ጴጥሮስ አማኞች መጽሐፍ ቅዱስን ከሚያዛቡ ሐሰተኛ አስተማሪዎች እንዲጠበቁ ያስጠነቅቃል (2ኛ ጴጥ. 2፡1-22)

አማኞች በእምነታቸው እና የእግዚአብሔርን ቃል በማወቅ የማያድጉ ከሆነ በአደገኛ ሁኔታ ላይ ይወድቃሉ። ሐሰተኛ ትምህርቶች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሊስፋፉ የሚችሉት በዚህ ጊዜ ነው። በጴጥሮስ ዘመን በአማኞች ሕይወት ውስጥ እየተከሰተ የነበረው ችግር ይህ ነበር። የ2ኛ ጴጥሮስ መልእክት ዋነኛ ትምህርት ክርስቲያኖችን ስለ ሐሰተኛ ትምህርትና አስተማሪዎች ማስጠንቀቅ ነበር።

በብሉይ ኪዳን ዘመን እውነተኛ ነቢያት በተነሣ ቁጥር ሐሰተኛ ነቢያትም ይነሡ ነበር። ከእግዚአብሔር እውነትን የሚናገሩ ሰዎች በሚነሡበት ጊዜ ውሸትን ከራሳቸው አመንጭተው የሚናገሩ ሰዎችም ብቅ ይሉ ነበር። የእነዚህም ሰዎች እሳብ ዋነኛው ምንጭ ሰይጣን ነው። ጴጥሮስ ሰዎች የእግዚአብሔርን እውነት ስተው ውሸትን በሚከተሉባት ጊዜ ምን እንደሚከሰት ታሪካዊ ምሳሌዎችን ይጠቅሳል።

ሀ. መላእክት፡- መላእክት ኃጢአት በሠሩ ጊዜ፥ እግዚአብሔር ወደ ገሃነም ጥሎ በጨለማ ጉድጓድ ለፍርድ ሊጠበቁ አሳልፎ ሰጥቷቸዋል። ምሁራን ይህ ሁለት ነገሮችን ሊያመለክት እንደሚችል ይናገራሉ። በመጀመሪያ፥ ይህ የመጀመሪያውን የሰይጣን ውድቀት እና እርሱን ተከትለው በኃጢአት የወደቁትን መላእክት ያመለክታል ይላሉ። ስለ እነዚህ ውድቀቶች መጽሐፍ ቅዱስ በኢሳ. 14፡12-15 እና በሕዝ. 28፡11-17 ላይ ይናገራል። ነገር ግን መጽሐፍ ቅዱስ በየትኛውም ስፍራ ሰይጣን ወደ ጉድጓድ እንደ ተጣለ አይናገርም። ይህ ወደፊት የሚመጣ ነገር ነው (ራእይ 20፡1-3)። ሁለተኛ፥ ሌሎች ምሁራን ጴጥሮስ በዘፍጥረት 6፡2 ስለተጠቀሱት የእግዚአብሔር ወንዶች ልጆች እየተናገረ ነው ይላሉ። በእነርሱ አስተሳሰብ እነዚህ መላእክት ከሰዎች ሴቶች ጋር ጋብቻ የፈጸሙ ናቸው። እግዚአብሔርን በፍርድ እነዚህን መላእክት ወደ እስር ቤት ልኳቸዋል። በመጨረሻው ፍርድ ሰይጣን እና መላእክቱ ሁሉ ፍርድን እስከሚቀበሉበት ጊዜ ድረስ ታስረው ይቆያሉ። እነዚህ መላእክት መቼ እንደ ወደቁ ባናውቅም፥ የተላለፈልን መልእክት ግልጽ ነው። ይኸውም በእግዚአብሔር ላይ ማመጽ ታላቅ ቅጣትን እንደሚያመጣ ያስረዳል።

ለ) የኖኅ ዘመን ዓለም፡- በዚህ ጊዜ እግዚአብሔር የሰው ልጆችን (ዐመፀኞችን) ያወደመ የጥፋት ውኃ ሰድዷል። እግዚአብሔር ይህን ከማቅረቡ በፊት የጽድቅ ሰባኪ በሆነው በኖኅ በኩል ሲያስጠነቅቃቸው ቆይቶ ነበር። የእግዚአብሔርን ማስጠንቀቂያ ሰምተው የታዘዙት (ኖኅና ቤተሰቡ) ብቻ ከጥፋት ውኃው ሊተርፉ በቅተዋል። ወደፊትም እንዲህ ዓይነት ዓለም ዓቀፍ የፍርድ ቀን ይመጣል። አብዛኛውን ሰው ሳንከተል እንደ ኖኅና ቤተሰቡ የጽድቅ ሕይወት ለመኖር እንመርጥ ይሆን? ወይስ አብዛኛዎችን የጥፋት ሰለባዎች እንከተል ይሆን?

ሐ) ሰዶምና ገሞራ፡- በአብርሃምና ሎጥ ዘመን እግዚአብሔር እነዚህን በክፋት የተሞሉትን ከተሞች ቀጥቷቸዋል። ከዚህ ቅጣት ያመለጡት ሎጥና ሴት ልጆቹ ብቻ ነበሩ።

እነዚህ ምሳሌዎች እግዚአብሔር ጻድቃንና ለእርሱ በመታዘዝ የሚኖሩትን በዐመፀኛነት እንዳሻቸው ከሚኖሩት የሚለይ መሆኑን ያሳያል። እግዚአብሔር ጻድቃንን ከፍጻሜው ጥፋት ይታደጋቸዋል። ይህ ምናልባትም እግዚአብሔር በአሁኑ ዘመን በዓለም ላይ ከሚያመጣው ቅጣት መትረፍን ሊያመለክት ይችላል። እግዚአብሔር ሌሎች ከተጋፈጧቸው የመከራ ጊዜያት ልጆቹን እንደ ጠበቀ የሚያሳዩ ብዙ ምሳሌዎች አሉ። ነገር ግን ጴጥሮስ አጽንኦት የሰጠው ከዘላለማዊ ፍርድ እና ከሲዖል ስለ መዳን ነው።

ኃጢአተኞች አንዳንድ ጊዜ በምድር ላይ የእግዚአብሔርን ፍርድ ይቀበላሉ። ነገር ግን በመጨረሻው ዘመን ዘላለማዊ ፍርድን እንደሚቀበሉ የተረጋገጠ ነው። ጴጥሮስ በእግዚአብሔር ላይ የሚያምጹትን ሰዎች ዐመፀኛነት በዚህ መልእክት ውስጥ ገልጾአል። እነዚህ ሰዎች ትእቢተኞች ሆነው በእግዚአብሔር ላይ ይሳለቃሉ። በወሲባዊ እርካታዎች ላይ ያተኩራሉ። ሁል ጊዜም ተጨማሪ ገንዘብ፥ እንዲሁም እርካታ ለማግኘት ይፍጨረጨራሉ። ይህም ገንዘብን ከመውደድ የተነሣ ነው። በእስራኤል ሕዝብ ላይ የእግዚአብሔር ፍርድ እንዲመጣ ያደረገውን እና የኋላ ኋላ ለሞት የተዳረገውን የበለዓምን ታሪክ የሚመስል ሕይወት እንዲኖሩ ያስገድዳቸዋል (ዘኁል 22-24)። ለሰዎች የራስ ወዳድነት ምኞቶች ማራኪ የሆኑትን ነገሮች ይናገራሉ። አማኞች መስለው ይቀርባሉ። ነገር ግን የኃጢአት ባሪያዎች መሆናቸውን በተግባራቸው ያሳያሉ። ወደ ኃጢአት ሕይወታቸው በሚመለሱበት ጊዜ ውስጣዊ የውሻነት ወይም የአሳማነት ባህሪያቸው ብቅ ይላል። ይህም ደግሞ ልደት ያልዳሰሰው አሮጌ ባህሪ ነው። :

ጴጥሮስ ሊያስተላልፍ የፈለገው መልእክት በረጅም ጊዜ ቆይታ ሐሰተኛ አስተማሪዎችን ከአኗኗራቸው ለይተን ልናውቅ እንደምንችል ነው። ለጊዜው መንፈሳዊያን መስለው ሊያሳስቱ ይችላሉ። ትምህርታቸውና ተግባራቸው ሊያስገርመን እና ሊማርከን ይችላል። የኋላ ኋላ ግን እውነተኛ ባህሪያቸው ይታያል። ሐሰተኛ አስተማሪዎች ብዙውን ጊዜ የኋላ ኋላ በሥልጣን፥ በገንዘብ ፍቅር ወይም በወሲብ ኃጢአት ይወድቃሉ። ስለሆነም ማራኪ የሚመስሉንን ፈጥነን መከተል የለብንም። መጽሐፍ ቅዱስን በሚገባ አጥንተን በማወቅ ሰዎች የሚያስተምሯቸውን ከፊል እውነቶች ልንላይ ይገባል። በሐሰተኛ ትምህርት ከወደቅን እንደ እነዚያ መላእክት፥ በጥፋት ውኃው ዘመን፥ እንዲሁም በሰዶምና ገሞራ ከተሞች እንደነበሩት ሰዎች የእግዚአብሔርን ጽኑ ቁጣ እንቀምሳለን። ስለሆነም ጻድቃን መሆናችንና ለተገለጠው የእግዚአብሔር ፈቃድ ለመታዘዝ መመላለሳችንን ማረጋገጥ ይኖርብናል!

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) በጊዜ ብዛት በአንድ ሐሰተኛ አስተማሪ ሕይወት ውስጥ የተከሰቱትን ነገሮች በመመልከት ሐሰተኛነቱን ለማወቅ ስለቻልክበት ሁኔታ ግለጽ። ለ) ከዚህ ውጭ ሐሰተኛ አስተማሪዎችንና ሐሰተኛ ትምህርቶችን እንዴት ለይተን ልናውቅ እንችላለን?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: