የተናገረውን ለመጠራጠር የሚያስችል በቂ መረጃ የለንም። ጸሐፊው ሐዋርያው ጴጥሮስ መሆኑ ክርስቶስ በተራራ ላይ መልኩን በለወጠ ጊዜ እንዳየው ከሚናገረው አሳብ ጋር ይጣጣማል (2ኛ ጴጥ. 1፡16-18፤ ማቴ. 17፡1-13)። እንዲሁም ደግሞ ጴጥሮስ ይህ ሁለተኛ መልእክቱ እንደሆነ ይናገራል (2ኛ ጴጥ. 3፡1)። ጸሐፊው በተጨማሪም፥ «የተወደደ ወንድማችን» (2ኛ ጴጥ. 3፡15) ሲል የገለጸው ጳውሎስ በኖረበት ዘመን እንደኖረ ይናገራል። ይህ ሁሉ ማስረጃ የዚህ መልእክት ጸሐፊ ሐዋርያው ጴጥሮስ መሆኑን ያመለክታል። በ1ኛ ጴጥሮስና 2ኛ ጴጥሮስ መልእክቶች መካከል ያለውን የመግቢያ ልዩነት መመልከቱ አስገራሚ ነው። በ2ኛ ጴጥሮስ፥ ጴጥሮስ ራሱን በሙሉ ስሙ ስምዖን ጴጥሮስ ሲል ይጠራዋል። ስምዖን አይሁዳዊ ስሙ ሲሆን፥ ጴጥሮስ ደግሞ የግሪክ ስሙ ነበር። ይህንንም ስም የሰጠው ደግሞ ክርስቶስ ነበር። በ1ኛ ጴጥሮስ፥ ሐዋርያ መሆኑን ሲያመለክት በ2ኛ ጴጥሮስ ደግሞ ባሪያ የሚለውን ቃል ያክላል። ጴጥሮስ ክርስቲያኖች ሐዋርያነቱንና ከዚህ ጋር በተያያዘ በሐዋርያዊ ሥልጣኑ መልእክቱን እንደ ጻፈ መዘንጋት እንደሌለባቸው ተገንዝቦ ነበር። ከሁሉም በላይ ግን ጴጥሮስ ክርስቲያኖች ልክ እንዴት እርሱ ክርስቶስን ለማገልገል የሚፈልግ መሆኑን እንዲገነዘቡለት ይፈልጋል። ምናልባትም ጴጥሮስ ክርስቶስ በተያዘበት ሌሊት የነበሩትን ሁኔታዎች እያስታወሰ ይሆናል። እንደ ሌሎች ደቀ መዛሙርት ሁሉ መሪና በክርስቶስ መንግሥት ውስጥ ታላቅ መሆን ይፈልግ ነበር (ሉቃስ 22፡24-30)። እንደ ሌሎች ደቀ መዛሙርት ሁሉ ጴጥሮስ ራሱን ዝቅ አድርጎ የሌሎችን ደቀ መዛሙርት እግር ለማጠብ አልፈለገም ነበር (ዮሐ 13፡1-17)። አሁን ከረጅም ጊዜ በኋላ ክርስቶስ ራሱን ዝቅ አድርጎ የደቀ መዛሙርቱን እግር ያጠበበትን ሁኔታ ሲያስታውስ እንመለከታለን። እንዲሁም በክርስቶስ መንግሥት ሰው ታላቅ የሚሆነው ሌሎችን በማገልገል እንደሆነ የሚያስረዳውን የክርስቶስን ቃል አስታውሷል። በመሆኑም አሁን በሕይወቱ መጨረሻ ፥ ጴጥሮስ ሰዎች በሐዋርያነቱ ብቻ ሳይሆን በባሪያነቱ እንዲያስታውሱት ይፈልጋል። የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ብዙ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች እራሳቸውን ለሌሎች በሚያስተዋውቁበት ጊዜ ባላቸው ኃይል፥ ሥልጣን ወይም ትምህርት ላይ ትኩረት የሚሰጡት ለምንድን ነው? ለ) ብዙ መሪዎች እንደ ባሪያ ለመታወቅ የማይፈልጉት ለምንድን ነው? ሐ) የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ራሳቸውን በቀዳሚነት እንደ ሽማግሌዎች ወይም መሪዎች ሳይሆን፥ እንደ ባሪያዎች ቢመለከቱ ባህሪያቸው እንዴት ይለወጣል? ጴጥሮስ መልእክቱን የጻፈው ለማን ነው? ጴጥሮስ መልእክቱን ለማን እንደሚጽፍ ሲገልጽ፥ «በአምላካችንና በመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጽድቅ ካገኘነው ጋር የተስተካከለ የክብር እምነት ላገኛችሁት» ይላል። በሌላ አገላለጽ፥ ጴጥሮስ የሚጽፈው ለአማኞቹ ሁሉ ነበር። እነዚህ አማኞች እንደ ሰሜናዊ ትንሹ እስያ ባሉ የተወሰኑ አካባቢዎች የሚኖሩ አልነበሩም። ነገር ግን ይህ አጠቃላይ መልእክት በትንሹ እስያ ውስጥም ያሉትን አማኞች ያካትት ነበር። ምክንያቱም ጴጥሮስ ይህ ለእነርሱ የሚልከው ሁለተኛ መልእክት እንደሆነ ይናገራል። የመጀመሪያው መልእክት አንደኛ ጴጥሮስ ብለን የምንጠራው ነው (2ኛ ጴጥ. 3፡1)። በዚህ አጭር መግቢያ ውስጥ ሁለት ጠቃሚ እውነቶችን ልንመለከት እንችላለን። በመጀመሪያ፥ ጴጥሮስ በአማኞች መካከል የደረጃ ልዩነቶችን ለመመልከት አልፈለገም። ምንም እንኳን እርሱ ክርስቶስን ያየና ሐዋርያዊ ሥልጣን ያለው ቢሆንም፥ በክርስቶስ የሚያምኑ ክርስቲያኖች ሁሉ ለእርሱ እኩል ነበሩ። በሮም ግዛት ውስጥ የተበተኑ አሕዛብ ክርስቲያኖች እምነት ልክ እንደ እርሱ እምነት ውድ ነበር። ሁለተኛ፥ ጴጥሮስ ስለ ክርስቶስ አምላክነት ግልጽ የሆኑትን ትምህርቶች ይሰጣል፡፡ ጴጥሮስ ክርስቶስን አምላክና አዳኝ ሲል ይጠራዋል። 2ኛ ጴጥሮስ የተጻፈበት ጊዜና ቦታ የውይይት ጥያቄ፡– 2ኛ ጴጥ. 1፡12-15 አንብብ። ጴጥሮስ በቅርቡ ምን እንደሚደርስበት ይጠባበቃል? ምንም እንኳን ጴጥሮስ የ2ኛ ጴጥሮስ መልእክትን በሚጽፍበት ጊዜ ገና እስር ቤት ውስጥ ባይገባም፥ ጴጥሮስ እንደሚሞት ያውቅ ነበር። ለዚህም ምክንያቱ ክርስቶስ በቅርቡ እንደሚሞት የገለጠለት መሆኑ ነው። 2ኛ ጴጥሮስ የተጻፈው ከ1ኛው የጴጥሮስ መልእክት በኋላ መሆኑ ግልጽ ነው (2ኛ ጴጥ. 3፡1)። ይሁንና፥ ከአንደኛው መልእክት በኋላ ሁለተኛው መልእክት ምን ያህል ዘግይቶ እንደ ተጻፈ አናውቅም። የቤተ ክርስቲያን ታሪክ እንደሚያመለክተው፥ ጴጥሮስ በሰማዕትነት የሞተው በኔሮ የስደት ዘመን ነበር። ኔሮ የሞተው 68 ዓ.ም ስለነበረ ጴጥሮስ ይህን መልእክት ከዚያ ቀደም ብሎ መጻፉ የተረጋገጠ ነው። በተለይ መልእክቱ 65-68 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ የተጻፈ ይመስላል። ጴጥሮስ ይህንን ደብዳቤ በጻፈበት ወቅት የት እንደነበረ በትክክል ለማወቅ አይቻልም። ምናልባትም ከሮም ከተማ ለሁሉም አማኞች፥ በተለይም በትንሹ እስያ ለሚገኙ ክርስቲያኖች የጻፈ ይመስላል። (ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የ2ኛ ጴጥሮስ መግቢያ Read More »