እጸልይላችኋለሁ (ፊል 1፡9-11) 

“ፍቅራችሁ በጥልቅ እውቀትና በማስተዋል ሁሉ በዝቶ እንዲትረፈረፍ እጸልያለሁ። ይኸውም ከሁሉ የሚሻለውን ለይታችሁ እንድታውቁ፣ እስከ ክርስቶስም ቀን ድረስ ንጹሓንና ነቀፋ የሌለባችሁ እንድትሆኑ፣ ለእግዚእብሔር ክብርና ምስጋና በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በሚገኘው የጽድቅ ፍሬ እንድትሞሉ ነው።”

ጳውሎስ በፊልጵስዩስ ላሉት ወዳጆቹ የሚያድግ ፍቅር ስለነበረው ሲያስታውሳቸው ደስተኛ ይሆናል። በጸሎት ወደ ጌታው የጸጋ ዙፋን በቀረበ ጊዜ ሁሉ እነርሱን በፊቱ እያስታወሰ ደስተኛ ነበር። በብሉይ ኪዳን ጊዜ ሊቀ ካህኑ በልቡ ላይ የሚደርበው ኤፉድ የተባለ ልዩ ልብስ ነበረው። በዚህም ላይ በእያንዳንዱ የእስራኤል ነገዶች ስም በከበረ ድንጋይ የተቀረጹ አሥራ ሁለት ድንጋዮች ይገኛሉ (ዘጸ. 28፡15-29)። ጳውሎስም እንደሚያደርገው ሁሉ እርሱም በፍቅር ለሕዝቡ ያለውን ፍቅር በልቡ ይሸከም ነበረ። ምናልባትም በዚህ ሕይወታችን የምንለማመደው ከፍተኛው ክርስቲያናዊ ሕብረትና ደስታ የሚገኘው፥ ከጸጋ ዙፋኑ ሥር በፍቅር አብረን ስንጸልይና አንደኛችን ለሌላው ስንጸልይ ነው። 

ይህ ጸሎት አማኞች በመንፈሳዊ ሕይወታቸው ብስለት እንዲያገኙ ነው፤ ጳውሎስ ይህንን የጀመረው በፍቅር ነው። ያም ሆነ ይህ የክርስቲያን ፍቅራችን እንደሚገባ ከሆነ የቀሩት ነገሮች ሁሉ ይከተሉናል። የሚለማመዱት ፍቅር የሞላ ፍቅርና ቀናዒ ፍቅር እንዲሆንላቸው ይጸልያል። የክርስቲያን ፍቅር እውር ፍቅር አይደለም! ልብና አሳብ አብረው ስለሚሠሩ ልንወደውና ልንጠላው የሚገባንን ለይተን እናውቃለን። ጳውሎስ ወዳጆቹ በዚህ ዓይነቱ ፍቅር በሙላት እንዲያድጉ ይፈልጋል፥ ይኸውም «የተለያዩ ነገሮችን መለየት» እንዲችሉ ነው። 

የመለየት ችሎታ የማደግ ምልክት ነው። አንድ ሕፃን ለመናገር በሚለማመድበት ጊዜ አራት እግር ያለውን እንሰሳ ሁሉ «ውው.. ውው» እያለ ይጣራል። በኋላ ግን ድመቶች፥ ውሾች፥ አይጦች፥ ላሞች እና ሌላ ባለአራት እግር ፍጥረቶች እንዳሉ ይገነዘባል። ለሕፃን ልጅ አንድ መኪና ከሌላው መኪና ጋር አንድ ነው፥ ግን ወደ ጎልማሣነቱ ሲቃረብ ወላጆቹ ከሚጠሩት የመኪና ስም ፈጥኖ የሞዴሉን ልዩነት እንኳን ይናገራል። እርግጠኛ የሆነ የማደግ ምልክቶች አንደኛው መለየት የሚችል ፍቅር ነው። 

ጳውሎስ ደግሞ ለክርስቲያኖች «ቅንና አለነውር» የሆነ ባሕርይ እንዲኖራቸው ይጸልያል። ከግሪክ ቃል የተተረጎመው ቅን የሚለው ቃል የተለያየ ትርጉም አለው። አንዳንዶቹ «በፀሐይ ብርሃን የተፈተነ» ብለው ይተረጉሙታል። ቅን የሆነ ክርስቲያን በብርሃን መቆም አይፈራም። አንድ ሰው ለታላቁ እንግሊዛዊ ሰባኪ፥ ለቻርልስ ስፐርጀን የሕይወት ታሪክህን ለመጻፍ እፈልጋለሁ ሲል ይነግረዋል። ስፐርጀን ግን «የእኔን ሕይወት ታሪክ በደመና ላይ መጻፍ ትችላለህ። ምንም የተደበቀ ነገር የለኝም» ሲል መልሶለታል። 

ሌሎች ደግሞ፥ ቅን ማለት «በወንፊት ውስጥ ተንገዋልሉ» መውጣትን ያመለክታል ይላሉ፡ ይህም አሳብ ገለባን ከማስወገድ ወይም ከማበራየት ዘዴ ጋር የተያያዘ ነው። በሁለቱም ትርጉሞች ላይ እውነቱ አንድ ነው፤ ጳውሎስ ለወዳጆቹ ፈተናን ማለፍ የሚችል የዚህ ዓይነቱ ባሕርይ እንዲኖራቸው ይጸልይላቸዋል። 

ጳውሎስ የሚጸልይላቸው የበሰለ የክርስቲያን ፍቅር እና ባሕርይ እንዲኖራቸው እና «ለክርስቶስ ቀን ያለ ነውር እንዲሆኑ» ነው (ቁ. 10)። ይህም ማለት የእኛ ሕይወት ለሌሉች መሰናከያ ምክንያት እንዳይሆንና ኢየሱስ ሲመለስ በክርስቶስ የፍርድ ወንበር ፊት ለመቅረብ ዝግጁ እንዲሆን ነው (2ኛ ቆሮ. 5:10 እና 1ኛ ዮሐ. 2:28 ተመልከት)። እኛ መንፈሳዊነትን መለየት እንድንለማመድ መከተል የሚገባን ሁለት መፈተኛ መንገዶች እንደሚከተለው ቀርበዋል፡- (1) ለሌሉች መሰናክል የሆንኩበት ጊዜ አለን? (2) ኢየሱስስ ሲመጣ አፍር ይሆንን? 

ከዚህ በተጨማሪም ጳውሎስ የበሰለ የክርስቲያን አገልግሎት እንዲኖራቸው ይጸልያል። ሕይወታቸው የጽድቅ ፍሬ የተሞላ እንዲሆን ይፈልጋል (ቁ. 11 አዲስ ትርጉም)። የእርሱ ፍላጎት «በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት» ውስጥ በምናደርገው ተሳትፎ የተወሰነ አይደለም፥ ግን ከክርስቶስ ጋር በምናደርገው ኅብረት በምናስገኘው የመንፈስ ፍሬ ዓይነት ላይ ጭምርም ነው። «በእኔ ኑሩ እኔም በእናንተ። ቅርንጫፍ በወይኑ ግንድ ባይኖር ከራሱ ፍሬ ሊያፈራ እንዳይቻለው፥ እንዲሁ እናንተ ደግሞ በእኔ ባትኖሩ አትችሉም» (ዮሐ. 15፡4)። ብዙ ክርስቲያኖች በክርስቶስ ከመኖር እና ፍሬን ለማግኘት ሕይወታቸውን ከመስጠት ይልቅ «ውጤት ለማግኘት» በራሳቸው ጥረት ይሞክራሉ። 

እግዚአብሔር በሕይወታችን ማየት የሚፈልገው «ፍሬ» ምንድን ነው? በእውነት እርሱ የሚፈልገው «የመንፈስ ፍሬ» (ገላ. 5፡22-23) ማስገኘታችንን ነው። የክርስቲያን ባሕርይ እግዚአብሔርን ያስከብራል። ጳውሎስ የጠፋውን ነፍስ ለክርስቶስ ማዳንን ፍሬ ከማፍራት ጋር ያመሳስለዋል (ሮሜ 1፡13)። እና «ቅድስናን» ደግሞ እንደ መንፈስ ፍሬ ይጠራዋል (ሮሜ 6፡22)። «በበጎ ሥራ ሁሉ ፍሬ አፍሩ» (ቆላ. 1፡10) ብሎ አጥብቆ ያሳስባል። በዕብራውያን ላይ ደግሞ የእኛ ምስጋና «የከንፈራችን ፍሬ» (13፡15) መሆኑን ያስታውሰናል። የፍሬ ዛፍ ፍሬ በሚያፈራበት ጊዜ አንዳችም ዓይነት ጩኸት አያሰማም፤ ሕይወት በውስጡ እንዲሠራ ብቻ ይፈቅዳል፤ ውጤቱም ፍሬው ራሱ ነው። «እኔ የወይን ግንድ ነኝ እናንተ ቅርንጫፎች ናችሁ። ያለ እኔ ምንም ልታደርጉ አትችሉምና በእኔ የሚኖር እኔም በእርሱ፥ እርሱ ብዙ ፍሬ ያፈራል» ( ዮሐ. 15፡5)። 

በመንፈስ ፍሬ እና በሰው «የሃይማኖት አገልግሎት» መሀል ያለው ልዩነት ለኢየሱስ ክርስቶስ ክብር በሚያመጡት ፍሬ ላይ ነው። ምንጊዜም አንድን ነገር በራሳችን ኃይል ስንሠራ፥ እኛ ስለሠራነው የመመካት ፍላጎት ይኖረናል። እውነተኛ የመንፈስ ፍሬ እጅግ ያማረ እና ግሩም ነው። ክብሩ ወደ እግዚአብሔር ብቻ እንጂ ማንም ሰው ለራሱ «ዋጋ ይገባኛል» አይልም። 

እውነተኛ የክርስቲያን ኅብረት ከተራ ወዳጅነት ያለፈና ያለንን በጋራ ለመካፈል የሚያስችል ጥልቅ መተሳሰብ መሆን አለበት። «አስታውሳችኋለሁ … በልቤ ውስጥ ትኖራላችሁ … እጸልይላችኋለሁ አላቸው»። እንዲህ ዓይነት ኅብረት ደስታን ያስገኛል፥ ይህን ኅብረት ለማግኘት ደግሞ አንድ አሳብ መሆን ነው። 

አንድ ሰው ወደ ኒውዮርክ ከተማ ለልዩ ቀዶ ጥገና ሕክምና መሄድ ግድ ቢሆንበትም እርሱ ግን ርቆ መሔዱን አልወደደውም ነበር። «ለምንድን ነው የዚህ ዓይነቱ ሕክምና በአካባቢያችን የማይሰጠው?» ብሉ ሐኪሙን ጠየቀው። «በዚያ በግር ግር በተሞላ ታላቅ ከተማ ውስጥ አንድ ሰው እንኳ አላውቅም» አለው። ነገር ግን ባለቤቱና እርሱ ከሆስፒታሉ ሲደርሱ እነርሱን ለመገናኘት የመጣ አንድ መጋቢ አገኙ። ከተማውን እስኪለማመዱትም በእርሱ ቤት እንዲቀመጡ ጋበዛቸው። ቀዶ ጥገናው አስጊ ስለነበረ በሆስፒታሉ ውስጥ ለመቆየት የነበረው ዕድል ረጅምና አስቸጋሪ ነበር፤ ነገር ግን የባለቤቱና የመጋቢው ኅብረት ደስታን አስገኘለት። እኛም እነዚህን መሰሎቹ አጋጣሚዎች ለወንጌል ኅብረት ማጠናከር መንገድ እንደሚከፍቱ እስካመንበት ድረስ ሁኔታዎች ደስታችንን ሊነጥቁን እንደማይችሉ እርግጠኞች እንሆናለን። 

በተግባር ላይ እናውለው! 

እስቲ በዚህ ሳምንት ውስጥ ሁኔታዎች ሁሉ ወደ ክርስቲያን ወዳጆችህ እንድትቀርብ እንዲያደርጉህ ሞክር። አንድ አሳብ ብቻ ካለህ – ማለትም የምትኖረው ለክርስቶስና ለወንጌል እስከሆነ፥ ያለምንም ጥርጥር ከዚያ በኋላ መከራዎችህና ችግሮችህ የወንጌልን ኅብረትን እንደሚያጠነክሩ ትገነዘባለህ፥ ያም ኅብረት ከፍተኛ ደስታን ያጎናጽፍሃል። በ1966ዓ.ም፥ በሰዓት በ90 ማይል ፍጥነት የሚበር መኪና ገጭቶኝ በአስጊ ሁኔታ ላይ እገኝ ነበር። ሆኖም በዚያ ሳቢያ የመሠረትኩት መልካም ኅብረት ውጤት የደረሰብኝን ሕመምና ችግር ሁሉ የሚያስረሳ ነበር። ያም አጋጣሚ ነበር ወደ እግዚአብሔር ሕዝብ እንድቀርብ ያስቻለኝ። 

«ለእኔ ሕይወት ክርስቶስ፥ ሞትም ጥቅም ነውና።» (1፡21)። 

ምንጭ፣ ጽሑፍ በ ዋረን ደብልዩ ዌርዝቢ፣ ትርጉም በመስፍን ታዬ፣ እርማት በ ዓብይ ደምሴ

2 thoughts on “እጸልይላችኋለሁ (ፊል 1፡9-11) ”

  1. እግዚአብሄር ይባርካችሁ የወንጌልን እውነት እንዲህ ማቅረባችሁ ለምንጠቀም ሰዎች በጣም እድለኞች ነን
    kassu boston

Leave a Reply

Discover more from

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading