ጴጥሮስ ክርስቶስ ቃል እንደገባው ተመልሶ አይመጣም የሚለውን አሳብ ፉርሽ ያደርገዋል (2ኛ ጴጥ. 3፡1-18)

በመቀጠልም ጴጥሮስ በአብያተ ቤተ ክርስቲያናት እየተሰራጩ ካሉት ሐሰተኛ ትምህርቶች የአንደኛውን አስተምህሮ ሲያፈርስ እንመለከታለን። የክርስቶስን ዳግም ምጽአት የተጠራጠሩ ሰዎች የነበሩ ይመስላል። «ሰዎች ሁልጊዜም ስለ ዓለም ፍጻሜ ሲተነብዩ ኖረዋል። ይሄ እስካሁን አልተከሰተም። ክርስቶስም በቶሎ እመለሳለሁ ብሎ ነበር። ነገር ግን ይኸው ከ30 ዓመታት በኋላም ብቅ አላለም። ይህም የክርስቶስ ዳግም ምጽአት የሚባል ነገር እንደሌለ ያሳያል» ይሉ ነበር። ጴጥሮስ ይህንን አሳብ የሚያፈርሱ ምላሾችን በሚከተለው መልክ አቅርቧል።

ሀ. እንዲህ ዓይነት ነገር የሚናገሩ ሰዎች የጥፋት ውኃውን ትምህርት ዘንግተዋል። ይህ እግዚአብሔር ወደ ሰዎች ታሪክ በታላቅ ኃይል ገብቶ የማያምኑ ሰዎችን ያጠፋበትን ዘመን የሚያሳይ ነው። ከዚያ በኋላ እግዚአብሔር ዓለምን በጥፋት ውኃ እንደማያጠፋ ቃል ገብቷል። ይህ ማለት ግን እግዚአብሔር ዓለምን አያጠፋትም ማለት አይደለም። በቀጣዩ ጊዜ በእሳት ያጠፋታል።

ለ. ብዙ ሰዎች የእግዚአብሔርን የጊዜ ጽንሰ አሳብ አይረዱም። እግዚአብሔር እንደ እኛ በጊዜ የታሰረ አምላክ አይደለም። ጊዜ አሁን እኛ በምናውቀው መልኩ የተጀመረው እግዚአብሔር ዓለምን ሲፈጥር ነው። ነገር ግን እግዚአብሔር ከፍጥረት በፊት ስለነበር፥ እርሱ ከጊዜ ውጪ ነው። በሰማይ ጊዜን ለቀን እና ለሌሊት በዓመታት፥ በወራት፥ በቀናት፥ በ24 ሰዓታት፥ በደቂቃዎች እና በሰኮንዶች የሚከፍሉ ጸሐይና ጨረቃ የሉም። እነዚህ በምድር ላይ ብቻ የምናያቸው ነገሮች ናቸው። ይህም ማለት ለእግዚአብሔር ቅርብ የሆነው ጊዜ በጊዜ ለተወሰኑት ሰዎች ሺህ ዓመት ሊሆን ይችላል። ለዘላለማዊ አምላካችን፥ ሺህ ዓመት አጭር ሊሆን ይችላል። ልክ እንደ አንድ ቀን ጥቂት ጊዜ ብቻ ሊሆን ይችላል።

ሐ) ክርስቶስ ያልተመለሰበት ዋናው ምክንያት ከምሕረቱና ከትዕግሥቱ የተነሣ ብዙ ሰዎች እንዲያምኑ ዕድል ለመስጠት ነው። እርሱ ለማመን የማይፈልጉትን ሰዎች ለመቅጣት ደስ አይሰኝም። ስለሆነም ሕይወታቸውን ለውጠው በክርስቶስ እንዲያምኑ ይጠብቃል።

መ) ምንም እንኳን ጊዜው ረጅም ቢመስልም፥ የእግዚአብሔርን ቃል ማመን አለብን። ክርስቶስ ዳግም እመለሳለሁ ብሏል። አሁን ያለችውን ምድር እንደሚያጠፋ እና አዲስ ሰማይን እና አዲስ ምድር ለመፍጠር ቃል ገብቷል (ኢሳ. 65፡17 አንብብ)። የጌታ ቀን በሚመጣበት ጊዜ የትዕግሥትና የምሕረት ወቅት ይመጣል። እግዚአብሔር በዘፍጥረት 1 የፈጠራቸውን ሰማያትና ምድር ያጠፋል። በእግዚአብሔር ላይ በማመጽ የማይመለሱ ሰዎች በጥፋት ውኃ ዘመን እንደ ነበሩ ሁሉ ይቀጣሉ (ይጠፋሉ)። ነገር ግን እርሱን በመምሰል የሚመላለሱ የእግዚአብሔር ልጆች ወደ ጽድቅ ቤታቸው ይሄዳሉ። ይህም አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር ነው።

አማኞች በእግዚአብሔር የፍርድ እሳት ወደማይጠፋ ቤታችን ለመሄድ አሁን በሕይወታችን እግዚአብሔርን ለማስደሰት ልንወስን ይገባል። በእግዚአብሔር ፊት ነቀፋና እንከን የሌለን ሆነን ከእርሱ ጋር በሰላም ልንመላለስ ይገባል።

ሐሰተኛ አስተማሪዎች የጳውሎስን መልእክቶች በተሳሳተ መንገድ እየጠቀሱ ክርስቲያኖችን ወደ ተሳሳተ አቅጣጫ የሚመሩ ይመስላል። ከመልእክቱ የየትኞቹን ክፍሎች እንደ ጠቀሱ አናውቅም። ምናልባትም ጳውሎስ ድነትን (ደኅንነትን) ያገኘነው ሕግን በመጠበቅ ሳይሆን በእምነት ነው ሲል ያስተማረውን ሊሆን ይችላል (ለምሳሌ፥ ገላ. 2፡14-21)። ከዚህም የተነሣ፥ እነዚህ ሐሰተኛ አስተማሪዎች ክርስቲያኖች የፈለጉትን ነገር ሊያደርጉ እንደሚችሉ ያስተምሩ ነበር። ኃጢአት ጭምር ሊሠሩ እንደሚችሉ በመግለጽ ይናገሩ ጀመር። ጴጥሮስ፥ «የተወደደ ወንድማችን ጳውሎስ» በማለት ለጳውሎስ የነበረውን ፍቅር ከገለጸ በኋላ፥ እነዚህ ሐሰተኞች የጳውሎስን መልእክቶች ብቻ ሳይሆን መጽሐፍ ቅዱስን ሁሉ በተሳሳተ መንገድ እየተረጎሙ በማስተማር ላይ መሆናቸውን አስረድቷል። ጴጥሮስ የጳውሎስ መልእክቶች ከብሉይ ኪዳን ቅዱሳት መጻሕፍት ጋር እኩል መሆናቸውን ገልጾአል። እርሱም ሆነ ሌሎች መንፈስ ቅዱስ የብሉይ ኪዳን ነቢያትን በተጠቀመበት መንገድ ጳውሎስና ሌሎችን ሥልጣን ባለው መንገድ የተጠቀመ መሆኑን ተገንዝበው ነበር (2ኛ ጴጥ. 1፡21)።

ይህ ትምህርት ለአማኞች ጠንካራ ማስጠንቀቂያ ነው። አንድ ሰው ከመጽሐፍ ቅዱስ አንድ ወይም ሁለት ጥቅስ ጠቀሰ ማለት ትምህርቱ ትክክል ነው ማለት አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረውን ትምህርተ አሳብ በተሳሳተ መንገድ መተርጎም ወይም መጠቀም ተገቢ አይሆንም። ስለሆነም፥ እግዚአብሔር በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለማስተላለፍ የፈለገውን መልእክት በትክክል መረዳታችንን በጥንቃቄ ማረጋገጥ አለብን። ዛሬ አብያተ ክርስቲያናችንን ከሚያውኩት መናፍቃን አብዛኞቹ የፈለቁት ሐሰተኛ አስተማሪዎች የተወሰኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን ከዐውዳቸው ውጭ የትምህርታቸው መሠረት አድርገው በመጠቀማቸው ነው። የእግዚአብሔርን ቃል በይበልጥ ባጠናንና የመጽሐፍ ቅዱስን ዐበይት ትምህርቶች ባወቅን መጠን፥ የሚመጡትን ትምህርቶች ሁሉ መርምረን እውነተኛውን ከሐሰተኛው ለመለየት እንችላለን።

የውይይት ጥያቄ፡- ጴጥሮስ የሐሰተኛ ትምህርት መድኃኒቱ መጽሐፍ ቅዱስን በአግባቡ መተርጎምና በሚገባ ማወቅ እንደሆነ ይናገራል። ሀ) ግንዛቤህና አስተምህሮህ መጽሐፍ ቅዱሳዊ እንዲሆን ምን እያደረግክ ነው? ለ) የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ሁሉንም የእግዚአብሔር ቃል በበለጠ ለማወቅ ምን እያደረጉ ናቸው? ሐ) ይህ ትምህርት፥ «መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት አያስፈልገኝም፥ መንፈስ ቅዱስ ትክክለኛውንና ትክክለኛ ያልሆነውን ለይቼ እንዳውቅ፥ እንዲሁም ምን ማለት እንዳለብኝ ያስተምረኛል» ለሚሉ ሰዎች ምላሽ እንድንሰጥ የሚያግዘን እንዴት ነው?

ሽማግሌው የመጨረሻ ምክሩን ሰጥቷል። ይኸውም፥ «በእውቀት እደጉ (በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና እውቀት እደጉ)፥ የእግዚአብሔርን ቃል ተጠቀሙ፤ መጽሐፍ ቅዱስን አለአግባብ እየተጠቀሙ ከፊል እውነት የሚያስተምሩትን ሰዎች በጥንቃቄ ተመልከቱ» የሚል ነበር። ይህንን በምናደርግበት ጊዜ፥ ራሳችንን በሐሰተኛ ትምህርት ከመወሰድ እንጠብቃለን። ለአዳነን ለኢየሱስ ክርስቶስ ስም ክብርን እናመጣለን። ለክርስቶስ ክብርን እያመጣህ ነው?

የውይይት ጥያቄ፡– ከ2ኛ ጴጥሮስ ያስገረመህን አንዳንድ እውነቶች ዘርዝር። መንፈስ ቅዱስ እነዚህን እውነቶች ከሕይወትህ ጋር እንድታዛምድ የሚፈልገው እንዴት ነው?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

1 thought on “ጴጥሮስ ክርስቶስ ቃል እንደገባው ተመልሶ አይመጣም የሚለውን አሳብ ፉርሽ ያደርገዋል (2ኛ ጴጥ. 3፡1-18)”

Leave a Reply

%d bloggers like this: