3ኛ ዮሐ 1:1-15

፩. ዮሐንስ ጋይዮስ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ስላበረከተው ታማኝነት የተሞላበት አገልግሎት ያመሰግነዋል (3ኛ ዮሐ 1-8)

አንድ ሰውዬ ዮሐንስን ለመጎብኘት መጥቶ ነበር። ይኸው ግለሰብ በትንሹ እስያ ከሚገኙት አብያተ ክርስቲያናት አንደኛዋ በምን ዓይነት ሁኔታ ውስጥ እንዳለች ለዮሐንስ ገለጸለት። ይኸው መልእክት ለዮሐንስ የመልካምና የክፉ ዜናዎች ቅልቅል ነበር። መልካሙ ዜና የእግዚአብሔር ደፋርና መንፈሳዊ አገልጋይ የነበረውን ጋይዮስን የሚመለከት ነበር። ስለሆነም ዮሐንስ ጋይዮስን ስለ ሁለት ነገሮች ያመሰግነዋል። በመጀመሪያ፥ ዮሐንስ ጋይዮስን ስለ መንፈሳዊ ባሕሪው ያመሰግነዋል። ጋይዮስ እንደ እግዚአብሔር ቃል እምነት ታማኝ ነበር። ሌሎች አማኞች በአንዳንድ የእምነት ክፍሎቻቸው ወዲያ ወዲህ እያሉ ሲፍገመገሙ ጋይዮስ ግን የእግዚአብሔርን እውነት አጥብቆ ይዞ ነበር። በተጨማሪም ጋይዮስ በእውነት ይመላለስ ነበር። ጋይዮስ ባመነውና የእግዚአብሔር ቃል በሚያስተምረው እውነት ላይ ተመሥርቶ ቆሞ ነበር።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ሌሎች፥ በተለይም ታዋቂ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ስሕተት እየፈጸሙ ትክክለኛውን ነገር ማከናወን ለምን አስቸጋሪ እንደሚሆን ግለጽ። ለ) የቅርብህ የሆነ ሰው እውነትን ለማመቻመች በመረጠ ጊዜ እውነትን ለመከተል አስቸጋሪ ውሳኔ የወሰንክበትን ሁኔታ በምሳሌነት ጥቀስ።

ሁለተኛ፥ ዮሐንስ ጋይዮስን እንግዶችን በመቀበሉ ያመሰግነዋል። ከእነዚህ እንግዶች አብዛኞቹ ከቦታ ቦታ እየተዘዋወሩ የሚሰብኩና ዮሐንስ በዚያች ቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንዲያገለግሉ የላካቸው አስተማሪዎች ሳይሆኑ አይቀሩም። እነዚህ ከቦታ ቦታ የሚጓዙ አስተማሪዎች ደመወዝ ስላልነበራቸው፥ ድጋፍ የሚያገኙት ከእግዚአብሔር ሕዝብ እርዳታ ነበር። ዮሐንስ ጋይዮስና ቤተ ክርስቲያኑ እነዚህን አስተማሪዎች እንዲቀበሉ፥ እንዲንከባከቡ እና ወደ ሌላ ከተማ በሚሄዱበት ጊዜ በጉዞአቸው እንዲረዳቸው ያበረታታቸዋል።

፪. ዮሐንስ ዲዮጥራጢስ ሐዋርያዊ ሥልጣኑን ለመታዘዝና አስተማሪዎቹን ለመቀበል ባለመፈለጉ ከእርሱ እንዲጠነቀቅ ይመክረዋል (3ኛ ዮሐ 9–11)

«ሥልጣን ለብልሹነት (ሙስና) ያጋልጣል። ፍጹም የሆነ ሥልጣን ደግሞ ፍጹማዊ ብልሹነት ያስከትላል።» ይህ ብዙ ሰዎች የመሪነትን ሥልጣን በሚይዙበት ጊዜ በሕይወታቸው ውስጥ የሚከሰተውን ሁኔታ የሚገልጽ አባባል ነው። ሁላችንም በጣም የተከበሩ የቤተ ክርስቲያን ምእመናን ሥልጣን በሚይዙበት ጊዜ ሲለወጡ አይተናል። ለሰዎች ያስቡና ያገለግሉ የነበሩ ግለሰቦች በአምባ ገነናዊ ሥልጣን የሚገዙ ገዢዎች ሆነው ቁጭ ይላሉ። በዚህም ጊዜ፥ «ልትታዘዙኝ ይገባል። እኔ መሪያችሁ ነኝ» የሚል መልእክት በተግባራቸው ያስተላልፋሉ። «እኔ እስካልፈቀድኩ ድረስ ምንም ነገር ልታደርጉ አትችሉም» ሲሉ የበላይነታቸውን ይገልጻሉ። ይህ የዓለምን የአመራር ስልት የተከተለ አሠራር በጣም አውዳሚ ነው። ይህ የሰዎችን መንፈሳዊ ደስታ ያጠፋል። ሰዎች የእግዚአብሔርን ቃል ለመስማት ያላቸውን ዝንባሌ ያጠፋዋል። በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሰዎች እግዚአብሔርን ለማገልገል ምን ማድረግ እንዳለባቸው የመንፈስ ቅዱስን ድምጽ የሚሰሙበትን ነጻነት ያርቃል። ሁሉም ነገር በመሪው በኩል ማለፍ ስላለበት፥ ማንም ሰው ምንም ነገር ለማድረግ ፈቃደኛ አይደለም። ይህም ማኅበረ ምእመናኑ መሪውን የሚፈሩ ሰዎች ያደርጋቸዋል።

ዮሐንስ የሚጽፍላት ቤተ ክርስቲያን በዚህ ዓይነት ችግር ውስጥ ነበረች። ዲዮጥራጢስ የሚባል አምባገነናዊ መሪ ተነሥቶ ነበር። ዲዮጥራጢስ ከሐዋርያው ዮሐንስ የበለጠ ሥልጣን አለኝ ብሎ የሚያስብ ሰው ነበር። ዮሐንስ ከቦታ ቦታ እየተጓጓዙ የሚያገለግሉ አስተማሪዎችን እንደ ላከ የገለጸበትን ደብዳቤ በጻፈለት ወቅት ዲዮጥራጢስ ሊቀበለው አልፈለገም። እርሱ ብቻውን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ፍጹም ሥልጣን ያለው ሰው ለመሆን ፈለገ። ሰዎች እርሱን ብቻ እንዲሰሙ እንጂ ከእርሱ ሌላ ከማንም መመሪያ እንዳይቀበሉ አደረገ። የዚህ ሰው አምባገነናዊ አመራር በአያሌ መንገዶች ሊታይ ይችላል፡

ሀ) ዲዮጥራጢስ በአንደኛ ደረጃ ለመከበር ፈለገ።

ለ) ዲዮጥራጢስ ሁልጊዜም ትክክል ነኝ፥ ስለሆነም ሰዎችን መስማት የለብኝም የሚል አሳብ ነበረው።

ሐ) ዲዮጥራጢስ በሐሜት የሌሎች መሪዎችን ስም አጎደፈ። ዲዮጥራጢስ ሌሎች መሪዎች፥ አንድን ነገር የሚያደርጉት በተሳሳተ ዓላማ እንደሆነ ያስብ ነበር። ይህንንም የሚያደርገው የሰዎችን ልብና አስተሳሰብ ለማየት እንደሚችል በማመን ነበር። ሰይጣን መሪዎችን ለማሸነፍ ከሚጠቀምባቸው መንገዶች አንዱ ስለ ሌሎች መሪዎች ወይም ግለሰቦች ዓላማ የተሳሳተ ግንዛቤ እንድንይዝ በማድረግ ነው። አሳባችንን የምናስደግፍበት ተጨባጭ መረጃ ሳይኖረን እነዚህ ሰዎች እግዚአብሔርን በንጹሕ ልቦና ለማገልገል የሚፈልጉ መሆናቸውን ከማሰብ ይልቅ ትክክል ባልሆኑ ዓላማዎች እንደሚመሩ ብንናገር፥ በእነዚህ ሰዎች ላይ ኃጢአትን እንፈጽማለን። አንድ ሰው አንድን ጉዳይ ከእኛ በተለየ ዓይን መመልከቱ የተሳሳተ ዓላማ እንዳለው አያመለክትም።

መ) ዲዮጥራጢስ ከእርሱ የተለየ አመለካከት ካላቸው ሰዎች ጋር ኅብረት ለማድረግ የማይፈልግ ከፋፋይ ነበር። ከዮሐንስ ተልከው የሄዱት ተጓዥ አስተማሪዎች ቤተ ክርስቲያንን እንዲጎበኙ እንኳን አልፈቀደላቸውም።

ሠ) ዲዮጥራጢስ አምባገነናዊ ነበር። እርሱ የፈለገውን ነገር ያላደረገው ሰው ከቤተ ክርስቲያኑ እንዲባረር ያደርግ ነበር። ስለሆነም፥ እነዚህን ተጓዥ አስተማሪዎች በቤቱ እንግድነት የተቀበለ አማኝ ሁሉ ከቤተ ክርስቲያኑ ኅብረት እንዲባረር አድርጓል።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) አንዳንድ ሰዎች መሪዎች ከሆኑ በኋላ ባሕሪያቸው እንዴት እንደሚለወጥ ግለጽ። ለ) ሽማግሌዎች ወይም መሪ ሽማግሌ የዲዮጥራጢስን ዓይነት እርምጃ መውሰድ በሚጀምርበት ጊዜ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ምን ይከሰታል? ሐ) ማር. 10፡35-45 አንብብ። የዲዮጥራጢስ አመለካከት ክርስቶስ ተከታዮቹ እንዲኖራቸው ከፈለገው አመለካከት የሚለየው እንዴት ነው?

ዮሐንስ ጋይዮስ እንደ ዲዮጥራጢስ ዓይነት ክፉ መሪ እንዳይሆን በማስጠንቀቅ ይህን ክፍል ይደመድማል። ይልቁንም ጋይዮስ ሌሎችን ማገልገሉንና መልካም ማድረጉን መቀጠል ያስፈልገው ነበር። በክፋት ለመሸነፍ የሚፈቅዱ ሰዎች እግዚአብሔርን ሊያዩ እንደማይችሉ ዮሐንስ ያስጠነቅቃል።

፫. መደምደሚያ (3ኛ ዮሐ 12-15)

በመደምደሚያው ላይ ዮሐንስ ድሜጥሮስ የተባለ ሌላ ግለሰብ ያስተዋውቃል። ድሜጥሮስ ማን እንደሆነ አናውቅም። ነገር ግን ይህ ሰው የዮሐንስን መልእክት በጋይዮስ እንደ ደረሰ የሚያስቡ ሰዎች አሉ። ዮሐንስ ዲሜጥሮስ ለእውነት በመታመኑ መንፈሳዊነቱን ያረጋገጠ ክርስቲያን መሆኑን ይመሰክራል።

ዮሐንስ ጋይዮስን መጥቶ እንደሚጎበኘው በመግለጽ መልእክቱን እንደሚደመድም ይገልጻል። ዮሐንስ የሌሎች አማኞችን ሰላምታ ካስተላለፈ በኋላ ይህንን አጭርና ዳሩ ግን ኃይለኛ የሆነ መልእክት ይደመድማል።

ለቤተ ክርስቲያን ሽማግሌዎች እጅግ ወሳኝና ዳሩ ግን አስቸጋሪ ከሆኑት ነገሮች አንዱ ስለ ክርስቲያናዊ አመራር ተገቢውን አመለካከት ማዳበር ነው። ብዙ መሪዎች በራሳቸው ስለማይተማመኑ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚደረገውን ነገር ሁሉ እኔ ካላደረግኩ ሲሉ የሙጥኝ ይላሉ። ሌሎች መንፈስ ቅዱስ ከእነርሱ በቀር በሌሎች ሰዎች ልብ ውስጥ አልፎ የመሪነትን አገልግሎት እንዲያከናውኑ ያግዛቸዋል የሚል እምነት አይኖራቸውም። እንዲህ ዓይነቱ መሪ እኔ ብቻ ትክክል ነኝ በማለት ለሰዎች ትእዛዝ የመስጠት መብት እንዳለው ያስባል። አንዳንድ መሪዎች ንጉሣዊ ሥልጣን ያላቸው ይመስል ሰዎች የተለያዩ ነገሮችን እንዲያደርጉ ያዝዛሉ። እንዲህ ዓይነቱ መሪ ከቤተ ክርስቲያን ውስጥ የጌታን ደስታ ከማስወገዱም በላይ፥ መንፈስ ቅዱስ ሰዎችን ወደ አዳዲስ አገልግሎቶች እንዳይመራ ይገድባታል። በዚህም ጊዜ የቤተ ክርስቲያን ራእይ ይሞታል። ምክንያቱም በአንድ የቤተ ክርስቲያን መሪ ተወስኗልና። ሰዎች ወደ ቤተ ክርስቲያን ቢመጡም፥ በዚያ አካባቢ የፍቅርና የነጻነት ስሜት ስለማይታይ ፈጥነው ወደ ቤታቸው ይመለሳሉ። ራሱን የእግዚአብሔርና የሰዎች ባሪያ አድርጎ የሚመለከት መንፈሳዊ መሪ መኖሩ ምንኛ የተሻለ ነው። እንዲህ ዓይነቱ አገልጋይ መንፈስ ቅዱስ በእርሱ ውስጥ ብቻ እንደሚሠራና ለእርሱ ብቻ ጥበብን እንደሚሰጥ ከማሰብ ይልቅ በሌሎችም ሰዎች ሕይወት ውስጥም እንደሚሠራ ያምናል። መንፈሳዊ መሪ አማኞች፥ ስጦታዎቻቸውን ችሎታዎቻቸውን በመጠቀም እግዚአብሔርን እንዲያገለግሉ ያበረታታል እንጂ፥ ስጦታዎቻቸውን ለመጫን አይሞክርም። እንዲህ ዓይነቱ መሪ ለቤተ ክርስቲያን ታላቅ በረከት ነው!

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ምን ዓይነት መሪ ነህ? ሰዎች አንተን ብቻ እንዲያደምጡ የምትፈልግ በራስህ የማትተማመንና አምባ ገነናዊ ነህ? ወይስ ሰዎችን አምነህ እግዚአብሔር በስጦታዎች ባበለጸጋቸው አካባቢዎች እንዲያገለግሉ ታበረታታቸዋለህ? ለ) አንድ የምታውቀው፥ የምታምነውና በግልጽ የመሪነት አገልግሎትህን የሚገመግም ሰው ፈልግና አመራርህ አምባ ገነናዊ ወይም አገልጋያዊ መሆኑን እንዲነግርህ ጠይቀው። ሐ) አሁኑኑ ጊዜ ወስደህ ልብህንና የመሪነት አገልግሎትህን መርምር። እግዚአብሔር እንደ ጋይዮስ እንጂ እንደ ዲዮጥራጢስ እንዳትሆን እንዲያግዝህ ጸልይ።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: