የመጀመሪያው ዓላማ፡ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሐሰት ትምህርት መስፋፋት ጴጥሮስን አሳስቦት ነበር። ስለሆነም፥ የዚህ መልእክት ቀዳማይ ዓላማ ክርስቲያኖች በሐሰተኛ ትምህርቶች እንዳይወሰዱ ለማስጠንቀቅ ነው። ጴጥሮስ እንደሚለው፥ በመጨረሻው ዘመን ከሚከሰቱት ዐበይት ነገሮች አንዱ በፍጥነት የሚራሱ ሐሰተኛ ትምህርቶች መኖራቸው ነው። ክርስቲያኖች እውነተኛ የሆነውንና ያልሆነውን እንዴት ለይተው ሊያውቁ ይችላሉ? ለዚህ መረጃ ቀዳማዊው ምንጭ መንፈስ ቅዱስ በሰዎች ልብ ውስጥ ከማደሩ የተነሣ አማኞች ከሐዋርያት የተላለፈውን መጽሐፍ ቅዱስ በጥንቃቄ መጠበቅ አለባቸው። ጴጥሮስ ክርስቶስን እንዳየና የእግዚአብሔርም ቃል «ልጄ» እያለ ሲጠራ እንደሰማ ይናገራል። እነዚህ የወንጌል እውነቶች ለአማኞች ተላልፈዋል። እኛም እነዚህን እውነቶች በጥንቃቄ መጠበቅ ይኖርብናል።
2ኛ ዓላማ፡ ጴጥሮስ አማኞች በእምነታቸው ማደጋቸውን እንዲቀጥሉ ለማበረታታት ይፈልጋል። መዳን ብቻ በቂ አይደለም። የእግዚአብሔር ዓላማ በባህሪ እንድናድግና ውጤታማ የተቀደሰ ሕይወት እንድንኖር ማስቻል ነው። አማኞችን ከሐሰተኛ ትምህርት የሚጠብቃቸው ትልቁ ነገር በእውቀትና በመንፈሳዊ ባህሪ ማደግ፥ እንዲሁም በእምነታችን መትጋት ነው። ስለሆነም ጴጥሮስ ይህን መልእክት፥ «በእግዚአብሔርና በጌታችን በኢየሱስ እውቀት» በሚሉ ቃላት ይጀምራል (2ኛ ጴጥ. 1፡2)። ሲደመድምም፥ «በጌታችንና በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና እውቀት እደጉ» ይላል (2ኛ ጴጥ. 3፡18)።
3ኛ ዓላማ፡ የእግዚአብሔር ቃልና የተስፋ ቃሎቹ ፍጹም እውነትና ልንደግፍ የምንችልባቸው መሆናቸውን ማስተማር። አብዛኞቹ ሐሰተኛ ትምህርቶች የእግዚአብሔርን ቃል የማጣመም ውጤቶች ናቸው። ስለሆነም ለአማኞች መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ቃል መሆኑን ማወቅ ብቻ ሳይሆን ሐሰተኛ ትምህርቶችን ለመመርመር መጽሐፍ ቅዱስን መጠቀሙ ጠቃሚ ነው። ጴጥሮስ ጳውሎስ የጻፋቸው መልእክቶችም የእግዚአብሔር ቃል በመሆናቸው አማኞች ሊከተሏቸው እንደሚገባ ይናገራል። ጴጥሮስ በተደጋጋሚ ክርስቲያኖች የእግዚአብሔርን ቃል እውነቶች እንዲያስታውሱ ይመክራቸዋል (2ኛ ጴጥ. 1፡12-15፤ 3፡1)።
ለዛሬው ዘመን ክርስቲያኖች ጥሩና ጥሩ ያልሆነውን ነገር ከእግዚአብሔር ቃል ውጭ ባሉ ነገሮች ይገመግማሉ። ስለሆነም የመጽሐፍ ቅዱስ ተጨባጭ ዓላማ ዋጋ አጥቷል። ሰዎች የወደዱትን ነገር ይቀበላሉ። ክርስቲያኖችም ብዙውን ጊዜ አንድን ነገር ለመቀበል ወይም ላለመቀበል እነዚህን ሦስት ምንጮች ይጠቀማሉ።
ሀ) ስሜት፡ አንድ ነገር ጥሩ ስሜት ከሰጠን ወይም ላሜታችንን ካነሣሣ፥ ብዙ ክርስቲያኖች ይከተሉታል። የሰዎችን ስሜት በከፍተኛ ደረጃ የሚያነቃቃ ነገር በመንፈስ ቅዱስ የተሞላ ነው ተብሎ ይታመናል። ምንም እንኳን መንፈስ ቅዱስ ስሜታችንን ሊያነሣሣ ቢችልም ሁልጊዜም የሚሠራው በእውነት ላይ ተመሥርቶ ነው።
ለ) በአስደናቂ ነገሮች ላይ የሚመሠረቱ የሊቆች ትምህርቶች አሉ። ብዙ ሰዎች ብዙም መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት ሳይኖራቸው በአስደናቂ ነገሮች ላይ (ተአምራት፥ በመንፈስ መገንደስ፥ ወዘተ…) የሚያተኩሩትን የታዋቂ አገልጋዮች ጽሑፎች፥ ካሴቶች ወይም ቪዲዮዎች ይከታተላሉ።
ሐ) ወደ ትውፊት (ልማድ) የሚያተኩሩ ሰዎችም አሉ። እነዚህ ሰዎች፥ «በቤተ ክርስቲያናችን ውስጥ ሁልጊዜም የምናደርገው እንደዚህ ነው። ሲወርድ ሲዋረድ ወደ እኛ የመጣው እንዲህ ነው» ይላሉ። ልማድ ለእምነታችን እርጋታን ሊሰጥ እይችልም። ነገር ግን ሁልጊዜም ልማድ ከመጽሐፍ ቅዱስ ሥልጣን ሥር መዋል አለበት።
ጴጥሮስ የመናፍቅነትና ሐሰተኛ ትምህርት በተትረፈረፈበት ዘመን ውስጥ የምንኖር ሰዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ እንድናተኩር ሁሉንም ነገር በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ተመሥርተን እንድንመረምር ይመክረናል። እግዚአብሔር የተቀባይነት ፊርማውን ያኖረው በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ብቻ ነው።
የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ቤተ ክርስቲያንህን ያወከውን ሐሰተኛ ትምህርት ጥቀስ። ለ) በዚህ ጊዜ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች የሰጡት ምላሽ ምን ነበር? ሁኔታውን እንዴት ተቋቋሙት? ሐ) ብዙ ወጣቶች ለእውነት አስፈላጊነት ደንታ የሌላቸው ለምንድን ነው? መ) እውነት የሆነውንና ያልሆነውን ለመለየት መጽሐፍ ቅዱስ ምን አስተዋጽኦ ያበረክታል? ሠ) ክርስቲያኖች አንድን ትምህርት ወይም አሳብ በስሜቶች፥ ልማድ፥ ወይም አስደናቂ ነገሮች ላይ በሚያተኩር አገልጋይ ቃላት ሊገመግሙ እንደሚችሉ በተመለከትካቸው ነገሮች ላይ ተመሥርተህ አብራራ።
4ኛ ዓላማ፡ ክርስቶስ ተስፋ እንደተገባው ለምን በፍጥነት አልተመለሰም? የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ፡፡ ክርስቲያኖች ከተቸገሩባቸው ነገሮች አንዱ የክርስቶስ በፍጥነት አለመመለስ ይመስላል። በቶሎ እንደሚመለስ ተስፋ የሰጠው ክርስቶስ ሠላሳ ዓመታት ካለፉ በኋላም ብቅ አላለም። በመሆኑም አንዳንድ ሰዎች ክርስቶስ የተናገረውን ስለማድረጉና አለማድረጉ መጠራጠር ጀመሩ። ጴጥሮስ ለዚህ ምላሽ በመስጠት፥ ሀ) የእግዚአብሔር የጊዜ አመለካከት ከሰዎች እንደሚለይ ያብራራል። ለእኛ ረጅም ጊዜ (ሺህ ዓመታት) ለእርሱ አጭር ነው (አንድ ቀን)። ለ) ክርስቶስ በፍጥነት ያልተመለሰበት ዋነኛው ምክንያት ብዙ ሰዎች ንስሐ ገብተው በክርስቶስ ለማመን ዕድል እንዲያገኙ ነው። ይህም ክርስቶስ በሚመለስበት ጊዜ ከሚመጣው የእግዚአብሔር ፍርድ እንዲያመልጡ ያስችላቸዋል።
(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)