የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ስለ 3ኛ ዮሐንስ ከመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት አንብብ። በመዝገበ ቃላት ውስጥ የጸሐፊው፥ መልእክቱን ስለሚቀበሉ ሰዎች እና ስለ መልእክቱ ዓላማ የተሰጠውን ጠቅለል አድርገህ ጻፍ። ለ) 3ኛ ዮሐ 1 አንብብ። ጸሐፊው ማን ነው? መልእክቱ የተጻፈው ለማን ነው? ይህንን ከ2ኛ ዮሐ 1 ጋር አነጻጽር። እነዚህ ሁለቱ መልእክቶች የሚመሳሰሉት እንዴት ነው?
፩. የ3ኛ ዮሐንስ ጸሐፊ
የ3ኛ ዮሐንስ መልእክት ጸሐፊ ራሱ የ2ኛ ዮሐንስ መልእክት ጸሐፊ መሆኑ ግልጽ ነው። በሁለቱም መልእክት ውስጥ ጸሐፊው ራሱን «ሽማግሌው» ሲል ይገልጻል። እንዲሁም ጸሐፊው እንደ «እውነት» እና «ፍቅር» የሚሉትን ቃላት ይጠቀማል። [ሁለቱም መልእክቶች «በፍቅር መዋደድ» (2ኛ ዮሐ. 1፣ 3ኛ ዮሐ. 1) እና «በእውነት መመላለስ» (2ኛ ዮሐ. 4፥ 3ኛ ዮሐ. 4) የሚሉትን ተመሳሳይ አሳቦች ይጠቀማሉ።] ስለሆነም፥ የ2ኛ ዮሐንስ መልእክት ጸሐፊ የ3ኛው ዮሐንስ መልእክት ጸሐፊ መሆኑ ግልጽ ነው። ቀደም ሲል እንደተመለከትነው፥ ምንም እንኳን ሽማግሌው ዮሐንስ በቀድሞይቱ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የነበረ ሌላ አገልጋይ እንደሆነ የሚያስቡ ምሁራን ሲኖሩም፥ የእነዚህ መልእክቶች ጸሐፊ ሐዋርያው ዮሐንስ ይመስላል።
፪. መልእክቱ የተጻፈው ለማን ነበር?
ጸሐፊው መልእክቱን ለማን እንደላከ ሲገልጽ፥ «በእውነት እኔ ለምወደው ለተወደደው ጋይዮስ» ይላል። ጋይዮስ በሮም ግዛት ውስጥ የተለመደ ስም ሲሆን፥ በአዲስ ኪዳን ውስጥ ጋይዮስ የሚባሉ ብዙ አማኞች ተጠቅሰዋል። ከእነዚህም መካከል የመቄዶንያው ጋይዮስ (የሐዋ. 19፡29)፥ የደርቤው ጋይዮስ (የሐዋ. 20፡4)፥ የቆሮንቶሱ ጋይዮስ (ሮሜ 16፡23)፥ እንዲሁም ይኸው በ3ኛ ዮሐንስ ውስጥ የተጠቀሰው ጋይዮስ ይገኙባቸዋል። ምንም እንኳን በዚህ ስፍራ የተጠቀሰው ጋይዮስ ከላይ ከተጠቀሱት አንዱ ሊሆን ቢችልም፥ ይኼኛው ጋይዮስ በትንሹ እስያ ውስጥ ብዙም የማይታወቅ የቤተ ክርስቲያን መሪ የነበረ ይመስላል። በዚህ አገልጋይ ቤት ውስጥ ቤተ ክርስቲያን ትሰባሰብ ነበር። ዮሐንስ ጋይዮስን በደንብ በሚገባ ያወቀ ሲሆን፥ ምናልባትም በቤቱ ውስጥ ስለምትሰባሰበው ቤተ ክርስቲያን ምክር ሊሰጠው ፈልጎ ይሆናል። ምንም እንኳን ደብዳቤው የተጻፈው ለጋይዮስ ቢሆንም፥ ዮሐንስ ደብዳቤው (ቢያንስ ከደብዳቤው የተወሰነውን መልእክት) በቤተ ክርስቲያኒቱ ምእመናን እንደሚነበብ ተስፋ የሚያደርግ ይመስላል። ይህም ክርስቲያኖቹ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ችግር የሚፈጥሩትን መሪዎች እንዴት እንደሚቋቋሙ ለማወቅ ያግዛቸዋል። አንዳንድ ምሁራን ጋይዮስን ወደ ክርስቶስ ማመን ያመጣው ዮሐንስ እንደነበረ ያምናሉ።
፫. 3ኛ ዮሐንስ የተጻፈበት ዘመንና ስፍራ
የ2ኛና 3ኛ ዮሐንስ መልእክቶች በተመሳሳይ ጊዜና በተመሳሳይ ስፍራ የተጻፉ ይመስላል። ምንም እንኳን ይህ ግምት ቢሆንም፥ አብዛኛዎቹ ምሁራን ዮሐንስ ይህን መልእክት ከ85-95 ዓመተ ምሕረት ባለው ጊዜ በኤፌሶን ከተማ ሆኖ እንደ ጻፈው ያምናሉ።
፬. የ3ኛ ዮሐንስ መልእክት ዓላማ
የ2ኛና የ3ኛ ዮሐንስ መልእክት ዓላማዎች ተመሳሳይ ናቸው። 3ኛ ዮሐንስ የተጻፈው ለጋይዮስና በቤቱ ውስጥ ለምትሰበሰበው ቤተ ክርስቲያን ነበር። መልእክቱ የተጻፈባቸው ምክንያቶች የሚከተሉት ናቸው፡-
የመጀመሪያው ዓላማ፡ ዮሐንስ የላካቸውን አስተማሪዎች ሌሎች የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ሳይቀበሷቸው ጋይዮስ ግን ስለተቀበላቸው ላከናወነው መልካም ተግባር ምሥጋና ለማቅረብ።
ሁለተኛ ዓላማ፡ ክርስቲያኖች ዲዮጥራጢስ ከተባለ የቤተ ክርስቲያን መሪ ተግባራት እንዲጠነቀቁ ለማሳሰብ። ዲዮጥራጢስ ሐሰተኛ ትምህርት ማስተማሩን የሚያመለክት መረጃ በዚህ ክፍል ውስጥ አልተጠቀሰም። ነገር ግን ሰውየው የሥልጣን ጥመኛ በመሆኑ ምክንያት እርሱ ያላጸደቀው ምንም ነገር እንዳይከናወን ያገደ ይመስላል። ዮሐንስ ከስፍራ ስፍራ እየተጓዙ እማኞችን የሚያስተምሩትን እስተማሪዎች የላከ ይመስላል። ነጎር ግን በእስያ ከሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት የአንደኛዋ መሪ የሆነው ዲዮጥራጢስ እነዚህ አስተማሪዎች ተግባራቸውን እንዳያከናውኑ የከለከለ ይመስላል። እንዲሁም እነዚህን አስተማሪዎች በእንግድነት ለመቀበል የፈለጉትን ሰዎች ከቤተ ክርስቲያን ያባረረ ይመስላል። ዮሐንስ ጋይዮስ እነዚህን አስተማሪዎች ስለረዳ ያመሰግነዋል። ዲዮጥራጢስ ደግሞ ዮሐንስ ወደዚያው አካባቢ በመጣ ጊዜ ቅጣት እንደሚጠብቀው ያስጠነቅቀዋል።
ሦስተኛ ዓላማ፡ አማኞች እውነትን እንዲያውቁና በዚሁ እውነት ላይ ጸንተው እንዲቆሙ (በተለይም አንዳንድ አስተማሪዎች ሐሰትን በሚያስፋፉበት ወቅት) ለማስገንዘብ።
፭. የ3ኛ ዮሐንስ ልዩ ባሕርያት
- ይህ በአዲስ ኪዳን ውስጥ ከሚገኙት ሦስት ግላዊ ደብዳቤዎች አንዱ ነው። (ሦስቱ ግላዊ መልእክቶች ፊልሞና፥ 2ኛና 3ኛ ዮሐንስ ናቸው። ጢሞቴዎስና ቲቶ ለግለሰቦች የተላኩ መልእክቶች ቢሆኑም፥ በቀዳሚነት ቤተ ክርስቲያንን የሚያመለክቱ አሳቦች ስለተካተቱባቸው ከግላዊ መልእክቶች የተለዩ ናቸው።) ምንም እንኳን እነዚህ መልእክቶች ለግለሰቦች የተላኩ ቢሆኑም፥ አሳባቸው ለወጣቶች ሁሉ የሚጠቅም ነው። ለዚህም ነው እነዚህ ደብዳቤዎች፥ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተካተቱት።
- ዮሐንስ ስለ ክርስትና ላለው ግንዛቤ መሠረት የሆኑለትን ሁለት ቃላት ያያይዛቸዋል። በመጀመሪያ፥ ክርስትና በእውነት ላይ የተመሠረተ ነው። በዚህ አንድ ምእራፍ ውስጥ ውስጥ እውነት ስድስት ጊዜያት ተደጋግሞ ተጠቅሷል። ሁለተኛ፥ እውነት በፍቅር መገለጽ አለበት።
- ዮሐንስ ሁለት ዓይነት የቤተ ክርስቲያን መሪዎችን ያነጻጽራል። ጋይዮስ መንፈሳዊ የቤተ ክርስቲያን መሪ ነበር። ለእውነት የሚታመንና ፍቅርን ያሳየ አገልጋይ ነበር። ይህንንም ያደረገው ሌሎች አማኞች ለተወሰኑ ግለሰቦች ፍቅርን እንዳያላይ ጫና እያሳደሩበት ሳለ ነበር። በሌላ በኩል ዲዮጥራጢስ የዓለማዊ መሪ ምሳሌ ነው። ራሱን ከሐዋርያው ዮሐንስ ከፍ አድርጎ በመመልከት ሥልጣንና ኃይልን ይሻ ነበር። የሚደግፉት ሰዎች ብቻ እንዲያገለግሉ የሚፈልግ ጠባብ አስተሳሰብ የተጫነው ሰው ነበር። እርሱ የማይደግፈውን ሰው የደገፈ ግለሰብ ከዲዮጥራጢስ ቤተ ክርስቲያን ይባረር ነበር። ይህ ሰው ፍቅር የማያውቅና በሐሜት የሰዎችን ስም የሚያጎድፍ አገልጋይ ነበር።
፮. የ3ኛ ዮሐንስ አስተዋጽኦ
- ዮሐንስ ጋይዮስን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ላከናወነው የታማኝነት አገልግሎት ያመሰግነዋል (3ኛ ዮሐ 1-8)።
- ዮሐንስ፥ ዲዮጥራጢስ የዮሐንስን ሥልጣንና አስተማሪዎችን ባለመቀበል ስለፈጸመው ጥፋት ለጋይዮስ ይነግረዋል (3ኛ ዮሐ. 9-11)።
- ማጠቃለያ (3ኛ ዮሐ 12-14)
(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)