ትምህርት ብሉይ ኪዳን

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) የመጽሐፍ ቅዱስ ሁለት ዋና ዋና ክፍሎች የትኞቹ ናቸው? ለ) እንደዚያ ተብለው ለምን ተጠሩ? ሐ) ኪዳን የሚለውን ቃል ትርጉም ከመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት በመመልከት የተሟላ ትርጉም ጻፍ። መ) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙ የተለያዩ ኪዳኖችን ዘርዝር። ሠ) ኪዳን የሚለው ቃል ከእግዚአብሔር ጋር ያለንን ግንኙነት እንዴት ይገልጻል?

ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ቃል መሆኑን እናምናለን። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እግዚአብሔር ራሱን ለእኛ ይገልጥልናል። እርሱ ምን እንደሚመስልና ከእርሱ ጋርም ሕያው የሆነ ግንኙነት እንዲኖረን ከእኛ ምን እንደሚፈልግ እንማራለን። መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ቃል በመሆኑ ስለ እግዚአብሔር ማንነት፥ ወደ መንግሥተ ሰማያት ስለሚወስደው መንገድ፥ ለእግዚአብሔር ስለመኖር ያለንን አሳብ ሁሉ የምንበይንበት መመዘኛ ነው። ማንኛውም አሳባችን፣ የባሕላችን አስተምህሮት፥ ወይም የሌሎች ሰዎች ትምህርት በመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት መመዘን አለበት። ከመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ጋር የማይስማማ ማንኛውም ትምህርት መወገዝ አለበት። እንዲሁም እግዚአብሔር ስለ ራሱና ስለ ፈቃዱ የገለጠውን ነገር በሚገባ እንድንረዳ መጽሐፍ ቅዱስን በትክክል መተርጎም እንዳለብን ተምረናል። ይህንን ካላደረግን ግን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የራሳችንን አሳብ እንጨምራለን፥ መጽሐፍ ቅዱስንም እንዳይናገረን እናደርገዋለን።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) «ብሉይ» የሚለው ቃል ትርጉም ምን እንደሆነ አንድን የኦርቶዶክስ ካህን ወይም ሌላ ሰው ጠይቅ። ለ) «ኪዳን» የሚለው ቃል ትርጉም በአማርኛ ምንድን ነው?

እኛ ክርስቲያኖች መጽሐፍ ቅዱስ ሁለት ዋና ክፍሎች እንዳሉት እናውቃለን። የመጀመሪያው ክፍል «ብሉይ ኪዳን» ሲባል፥ ሁለተኛው ደግሞ «አዲስ ኪዳን» ይባላል። በኢየሱስ የማያምኑ አይሁድ የዕብራውያን መጽሐፍ ቅዱስ በሚባለው ብሉይ ኪዳን ብቻ ያምናሉ። ለእነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ሁለቱ ስሞች ለምን እንደተሰጡ ለመረዳት ሁለት ዋና ዋና ቃላትን መመልከት ያስፈልገናል።

፩. ኪዳን፡-. ኪዳን የሚለው ቃል ትርጉሙን የወሰደው ሁለት ሰዎች ወይም ቡድኖች በመካከላቸው እርስ በርስ ከሚያደርጉት ስምምነት ነው። ከብዙ መቶ ዓመታት በፊት ኢየሱስ ከሞተና አሁን በአዲስ ኪዳን ውስጥ ያሉ በርካታ መጻሕፍት ከተጻፉ በኋላ ክርስቲያኖች ቅዱሳት መጻሕፍትን ለመግለጥ «ኪዳን» የሚለውን ቃል መጠቀም ጀመሩ። መጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔር ራሱንና ፈቃዱን የገለጠበት መሆኑና እግዚአብሔር ራሱን ከሰው ልጆች ጋር በኪዳን ወይም በስምምነት ግንኙነት እንዲኖረው እንዳደረገ ተገነዘቡ። በማንኛውም «ኪዳን» ውስጥ ሦስት ዋና ዋና ክፍሎች አሉ፡- በመጀመሪያ፥ በኪዳኑ ውስጥ የሚካተቱ አባላት አሉ። በመጽሐፍ ቅዱስ «ኪዳን» የሚለው ቃል የሚናገረው እግዚአብሔር ከተለያዩ ሰዎች ጋር ኅብረት እንዳደረገ ነው። አንዳንድ ጊዜ እግዚአብሔር እንደ አብርሃምና ዳዊት ካሉ ጋር ስምምነት አድርጓል። በሌላ ጊዜ ደግሞ እግዚአብሔር ከኖኅ ጋር እንዳደረገው ዓይነት ከሰው ልጆች ሁሉ ጋራ ስምምነት አድርጓል። የብሉይ ኪዳን ዋና ክፍል ግን እግዚአብሔር ከአብርሃም ልጆች ጋር (ማለትም ከአይሁድ ጋር) ስላደረገው ኪዳን የሚናገር ነው።

የውይይት ጥያቄ፥ የአዲሱ ኪዳን ስምምነት የተደረገው ከማን ጋር ነው? ]

ሁለተኛ፥ ቃል ኪዳኑ እንዲጠበቅ እንዲሟላና እንዲፈጸም በአንዱ ወይም በሁለቱም የኪዳኑ አባላት መጠበቅ ያለባቸው ቅድመ ሁኔታዎች በኪዳኑ ውስጥ መኖር አለባቸው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሁለት ዓይነት ኪዳኖች ይገኛሉ። በሲና ተራራ ለአይሁድ ተሰጥቶ እንደነበረው (ዘጸ. 19:24) ዓይነት ያሉ አንዳንድ ኪዳኖች ቅድመ ሁኔታዎች ነበሩዋቸው። በሌላ አባባል እግዚአብሔር «እነዚህን ትእዛዛት ከጠበቃችሁ ለእናንተ እንደዚህ አደርግላችኋላሁ» ብሏል። ሌላው ዓይነት ኪዳን ግን ምንም ዓይነት ቅድመ ሁኔታ የሌለው የተስፋ ቃል ኪዳን ብቻ ነበር። የእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ግን ምንም ዓይነት ቅድመ ሁኔታ የሌለው የተስፋ ቃል ብቻ ነበር። እግዚአብሔር ቃል ኪዳን ለገባላቸው ሰዎች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ አንድ ነገር እንደሚያደርግላቸው ተናግሯል (ዘፍ. 12፡1-3)። የዚህ ቃል ኪዳን ምሳሌ እግዚአብሔር ከአብርሃም፥ ከዳዊትና ዛሬም ከክርስቲያኖች ጋር ያለው አዲሱ ቃል ኪዳን ዓይነት ነው። እግዚአብሔር በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሰጣቸውን ኪዳኖች በምናጠናበት ጊዜ ቅድመ ሁኔታ ያላቸውንና የሌላቸውን ለይቶ ማየት አስፈላጊ ነው።

ሦስተኛ፡ በኪዳኑ ውስጥ አንዱ ክፍል ለሌላው የሚሰጣቸው ተስፋዎች አሉ። በብሉይ ኪዳን ብዙ ጊዜ ኪዳኑን የሚጀምር እግዚአብሔር ስለሆነ፥ ተስፋንም ለተለያዩ ሰዎች የሚሰጥ እርሱ ነው። እነዚህ ተስፋዎች እንደሚፈጸሙ ጥርጥር የለም። ምክንያቱም ተስፋውን የሰጠው ሊዋሽ ወይም አሳቡን ሊቀይር የማይቻለው አምላክ ስለሆነ ነው።

የውይይት ጥያቄ፥ ኤር. 31፡31-34 አንብብ። በእነዚህ ቁጥሮች እግዚአብሔር ለእስራኤላውያን የሰጣቸው ተስፋ ምንድነው? 

የውይይት ጥያቄ፥ ማቴ. 26፡26-29 አንብብ። ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ የሰጠውን ጽዋ ምን ብሎ ጠራው? የመጀመሪያዎቹ 39 መጻሕፍት ብሉይ ኪዳን፥ 27ቱ ደግሞ አዲስ ኪዳን ተብለው እንዲጠሩ የወሰኑት የጥንት ክርስቲያኖች እግዚአብሔር ከሰዎች ጋር ያለው ኅብረት እምብርት የኪዳኑ አሳብ እንደሆነ ተገንዝበው ነበር።

በብሉይ ኪዳን ውስጥ እግዚአብሔር ለሰው ልጅ የሰጣቸው አያሌ የተለያዩ ኪዳኖች ይገኛሉ። 

  1. ከኖኅና ከሰው ልጆች ሁሉ ጋር የተደረገ ኪዳን (ዘፍጥ. 9፡1-17)፥ – የሰውን ዘር ካጠፋው ውኃ በኋላ እግዚአብሔር ከኖኅና ከእርሱ በኋላ ከተነሡ የሰው ልጆች ሁሉ ጋር ቃል ኪዳን አደረገ። በዚህ ኪዳን ውስጥ ይታዘዙት ዘንድ እግዚአብሔር የሰጣቸው ግልጥ የሆኑ ትእዛዛት ነበሩ። ደግሞም በዚያ ቃል ኪዳን ውስጥ የሰውን ልጆች በውኃ ላያጠፋ እግዚአብሔር የገባውም ቃል ኪዳን ነበር። ብዙውን ጊዜ በሰማይ ላይ የምናየው ቀስተ ደመና ያንን ቃል ኪዳን የሚያስታውስ ነው። 
  2. ከአብርሃምና ከዘሩ ጋር የተገባ ቃል ኪዳን (ዘፍጥ. 12፡1-3)። 

የውይይት ጥያቄ፥ ዘፍ. 12፡1-3 አንብብ። እግዚአብሔር ለአብርሃም የሰጠውን የተለያዩ ቃል ኪዳኖች ዘርዝር።

በብሉይ ኪዳን ከምናያቸው ቃል ኪዳኖች ሁሉ እጅግ በጣም አስፈላጊ የሆነው እግዚአብሔር ከአብርሃም ጋር ያደረገው ነው። እግዚአብሔር ከዘፍጥ. 12-25 እንዲሁም በአጠቃላይ በብሉይ ኪዳን ላይ በዚህ ቃል ኪዳን ላይ መመሥረቱን ቀጠለ። ይህ ቃል ኪዳን በብሉይና በአዲስ ኪዳን ውስጥ ያሉትን ሌሎች ቃል ኪዳኖች ለመረዳት የሚያስችል መሠረት ነው። ከአብርሃም ጋር በተገባው ቃል ኪዳን ውስጥ በቀጥታ አብርሃምን ራሱን ብቻ የሚመለከቱ በርካታ የተስፋ ቃሎች አሉ፤ ነገር ግን ለብሉይ ኪዳን ትምህርቶችና ታሪክ መሠረት የሆኑ ሌሎች በርካታ የተስፋ ቃሉችም አሉ።

ሀ. እግዚአብሔር የአብርሃም ዘሮች የሆኑትን አይሁድ ወይም እስራኤላውያን ታላቅ ሕዝብ እንደሚሆኑ የተስፋ ቃል ሰጣቸው። የብሉይ ኪዳን የታሪክ መጻሕፍት ከዘጸአት ጀምሮ እስከ 2ኛ ዜና ድረስ ይህ ሕዝብ እዚህ ግባ ከማይባል ከአንድ ቤተሰብ ወደ ታላቅ ሕዝብነት እንዴት እንዳደገ የሚናገሩ ናቸው።

ለ. እግዚአብሔር የአብርሃም ዘሮች የተስፋ ምድር የሆነችውን ከነዓንን እንደሚወርሱ ተናገረ። ይህች ምድር የእነርሱ ርስት ትሆናለች አለ። የኢያሱ፥ የመሳፍንትና የ1ኛና 2ኛ ሳሙኤል መጻሕፍት እነዚህ የተስፋ ቃሉች በረጅም ጊዜ ውስጥ እንዴት እንደተፈጸሙ የሚናገሩ ናቸው።

ሐ. እግዚአብሔር ከአብርሃም በተለይም ከይሁዳ የዘር ግንድ አንድ ልዩ የሆነ ንጉሥ እንደሚወጣ የተስፋ ቃል ሰጣቸው (ዘፍጥ. 17፡6፥16፤ 49፡10)። ይህ የተስፋ ቃል በመጀመሪያ በዳዊት ተፈጸመ። በመጨረሻም በኢየሱስ ክርስቶስ ተፈጽሟል። 

  1. እግዚአብሔር በሲና ተራራ ከእስራኤል ሕዝብ ጋር ቃል ኪዳንን አደረገ (ዘጸ. 19-24)። እግዚአብሔር ምንም ዓይነት ቅድመ ሁኔታዎችን ከሰዎች ካልጠየቀባቸው ከሌሉቹ ቃል ኪዳኖች በተቃራኒ፥ በሲና ተራራ እግዚአብሔር ከአይሁድ ሕዝብ ጋር ያደረገው ስምምነት ቃል ኪዳኑ ይፈጽም ዘንድ እነርሱም ሊያሟሉት የሚገባ ቅድመ ሁኔታ ነበር። ብሉይ ኪዳን ብለን ከምንጠራቸው ከሠላሳ ዘጠኙ መጻሕፍት መካከል አብዛኛዎቹ እግዚአብሔር ከእስራኤል ጋር ስለገባው ቃል ኪዳን ከሚናገሩ ነገሮች ጋር የተያያዙ ነበሩ። በብሉይ ኪዳን እግዚአብሔር ከእስራኤል ጋር ቃል ኪዳን እንዴት እንደጀመረ (ዘፍጥረት እስከ ዘዳግም)፥ ለእስራኤላውያን የከነዓንን ምድር በመስጠት የገባላቸውን ተስፋ እንዴት እንዳከበረ (ኢያሱ እስከ 2ኛ ሳሙኤል)፥ እንዲሁም እስራኤላውያን ከእግዚአብሔር ጋር የነበራቸውን ቃል ኪዳን እንዴት እንዳፈረሱና ለጊዜው እንደተፈረደባቸው (1ኛ ነገሥት እስከ ሚልክያስ) እናነባለን። 
  2. ከካህኑ ከፊንሐስ ጋር የተገባ ቃል ኪዳን (ዘኁል. 25፡10-13)። በዚህ ቃል ኪዳን እግዚአብሔር ለፊንሐስ ዘሮች ካህናት የመሆን መብት ሰጥቷል።
  3. ከንጉሥ ዳዊት ጋር የተገባ ቃል ኪዳን (2ኛ ሳሙ. 7፡5-16)፡ እግዚአብሔር ለዳዊት የእርሱ ዘሮች በእስራኤል ሕዝብ ላይ ንጉሥ የመሆን መብት እንዳላችው ቃል ኪዳን ገባለት። በ መጨረሻ ይህ ቃል ኪዳን የይሁዳ አንበሳ በሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ ተፈጸመ። እርሱ በእስራኤልና በሕዝቦች ሁሉ ላይ ንጉሥ ነው። አንድ ቀን ኢየሱስ ወደዚህች ምድር በመመለስ እንደገና ይነግሣል (ራዕ. 20፡4)። 
  4. አዲስ ቃል ኪዳን (ኤር. 31፡31-34)፥ የእስራኤል ሕዝብ እግዚአብሔር በሲና ተራራ ከቃል ኪዳኑ ጋር የሰጣቸውን ቅድመ ሁኔታ መጠበቅ ስላልቻሉ፥ እግዚአብሔር አዲስ ቃል ኪዳን እንደሚሰጥ አስታወቀ። በዚህ ቃል ኪዳን እግዚአብሔር ሕግን እንደሚያደርግና ለሰዎችም ይህንን ሕግ የመታዘዝ ችሉታ በልባቸው እንደሚሰጣቸው ተስፋ ሰጥቷል። ኢየሱስ በመስቀል ላይ በሞተ ጊዜ ይህንን አዲስ ቃል ኪዳን እንደጀመረው ሐዋርያት በኋላ ተገነዘቡ። 

፪. ብሉይ ኪዳን፡- የመጀመሪያዎቹን 39 ቅዱስ መጻሕፍት «ብሉይ» ብለው በመጥራታቸው የቀድሞዎቹ ክርስቲያኖች ከኢየሱስ መምጣት ጀምሮ አንድ አዲስ ነገር እንደተፈጸመ ያሳዩናል። በኤር. 31 የተሰጡት ተስፋዎች ተፈጽመዋል። እነዚህ የቀድሞ ክርስቲያኖች የመጀመሪያዎቹን 39 መጻሕፍት ብሉይ ብለው የጠሩባቸው ሦስት ምክንያቶች አሉ፡-

ሀ. እግዚአብሔር አዲስ ቃል ኪዳንን በኤር. 31፡31-34 ላይ ስለሰጠ የቀድሞው ቃል ኪዳን አሮጌ ወይም ጊዜ ያለፈበት ሆኗል፡፡

ለ. ኢየሱስ ከመሞቱ በፊት በነበረው ሌሊት የሚያፈሰው ደም ይቅርታን የሚያስገኝ የቃል ኪዳን ደም እንደሆነ ተናግሮ ነበር። ይህንን ቃል ኪዳን ኢየሱስ አዲስ ቃል ኪዳን ብሎ ባይጠራውም እንኳ እግዚአብሔር እውነተኛ የኃጢአት ይቅርታ የሰጠበት በትንቢተ ኤርምያስ የምናገኘው አሳብ መሆኑ ግልጽ ነው።

የውይይት ጥያቄ፥ ዕብ. 7፡ 18-22፤ 8፡6-13 አንብብ። ሀ) የዕብራውያን ጸሐፊ የቀድሞውን ቃል ኪዳን የጠራባቸውን ስሞች ዘርዝር። ለ) ይህ ጸሐፊ አዲሱን ቃል ኪዳን የጠራባቸውን ስሞች ዘርዝር። ሐ) ጸሐፊው ስለ ቀድሞው ቃል ኪዳን ምን ይላል?

ሐ. በሲና ተራራ የተሰጠው ቃል ኪዳን በዕብራውያን መልእክት «የቀድሞው፥ አሮጌው፥ የፊተኛውና ዘመኑ ያለፈበት» ተብሏል። በሌላ በኩል ኢየሱስ የጀመረው ቃል ኪዳን «አዲስ፥ የተሻለና የላቀ» ቃል ኪዳን ተብሉአል። እነዚህ ቃላት ሁሉ የሚያሳዩት ኢየሱስ ወደ ምድር ከመጣበት ጊዜ ጀምሮ ከእግዚአብሔር ጋር አዲስ ስምምነት የተደረገበት አዲስ ዘመን መጀመሩን የቀድሞ ክርስቲያኖች ምን ያህል ተገንዝበውት እንደነበር ነው። እንደ አንዳንድ የብሉይ ኪዳን ቃል ኪዳኖች፣ ይህ አዲስ ቃል ኪዳን በቅድመ ሁኔታ ላይ ያልተመሠረተ ነው፤ በሰው ፍጹም መታዘዝ ላይ ሳይሆን፥ በእግዚአብሔር የተስፋ ቃላት ላይ የተመሠረተ ነው።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) የአዲስ ኪዳን የተስፋ ቃል በሲና ተራራ የተሰጠውን ሕግ በሙሉ ስለመጠበቅ አስፈላጊነት ለእኛ ምንን ያመለክታል? ለ) በአሁኑ ጊዜ ያሉ አንዳንድ ክርስቲያኖች በሲና ተራራ ለአይሁዳውያን ከተሰጡት ሕጎች አንዳንዶቹን የሚከተሉት ለምንድነው? ሐ) እነርሱ ከሚከተሏቸው ሕጎች አንዳንዶቹን ዘርዝር።

ስለ ብሉይ ኪዳን ቃል ኪዳኖችና ከአዲስ ኪዳን ጋር ስላላቸው ግንኙነት የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራን አስተሳሰብ የተለያየ ነው። አንዳንድ ክርስቲያኖች ቃል ኪዳን አንድ ብቻ ነው፤ ይህም ብቸኛ ቃል ኪዳን እግዚአብሔር ከሕዝቡ ጋር የገባው ቃል ኪዳን ነው ይላሉ። በብሉይ ኪዳን ቃል ኪዳን የተደረገው በሥጋም በመንፈስም የአብርሃም ልጆች ከነበሩት አይሁዳውያን ጋር ሲሆን፥ በአዲስ ኪዳን ደግሞ የአብርሃም መንፈሳዊ ልጆች ከሆኑት ከእግዚአብሔር ልጆች ጋር ነው (ገላ. 4፡21-31 ተመልከት)። ሌሉች ክርስቲያኖች ደግሞ ፍጹም የተለያዩ ሁለት ቃል ኪዳኖች ናቸው ይላሉ። የመጀመሪያው ከእስራኤል ሕዝብ ጋር ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በኢየሱስ ክርስቶስ አምነው የተሠዋው ለኃጢአታቸው እንደሆነ ከተቀበሉት ሰዎች ሁሉ ጋር ነው። እነዚህኞቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራን እግዚአብሔር በሥጋ የአብርሃም ዘር ለሆኑ የገባቸው ቃል ኪዳኖችና ለቤተ ክርስቲያን የገባቸው ቃል ኪዳኖች በግልጽ መለየት አለባቸው ይላሉ። እነዚህ ልዩነቶች እንደዋና ነገር የማይታዩ ቢሆኑም እንኳ ብሉይ ኪዳንን የምንረዳበትና የምንተረጉምበት አብዛኛው መንገድ የተመሠረተው የብሉይና የአዲስ ኪዳን ልዩነቶች ምን እንደሆኑ ባለን መረዳት ላይ ነው።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) በብሉይ ኪዳን የሚገኙ ቃል ኪዳኖችን በሙሉ ከልስ። ለ) የቅዱሳት መጻሕፍት ክፍሎችን በሙሉ አንብብ። ሐ) በእነዚህ ክፍሎች ውስጥ እግዚአብሔር የሰጠውን የተስፋ ቃላት ዘርዝር። መ) ለእነዚህ የተስፋ ቃላት የተሰጡ ሌሉች ቅድመ ሁኔታዎችን ዘርዝር። ሠ) ዛሬ ከእኛ ጋር በቀጥታ የሚያያዙ የተስፋ ቃላት የትኞቹ ናቸው? ረ) በብሉይ ኪዳን ዘመን ይኖሩ ለነበሩ ሰዎች ብቻ የሚሆኑትስ የተስፋ ቃላት የትኞቹ ናቸው?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: